Saturday, 27 January 2024 00:00

ሦስት መዓዘን (ተከታታይ ልብ ወለድ)

Written by  በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(9 votes)

ከተሰደደበት የበርባሮስ ጨለማ ሲመለስ አይኖቹ እየታመሙ ነው የተገለጡት፡፡ ከበላዩ የሚታየው ጥርት ያለ ሰማይ ነው፡፡ ፀጥ ያለ ሰማይ፡፡ ሁሉም ነገር በመልካም ሁኔታ ጉዞውን ጠብቆ እየሄደ እንደሆነ የሚሳበክ የሚመስል ሰማይ፡፡ ሰማይ፡፡ የምድር ደረት ላይ ተጣብቆ አልነሳ ያለው ሰውነቱን ተሸክሞት እንደሆነ ያወቀው እግሩ አካባቢ ህመም ሲሰማው ነው፡፡ በፍጥነት ከተጋደመበት መነሳት እንደማይችል አውቆታል፡፡ በተጋደመበት ሆኖ ለማሰብ እና ለማሰላሰል ሞከረ፡፡ “ትላንት ምን አድርጌ ባድር ነው፣ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ገብቼ የነቃሁት?” እያለ ለማስታወስ ሞከረ፡፡
ባዶ ትዝታ፡፡
የትኛውንም የአዕምሮውን ክፍል ቢያማክር፣ ምንም አይነት መልስ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ እንዳልሞተ ይገባዋል፡፡ እያዳመጠና እያየ ነው፡፡ የሞተ ሰው ደግሞ አያመውም፡፡ እንዴት እና በምን ጥበብ ትላንቱን እንደረሳ የሚያውቀው ታሪክ የለውም፡፡ ሀሳቡም ሆነ ሁሉነቱ ያለው አሁን እና አሁን ውስጥ ብቻ ነው፡፡
እንደምንም ብሎ ስሙን ለማስታወስ ሞከረ፡፡ ስሙን አያውቀውም፡፡ ስሙ ብርሀኑን ካከሰመው ትዝታው ጋር በጭንቅላቱ ውስጥ አብሮ ሞቷል፡፡ እየሆነ ያለውን ነገር ለማመን እውቀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሰው በውስጡ ተንጠፍጥፎ የቀረ እውቀት እንኳን የለውም፡፡
ባዶ…ምንም…ፀጥታ….
ጭንቅላቱ በዚህ ሰዓት ላይ ልክ እንደ ታቡላ ራሳ የያዘው ነገር የለውም፡፡ ልክ እንደተወለደ ህፃን ልጅ ነው፡፡ ህሊናው ሀይማኖት የለውም፤ የሚፀልይለትን አምላኩን አስሶ ሊያገኝለት አልተቻለውም፣ ውበት የሚባል ታሪክን ተመልክቶ መተርጎም አይቻለውም፣ ሲያስብ ሀሳቡን ከቦታ ቦታ የሚሰዱለት ሚስጥራዊ ቃላቶች ግን አሉት፡፡ ለራሱ ብቻ የሚገቡት ቃላቶች፡፡ ህልም ልይ ቢል አንዳችም ቀለምንና ድምፅን አመንጭቶ ትርጉም ያለው ምናብ የሚለግሰው ትዝታ የለውም፡፡ ፈፅሞ ያልጠፋው ስጋው ውስጥ ነፍሱ ተሰውራበታለች፡፡
እነዚህን መሰረታዊ የእውቀት አምዶች ላይ የሱ ትውስታ ምንም ትርጉም እንደሌለው ገባው፡፡ የመጀመሪያውን ሰው …አዳምን የሆነ መሰለው፤ ያለ እናት ያለ አባት የተሰራ እና ከምድር የተለበደ መስሎታል፡፡ በተኛበት ሆኖ “ምነው ባልነቃው” የሚል የስሜት ዳሰሳ ውስጥ ገባ፡፡ ሆኖም ውሀ እየጠማው ነው፤ ሆዱም ቢሆን ምግብን በመመኘት የሚሰማኝ ካለ ብሎ እየጮኸ ነው፡፡
ድንገት የአንዲት የወፍ ዝማሬ ከተሰደደበት ወና ሀሳብ አነቃው፡፡ ህይወት ያለው ነገር ከሱ ብዙም ሳይርቅ ድምፅ እያሰማ መሆኑን አምኖ እንደምንም ታግሎ ከተጋደመበት ተነሳ፡፡ እግሩ ቆስሏል፡፡ አካባቢውን ተመለከተ…አንዲት ባህርዳርቻ ስር አሸዋ ላይ ነው ተጋድሞ የነበረው፡፡ ከጀርባው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ጎርፍ መስሎ ከፊቱ ካለው ባህር ጋር ሊቀላቀል አንዲት ትዕዛዝ የሚጠብጥ ይመስላል፡፡ እንደምንም ብሎ ከተቀመጠበት ተነሳ፡፡
ወደ የት መሄድ እንዳለበት አያውቅም፡፡ ወደ የት መሄድ እንደሌለበት ብቻ ነው የሚያውቀው…ወደ ባህሩ፡፡ ፊቱን አዙሮ ወደ ጫካው ተቀላቀለ፡፡
የጫካው አደራደር ልብን በስርዓት እንድትመታ የሚያዛት ይመስል፣ የዚህ ሰው ልብ ከጫካው ፀጥታ ጋር አብሮ መረጋጋት ጀመረ፡፡
ያገኘውን መንገድ እየሰነጣጠቀ ተጉዞ እንደሱ ሰው የሚመስል ፍጥረት በፍጥነት ማግኘት እንዳለበት ገብቶታል፡፡ ተከትሎት የሚሄደው የእግር ኮቴ ራሱ የለውም …ሁሉም መንገዶች ወደ ሁሉም ስፍራዎች ይወስዳሉ፡፡ እጣ ፈንታው ላይ ሙሉ እምነቱን ጥሎ፣ ነፃ ፈቃድ እንደሌለው አምኖ ለጉድ የፈጠረው እና ምንነቱን የማያውቀው ፈጣሪው ወዳሻው መንገድ አንዲመራው በማመን ፊት ለፊቱን ይዞ ጉዞ ጀመረ፡፡
2
ኤልዛቤት፡፡ አይኖቿን ስትገልጣቸው ምንም ነገር ለመመልከት አልቻለችም፡፡ የታወረች መሰላት፡፡ ሆኖም እንዳልታወረች ታውቀዋለች፡፡ ማየት ያቻለችው የብሌኗ መስታወት ያየውን ብርሀን ማንፀባረቅ ስላቃተው ሳይሆን፣ በጭንቅላቷ ላይ የጠለቀው ጨርቅ እንደሆነ ለመረዳት ብዙ አልቆየችም፡፡ ሆኖም የት እንዳለች አታውቅም፡፡ ማን እዚህ ስፍራ እንዳመጣት አታውቅም፡፡ ስትሰቃይ ግን ትዝ ይላታል፡፡ ስትደማ፡፡
እጆቿ የፍጥኝ ከተቀመጠችበት ወንበር ጀርባ ታስሯል፡፡ ጣቶቿ ለብቻቸው የብቻቸውን ህመም እየታመሙ ናቸው፡፡ የተቀረው ሰውነቷ ህይወት ርቆት፣ የሚያዘው ጭንቅላት ጥሎት ተሰዶበት ከከበበው ጨለማ ጋር አብሮ በድን ሆኗል፡፡ እንዲህ ባለ የጭንቅ ሰዓት ላይ የማይታሰብ አይነት ሀሳብ የለም፡፡ እንግዳ በሆኑ ሀሳቦች እየተሽከረከሩ ወደ እውነቱ ለመጠጋት መሞከር ግድ ነው፡፡ ነገር ግን ኤልዛቤት ነጥራ የምታርፍበት የሀሳብ ሜዳ የላትም፡፡ ሜዳውም ቢኖር ከህመም ውጭ በውስጡ ምንም አይነት ትዝታ የለውም፡፡ ከሁለቱ አንዱ ናት…ወይ በሜዳው መሀል ላይ የቆመችው ወይም ሜዳው ራሷ ናት፡፡
በዚህ ዝግ ቤት ውስጥ ዝግ ሀሳቦቿን ተሸክማ ባለችበት ሰዓት ላይ፣ በሩ ተከፍቶ አራት የሚሆን የእግር ኮቴ ራሱን በአራት እያባዛ ወዳለችበት ሲቀርብ ተሰማት፡፡ የተሸከመችው ንፁህ ነፍስ ንፁህ ተስፋን ብቻ ስለሚነግራት አሁንም ያላትን ከማድረግ አልተቆጠበችም፡፡
“እርዱኝ እባካችሁ… የት እንዳለሁ አለው….?”  
የመጨረሻዎቹን ሁለት ሆሄያት ሳታወጣቸው ድንገተኛ በሆነ ጥፊ ወደ መጡበት ተሰደዱ፡፡ የተመታችው ጥፊ መንጋጋዋ ስር ነበርና ራሷን አሳታት፡፡ ሆኖም ጭል ጭል የምትል የድምፅ ነፀብራቅ በጆሮዋ ውስጥ እንደሰመመን እያደረገች በጭላንጭል ትፈሳለች፡፡
“ምን ባናደርጋት ነው የሚሻለው? የሰጠናት መድሀኒት ጭራሹን ትውስታዋን እያጠፋው እየሄደ ነው፡፡ ምን አይነት ዶክተር ይዘህብኝ እንደመጣህ በኋላ ላይ በደንብ ቁጭ ብለን እናወራበታለን?”
“መድሀኒቱ ትክክለኛ ነው፡፡ ሆኖም በውትድርና ስልጠናዋ ላይ ይህንኑ መድሀኒት እንዴት አድርጋ መቆጣጠር እንደምትችል ሳታጠና አትቀርም፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነገርኩህ ነው…ልጅቷ እጅግ ሲበዛ አዋቂ ናት፡፡ ለዛም ነው ከዛ ሁሉ ሰራዊት መካከል ተመርጣ የስለላ የስራ ዘርፍ እንድታገኝ የተደረገው፡፡”
“ይሄ መረጃ በዚህ ሰዓት ላይ ለኔ የሚሰጠኝ ምንም አይነት ጥቅም የለውም፡፡ የምፈልገው መረጃ ብቻ ነው፡፡ አሁን ሳየው ወጪ ብቻ እየሆነችብኝ ነው፡፡ ለዚህች በመድሀኒት ብቻ ሳይሆን የገነት በር ላይ አቁመሃት ሚስጥሩን አውጭና ገነት ትገቢያለሽ ብትላት አሻፈረኝ የምትለው አይነቷ ናት፡፡ እኔም ብሆን ከዚህ በላይ የምታገስበት ጉልበት የለኝም፡፡ ብትወገድ ነው የሚሻለኝ፡፡”
“እባክህን ትንሽ እንታገስ፡፡ ይህን ሚስጥር አገኘን ማለት ለአመታት የሚያታግለንን ትግል አቀለልን ማለት ነው፡፡ ኤልዛቤል ታስፈልገናለች፡፡ እባክህን አትግደላት…አንድ ሙከራ ብቻ ስጠኝ፡፡ ከዛ በኋላ እንደፈለክ ታደርጋታለህ፡፡”
“አንድ ሳምንት ብቻ ነው ያለህ፡፡ አንድ ሳምንት፡፡”
ይህን ተናግሮ አንደኛው ባለ ሁለት እግር ወጣ፡፡ ይህን ኤልዛቤል ምሰሶውን የሳተው ጭንቅላቷን እየወዘወዘች ታደምጣለች፡፡ አንደኛው ሰው ከወጣ በኋላ ለነፍሷ ሲታገልላት የነበረው ሰው በርከክ ብሎ ወደ ጆሮዎቿ ተጠግቶ ይህን ጠየቃት…
“ኤልዛቤል እየሰማሽኝ ነው?”
እንደምንም ብላ ራሷን ለማወዛወዝ ሞከረች፡፡
“እባክሽን ኤልዛቤል የምልሽን ስሚኝ፡፡ እጅግ ለዚህች ሀገርም ሆኖ ለመላው የሰው ልጅ ሊጠቅም የሚችል ፕሮጀክት ቀርፀን በመንቀሳቀስ ላይ ያለን ሰዎች ነን እንጂ አንቺ እንደምታስቢን ባንዳዎች አይደለንም፡፡ ልክ እንደኛ አንቺም ለሀገርሽ እድሜሽንና እውቀትሽን ገብረሻል፡፡ ሴትነትሽ ሳይዝሽ ሀገርሽንና ህዝብሽን ልትጠብቂ መሳሪያሽን ወድረሽ ተዋግተሸል፡፡ ሆኖም አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ… የት ድረስ ነው ትግልሽ? ማን ድረስ ነው አላማሽ? ለማን ብለሽ ነው ሞትሽ?
“ውብ ሴት ነሽ፡፡ የትምና ማንም ጋር የመኖር እድልሽ ከምድር ይሰፋል፡፡ በዛውም ልክ የውስጥሽን ፅናት ከስቃይሽ እኩል አብሬ አድምጬዋለሁ፡፡ እዚህ ድረስ አይቼሻለሁ…ማንም ሳያየኝ፡፡ ሆኖም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያለንን እድል እንጠቀመው…ሁለታችንም፡፡ የምፈልገውን ንገሪኛና እኔው ራሴ ከዚህ የስቃይ ጨለማ ውስጥ ተደብቀሽ እንድታመልጪ አድርጌ ከሀገር አስወጣሻለሁ፡፡ እመኚኝ፡፡ ካላመንሺኝ በነአላማሽ የታገልሽላት ምድር አፈር፣ ማንነትሽንና ገድልሽን ሳትነግርልሽ ሰልቅጣ ትውጥሻለች፡፡ ይህን ስናገር ደግሞ በኔ እርግጠኛ ሁኚ…ስንት ጀግና እዛ ፀጥ ያለው  …ቃላት…ብርሀን…እና ፈጣሪ የሌሉበት ጉድጓድ ውስጥ ከአፈር ጋር አብሮ ሲሰጥም ተመልክቻለሁ፡፡
ቀናቶችሽ ላይ የመወሰን አቅሙ ያለሽ አንቺ ብቻ ነሽ፡፡”  ይህን ተናግሮ ክፍሉን ለቆ ወጣ፡፡ የብረቱም በር ተዘጋ፡፡ እንደገና ሌላ ፀጥታ…እንደገና ሌሎች እንግዳ ሀሳቦች፡፡ ኤልዛቤት ሲያወራት የነበረችው ሴት ማን እንደሆነች ሳትጠይቀው ነው ጥሏት የወጣው፡፡
 3
ራሱን በመስታወት ውስጥ ለረዥም ሰዓታት ነው ሲመለከተው የቆየው፡፡ ሙሉ ሱፉን ለብሷል፡፡ በየመሀሉ ፈገግ ይላል፡፡ ፈገግታው የእርግጠኝነት መንፈሱን ያሳብቅበታል፡፡ አዎን….ራሱን ለማጥፋት ዝግጁ ነው፡፡ ይንንም ለማድረግ በቂ ምክንያት ነበረው፡፡ ማንም ሳይሆን የሚገባው ራሱ ብቻ ነው የሚረዳው፡፡ ምክንያት አልባ የሆነ  ማህበረሰብ ውስጥ በምክንያት ብቻ መኖር የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ደርሶበታል፡፡ ከዛም በላይ ጠላቶቹ ሳይቀድሙት እሱ ሊቀድማቸው እንደሚገባ በጭንቅላቱ ውስጥ ሰግስጎት ያለው እውቀት ለብቻው ይሰብከዋል፡፡
ዞር ብሎ የገዛ የግድግዳውን መልክ ሸፍኖ የተደቀደቀ የመፅሐፍ ክምርን ተመለከተ፡፡ ከመስታወቱ ራሱን አሳርፎ እያንዳንዱን መፅሐፍቶቹን በጣቶቹ እየዳበሰ ያልፋቸው ጀመር፡፡ እነዚህ መፅሐፍት እሱ ቤት ውስጥ እስኪገቡ ድረስ በመሀል ብዙ መከራ አሳልፏል፡፡ አስፈሪ ዘመናትን ነፍሱ ሳትወድ በግዷ ሰልጥና አድጋለች፡፡
እነዚህ መፅሐፍት የሆነ ወቅት ላይ በዝርያዎቹ መካከል እንደ ታላቅ ሰው እንዲቆጠር አድርገውታል፡፡ እነዚሁ መፅሐፍት ከሱ ዘንድ ስላሉ ብቻ በአላዋቂያን መካከል እንደ አምላክ የታየበትም ወቅት ነበር፡፡ ሆኖም አሁን እነዚህ የገፅ ጫካዎች ውጠው ሊያጠፉት ነው፡፡ አኑረው ሊገሉት ነው፡፡ ሊያስገድሉትም ነው፡፡ ህይወቱ ላይ ቤዛ የነበሩት የቃላት አረፋዎች ዛሬ ላይ ሄምሎክ ሆነው ነው የመጡበት፡፡
እያያቸው እንባው መጣበት፡፡ የምርም መፅሐፍቶቹን ይወዳቸዋል፡፡ ያከብራቸዋል፡፡ እንደ አምላኩ መልክ አድርጎ እያያቸው አንዳንዴ በመካከላቸው ውስጥ ፍራሹን አነጥፎ ይተኛባቸዋል፡፡ ይህም ህይወት ሆኖት ቆይቶ ነበር፡፡ “ነበር”…እጅግ አደገኛ ቃል ናት፡፡ በትዝታ ድክመት ውስጥ የምትመላለስ አፍራሽ የሆሄዎች ድሪያ የሆነች ነገር…ይህች “ነበር” የተባለች ቃል፡፡  
መሞት የፈለገው ታንቆ ነው፡፡ እንደ ጥንቱ፡፡ በብራናዎቹ የመፅሐፍ ቅጠሎች ላይ ያሉት ጀግኖች እንደሚሞቱት ለመሞት ነው ከተሸከመው ስጋው ውስጥ  ሞትን  ጎትቶ የጠራው፡፡   
ከመኖሪያ ቤቱ መሀከል ላይ ያስቀመጠው ኩርሲ ላይ ወጣ፡፡ ገመዱ በጭንቅላቱ ትክክል ነበር የተሰቀለው፡፡ ሁሉም ነገር ዘካሪያስን ከምድር መልክ ላይ አፍዝዞ ለማጥፋት ቦታ ቦታውን ይዞ እየጠበቀው ነው፡፡ ዘካሪያስ በቀስታ ገመዱን በአንገቱ ውስጥ አጠለቀው፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አይኖቹ እያዩ መሆኑን ስለተረዳው በቀስታ ዞር ብሎ ለመጨረሻ ጊዜ ብዙ ያደርጋል፣ ብዙ ይሆናል ብሎ ሲናፍቀው የነበረው ራሱንና እዚህ ድረስ በእውቀትና በጥበብ እያንደረደሩ ያመጡትን መፅሐፍት ከቃኛቸው በኋላ የቆመበትን ኩርሲ በግራ እግሩ መታው፡፡
የዘካሪያስ አንገት ለገመዱ ሸክም ሆነው፡፡ እንደታነቀ አንገቱ አልተቀጨም፡፡ አስጨናቂ ጣር ውስጥ ገባ፡፡ የስቃዩ ንዝረት ቢከብደው ራሱን ለማስለቀቅ የገዛ ገዳዩ ከሆነው ገመድ ጋር መልሶ መተናነቅ ውስጥ ዘለቀ፡፡
ሆኖም የገዛ እጁ እያነቀው ያለውን ገመድ ማነቅ ከብዶት ስር እንደሌለው ዛፍ ለብቻው መወዛወዝ ጀመረ፡፡ ሁሉም ነገር ወደ መጨለሙ እየገባ ባለበት ሰዓት ላይ…አይኖቹ የሚያዩትን ትተው የማይታየውን ለማሰስ ከሽፋሽፍቱ ስር ለመደበቅ በሚታገሉበት ደቂቃ ላይ…ህይወትና ሞት ከዳርና ከዳር ሆነው ሊያመልጥና ሊዋሀድ ያለችውን የዘካርያስን ነፍስ መናጠቅ ውስጥ ባሉበት ሰከንዶች ውስጥ የገዛ በሩ ተከፍቶ አንዲት ሴት በፍጥነት መጥታ ስትቀርበው ጥላ መስላ ታየችው፡፡ ሁሉም ነገር በቅደም ተከተል ተፈፀመ፡፡
ስቃይ…ተስፋ…እጅ መስጠት…ፀጥታ…ጨለማ፡፡
በልሙት አልሙት ስትሰቃይ የከረመችው የዘካሪያስ ነፍስ፤ ጨለማዋን ተሸፋፍና ለጊዜውም ቢሆን ለጥ አለች፡፡             
(ይቀጥላል…)Read 244 times