Thursday, 01 February 2024 21:03

1.1 ቢ. ብር የወጣበት ኃይሌ ሆቴል ወላይታ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ባለ አራት ኮከቡ ዘጠነኛው ኃይሌ ሆቴል ወላይታ በዛሬው ዕለት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አብስሯል፡፡ ሆቴሉ  ትልቁን ዳሞታ ተራራን ተንተርሶ  በኮረብታማዋ ወላይታ ሶዶ ከተማ እምብርት ላይ የተገነባ ነው።

 ሆቴሉ ተሰርቶ ለመጠናቀቅ አራት ዓመታትን የፈጀ ሲሆን፤ እስካሁን 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል ብሏል፤ በሆቴሉ ዳሞታ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ።

 ሆቴሉ 107 ዘመናዊ የማረፊያ አልጋዎች፣ ከ15-600 ሰው የመያዝ አቅም ያላቸው 7 የስብሰባ አዳራሾች፣  የጤናና የውበት መጠበቂያ -  የጂም የሳውና የስቲም ባዝና የማሳጅ አገልግሎት  እንዲሁም የወላይታ ህዝብ የምግብ ሜኑን ጨምሮ የተለያዩ የሐገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ምግቦችን የያዙ ሦስት ዘመናዊ ሬስቶራንቶች የለስላሳና የአልኮል መጠጦች አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት ባሮችን በውስጡ ይዟል።

በአሁኑ ወቅት ለ160 ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ለ300 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።

  "አንድ ኢንቨስተር  ኢንቨስት ሊያደርግ ሲነሳ መጀመሪያ የሚያየው የአካባቢው ህዝብና መንግስት ምን ያህል ቀና ናቸው የሚለውን ነው" ያለው ሐይሌ፤ የወላይታ ህዝብ ላሳየው ቅንነትና ትብብር አመስግኗል። ሆቴሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና መቀመጫ ለሆነችውና በፈጣን  እድገት ላይ ለምትገኘው ወላይታ ሶዶ ከተማም ሆነ ለነዋሪዎቿ ድምቀት  ብሎም የስራ እድል ይዞ የመጣ የህዝብ ሐብት ነው  ያለው ሐይሌ፤ ለቱሪዝም ፍሰትና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ይጫወታልም ብሏል።

ከ14 ዓመት በፊት በሐዋሳ ከተማ የተጀመረው የሐይሌ ሪዞርት፣ ዛሬ ላይ በተመሳሳይ የአገልግሎት ጥራት 9ኛ ሆቴሉን በወላይታ እያስመረቀ ሲሆን፤ በቀጣይ በጅማ በደብረ ብርሃንና በሻሸመኔ ሐይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ተከፍተው ስራ ይጀምራሉ ተብሏል።

 ኃይሌ በአካባቢው በተፈጠረ አለመረጋጋት የሻሸመኔና  በዝዋይ ያሉት ሆቴሎቹ ውድመት እንዳሳዘነው ገልፆ፣ ምንም እንኳን መንግስት  ካሳ ባይከፍለውም (እንዲከፍለኝ እጠብቃለሁ ብሏል)፤ሆቴሎቹ ግን መገንባትና ስራ መስራት ስላለባቸው የዝዋዩ ስራ ላይ ሲሆን የሻሸመኔው ግን እንደገና ፈርሶ በአዲስ መልክ እየተገነባ ስለመሆኑ አብራርቷል። በወላይታው የሆቴሉ ግንባታ ላይ የግብአት እጥረት ከፍተኛ  ተግዳሮት እንደነበረ ኃይሌ ተናግሯል። በዘጠኙም ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በአጠቃላይ  1ሺ 800 ሰዎች ተቀጥረው እየሰሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1370 times