Saturday, 27 January 2024 00:00

“ከእንግዲህ ሰው ሆኖ ለሚወለድ ይብላኝ“

Written by  አጥናፉ አለማየሁ
Rate this item
(0 votes)

የወንድሙ ገዳን «አሌፍ ቤት» መጽሐፍን እያነበብኩ ነው። ስጨርሰው ይሄ «ድንቢጮ»የተባለ ሰውዬ ሊያስበጨኝ ወይም ሊያበጭጨኝ፤ ሊያዳብረኝ ወይም ሊያደናብረኝ ይችላል ብዬ ገመትኩ። ማንበቤን ግን አላቋረጥኩም፡፡ የዚህ ሰሞን የማታ የማታ ስራዬ እሱው ሆኗል። ድንቢጮ በዛ አጭር ቁመቱ የሁላችንንንም የዘመናት ጉድ ተሸክሟል። የምንናገረውንም የማንናገረውንም በይፋ ፊት ለፊት ይነግረናል፡፡ አንዳንዴም ደንብ መስሎን የያዝነው ነገር ሁሉ እንዴት እንደጎዳን፣ እንዳስጎነበሰን እንዳቀጨጨና እንዳሳረነን ያስረዳናል። ጊዜ አግኝቼ የማነበው ማታ ማታ ነው ብያለሁ።
 ዛሬም አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ እያነበብኩ ነው። የሆነ ቦታ ላይ ስደርስ ሀያል እንቅፍ ጣለኝ። በህልሜ ሎሬት ፀጋዬ ይታየኛል።ጋሽ ጸጋዬ ያልተቋጨ ጋቢ ለብሷል፤ ዘርፋፋ ካቦርት ደርቧል። በአሉ ግርማ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ሰለሞን ደሬሳ፣ አቤ ጎበኛ፣ አያ ሙሌ (ሙሉጌታ ተስፋዬ) ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ሰይፉ መታፈሪያ፣ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ተከትለውታል። ሌሎች አያሌ ደራሲዎች መንገዱን ሞልተውት እየተጓዙ ነው። እኔም የሆነ ቦታ ያለሁ ይመስለኛል። ጋሽ ፀጋዬ ያለቅሳል፤ እንባው እንደ ዝናብ ወደ መሬት ይወርዳል፤ ገሞራው ጠጋ ብሎ “ምነው! ፀጋዬ ምን ሆንክ?“ የሚለው ይመስለኛል።
የአሌፍ ቤቱ ድንቢጮ አሳዘነኝ፤ ቀድሞ ስናገር የሰማኝ አልነበረም። ለፍልፌ ነበር። እኔስ ኖሬዋለሁ ሲደላኝ ሲከፋኝ - ከእንግዲህ ሰው ሆኖ ለሚወለድ ይብላኝ እያልኩ። ይኸው ሰው ሆነው ተወልደው የሚደርስባቸውን ጉድ ተመልከቱ፤ «አለፍ ቤት»ን ከጋቢው ስር አውጦቶ አሳየ። ይህ የዘመናት መከራችን ሰነድ ነው። ሁሉም ደራሲዎች አንገታቸውን ደፉ፤አዘኑ አለቀሱ፤ ገሞራው ቀጠለ፡፡ እኔ ፊቱንም መሮኝ ነው የከረምኩት፤ የጻፍኩትን አልሰማችሁም እንዴ?
“አልሰማንም“ አሉ በጋራ ድምጽ፡፡
« … እንደ ኪሩብ ሁሉ - ክንፍ አካል ቢኖረኝመች እጠበስ ነበር - በዚህ ዓለም በቃኝ ስላጣሁ ብቻ ነው - መሸሻ መድረሻ
በዚች በሽት ዓለም - የኖርኩ እንደውሻ …» አለ ጋሽ ኃይሉ፤ እንባው በጉንጮቹ የሚወርድ ይመስለኛል። ደበበ ሰይፉ ቀጠለ ፤ቱግ ብሎ ተናዷል። እኔስ እንዴት እንደሞትኩ ረሳችሁት እንዴ ? ምን ብዬ እንደመጣሁ ልንገራችሁ?
«አዎ ! ንገረን» በአንድነት ድምፅ ጮሁ፡፡
ምነው ሞተ ቢሉ
ንገሩ ለሁሉ
ሳትደብቁ ከቶ
«ከዘመን ተኳርፎ
ከዘመን ተጣልቶ።» ከዘመን ተኳርፌ ነው የመጣሁት
ሁሉም በእንባ ተራጨ። ስብሐት በቀስታ እርምጃ ወደፊት ወጣ፡፡ ትልቅ ፌስታል በእጁ አንጠልጥሏል፡፡ ጢሙ ከመሬት ጋር ይተሻሻል፤ የገዛ  የጢም ጸጉሩን እየረጋገጠ፣ እየደፈጠጠ፣  የምሬት ለቅሶ እያለቀሰ እንዲህ አለ፤
«…ማልቀስ እንጂ መበቀል ለምኔ
ሟች ወገኔ ገዳይም ወገኔ
ምን ሊረባኝ አበሻዊ ወኔ …
ማርያም አስመረይቲ
በቀን ፍዳችንን ተመከቺ
በሌት እንባችንን ተመልከቺ…
መሬት የወደቀው ጢሙ እስኪጨቀይ ድረስ አለቀሰ። በአሉ፣ ስብሐት ጎን ቀረብ ብሎት ቆመ ፊቱ በእንባ ርሷል፣ እንደገና ደግሞ ይስቃል ሁሉም ግራ ተጋብቶ ያየዋል። ከብዙ ሳቅና ለቅሶ በኋላ እንዲህ አለ፤
እንባ እንባ ይለኛል
ይተናነቀኛል…
እንባ ግን የታባቱ
ደርቋል ከረጢቱ
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እየነደደች
መከረኛ ነፍሴ።
በአሉ ይሄን ገጥሞ ስብሐትን ደግፎ እየተላቀሱ ወደ ኋላ ሲሄዱ፣ አያ ሙሌ (ሙሉጌታ ተስፋዬ) ሁሉንም እየገፈታተረ ወደፊት መጥቶ፤ «እውነት በመንበርህ የለህማ» የሚለውን ግጥሙን ድምጹን ከፍ አድርጎ፣ በምሬት ማነብነብ ጀመረ፡
እውነት በመንበርህ የለህማ
…ምነው የማርያም ልጅ የስርየት ቀንህ ራቀ
ምነው ታምርህ ረቀቀ
በየጥሻው ተወትፈን እንደተምች ስንረፈረፍ
ቅኔ በበቀቀን ሲዘረፍ
አቀርቅረን ስናንቋርር
ቅሪታችንን ስናንቃርር
እንደ ቀላጤ አከንባሎ ቁልቁል ባፍጢም ተተክለን
በእርኩስ አመዳይ ተበክለን
እንዲህ የትም ስንቀር እያየህ ዝም ካልክማ
እውነት … እውነት ከመንበርህ የለህማ!
ምነዋ መንግሰተ ሰማይ!
የምህረትሽ ቀን ራቀ?
ምነው ትንግርትሽ ረቀቀ ?
ምነው ኪዳንሽ ታጠፈ ወዝሽ ወዘናሽ ነጠፈ?
እንደ ዳጉሳ ድፍድፍ … ላቦትሽ ተንጠፈጠፈ
አሳርሽ ጠሎ አሰፈፈ…
ሁሉም የአያ ሙሌን ግጥም በጸጥታ እያዳመጠ እንዳለ፣ ድንብጮ ከምን ላይ ተወርውሮ እንድሆን ሳላየው ጀርባዬን ሲረግጠኝ፣ ወደፊት ተንደርድሬ ምድር ላይ የተደፋሁ ይመስለኛል። ለመነሳት ፈልጌ ስንደፋደፍ ድንቢጮ ጀርባዬ ላይ ተቆልሏል።
«ድንብጮ ምን ነካህ?»
«ለምን የራስህን ህልም አታልምም?» አለኝ። ከእንቅልፌ ነቃሁ። ግን በህልም ዓለም የሰው ህልም ይታለማል እንዴ? ብዬ ራሴን ጠየኩ። ድንቢጮ ያን ከመሰለ ህልም ስለቀሰቀሰኝ ተናድጄአለሁ፡፡ የተረገመ ጎደሎ፣ ምን አባቱ ያጉደለድለዋል፣ የሰው ጉድልድል፣ የተጉደለደለ ክፉ ድንቢጮ፣ የተድባጨቦጨ፣ ምን ያድቦጨቡጨዋል? እባካችሁ ያድቦጭቡጭ አባቱና...! ስድቤን ስጨርስ «አለፍ ቤት»ን ከራስጌዬ አንስቼ ማንበብ ጀመርኩ ድንቢጮ መቃብሩን የሚቆፍርበት ቦታ ላይ ነበርኩ እንዲህ እያለ ይለፈልፋል « መቃብሬን ቆፈርኩ። ምን ቆፍሬ አፈሩን ልቀብር? አፈሩን ቆፍረን ስንጨርስ የት ይቀብሩናል?…» እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። ስንቱ ተናግሬ እችለዋለሁ? አንብቡትና እንደ እኔ ወይ ድንቢጮ በሉ።
አንድ ሰው ቢጣራ አይሰማም ቃሉ
እስቲ ሁላችሁም ወይ ድንቢጮ በሉ
ሁላችሁም ወይ ድንቢጮ በሉ

Read 574 times