Sunday, 28 January 2024 20:19

የቴዎድሮስ ታደሠ የመዝጊያ ስንኞች

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

 ‹‹አልገባኝምና መቼም አልፈታውም፤
የምኞትን ፈረስ፣ ልጓም አይገታውም፤››


ቴዎድሮስ ታደሠ 1977 ዓ.ም ላይ በ‹‹ሉባንጃዬ›› አልበም ሥራውን ጀመረ፤ የዜማ ደራሲ እንደሆነ ይታወቃል፤ ‹‹ሉባንጃዬ››፣ ‹‹ምን አሉ››፣ ‹‹ዝምታ›› እና ሌሎች የዜማ ድርሰቶቹ ናቸው፤ የግጥም ሀሳብም ያቀርባል፤ ዜማ ሲያጠና ጎበዝ ነው፤ የአስቴር አወቀን ‹‹እትቱ›› በመድረስም ሆነ በማጥናትና ማስጠናት ከአበበ መለሠ ጎን እንደነበር አይዘነጋም።
በግሌ ከሚያስደንቀኝ ጎኑ መካከል፣ የበርካታ ዘፈኖቼ የመዝጊያ ስንኞች የመላውን ዘፈን ሀሳብ የሚሸከሙ መሆናቸው ነው፤ ቴዎድሮስ ታደሠ በመዝጊያ ስንኞቹ አስረግጦ ማለፍን ያውቅበታል። ንሱ በዚህ! ተወዳጅ ከሆኑ ስራዎቹ የጥቂቶቹን ዘፈኖች የመዝጊያ ስንኞች እንመልከትማ፡-
1ኛ፡-   
‹‹አዙሮም ካስተዋለ፣ መከራን ያልፋል ካለ፤
ቢቀጥንም አንገት ነው፣ ራስን ከቻለ፤››
የላብ አደሩን፣ የሠርቶ ነዋሪውን፣ ራሱን ለመቻል የሚውተረተረውን፣ በራሱ ተስፋ የማይቆርጠውን…. ሰው ሕይወት የተረከበት ‹‹ልደሰት በወዜ›› የተሰኘ ድንቅ ዘፈን ውስጥ የተካተተ የመዝጊያ ስንኝ ነው ይኼ፤ ግጥም፡- ይልማ ገ/አብ፤ ዜማ፡- አበበ መለሠ፤ የሰው ልጅ ለዕለት ጉርሱ፣ ለዓመት ልብሱ ከበቃ፣ ከጠረቃ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው ባይ ነው፤ በእነዚህ ስንኞች ውስጥ፣ የራስን ቦይ መማስ፣ በላብ ማደር፣ ለራስ መኖር፣ ራስን ማሳደር…. ተካተዋል፤ ለራስ መልፋት ጉዳት እንዳልሆነ ዕሙን ነው ባይ ነው ስንኙ! በበኩሌ እንዲህ ያለ ስንኝ ‹‹ቢቀጥንም አንገት ነው፣ ራስን ከቻለ›› እንደ አባባል ሊያገለግል ይችላል ብዬ አምናለሁ!
2ኛ፡-
‹‹ጤንነትሽን እንጂ፣ የምመኝልሽ፤    ከእንግዲህስ ላንቺ፣ ጨርቅም አልጥልልሽ፤››
ከላይ የተቀነጨቡ ስንኞች ‹‹በመላ በሰበብ›› ከተሰኘ ዘፈን ገላ የተወሰዱ ናቸው፤ እግረኛ፣ ዘወርዋራ፣ ተንከላዋሽ፣ ሲያዝሏት ነካሽ፣ ሲያወርዷት አልቃሽ፣ መንታላ፣ ከልታማ… እንስት እዚህ ዘፈን ውስጥ አለች፤ ማር ሲሏት እሬት የፈቀደች፤ ታዲያ ይኼ ባለድምጽ ይበግናል፤ በግኖም አልቀረ፤ መሀል አካባቢ ላይ፡- ‹‹አንቺ ሰው ለመንገድ ትሽከረከሪያለሽ/ተይ የትም አትህጂ፣ የትም ትቀሪያለሽ›› ይላታል፤ ብስጭት ብቻ ሳይሆን ቁጭት አለ ውስጡ፤ ለእሷም/ለመውደቂያዋም ያዝናል፤ ለአመሻሽዋ ስጋት ልቡ ይገባል፤ በኋላ እንደማትመለስ ያውቃል፤ ወደሱ እንዳታይ ልቧን የቀየዳትን ልጓም አንጣር፣ በአንጣር፣ ገጥ በገጥ መመርመር ይይዛል፤ ወላ ‹‹የኔው እሹሩሩ የኔው ማቀናጣት፤ ይኼው መንገብገቤ አበቃኝ ለማጣት›› ይሰኛል። ቢያስራት ቢሰራት ውልፍች አልልም አለችው፤ ፍቅር የመታደል እንጂ የመታገል ጉዳይ እንዳልሆነ ሲገባው፣ ‹‹ጤንነትሽን እንጂ፣ የምመኝልሽ፤ ከእንግዲህስ ላንቺ፣ ጨርቅም አልጥልልሽ፤›› በማለት ይደመድማል!
#3ኛ፡-
‹‹ማሰሪያ ፋሻውን ፈልገን፤
እንግዲህ ሰባራው ይጠገን፤››
እነዚህ ‹‹ፍቅሩን አይንፈገን›› ከሚል ዘፈን የተወሰዱ ስንኞች ናቸው፤ ግጥም፡- ተመስገን ተካ፤ ዜማ፡- ሱራፌል አበበ፤ በዚህ ዘፈን ውስጥ በጅምር ሊቆም የዳዳው ፍቅር ወለል ብሎ ይታያል፤ አበበ ከመባሉ ሊረግፍ ይሠራራዋል፤ አልጎመራም፤ ግና ሊበሳና ይቃጣዋል፤ ጀማመሩት እንጂ አልዘለቁትም፤ ቆረሱት እንጂ አልጎረሱትም፤ ቀመሱት እንጂ አላጣጣሙትም፤ ከአፍ ያልወረደ ለጉሮሮ አይጥምምና ግና ጅማሮ ላይ ናቸው፤ ታዲያ ባለድምጹ በጅምር ካላሸነው፣ ለምርኩዝ ያበቃናል እያለ ይገኛል። እንግዲህ እግዚሔር ያበጃጀው፤ ሰባራችንን ይጠግን፤ ጥበቃው አይለየን፤ ፍቅራችንን እነበረበት እንመልሰው ነው ቅሉ!  
4ኛ፡-    
‹‹መውደድ ያገሬ ሰው፣
ፍቅር አይገዛ፣ ደሞ እንዳልዋሰው፤››
ከ‹‹ባልቦ በድሪዋ›› ዘፈን የተቀነጨበ፤ ግጥም፡- ዓለምጸሐይ ወዳጆ፤ በዚህ ዘፈን ሠርክ ይማጠናታል፤ እንኳን እሷንና ታናሽ እህቷን ሲያይ እንደሚወበራ ያብራራል፤ አልሆነም፣ ከሰንበት ውጭ አያያትም፤ እሷን፣ አልቦዋን፣ ድሪዋን፣ የአንገቷን ግማድ… ሁሉ ነገሯን ይወዳል፤ ቀዬዋ ሩቅ ነው፤ ተጨበጠ፤ ጣመነው፤ ስጋት ልቡ ገባ፤ ተብከነከነ፤ ዝም፣ ክልትም፣ ውሃ አይላመጥም ሆነበት ነገሩ፤ በኋላ ‹‹መውደድ ያገሬ ሰው፣ ፍቅር አይገዛ ደሞ እንዳልዋሰው›› ሲል መልዕክት ሰደደ።   
5ኛ፡-
‹‹ጥማቴ ሰው ባይሆን፣ ርሃቤም ችግሬ፤
ሠርቶስ የሚያበላ፣ ነበር እጅና እግሬ፤››
ይኼ ስንኝ የተወሰደው ከ‹‹ምናሉ›› ዘፈን ሲሆን፣ የዜማ ደራሲው ቴዎድሮስ ታደሠ ነው፤ የግጥም ደራሲው ደሞ ይልማ ገ/አብ ነው፤ 1983 ዓ.ም፤ ሠርቶ መብላት፣ ውሃ መጠጣት አላቃተውም፤ ፍላጎቱ ከከርስ ይዘላል፤ ሰው የሌለበት እህል ውሃ ድካም ነው፤ ትርጉም አልባ፤ ‹የጥርሷ ንቅሳት ላዩን ያማረው፤ ያንገበግበዋል ልክ እንደ እግር እሣት›፤ ሞሰቡ አልተራቆተም፤ ማድጋው ጥርኝ ውሃ አላጣም፤ የሰው ድሃ ነው፤ ራሱን ለማኖር፣ ራሱን ለማሳደር ቅንጣት ታህል የአካል ድካም አልተሰማውም፤ ግና ሆዱ ጉርስ አላሻም፤ የልቡ መሻት ፍቅር ምግቡ እንዲሆን ነው!!          
ለአባባል የቀረቡ ሌሎች የቴዎድሮስ ታደሠ ስንኞች፡-
‹‹አፍቃሪዋ በዝቶ፣ ልቧን ስለነሳት፤
ፈረሰኛ ወስዶ፣ እግረኛ መለሳት፤››
(ወረት ልቧ ገብቶ መጥፎ ስፍራ ወደቀች ነው)
‹‹ከጥንት ጀምሮ፣ ስናየው የኖርነው፤
ሲነድ ሲቃጠል፣ የሚስቅ እሣት ነው፤››
(ሁለቱ ስንኞች የገሞራው ዮሐንስ ናቸው፤ ተመስገን ተካ አውዱን ጠብቆ አስግሯቸው ነው) ‹‹አልገባኝምና መቼም አልፈታውም፤የምኞትን ፈረስ፣ ልጓም አይገታውም፤››
(እቴ በገላሽ፤ ‹‹ጽጌረዳ›› አልበም)
‹‹እንደ ወላጅ እናት፣ ሳዝንልሽ ከሆዴ፤
ሰውነትሽን ጥለሽ፣ አሞራ ሆንሽ እንዴ፤!››
(ደራሲ፡- አያ ሙሌ!!)
በአጠቃላይ፣ ከላይ የተጠቀሱ መዘርዝሮች የቴዎድሮስ ታደሠ ዘፈኖች የመዝጊያ ስንኛቸው ላይ የታለመውን ሀሳብ አስረግጠው የሚናገሩ መሆናቸውን ነው፤ ዘፈኖቹ በባሕሪያቸው አስረግጦ፣ ደንግጎ፣ ውሳኔ አስተላልፈው ማብቃትን ታድለዋል። አመሰግናለሁ!

Read 204 times