Sunday, 04 February 2024 21:33

የካቲት ወይ ስትገባ ወይ ስትወጣ ባታንጎዳጉድ፤ መሬት ትጨነቅ ነበር!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የካቲት
ወይ ስትገባ
ወይ ስትወጣ
ባታንጎዳጉድ፤ መሬት ትጨነቅ ነበር!
የአንድ ንጉሥ አገር በጣም ሥቃይና ዕንባ በዛበት፡፡ ይኸውም በአንድ ሰብል በሚያጠፋና ሰው በሚገድል አውሬ ምክንያት ነበር፡፡ ንጉሡ መላ ፍለጋ ብዙ አውጥተው አውርደው ሲያበቁ፤ በመጨረሻ “ይህን አውሬ ገድሎ ወይም እስከ ህይወቱ አጥምዶ አገሬን ከሥቃይ ላወጣ ሰው ከፍተኛ ሽልማት እሰጣለሁ” አሉ፡፡ ሆኖም አውሬው እጅግ ግዙፍ በመሆኑ ሰው ሁሉ ወደ ጫካው መሄድ ፈራ፡፡ ንጉሡ የበለጠ ህዝቡን ለማበረታታት ብለው ከሽልማቱ በተጨማሪ ሴት ልጃቸውን እንደሚድሩለት አሳወቀ፡፡
በዚያ አገር የሚኖሩ የአንድ ደሀ ሰው ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩ፡፡ መጥተው ለንጉሡ አውሬውን እንደሚገድሉ ተናገሩ፡፡ ታላቅዬው ብልጥና ጉልበተኛ ሲሆን የሚመራው በምኞት ነበር፡፡ ታናሽዬው ደግሞ ሁሉ ነገሩ የዋህና ገር ነበረና በልበ-ቀናነቱ ብቻ ይመራ ነበር፡፡ ንጉሡ፤
“እንግዲህ አውሬውን ለማግኘታችሁ እርግጠኛ እንድንሆን ወደ ጫካው ከሁለት አቅጣጫ ግቡ” አሉ፡፡ በዚህ መሰረት ታላቅዬው በምዕራብ በኩል ገባ፡፡ ታናሽዬው ደግሞ በምሥራቅ፡፡
ታናሽዬው ትንሽ  መንገድ እንደሄደ አንድ ጥቁር ጦር የያዘ አጭር ሰው ድንገት ከጫካው ብቅ ብሎ፤
“እንካ ይሄንን ጦር ያዝ፡፡ ምክንያቱም ልብህ ንፁህ ነው፡፡ በዚህ ጦር አውሬውን ሳትፈራ ልትወጋው ትችላለህ፡፡ ምንም ጉዳት አያደርስብህም አይዞህ” አለና ሰጠው፡፡
ታናሽ ወንድም የተሰጠውን ጦር አንግቦ አመስግኖ መንገዱን ቀጠለ፡፡ ልበ - ሙሉ ሆነ፡፡ ጥቂትም ሳይጓዝ አውሬው ብቅ አለ፡፡ ገና ጦሩን ወድሮ እንደቆመ አመለኛው አውሬ ከፍርሃት በመነጨ ጭካኔ የዕውር የድንብሩን መጥቶ ጦሩ ላይ ተንደርድሮ ተሰካበት፡፡ ጦሩ ልቡ ላይ ተሰካና ሁለት ላይ ከፈለው፡፡ ታናሽ ወንድም የአውሬውን ሬሣ ተሸክሞ ለንጉሡ ሊያስረክብ መንገዱን ቀጠለ፡፡
በአንፃሩ ታላቅ ወንድሙ በሄደበት በተቃራኒው አቅጣጫ ሰዎች ሁሉ የሚዝናኑበት አንድ መሸታ ቤት አለ፡፡ ታላቅ ወንድም እዚህ መሸታ ቤት ሊገባ አሰበና “አውሬው እንደሆነ ከዚህ ጫካ ወጥቶ አይሄድም፡፡ ለምን ለድፍረት እንዲሆነኝ ጥቂት እህል ውሃ አልልም?” ብሎ ገባና ጥቂት መጠጥ ጠጣ፡፡
ከመሸታ ቤቱ ሲወጣ ታናሽ ወንድሙ አውሬውን ተሸክሞ ሲመጣ አየው፡፡ እቡይና እኩይ ልቡ ሸር አሳሰበውና፤
“ና ወንድም ዓለም አረፍ በልና ወይን ጠጣ” አለው፡፡ ምንም ተንኮል ያልጠረጠረው ታናሽ ወንድም፣ ግብዣውን ተቀብሎ ሲጠጣ ቆየ፡፡ ያ አጭር ሰውዬ ጦር እንደሰጠውና አውሬውን እንደገደለው ነገረው፡፡ ሲመሻሽ አብረው መንገድ ጀመሩ፡፡ ከጅረቱ ላይ ካለው ድልድይ አጠገብ ሲደርሱ ድቅድቅ ጨለማ ሆነ፡፡
ታላቅዬው ታናሽዬው እንዲቀድም ይነግረውና ግማሽ ድልድዩን አብረው ይሄዳሉ፡፡ ጥቂት ካደባ በኋላ ከኋላው ክፉኛ ይመታዋል፡፡ በዚህም የታናሽ ወንድም ህይወት ያልፋል፡፡
ቀጥሎም፤ ታናሽ ወንድሙን ድልድይ ሥር ቀብሮ፣ የአውሬውን ሬሳ ይዞ ወደ ንጉሡ ይሄዳል፡፡ ንጉሡም ተደስተው ልጃቸውን ይድሩለታል፡፡
ታናሽ ወንድሙ እስከመጨረሻው ሳይመጣ ቀረ፡፡ ታላቅ ፈጠን ብሎ፤
“ምናልባት ታናሽ ወንድሜን አውሬው በልቶት ይሆናል፡፡” ሲል ዋሸ፡፡ ሰው ሁሉ ግን አመነው፡፡
ሆኖም በዓለም ላይ ምንም ነገር ተሸሽጎ አይቀርምና፤ ከዓመታት በኋላ አንድ እረኛ ከብቶቹን ከዚያ ድልድይ ላይ እየነዳ ሳለ ታች አሸዋው ላይ አንድ ነጭ፤ የሚያበራ፣ ረዥም - አጥንት አየና ለጥሩምባ መሣሪያ ቢሆነኝ ብሎ ወርዶ ወሰደው፡፡ ከዚያም እየፋቀ በጥሩምባ ቅርጽ ሰራው፡፡ ሊነፋው ገና ወደ አፉ እንዳስጠጋው ግን አንድ ተዓምር ተከሰተ፤
“እረኛ ሆይ እረኛ ሆይ፤ የምትጫወተው
በእኔ አጥንት እኮ ነው፡፡
ተመትቼ ሞቼ በገዛ ወንድሜ
የገደልኩት አውሬ ተወስዷል በስሜ፡፡
ከውሃው አጠገብ አካሌን ቀበረ
ለንጉሡ ሴት ልጅ በተንኮል ተዳረ”
ሲል አጥንቱ ዘመረ፡፡ እረኛው በመገረም “ይሄን ጉድ ለንጉሥ ማሳየት አለብኝ” ብሎ ወደ ንጉሱ ሄደ፡፡ ቀርቦም አጥንቱን አሳየ፡፡ አጥንቷ እሱ ሳይናገር በፊት መዘመር ጀመረች፡፡ ንጉሱ ነገሩ ገባቸው፡፡ ቦታው ድረስ ጋሻ ጃግሬ ልከው አስቆፍረው የታናሽዬውን ሬሳ አወጡ፡፡ በቦታውም ታላቅ ወንድሙ ተገድሎ እንዲቀበር ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
***
በብልጥነትና በጉልበተኛነት የሰሩት ተንኮል ውሎ አድሮ ከመጋለጥ አያመልጥም፡፡ በልበ - ቀናነት የተሰራ ሥራ ግን ለብዙዎች ጠቀሜታው ሰፊ ነው፡፡ ግዙፉን አውሬ በንፁህ ልቡ ሊዋጋ የሄደው ልጅ ቀንቶት ያገኘውን ድል፤ በተንኮልና በዕቡይነት የነጠቀው ቀማኛው ታላቅ ወንድም ምንም ሳይቆይ ተጋልጧል፡፡ አውሬው ብዙ ጥፋት ያደረሰ ነበረና ከፍርሃቱ በመነጨ ጭካኔው ያልተወረወረ ጦር ላይ መሰካቱም “ደም ያሰከረው” እንዲሉ መሆኑ ነው፡፡ የታናሽ ውንድሙን ሞት በአውሬው ያሳበበው ታላቅ ወንድሙ የሰራው ግፍ ሳያንስ ውሸት መጨመሩ ሁለተኛ ጥፋት ነው፡፡
ምርጫንም ሆነ ድርድርን በልበ - ቅንነት ማካሄድ አንድ በጎ እርምጃ ነው፡፡ አፈ-ቅቤ ልበ-ጩቤ የሆነ አካሄድ ግን ማንንም ወደፊት አያራምድም፡፡ ዕውነቱን ገልጦ የሚወጣ ተዓምረኛ ጥሩምባ ከምድርም ይፍለቅ ከሰማይም ይዝነብ ብቅ የሚልበት ቀን እንዳለ ልብ ብሎ፤ እጅን ከግፍ አፍን ከቅጥፈት መሰብሰብ ወቅታዊው ብልህነት ነው፡፡ በሰፈሩት ቁና መሰፈር እንደማይቀር አለማስተዋል ከባድ እርግማን ነው፡፡ በድፍረት አሻፈረኝ ብለው ዘራፍ ካሉም “ሥጋ ሲመጣ ዳንኪራ፣ ዕዳ ሲመጣ ኩብለላ” መሆኑን ከወዲህ ለመገመት አያዳግትም፡፡
ለውጥን ቀስ በቀስ እንደሚገነባ ጥብቅ ካብ ማሰብ እንጂ በነቶሎ ቶሎ ቤት አሰራር ልናመጣው እንደማይቻል፣ ከተቻለም እንደማያዛልቅ መረዳት ለሀገራችን እጅግ ጠቃሚ መነሻ ይሆናል፡፡ ይህን መሰረት ያልያዘ ሂደት ውሎ አድሮ “የተማመኑበት ቢላዋ በጉበት ይሰበራል” ዓይነት እንደሚሆን ልብ ማለት ደግ ነገር ነው፡፡
በወርሃ የካቲት በኢትዮጵያ አያሌ እንቅስቃሴዎች እየፈሉ እንደነበሩ ሁሉ ወራቸው ሲገባ የሀሳብ፣ የዕውቀት፣ የለውጥ ንፋስ መንፈሱ ያለ ነው፡፡ ከየካቲት 23 እስከ መሬት ላራሹ፣ ከየካቲት 12 እስከ የካቲት 11 ብዙ አይተናል፡፡
ዛሬም ብዙ እንሰማለን፤ የተጨበጠም ያልተጨበጠም፡፡ ሁሉም ምን እንዳዘለ ጊዜ ያሳየናል፡፡ ለውጥ የጊዜ ልጅ ነው፡፡ “የካቲት ወይ ስትገባ ወይ ስትወጣ - ባታንጎዳጉድ፣ መሬት ትጨነቅ ነበር” የሚለው የሰሜኖች ተረት እንዲሁ አልተተረተም፡፡

Read 1679 times