Saturday, 27 January 2024 00:00

ወደፊት መሣይ ወደ ኋላ ጉዞ !

Written by  የአብፀጋ ተመስገን /maddbn/
Rate this item
(5 votes)

“በቃል ያሉት ይረሣል በፅሁፍ ያስቀመጡት ይረሳል” ይላሉ አበው። ለመሆኑ አበው ማናቸው? ጥንታዊ አባት ይሆኑ? እንደ አለቀ ገብረሃና ወይም እንደ አባ ምንይዋብ ቢጤ ሆነው በተራችነታቸው የሚታወቁ ጉምቱ ሰው? ማንን እንጠይቅ? በፅሁፍ የተቀመጠልንን ደጅ እንጥና እንዴ ፣ እነ መዝገበ ቃላትን።
አዲስ አበባ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከወረቀት ጋር ምን አታገለን። መፅሐፍ ገልጦ የአበውን ፍቺ ፍለጋ ከመባተል እጃችን ላይ ባለው ዘመናዊ ስልክ በቀላሉ ምላሹን ማግኘት እኮ እንችላለን። ጥሩ እንጀምራ ታዲያ፤ “ጎግልዬ አበው ማናቸው በሞቴ?” በለው በለው ደረደረልኝ፣ ፓ ! እንዲህ ነው እንጂ ! እስኪ እናንብበዋ ታዲያ ፤ “ ምክረ አበው “ ይላል ምንጩ ከውክፔዲያ ነው። የመጨረሻው ህዳግ ላይ የእርስዎን ሊጨምሩ ወይም ሊቀንሱ ይችላሉ ይላል። እስኪ ፍረዱኝ ባውቅ ኖሮ ለምን እጠይቃለሁ ፤ ደግሞ ማንኛውም ሰው ተነስቶ የራሱን ሀሳብ የጨመረውን ወይም የቀነሰውን ነው እንዴ የሚያመጣልኝ? እንደዚያ ከሆነ ታዲያ የመረጃውን ትክክለኝነት እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ ፣ ከመፅሐፍ አጣቅሼ? አዬዬዬ እንዲያ ከሆነማ ሀሜቱ እውነት ነው፤ “ ነገሩ ሁሉ እንደ ልጅ ጥሬና ብስል ነው እንዲያውም እንቶ ፈንቶው ይበዛል የሚሉት። ይሁን እስኪ ታገስ ብለን የደረደረልኝን ሙሉውን እንየው፤ በቀጣዩ ህዳግ ላይ” አቡነ ጴጥሮስ “ ይላል። አይ ጎግል ጀግናውን ሰማዕት አለመዘንጋትህ በጎ ነው ። እኔ ግን የጠየኩህ ሌላ ነው፤ እሱን መልስልኝ እንጂ! እሺ ቀጣዩን እንየው .... “ እገሌ ማናቸው?” አሄሄ አሁንስ አናደድከኝ ስትለግም ነው እንጂ አበው ማ እንደሆኑ እንዴት ላንተ ይጠፉሀል?” አይመልሰው የለም ሁሉን አዋቂ የቀለም ቀንድ ነው” እያሉ የሚያሞካሹህ ኩሸት ነው ማለት ነው?
እንደለመደብን የመዝገበ ቃላት መፅሐፋችንን ብንገልጥ ይሻላል። እዚያ ላይ ተፅፎ ከሆነ የትም አይሄድም፣ ተፅፎ የተቀመጠ ነገር እንደየሁኔታው የሚለግምና መልኩን የሚለውጥ አይደለም። ትላንትም ሆነ ነገ፤ ማንነቱን ሣይቀይር እንደነበረ ይቆየናል። ይኸው ቁልጭ ብሎ ተቀምጦልናል ፤ እንዲህ ነው እንጂ ገላገልከኝ አቦ ! ዙሪያ ጥምጥም የለ ፣ የእርስዎን ማከል ይችላሉ የለ ፣ ለተጠየቀው ነገር ምላሹን ብቻ ቁጭ ! አዝናለሁ በዚህኛው ቴክኖሎጂ አልተሳካለትም መፅሀፍ ተሽሎ ተገኝቷል በቅልጥፍና ያገዘኝ ፣ ጊዜዬን የቆጠበልኝ እሱ ነው። ዘመነኞቻችን ይኸን እውነት አስተውለው ይሆን ? እነሱማ የአበውን የተከበረ መንበር ነጥቀው ለ “ AI “ መስጠት እየዳዳቸው ነው። AI ን አበው promax እያሉ ማሞካሸት ጀምረዋል።  ለመሆኑ AI ማነው ? እሱማ ከእንግሊዝ አፍ ባጠረ ምህፃረ ቃል የሚጠራ ሲሆን “ Artefical Intelligence “ ነው ሙሉ ስሙ ። ታዲያ እሱ ማ ስለሆነ ነው ከባህር ማዶ መጥቶ በአበው የሚሠየመው ? በምን ተሽሎ ነው ?
  እንደሚሉት ከሆነማ ይሄ ረቀቅ መጠቅ ያለ ሳይሆን አይቀርም። አይሠራው አይተገብረው የለም። ያውም ደጅ አያስጠና ፣ ጊዜ አይፈጅ ፣ ቀብድ አይጠይቅ ... ከውንልኝ ያልከውን ሁሉ በሠከንዶች ሠርቶ ያስረክብሀል።  ኧረ ይሄ ነገር ግር እያለ መጣ ! ምን አይነት ነገር ነው ቆይ ? ይሠራል የተባለውስ እንደ ምን ያለ ነገር ነው ?   ነገሩማ እንዲህ ነው። በበይነ መረብ የሚዘወር የዲጂታሉ ዓለም ሶፍትዌር ሲሆን ፤ በመተግበሪያም ሆነ በዌብሳይት ይገለጣል። ቀደም ካሉት የበይነመረብ አገልጋዮች እጅግ በጣም የተራቀቀና ሁለገብ ነው። አንድ ባለሙያን ይሄንን አድርግልኝ ይሄን ስራልኝ ብለህ እንደምትጠይቀው ፤ ያሻህን ትፅፍለታለህ። እሱ ሆዬ ታዲያ እፍኝ በማይሞሉ ሠከንዶች የታዘዘውን አጠናቅቆ እነሆኝ ፣ እንካችሁ ይልሃል። ለምሣሌ ጭብጡ ስለ ሠላም ጉዳይ የሆነ በዚያ ዙሪያ የሚያጠነጥን አጭር ልብወለድ መፃፍ ፈልገህ አልሞላ ብሎህ ወይም “ ሀሲያ ጨብራሬ “ አልመጣ ብላ ቃላቶችህ ተሸሸጎብህና ደጁን ጠናህ እንበልና ፤ “ መሠረቱን በዚህ ጉዳይ ያደረገ 5 ገፅ የሚደርስ አጭር ልብወለድ ፃፍልኝ “ ብለህ የልብህን መሻት ነገርከው። AI ታዲያ ምንተስኖት ! ፍጥነቱ ለዚህ ነበር የተጨነቅኸው ይመስል ደቂቃ ሣይሞላ ፤ ሴራና ግጭቱ የተዋቀረ ሁሉንም የስነፅሁፍ አላባውያን የሚያሟላ ባለ አምስት ገፅ አጭር ልብ ወለድ ባለቤት አድርጎህ ቁጭ ይላል።
 ታዲያልህ ይህ ነገር አበው ተናገሩት አበው ተረቱት የተባለውን ምሣሌያዊ አነጋገር ሁሉ ወደ ምስል ለውጦ ማሣየት ጀምሯል። ለምሣሌ “ ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ “ ን ፤ ወተት የመሠለ የሙሽራ ልብስ የለበሠች ኮረዳ ፣ በሱፍ ከዘነጠ ጉብል ጋር በሙሽራ ደንብ እጃቸውን አቆላልፈው ፣ በሚዜዎቻቸው ታጅበው የልጁ ቤት ሲደርሱ ፣ ቤተሰቡና ጎረቤት መንደሩ በሙሉ ደጅ ወጥቶ በርበሬ በመቀንጠስ ተጠምዶ ሣለ ሙሹሮቹ በዚያ መሀል እያለፉ ያሳያል።
   ዘመነኞቻችን ይህን አይተው AI ን “ አበው promax “ አጠጋግተን ስንተረጉመው “ በዘመናችን አበው እጅግ ዘምነውና ተራቅቀው “ በማለት እያሞኳሻቸው ይገኛል። እኔንም ይህን እንድፅፍ ያነሳሳኝ ፣ ያስቆጣኝና ስጋት ውስጥ የከተተኝ ይሄ ፈሊጥ ነው። ለምን ቢባል ፤ እስኪ ይሄን ጉራማይሌ ቃል ማንነቱንና ከየትና እንዴት እንደመጣ እንገምግምና አብረን እንታዘብ ።
  አበውን እናውቃቸዋለንና “ promax “ ን እንመርምረው። ቃሉ የእንግሊዝኛ ሲሆን የሞባይል ስልኮችን በማከፋፈል የሚታወቅ ትልቅ ኩባንያ ለ “ marketing “ የሚጠቀምበት ነው። ይህ ቃል ከዚህ ግብሩም በማለፍ ፤ እጅግ ዘምኖ ወይም ተሻሽሎ በአዲስ መልኩ የመጣ ነገር የሚሞካሽበት ፈሊጥ ሆኗል።  የባህር ማዶ ቃል ድንበር ተሻግሮ በአማርኛችን ላይ ፈሊጥ የሆነው እውን በቋንቋችን አቻውን አጥተንለት ነው? በጭራሽ ! አንድ ብቻ ሣይሆን ብዙ ቃላትን ማሠለፍ እንችላለን። ምነው ታዲያ ቢባል ግን ሀቲቱ ብዙ ነው።
  የሰው ልጅ እዚህች ምድር ላይ መኖር ከጀመረ በኋላ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፤ ድካሙን ያቃልለት ፣ ውጣውረዱን ይቀንስለት ዘንድ በየዘርፉ አዳዲስ ነገሮችን እየፈበረከ ከትውልድ ትውልድ ሲቀባበል ፣ ተቀባዩም በተሰራለት ላይ አዲስ ጨምሮ ፣ እያሻሻለና እያዘምነ ዛሬም ድረስ በዚያው ሒደት አለ ።  መጀመሪያ መለስተኛ ቤት አሣህሎ የፈጠረውን   ኮምፒውተር በአካልም በአቅልም እየጠረበና እያሠላ አሻሽሎ ኪሳችን የሚሸጎጥ አድርጎታል ። አህያ የሚልሰውን አሞሌ ጨው ወዲያ ጥለን በወርቅና ብር ስንገበያይ ከርመን ምናባዊ ገንዘብ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ላይ ምናባዊ ገንዘብ ከሁሉ በተሻለ ትልቅ አቅም አለው። ሰውም ተማምኖ ይለዋወጠዋል። የሚጨበጥና የሚዳሰስ ነገር ላይ ካለን እምነት የተነሳ ነበር ያ ሁሉ ግድንድግ ነገር ዛሬ እንዲህ ሳቅ የሚያጭር ሊሆን ፤ በጊዜው መገበያያ ሆኖ ያለፈው።   ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ የሚዘወር እስካይመስል እድገትና ለውጡ ዕለት ተዕለት እየተምዘገዘገ አስደንጋጭ ደረጃ የደረሰ ከመሆንም አልፎ የሰውን ልጅ ህልውና ወደ መጋፋቱም ደርሷል።  እነ በይነመረብና መተግበሪያዎች ዲጂታሉ ዘመን አመጣሽ ዓለም ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ባህል ወግና ትውፊትን በማደብዘዝ የራሱን አሻራ እየተካ ነው። ጊዜ ቆጣቢና ህይወት አቅላይ አማራጮች ለከትና ገደብ ሊበጅላቸው ይገባል። በዚህ ልክ ከላባም ሲቀል ተገቢ አይመስለኝም። ጌጁን አልፈን ዳግም ወደ “ ሀ “ ፣ ወደ “ 0 “ ጫፉን ተሻግሮ  ድጋሚ እንደማንሰራራት ነው። ይሄ የማይመስል ቢሆንም  ትልቅ ሀቅ ነው፤ ምክንያቱም የዓለምን ስርዓተ አካሄድ በቅጡ ላጤነ በግልፅ የሚታይ ነውና ።
   ድሮ ያኔ በጊዜው በቆዳ የተሰራን ልብስ ዲዛይኑን ኮርጆ ፤ በዛሬው ዘመን ጨርቅና መሣሪያ አሥመስሎ በመሸመን ደርቦ መንጎማለል ፤ በዘመኑ እንጨት የታነፀን የጥንታዊ ሞዴል ታንኳን ዳግም ፈብርኮ እየቀዘፉ መደመም ፣ የጥንቱን ሙዚቃ በዘንድሮው ቴፕ ከፍቶ የጥንቱን ከዛሬው ዳንስ ቀይጦ መጨፈር ነው የተያዘው። አዲስ ይምሰል እንጂ አመዛኙ የታደሰ የተከለሰና የተበረዘ ነው።
   በቃን የምንለውን ጠንቅቀን ማወቅ ግድ ይለናል፤ እስኪያቅረን መጋቱ ትርፉ ሲተፉ ማደር ነው። አንዳንዱ እድገትና መሻሻል ገደብ ሊኖረው ይገባል። አሊያ ከልኩ ያለፈ እንደሆን መጃጀት ይመጣል፡፡ ዳግም ወደ ጨቅላነት ተመልሶ ጭቃ ማብኳት ይሆናል፡፡ ወደ ፊት እየመሠለን ወደ ኋላ የምንሄደው  የስርዝ ድልዝ ጉዞ ... ተጨባጭ ሆኖ መክረም ያለበትን አየር ላይ አንጠልጥሎ ውል አልባ ማድረግ ሠነፍ እረኛ ከሩቅ ይመልሳል እንዲሉ አበው ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው። ማን ያውቃል ወደ ድጉሱ ብራና እንመለስ እንደሆን ? አካሄዳችን ግን የዚህ አይነቱን ክፍተት በመተው ፍንጭ የሚሰጥ ነው። ቴክኖሎጂ ለብዙ ጉዳዮች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ፣ ከባዱንና የተወሣሠበውን በማቃለል ምስጉንነቱ እንዳለ ሆኖ አስከትሎ የሚያመጣቸው አሉታዊ መዘዞቹም አሸን ናቸው። እኔ ዛሬም ቢሆን  የምወግነው ከአበው ጎን ነውና  “ አሣን መብላት በብልሃት “ ብዬ በቃላቸው ተሠናበትኩ።

Read 1055 times