Saturday, 27 January 2024 00:00

የሱሰኛ የአንድ ቀን ግለ-ታሪክ

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(3 votes)

ስለ ሱሰኞች መፃፍ ይፈልጋል፡፡ ስለ ጫታቸው፣ ሲጋራቸው፣ ሀሺሻቸው፣ ቁማራቸው፣ የወሲብ ረሀባቸው፣ ስካራቸው…ስለ ሁሉም እብደታቸው መፃፍ ይፈልጋል፡፡ ግን እንዴት አድርጎ፤ አንድም ቀን ጫት ቅሞ በምርቃና መደንዘዝን አያውቅበትም፣ ሲጋራ አጭሶ ራስን የማንደድ ብልሀትን ከንፈሮቹ አይረዱትም፡፡ ስካርን አያውቀውም፣ እብደቱን አልደረሰበትም፡፡ ሆኖም ያያል…መሰሎቹ እሱን መምሰል አቅቷቸው፣ ሰውነታቸው ከብዷቸው፣ ማሰብ ፈልገው ከምክንያት የራቀው ጭንቅላታቸውን ሲያስጨንቁት ያያል፡፡ ሁሌም ይገረም ነበር፡፡ የገዛ ሱሳቸው በላያቸው ላይ ያጠለቁትን ስጋቸውን እያሳሳቀ እየቀማቸው፣ ቤት፣ ንብረታቸውን ከነቤተሰቦቻቸው እያጡም ቢሆን፣ ከያዛቸው ሱስ ጋር መከራቸውን ሲበሉ አስተውሏቸዋል፡፡
የሚኖረው ኮተቤ ነው፡፡ ኮተቤ፡፡ ተዓምራዊ መንደር፡፡ ብዙ ጉድ የያዘ ከተማ፡፡ የሚፈልጋቸው ሱሰኞች በሙሉ ካጠገቡ አሉለት፡፡ ማወቅ የሚፈልገውን ነገራት በሙላ የሚተርኩለትም የሚኖሩለትም ወጣቶች በብርሀን ፍጥነት ማግኘት ይችላል፡፡ እነሱ እንደ እሱ አይደሉም፡፡ ጠዋት ተነስተው የሚገኙት የስራ ገበታቸው ላይ ሳይሆን የአብዲ ወይም የሰያ ጫት መሸጫ መስኮት ስር ነው፡፡ በልምድ ይበልጡታል…በስንፍና ልምድ…በሱስ ልምድ፡፡
እስከዛሬ ሲፅፍ የነበረው ነገር በሙሉ የህይወትን ብርሀናማ ፀዳል የሚሳበክ ድርሰት ብቻ ነው፡፡ የህይወትን ጨለማ የትኛውም ደራሲ ቢሆን ለመሰሉ ማስተላለፍ የለበትም ብሎ የሚያምን ሰው ነው፡፡ ደስተኛ ሆኖ ነው ያደገው… አሁን ደስተኛ ነው፡፡ ሆኖ ም አዕምሮው አዲስ ነገር አምጣ እያለው ነው፡፡ ጨለማው ውስጥ አንድ ጊዜ እጅህን ከተህ አውጣው የሚል ድምፅ ማድመጥ ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ ወስኖ የማይነካው ያለውን የህይወት ጀርባ በቀስታ ሊዳብስ አስቦ ነው፣ ጠዋት ላይ አይኖቹን የገለጣቸው፡፡
ከቤቱ ወጥቶ የመንደሩ ድድ ማስጫ ጋር ሄዶ ቆመ፡፡ አንድ ወሳኝ ሱሰኛ ነው የሚፈልገው፤ የሱስን አለም ለአንድ ቀን ብቻ የሚያስጎበኘው፡፡ ሱሰኛን መለየት አይከብደውም፡፡ አብዛኞቹ አረማመዳቸው ብቻ ያሳብቅባቸዋል፡፡ ከሆዳቸው እጥፍ የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ አይናቸው የደፈረሰ ሆኖ የፀሀይ ብርሀን ከነመፈጠሩ ያልጎበኘው ነው የሚመስለው፡፡ ጥርሳቸው በሙሉ የተበላሸ ነው፡፡ ጠዋት ላይ የሁሉም መልክ ላይ የመኮሳተርና የጥልቅ ትካዜ ስሜት ነው የሚታይባቸው፡፡ የሚያስተክዛቸው የእለቱን የሱስ አድቬንቸራቸውን እያሰላሰሉት እንደሆነ ይገባዋል፡፡ ጫታቸውን ሲያገኙ ነው የመጀመሪያ ፈገግታቸው ወገግ ማለት የሚጀምረው፡፡ ስሜት ያላቸው አይመስሉም፣ አንድ ቦታ ላይ ፍዝዝ ብለው ሲያያቸው የሆነ ነገር የገባቸው ይመስለው ነበር፡፡ ምልከታው ግን የተሳሳተ መሆኑን ያወቀው በቅርብ ነው፡፡
ከርቀት በሰፈር ስሙ ግቤ የሚባለውን ሰው ተመለከተው፡፡ የግቤ ፊት ለየት የሚያደርገው ሁሉም ሰላሳ ሁለቱም ጥርሶቹ አሉ፤ ነገር ግን አንዱም መጀመሪያ እንደተፈጠረ ሆኖ እንዲኖር አልተፈቀደለትም፡፡ ሁሉም ጥርሶቹ የተሰባበሩ እና የተፈረካከሱ ናቸው፡፡ ደራሲው ይህን ሲመለከት መረጋጋት ውስጥ ገባ፡፡ ከግቤ ጋር ይህን አወዛጋቢ አለም ለአንዲት ቀን ሊያጣጥም ወስኗል፡፡
“ግቤ?” ብሎ ጠራው፡፡
ግቤ በዛ በጠዋት ስሙን ሰምቶት የማያውቅ ይመስል የተጠራበትን ቦታ ጥሎ ሌላ ቦታ ላይ አይኖቹን አስማሰናቸው፡፡ እንደምንም ብሎ ደራሲውን አየው፡፡ እየሮጠ ተጠጋው…
“ወዬ አለቃ….ምን እኮ ገና አይናችንን አልገለጥንም፡፡ ለዛ ነው የተሰወርሽብኝ፡፡”
“ዛሬ የት ነው የምትውለው?”  ደራሲው ጠየቀ፡፡
“ምን ደግሞ ለመዋል….ዛሬ ያሰብኩት መሰሉ ጋር ለመቃም ነው፡፡” ዞር ብሎ መንገድ ዳር  ቡና የምትሸጠው መሰሉን ጠቆመው፡፡
“ሌላ የተሻለ መቃሚያ ቦታ ማግኘት አይቻልም…?” ደግሞ ጠየቀ ደራሲው፡፡
“ምን ፍሉሱ ካለ ወሳኝ ቦታ ይታጣል ብለሽ ነው፡፡ ማሂ ጋር ብንሄድ ነገር አለሙ ረሀ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሴፍ ስለሆነ ከፈለግን ሽሻችንን አፈንድተን ቀናችንን ማስዋብ እንችላለን፡፡”
“ አሁን መሄድ እንችላለን፡፡ ዛሬ ካንተ ጋር ነው መዋል የፈለኩት፡፡ መንደሩ ውስጥ ያለውን ነገር ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ይህን የምታደርገው ግን ስራ ከሌለህ ብቻ ነው፡፡”
“ይሄው እኮ ስራውን አንተ ይዘህው መጣህ፡፡ አሁን እዚህ ጋ ተዘርግቶ የምታየው የተማረ ወጣት እኮ ቁጭ ብሎ እየጠበቀ ያለው አንተን መሰል ሀብታም መጥቶ ያነሳቸውና ከዛም እግሩ ስር ቁጭ ብለው ጫት እየተረበሱ ማጫወት ነው ስራቸው፡፡ የዘንድሮ ቃሚ የሚሰራው ስላጣ የሚያነበው ራሱ ነገ ምን ጨዋታ አለህ ሲባል ምላሱ እስኪደክም ድረስ አውርቶ ለማታው ጨብሲ የሚሆን ጥቂት ጨላ ለመቀበል ነው፡፡ ለማንኛውም…ዛሬ አንተን ስላገኘውህ ደስ ብሎኛል፡፡ ሌላዋን ጭዌ ጀበን ጀበን እያደረግን ብናወራት ምን ይመስልሀል?”
በጠዋቱ የጀበና ጫት ሊቅሙ የማሂ ድብቁ ጫት መቃሚያ ቤት ገቡ፡፡ ግቤ በኩራት እየተጀነነ ነው የገባው፡፡ ከብዙ ዘመን በኃላ ማሂ ጋር እንደሚቅም ሲያስብ ውስጡ እንደ ሰማይ ሰፍቶበት አረማመዱን ቀየረበት፡፡
እንደተቀመጡ ማሂ ከአንዲት ጓዳ ወጣ ብላ ሰላምታ ሰጠቻቸው፡፡ ግቤ የሚያረገውን ሲያሳጠው ደራሲው በግርምት እየተከታተለ ነው፡፡
“ሁለት ገለምሶ፣ ሁለት ሊትር ውሀ ሁለት፣ ለውዝ ዝም ብለሽ ሶስት አድርጊው…ከዛ ውጭ….ኦ ዋናውን ነገር ረስቼው አስር ኒያላና…ኒያላውን የምታፈነዳልኝ አንቺን የመሰለች ቆንጆ ቸከሰ ብታመጭልኝ ቀኑ ቦታ ቦታውን ያዘ አይባልም….?”
ማሂ እየሳቀች ወደ ውስጥ ዘለቀች፡፡ ግቤ ወደ ደራሲው ዞሮ …”ሳትወደኝ አትቀርም፣ እንደዚህ ለማንም ፈገግ ስትል አይቻት አላውቅም፡፡”  
ደራሲው ግቤ ስለሚያወራው ነገር ጉዳዩ አይደለም፡፡ እሱ የሚፈልገው ጫቱን ቅሞ ምን እንደሚያደርገው አፍጦ መጠበቅ ነው፡፡ ሲጋራውን አጭሶ የቱ የሰውነቱን ክፍል እያነቃለት እንደሆነ በጥሞና ማድመጡን ነው የሚፈልገው፡፡ እንዲያውም አሁኑኑ ግቤ ብድግ ብሎ እንዲሄድለት ይፈልጋል፡፡ ሆኖም አሁን ግቤ አለሙን እየቀጨ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የትኛውም የምድር ሀይል ከተቀመጠበት የሚያነሳው አይመስልም፡፡ ስጋቱ ለደራሲው ብቻ ሳይሆን ለማሂም እንደሆነ አስቦ እየመጣ ያለው የጫት አጎዛ ላይ አይኖቹን ተከለ፡፡
ጫቱ ቀረበ….ግቤም እያገላበጠ ካየው በኀኃላ…” ፐ ክትፎ ጫት ነው፡፡ ይሄንንማ በከባድ ሜዲቴሽን ውስጥ ሆነን ነው የምንቅመው፡፡ ጭዌም በሻንጣ በሻንጣ እኛ ጋር አለ፡፡ ዝም ብለሽ ብቻ የመረጥሽው ሀሳብ ላይ ክሊክ ማድረግ ነው፡፡”  
ደራሲው የውሸቱን ፈገግ ብሎለት የመጀመሪያውን የጫት እግር ከፌስታሉ ውስጥ መዞ አወጣው፡፡ አገላብጦ ተመለከተው፡፡ እያገላበጠ ፈራው፡፡ እያገላበጠ ተመኘው፡፡ ከቀንበጡ ላይ ያለውን ለጋ የጫት ቅጠል በጥሶ ግቤ ሲያደርግ እንዳየው የግራ መንጋጋው ጋር ሄዶ ከወተፈው በኃላ ዝም ብሎ ይድጠው ገባ፡፡ መረረው፡፡ እሬትነቱ ግቤ ጋር ተፅዕኖ የፈጠረ መስሎት ዞሮ ግቤን ሲያየው ግቤ ሆዬ ሩብ የሚያህለውን ጫት አፉ ወስጥ ሞጅሮ ጫት ባልጨመቀው ክፍቱ የአፉ ክፍል በመታገዝ ከማሂ ጋር ጭልጥ ያለ ቀደዳ ውስጥ ገብቷል፡፡
ደራሲው አንዲት ቃል ሳይተነፍስ እስከ አስራ አንድ ሰዓት ድረስ ሲቅም ዋለ፡፡ ድንገት ግን አስራ አንድ ሰዓት ላይ የምርቃናው ወጀብ መጥቶ ጭንቅላቱን ተቆጣጠረው፡፡ ሁለት ስሜት ፈጠረበት…አንደኛው ተነስተህ ብረር ብረር የሚል ነው፡፤ ሁለተኛው ደግሞ በጫት ቤት ውስጥ ያሉትን ቃሚዎች ከትካዜያቸው አባነህ የገባህንም ያልገባህንም ለፍልፍ የሚል ስሜት፡፡ ግቤ ወጧ እንዳማረላት ሴት አንድ ቦታ መቀመጥ አቅቶት በመቃሚያ ቤት ውስጥ ሽር ጉድ ይላል፡፡ ግቤን ጠልቶት ሊሞት ደረሰ፡፡
ቀኑን ሙሉ ግን እንደ ላም ያስገባውን የጫት ቅጠል ሲያመሰኩዋ አልዋለም፡፡ ማስታወሻ በየማህሉ ይፅፍ ነበር፡፡ ብዙ ነገሮች ታዝቧል፡፡ ብዙ ነገሮች፡፡ አንዱ ቃሚ ካንዱ ቃሚ በባህሪም ሆነ በሱስ ፍጆታው እንደማይገናኝ ተረድቷል፡፡ አንደኛው ቃሚ በትካዜና በምናብ አለምን ሲያስስ አንደኛው ደግሞ ለማስቆም የሚከብድ ርዕስ አንስቶ የሰዎችን ጆሮ ሲያስስ ይመለከታል፡፡ አንደኛው ጫቱም ሲጋራውም በሙላ እኔ ጋር ነው የሚል ይመስል ቀኑን ሙሉ ሁለቱንም የሱስ ቀንዲሎች አፉ ውስጥ ሲያመላልስ ውሎ ወደ ከሰዓት ላይ የሚናገረው ጠፍቶት አንዲት ቃል ህይወቱን ወደነበረችበት የምትመልስለት ይመስል ቃላት ሲያስስ ይመሽበታል፡፡ ሌላው ያለችውን ሩብ ጫት ቀስ ያለ በብዙ ውሀና ሲጋራ አጣጥሞ ይቅማታል፡፡ እንደዚህ አይነቱ ቃሚ የመጨረሻዋን ጫት ከፌስታሉ ውስጥ ካስወጣት የዛ ጫት ቤት ቆይታው እንደሚያከትምለት ስለሚረዳ በምንም አይነት ታሪክ ጫቱን ጨርሶ አይወጣትም…ለክብሩ ሲል አንድ እንጨት ያስተርፋል፡፡ በአጠቃላይ ጫቱ ሰዎቹን ከአንድ ገፀ ባህሪይ ወደ ሌላኛው እየወሰደ ሲያንገላታቸው ደራሲው በጥንቃቄ አስተውሏቸዋል፡፡
ደራሲው በጣም መረቀነ፡፡ ሀሳብ በሀሳብ ላይ እየተደራረበ ርቀቱን ማስረዳት የማይችለው የዓዕምሮ ጥልቀት ውስጥ እየገባ ስለብዙ ነገሮች አሰበ፡፡ ሆኖም እጅግ በጣም እያሰበ በሄደ ቁጥር ጭንቅላቱ ለብቻው እግር አውጥቶ እንዳይሮጥበት ሰጋ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ማሂ ላይ በጣም እያፈጠጠባት መሆኑ የገባው ሌሎቹን ቃሚዎች መከታተል የጀመረበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ልጅቷ በሽሻው ጭሽ መካከል ያንን ድሪያ አድርሃ ከሰል ስትማግድ በምርቃና ውስጥ ላያት ግብፅን ካነጿት አማልክት መካከል አንዷን መስላ ነው ቁጭ የምትለው፡፡ ውበቷ ከምርቃናው ጋር እንዴት ሆኖ እያደገ እንደሄደ ግን ደራሲው እስካሁን ማስረዳት አይችልም፡፡ ለግቤ ሂሳብ ከፍለው ወደ ሁለተኛው የሱስ ክፍለጊዜ እንዲሻገሩ ሀሳብ ጠብ አደረገለት፡፡
ሂሳባቸውን ከፍለው ከጫት ቤቱ እየወጡ ደራሲው ግቤን ጠየቀው…
“ምርቃናው ትንሽ ሳይከብደኝ አልቀረም፡፡ ጨብሲ ነገር የት እናገኛለን?”
“አረ ዘመዴ በዚህ ጉዳይ አያሳስብሽ እኔም ወደዛ እየመራሁሽ ነው፡፡” ግቤ ጥያቄው ከደራሲው በመምጣቱ እጅግ ተደስቷል፡፡
ወደ መጠጥ ቤቱ እየሄዱ ባሉበት ሰዓት ላይ ደራሲው በመረቀነ አይኑ የሚያልፍ የሚያገድመውን ህዝብ በመመልከት ላይ ነበር፡፡ ሁሉም የመረቀኑ መሰለው፤ ወይም ደግሞ በጣም እያፈጠጠባቸው መሰለው፡፡ ሁሉም ያሳዝናሉ፡፡ የገባበት ምርቃና ለሰው ልጅ በሙላ መፍትሄ የሚሰጥ እንዲመስለው የሚያደርገው ነው፡፡ ሆኖም ዝም ብሎ ከመቀደዱ በፊት ሁሉንም ነገሮች በጥሞና ሞክሮ መጨረስ አለበት፡፡ አሁን መጠጡን ከሲጋራው ጋር የሚያጋባበት ሰዓቱ ነው፡፡ ግቤም ማየት የሚፈልገው ቦታ ነው እየወሰደው ያለው፡፡ የሰፈሩ መጠሪያ ስያሜ አንድ ፌርማታ ይባላል፡፡
ብዛት ያላቸው ሴተኛ አዳሪዎች በገፍ የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡ ያለፈለት ዱርዬ ከቃመ በኋላ አለሙን የሚቀጨው እዚህ የፌርማታ አድባር ላይ ነው፡፡ ተያይዘው አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ገቡ፡፡ ጥቂት ብርሀን ያለበት፡፡ የጨለማው ግዝፈት ነፍስን የማጨለም አቅም አለው፡፡ ብዙ ጠጪ ስላልመጣ ከተደረደረው ወንበር በላይ ሴቶች ብቻ ነበሩ የሚታዩት፡፡
ወንበር ስበው ተቀምጠው ድራፍት መለጋት ጀመሩ፡፡ ደራሲው ስካሩ እየገባለት በሄደ ቁጥር ሊቆጣጠረው ያቃተው ደስታ ውስጥ ገብቶ ራሱን አገኘው፡፡ ተነስቶ ከግቤ ጋር እየጨፈረ ራሱን አገኘው፡፡ ድንገት ግቤ ጠጋ ብሎት አንድ ነገር ሹክ አለው….
“ከአቶ ፀጋዬ ጋር ትተዋወቃላችሁ እንዴ…?” ብሎ ጠየቀው፡፡
“ማናቸው አቶ ፀጋዬ… ? “ ብሎ ደራሲው ጠየቀው፡፡ግቤ አንድ ጊዜ ከት ብሎ ከሳቀ በኋላ ከደራሲው አይኖች ለጥቂት ደቂቃዎች ተሰውሮ ተመልሶ መጣ፡፡ የደራሲውን እጅ ይዞ ከመጠጥ ቤቱ ወጡ፡፡ ወደ አንድ ድብቅ የሰፈሩ መታጠፊያ እስኪደርሱ ድረስ ደራሲው ምንም የተናገረው ነገር አልነበረም፡፡ ጨለማው ውስጥ እንደገቡ ግቤ ከኪሱ ውስጥ በሪዝላል በደንብ ተደርጎ የተሰራ ሃሺሽ አውጥቶ ለደራሲው እያሳየው ይህን አለው…
“እንግዲህ ከአቶ ፀጋዬ ጋር ዛሬ በሰፊው ትተዋወቃላችሁ፡፡ “
ሃሽሹን ለኩሶ ሰጠው፡፡ ደራሲው ተቀብሎ ግቤ ሲያደርገው እንደነበረው እያደረገ በሰከረ ጭንቅላቱ ውስጥ ሌላ እንግዳ ስካር አስተናገደበት፡፡ አጭሰው እንደጨረሱ መራመድ ሲጀምሩ ደራሲው መራመድ አቃተው፡፡ ሰማዩ በላዩ ላይ እንዳይናድበት በመፍራት እጆቹን ወደ ላይ አነሳቸው፡፡ እውናዊው አለም መልኩን ቀይሮ ሃሽሹ አይኑና ጆሮው ሆኖ መስራት ጀመረ፡፡ ከዚህ ኋላ ወደ የትም ባይሄድና አልጋው ላይ ተወርውሮ ቢወድቅ ተመኘ፡፡ ሆኖም አሁን ከግቤ ጋር ነው፡፡ ግቤ ደግሞ ገና ምሽቱ አልተጀመረም እያለው ነው፡፡
በሰመመን እየተራመደ በአስፓልቱ ላይ የሚደባደቡ ጎረምሶች ህልም መስለው ይታዩታል፡፡ እንደምንም  ብለው መጠጥ ቤት ውስጥ ገቡ፡፡
አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል፡፡ ህይወት ድምቀት በድምቀት ሆናለች፡፡ ሴቶቹም ከምንም በላይ ገነው ተውበዋል፡፡
ሁሉም በራሱ ዳንስ ውስጥ እያበደ ነው፡፡ ደራሲው ግን ጥጉን ይዞ በመከራ እየተገለጠ ባለው አይኑ በገዛ እጁ ያመጣውን ቅዠቱን በመማግ ላይ ነው፡፡ ድንገት ራሱን ጠላው፡፡ ራሱ ራሱ እሱን ጠላው፡፡ ጥላቻ በጥላቻ፡፡ የገዛ ሰውነቱ ራሱ “ምን ብበድልህ ነው እዚህ መከራ ውስጥ አስገብተህ የወረወርከኝ?” እያለው ነው፡፡ ደክሞታል፡፡ አይኖቹ ተጨፈኑ፡፡
ጠዋት ላይ አይኖቹን ሲገልጥ በጨለማ ነከቦ ከአንድ አልጋ ላይ ተጋድሞ ራሱን አገኘው፡፡ በድንጋጤ ከተኛበት ተስፈንጥሮ ተነሳ፡፡ ከአልጋው ላይ ወረደ፡፡ ፊለፊቱ በሩን ስላገኘው ከፈተው፡፡
 ከደጅ የገባው ብርሀን ተደብቆ የነበረውን ገሀድ አወጣው፡፡ ከአንጋው ላይ ብቻውን አልነበረም፡፡ አንዲት ጠይም ሴት ብርሀን ባጭበረበረው አይኖቿ እያየችው በሩን እንዲዘጋው በመጠየቅ ላይ ናት፡፡ በድንጋጤ በሩን በላይዋ ላይ ዘጋው፡፡ ጊዜ አላባከነም፡፡ በፍጥነት ያንን መጠጥ ቤት ለቆ ወጣ፡፡ ጊዜ አላባከነም፡፡ በፍጥነት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡  አልጋው ላይ በትኖት የሄደው ወረቀቱን አንስቶ ብዕሩን ማድማት ጀመረ….እንዲህ እያለ….
ሱስ፡፡ ለስቃይ የተበጀ ደስታ፡፡ ለመከራ የተበጀ እረፍት፡፡ ለእብደት የተበጀ ጤነኝነት፡፡ ባዶነት ውስጥ ምክንያታዊነትን ፍለጋ የገዛ ነፍስን መቧጠጥ፡፡ ህመም፡፡ መክሰር፡፡ መርከስ፡፡ ከጊዜ ጋር መቋመር…ጊዜን ገሎ አብሮ መሞት፡፡ ድካም፡፡ ድካም፡፡ ድካም፡፡ ድካም፡፡...፡፡…፡፡


Read 1779 times