Sunday, 04 February 2024 00:00

ድምፃዊ አስቻለው ስለሥራዎቹ ያወጋል!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

-    አያቴ እንደሽልማት ታሪክ ትነግረኝ ነበር…
-    “ተራሮች የሚለኩት ባስቀመጡት ታሪክ ነው”
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከባህል ዘፈን አቀንቃኙ ድምፃዊ አስቻለው ፈጠነ ጋር ያደረገችው ቃለ-ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል በዕለተ ጥምቀት ለንባብ በቅቶ ነበር፡፡ ቀጣዩ ክፍል ባለፈው ቅዳሜ መውጣት ሲገባው በቴክኒክ ችግር ምክንያት ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ ቀሪውን ክፍል መዝለል ደግሞ ዋነውን የቃለ-ምልልሱን ክፍል እንደመተው የሚቆጠር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሁለተኛውን ክፍል ቢዘህ በዛሬው ዕትማችን ልናትመው ወደናል፡፡ በዚህ ቃለ-ምልልስ ጋዜጠኛ ናፍቆት እያንዳዱን የድምፃዊውን ዙፋንና የግጥም ስንኝ እየመዘዘች በስፋትና በጥልቀት አነጋግረዋለች፡፡ ድምፃዊ አስቻለውም በቅጡ አውግቷታል፡፡ አንብቡት- ትውዱታላችሁ፡፡
“አድዋ” የተሰኘውን ስራህን ስሰማ፣ በሙዚቃ መሳሪያ መልክ የገባውን ጨምሮ የፈረሰ ኮቴው ሳይቀር የአድዋ ጦርነት ከመቶ ዓመት በላይ ያለፈው ሳይሆን ትላንት የተካሄደ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ የቃላት ውበቱም ድንቅ ነው፡፡ እስኪ ትንሽ ነገር ስለአድዋ ንገረኝ…?
ስራውን ስለወደድሽው አመሰግናለሁ እኔ የሶሻል ተማሪ ነበርኩና በተቻለኝ መጠን ብዙ ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ በተጨማሪም ከአያቴ ጋር ነው ያደግሁት፡፡ ቅድመ አያቴም አድዋ ዘምተዋል፡፡ ፊት አውራሪ ቴኩስቲያ ይባላሉ፡፡ የእናቴ አባት ደግሞ ደጅአዝማች ቢሻው ይባላሉ፡፡ እሳቸው ደግሞ እስከ ጎዴ ድረስ ተዋግተዋል፡፡ ሜዳሊያቸው እኔ ጋ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ አያቴ ደጃዝማች ቢሻው፣ ተሰማ፣ የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ወንድም ነው፡፡ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በጣም ታዋቂ ነው፡፡ በግምጃ ቤት እነዚህ ሰዎች ታዋቂ ናቸው፡፡ ሴት አያቴ ስለነዚህ ሰዎች ትነግረኛለች፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ መፅሐፍ የሚወጣው ታሪክ ነው፡፡ አያቴ ለእኔ የምነነግረውን ታሪክ ለሌሎች ወንድሞቼ አትናገርም ነበር፡፡
ለሌሎቹ የማይናገሩትን እንዴት ላንተ ነገሩህ?
እኔ ታዛዥ ነኝ፡፡ ሶስት መቶና አራት መቶ እግር ቡና በየቀኑ ውሃ አጠጣለሁ፣ የአትክልት መስኖ ነበረን ያኔ፡፡ ከአስር በላይ ለሚታለቡ ከብቶች መኖ አቀርባለሁ እታዘዛለሁ፤ በዚህ ደስ ይላታል፡፡ አያቴ እንደ ሽልማት ታሪክ ትነግረኛለች፤ ቁጭ ብዬ አዳምጣለሁ፡፡ በአድዋ ጦርነት ቅድመ አያቶቻችን ነጭ ማርከው ተከፋፍለው ነበር፡፡ አንድ የእናቴ እህት ስትነግረኝ፤ ነጩ ተማርኮ አገው ምድር መጣ፤ ይሄ ነጭ እየሄደ ዞሮ ዞሮ መለመላው ይመለሳል፡፡ ሴቶችን ለግንኙነት ይጠይቃል፡፡ ሀበሻ ኩሩ አይደል “ወግድ ዞር በል” ይሉታል፡፡ ከዚያ አንዲት አገልጋይ (በዛን ጊዜ ገረድ ነው የሚባለው) ጥሙን ለመቁረጥ ገረዲቱን ሲጠይቃት ኧረ ወዲያ አለችና፡-
ወይ እንደ እናቱ ጥጥ አያሳሳ
ወይ እንዳባቱ ወግ አያነሳ
እባክህ አምላክ ወዘፍህን አንሳ፡፡ ብላ ተናገረች ወዘፍ ማለት መቀመጫ እይታ ማለት ነው፡፡ ወደ ምንሊክ ስንመጣ እንደነገርኩሽ አባቴ ክራሩን ይዞ በተደጋጋሚ ፋ፣ ፋኖ፣ እቴ መላ ዘውዴን ሲጫወት እየሰማሁ ነው ያደግሁት፡፡ ከዚያ ላይ ከአያቴ ያንን ታሪክ ስሰማና እኔም ሳስ አድዋ ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ ከዚያ አማርኛውን ጀመርነው፡፡ ኢቲቪ የሚሰራ ጋዜጠኛ ጓደኛሽ በግጥም ተሳትፏል፡፡ እዚህ ስራ ላይ ስሙን ለመጥቀስ ስላላስፈቀድኩ ነው፡፡ ከዚያ ወደ ኦሮምኛው ስንመጣ የተዋደቁት እነ ባልቻ ትዝ፡፡…. ይሉሻል፡፡ ምንም እንኳን ለአድዋ ድል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቢዋደቅም መሪዎቹ ያው ትዝ ይሉሻል፡፡ አብነት የሚባል ልጅ ከዜማው ጋር የሚዋሃድ ግጥም ፃፈ፡፡ “ፈረሰኞቹ ሄዱ የፈረንጅን የጠላትን አንገት ሊቆርጡ” ነው የሚለው፡፡
ትግርኛም አለው አይደል?
አዎ! ትግርኛው ደግሞ አድዋን ስታስቢ እነ አባሻውል፣ እነ መንገሻ ዮሃንስ ትዝ ይሉሻል! ሶሎዳ ተራራ በሀሳብሽ ይመጣል፤ ሰንሰለታማዎቹ የአድዋ ተራሮች ይታወሱሻል፡፡ ይህንን ሀሳብ ተወልደ ለሚባል ልጅ ነገርኩት፤ ፃፈው፡፡ ይህን ሲፅፈው አድዋ ላይ የሚደመጥ ሙዚቃ ደግሞ እምቢልታ ነው፤ እንደገና እምቢልታ ፍለጋ ገባን፡፡ እምቢልታው ጋሽ ዘሪሁን የሚባል ትልቅ ሰው ቤት ተገኘ፡፡ እንደገና እምቢልታውን ማን ይንፋው? እንደገና በሶስቱ ሜጀር ፋ ፋ ፋ … ተደርጎ ተቀረፀ እና ትግርኛው ላይ ምን የሚል ደስ የሚለኝ ስንኝ አለ መሰለሽ “ተራሮች የሚለኩት በቁመት ሳይሆን ባስቀመጡት ታሪክ ነው፣ ሶሎዳ ተራራ ከተራሮች ሁሉ ትልቁ ተራራ ነው ይላል፡፡ እኛም ለፋንበት፡፡ ሰውም ልክ አንቺ እንደወደድሽው ወደደው፡፡ እውነት ለመናገር እኔም እሱ ዘፈን በጣም ደስ ይለኛል፡፡
ወደ ትዝታው ዘፈን ስንመጣ
እየተከፈለ ልቤ እንደግራምጣ
አሁንስ ያመመኝ ያንቺ ፍቅር ጣጣ ብሎ ይጀምርና በአገውኛ አድርጎ መጨረሻ ላይ ደስ በሚል የህዝብ ዜማ ነው የሚያልቀው፡፡ እኔ በበኩሌ ትዝታ ራሱን የቻለ ቅኝት እንደመሆኑ ከሌሎች የሙዚቃ ዘውጎች ጋር በተለያየ ቋንቋ ተዋዝቶ ሲሄድ አይቼ አላውቅም እና ግን በጣም ሸግዬ አድርገህ ነው የተጫወትከው፡፡ ትዝታ ከዚህ ቀደም በዚህ መልኩ ተሰርቶ ያጋጠመህ አለ? እናንተስ እንዴት መጣላችሁ ሀሳቡ? አዲስ የሙዚቃ አብዮት እየመጣ ነው ልበል?
በጣም ትክክል ነሽ! ትዝታን በተመለከተ በብዛት ክራር ስይዝ የጋሽ ካሳ ተሰማን ስራዎች እጫወታለሁ፡፡ ታዲያ ትዝታን በክራር ስጫወት ትዝታ መለስ አደረገኝና ቻግኒ ይዞኝ ሄደ፡፡ ክራር

ስትጫወቺ መጀመሪያ ትደረድሪና እንደገና ትገርፊዋለሽ፡፡ ከዛ ግርፍና ድርድር ታደርጊዋለሽ፡፡ በዚህ ሰዓት ክራሩን እንደረድራለን የሚል ነገር መጣ፡፡ በዚህ ሰዓት ነው በትዝታ ቻግኒ የገባሁት፡፡ (አገውኛውን ግጥም ከነገረኝ በኋላ) “እናቴ ማህበር ስትሄድ ሽቶውን አዘጋጅተህ ጠብቀኝ” ይላል፡፡ የገጠር ፍቅር አለ አይደል? “ይቺ ናት ወይ ቆንጆዋ ልጅ ብዬ” ጨመርኩኝ፡፡ ያው ከዚያ ያንን የህዝብ ዜማ ቀየር አድርጌ የምስራቅ አፍሪካ እንዲመስል አድርገን የኔንም ክራር ጨምሬ በዚህ መልኩ ስራነው፡፡ ያለው የኔም የፍቅር ታሪክ እንደ ነገርኩሽ ነው፡፡
አለቅሳለሁ ስምል እግዜር ቅጣኝ ብዬ
ቅዱስ በንጉስ ቃል ቢሰጠኝ ተስዬ
ምጤን አጣጣምኩት ማልቀስ ተከልክሎ
መነኮሰ እምባዬ  ካምላኩ ተስሎ
ኩራት የፃፍኩበት ቀለም ከሰመና
መልክሽ እያሻረው ፍቅሬ ታጥቦ ፀና
እባክሽ እባክሽ ታረቂኝ
ተይ አታስጨንቂኝ… እያለ ይቋጫል ትዝታው፡፡ በጣም ጥልቅ ነው፤ ሰውም ወዶታል፡፡
ሙዚቃውን ሳዳምጠው በተለይ ግጥሞቹ ጥልቅ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ማለቴ ነው፡፡ አሁን “እንገር ወሎ” ላይ
“ፈንጅ ገባ ደሴ ቁንጅናሽን አይቶ
ላብሽን አንቆርቁሮ ሊያሰራው ነው ሽቶ”
የሚለው ሌሎቹም ለየት ከበድ ያሉ ናቸው፡፡ ይገርማል…
እየውልሽማ የኔ ዘፈን መጀመሪያ ግጥሙ ሌላ ነበር፡፡
ከጆሮ ግንዷ ስር እሚፈልቀውን ጠረን
ስታጠነውና ከህመሜ ልደን”
ነበር የሚለው፡፡ ይህን ስራ እየሰራን ክራር ይዘን ቁጭ ብለናል፡፡ አልወለድ አለኝ በቃ! ለመምቴ የሚባልም ልጅ አለ፤ አብሮኝ፡፡ በቃ ስናሻሽል ስንሰራ ነው የከረምነው ለአንድ ግጥም ይገርምሻል… አንድ ደብተር ነው የምጨርሰው እና ከዚያ በኋላ ነው ከላይ ያየሽው ግጥም የተወለደው፡፡ በዚህ አልበም ስራ አንደኛዬን ማህበራዊ ህይወቴ ዜሮ ገብቶ ነበርኮ፡፡ እዚሁ ላይ ውለን እያደርን፡፡ የወሎው በተለይኮ ጉድ ነው፡፡
ከንፈሯ ሲቀላ እንደ ዶሮ ክንታት
ልክ እንደ ቆቅ አውራ ሄጄ ልመግምጋት፡፡ ይላል፡፡ እዚያ ወሎ ላይ “ምግማጎሽ” የሚባል አለ፡፡ ምግማጎሽ ታውቂያለሽ?
ኧረ አላውቅም፡፡
ምግማጎሽ በነጦላ ተከናንበስ ከከንፈር ደጅሽ ጋር የምትሳሳሚው ነው፡፡ ክንታትስ ታውቂያለሽ?
ወይ ዛሬ! ክንታ አላውቅም፡፡ ምንድን ነው አስቼ?
የዶሮ ክንታ ማለት እዚህ ምን እንደምትሉት አላውቅም ግን አውራ ዶሮ አናት ላይ ያው ቀዩ ነገር ክንታት ነው የሚባው የከንፈርን እምቡጥ አበባ መስሎ መቅላት ከዶሮው ክንታት ጋር ነው ያገናኘሁት፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ማለቴ ነው
በዚህ አልበም ወሎም፣ ሸዋም፣ ጎንደርም ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ተሰርተዋል፡፡ ግን የዚህ አልበም መነሻ የሆነውና ከሰው መሆን ይሰማው (ሶሚክ) ጋር ያገናኛችሁን “አባይ”ን መዘንጋት ደግ አይደለም፡፡ እስቲ “እባይ” ስለተሰኘው ዘፈንህ ትንሽ እንጨዋወት …
መልካም! አባይ እንግዲህ ገነትን ከሚያጠጡት ወንዞች አንዱ ነው አይደል የሚባለው? አባይ በአገው ምድር “አባዊ” ይባላል፡፡ “አባዊ ናፉዳስ ጆባ ኢትዮጵያ ሀፉዙራማ” ይባላል፡፡ አባይ ኢትዮጵያን ይዞራል
ምስራ ኑቢያ ቱሲ ችግማ ከሱሲ ይላሉ


ምን ለማለት መሰለሽ. አባይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ኢትዮጵያን ዞሮ ምስርና ጉበያን (ግብፅና ሱዳንን) ያጠጣል፤ ለዘመናትም ይፈለሳል ይላሉ። ዘርዓ ብሩክ በፀሎት ላይ እያለ ዳዊቱ ይጠፋል:: ከዚያ "አንድ አግሽ" አሉት እዛ ላይ ቆፍር አሉት። ሲቆፍር ዳዊቱ ወጣ።
አሃ! የአባይ ማህፀን የሚባለው ሰከላ የሚገኘውና አሁን "ግሽአባይ" እየተባለ የሚጠራው የአባይ መፍለቂያ ቦታ ከዚህ ታሪክ መነሻ ነው ስሙን ያገኘው? አባይ የሚፈልቅበትን ቦታ ጎብኝቼ ነበር። እዚያ ቦታ ላይ የጠበል ቦታ አለ ሰዎች እየተጠመቁ እንደሚፈወሱም ስም ከአካባቢው ሰው ሰምቼ ነበር…
ትክክል ነው። ስያሜው ከዚያ የተገኘ ነው። በአገው "ግሽ" ማለት ቆፍር ማለት ነው። እንዳልሽው ትልቅ የጠበል ቦታ አለ። አባይ እንግዲህ ብዙ ተብሎታል።
መጀመሪያ ላይ፡- እኔ እናትህ ቆሜ በጧፍ እያበላሁ
          አንተም እየበራህ እኔም እየጠፋሁ
           ለዘመናት ላንተ አንጎራጉራለሁ
           ባንተም ስራ ሆነ በኔም እያፈራሁ
ታላለች እናት ናት። ብዙ ጊዜ በመብራ እጦት መከራዋ ያየች እናት ናት፡፡ እናም በእኛም በእሱም እያፈረች ነው ሀሳቡ። ከዚያ ደግሞ በአገውኛ ሀሳብ አለ። ከዚያ አፍሪካ አፍሪካ እያለ ያለፈውን አፍሪካን ብሶትና ደመና ዘመን ይገልፃል። ከዚያ ደግሞ መነን ጦቢያ ናት ይላል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያደረገችውን አስተዋፅኦ ለመግለፅ። ከዚያ ደግሞ፡-

        ድሪቶ ለብሶ ብጣሽ ባዘቶ
        ዘመን ሲተክዝ ከላይ ቃል ሰምቶ
        በእንባዋ ጅረት የጠየቀችው
        ጊዜዋ ቢደርስ እልል አለችው…. እያለ
ይቀጥልና መጨረሻ ላይ ሰለብሬት ያደርጋል። ማሚያ…ማሚያ….ማሚያ… እያለ። በዓለም ላይ እናት መገለጫዋ አንድ ይመስለኛል። ፈረንጁ ሁሉ እናቱን ማሚ ማም ነው የሚለው። በአገውኛም በጉምዝኛም ማሚያ ማለት እናቴ ማለት ነው።
        ለምፃችን ለምፁ ይንፃ ሀጢያቱም ይቅለልልሽ
        ይጥራ አባይ ከደም ቅላቱ ወዝ መልኩ ይንጠፍብሽ
        ከዚያ ከጊዮን ከርስ ከመዳፍሽ
        ካፈርሽ አፍሶ ዘገነ
አለም ሁሉ ቱሩፋትሽን በቅርጫት ዳቦ ለመነ… ይላል። ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት ትሆናለች። እያለ ይቀጥላል። እናም ኢትዮጵያ መልካም ዘመን ከደረመኑና ከክፉው ጊዜ ይነሳል ለማለት ነው የሞርኩት።
አልበምህን ሰርቶ ለማጠናቀቅ  ምን ያህል ጊዜ ወስዶ ለመጠናቀቅ?
ከሰው መሆን ጋር ሁለት ዓመት ከ8 ወር ነው የከረምነው። እንደሌላው ቢሆን አስር ዓመትም ይወስዳል። ስቱዲዮአችን የምታይው ነው። ቀን በቀን ነው የሚሰራው! ቀን በቀን ነው የምልሽ። ውልፊት የለም። እንደሌላው ስቱዲዮ ቀጠሮ አንይዝም። እኔ በሙዚቃው ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በ11 ዓመቴ ነው ክራር የያዝኩት። የእድሜ ዘመን ትሬኒንግ ልትይው ትችያለሽ።
እኔ ሶሚክን ሳውቀው በውጪ ሆኖ እንደሚያይ ሰው ትልቅ ሲኒማቶግራፈርና ፕሮዲዩሰር ነው፡፡ ትልልቅ ፊልሞችን፣ "እንደ ማር እስከ ጧፍ" ያሉ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን፣ ትልልቅ ማስታወቂያዎችን ሰርቷል። ግን አንተ እንደ ቅርብ ሰው ሰው መሆንን እንዴት ነው የምትገልፀው? ይሄንን ለምን ጠየቅኩህ መሰለህ? ድምፃውያን አልበም ለመስራት ከ5-10 ዓመት ይወስድባቸውና ለምን ቆየ ሲባሉ አቀናባሪው ሙዱ እስኪመጣ፣ ፕሮዲየሰሩ በቀጠሮ አመላለስን የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ እና ከዚህ አንፃር ነው ሶሚክ ምን አይነት ሰው ነው ያልኩህ?
ምን መሰለሽ? ጥበብን ለቢዝነስና ለገንዘብ ብለሽ ስራ ከጀመርሽ አስቸጋሪ ነው። ገንዘብ ያጋጫል። ይህ የተለመደ ነው። እኛ ግን ይሄ ነገር ለህዝብ ይጠቅማል፤ የኢትዮጵያን የሙዚቃ መሳሪያና ሙዚቃ ተጠቅመን ለህዝብ ጆሮ የሚመጥን ሥራ እንስራ ተባብለን ነው ስራ የጀመርነው። ሌላ ስሌት ውስጥ አልገባንም። ወደ ሶሚክ ስንመጣ በጣም ጎበዝ ልጅ ነው። የሰራው ስራ በጣም የገዘፈ እንደሚሆን ነው የሚታየኝ። አሁን ፍቅር እስከመቃብርን 12 ሲዲን ቀርጿል። እንዴት እንደስራው ብታይ ተዓምር ነው የምትይው።
አሃ አንተ ፍቅር እስከመቃብር ላይ ተሳትፎ የለህም እንዴ?
አይይይ… እንዲያው ምስጢር ማውጣት እንዳይሆንብኝ እንጂ የሙዚቃ ማጀቢያዎች ሰርቻለሁ፤ ዘፈንም ሰርቻለሁ።
ስለዚህ ሶሚክ በኪነጥበቡ በርካታ ትሩፋቶችን የሚሰጠንና እየሰጠን ያለ ልጅ ነው እያልከኝ ነው?
አዎ በሚገባ! ሰሚክ ድንቅ ልጅ ነው። የወደፊት ፕሮጀክቶቹን እናወራለን። በጣም ትልልቅ ፕሮጀክቶች ናቸው። እናም ደግሞ ልጁ ጤናማ የጥበብ ሰው መሆኑን የምታውቂው ስራውን ስራ በቃቸው… መኮፈስ መወጠር የለም። የሱን አቅም አውቀዋለሁ። እኔ የሰውን ችሎታና አቅም  እረዳለሁ። እድሜ ይስጠን እንጂ በሶሚክ ገና ብዙ የጥበብ ተዓምራትን እናያለን።
ቀደም ብለን ስናወራ በአልበሙ ያልተካተቱ በዛ ያሉ ሙዚቃዎች ነገር ግን ሌላ ዘውግ ያላቸው ስራዎች እንዳሉህ ነግረኸኝ ነበር፡፡ ምን ልታደርጋቸው ነው?
እኛ ሁሉንም እንሰራለን ብለን እናምናለን። ለቀጣዩ አልበም እርሾውን ሰጥተነዋል። ቀጣዩ አልበም የዛሬ ሶስትና አራት ዓመት ይወጣል አይደል። እኛ ግን ስራውን አሁን ነው የ

ምንጀምረው እና ቀሪዎቹ በቀጣዩ አልበም ተካትተው ይወጣሉ።
"እናትዋ ጎንደር" እና "ካሲናው ጎጀማ" ወጥተው ተወዳጅነትን ካተረፉ በኋላ በሀገርም ውስጥ ሆነ በውጭ ኮንሰርት እንስራ ተር እናድርግ የሚሉ ግብዣዎች ቢቀርቡልህም "እነዚህ ዘፈኖች ገና ቅምሻዎች ናቸው፣ ህዝቡን በደንብ ፈትፍቼ ላጉርሰውና ከዚያ ይደርሳል" ብለህ ግብዣውን ወደ ጎን ማለትህን ሰምተናል። አሁንስ ምን ታስባለህ?
አሁን እንግዲህ "ቡርቧክስ" የተሰኘ ባንድ አለን።  የባንድ ልምምድና የድምጽ ሙከራ እናደጋለን። አዲስ የሚሰሩ ክራሮች አሉ። ብዙዎቹ የድርድርና ቆዳ ናቸው የሰራናቸው። እነዚህ  ወደ መድረክ ሲመጡ የሚሰጡንን ውጤት በደንብ ካጤንን በኋላ በአገር ቤትም በውጪም ያሰብነው ስራ አለ።
ቪዲዮ እየተስራላቸው ያሉ ዘፈኖች አሉ ከአልበሙ?
"አስቻለ" ያው ቪዲዮ ተሰርቶለት ተለቅቋል። በቀጣይ "እንገር ወሎ"ን ለመስራት ወሎ እንሄዳለን። የሸዋውም "ፍየሌን ነብር በላት" እየተሰራላቸው ነው።
ከህዝብ ምን አይነት ግብረ መልስ ጠብቀህ ነበር? ከጠበቅኸው ምን ያህሉን አገኘህ?
የህዝቡን አስተያየት መለካት አይቻልም። ከሚገባው በላይ ነው እጅግ በጣም…...፡፡ ኮሜንት ሳይ "ኧረ አንቀጠቀጠኝ" የሚል ሁሉ አለ(ሳቅ…) እኔ በፊት ቲክቶክ ብዙ አላይም ነበር። ቲክቶክ ላይ ሙስሊሞቹ ልብሱን ለብሰው እንገር ወሎን ሲሰሩበት ጉድ ነው የምትይው። አገራችን እንደዚህ ናት አይገርምሽም። እኔ ኢትዮጵያ ወሎን እንድትሆን ነው የምፈልገው፡፡ እውነቴን ነው የምልሽ፡፡
"ዓለም ስትሰለጥን ወሎን ትመስላለች" ይባላል….
እውነት ነው። ወሎ ማለትኮ ቀድሜም ነግሬሻለሁ ነውር የሌለበት ኤሪያ ነው።  እዛ እነከድጃ ቤት ሄደህ የአይን ሻወር ብትፈልግ፣ ቴምር መብላት ቢያምርህ ሁሉ ሙሉ ነው። ወንድሟ እህቴ ላይ አፈጠጥክ ብሎ አያጉረጠርጥብህ… ኧረ ተይኝማ ወሎ ረሃ ነው እናቴ። እኔ አሁን የወሎ ሳዱላዎች ቤት ለማቅናት አረብ አገር ሄደው ሲሰቃዩ በጣም ነው የማዝነው… ሙች የምሬን ነው። ስንት ዘመን ይህን ስቃይ ተሸከሙ መሰለሽ? የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቆሻሻ ሆኖ ለጋና ወጣት የወሎ ቆንጆዎች አረብ አገር ሄደው ስቃያቸውን ሳስበው አለቅሳለሁ። ቻግኒ ብትሄጂ  በሰፈራ ከመጡ በርካታ ወሎዬዎች ጋር ነው የኖርነው። ተምረን ያደግነውም ከነሱ ጋር ነው።
"እመትሸዋ"ም በጣም ትልቅ ሀሳብ ነው'ኮ ….
እሱም በጣም ጥልቅ ነው። አንድ አሻግሬ ባዬ የተባለ ሰው ግጥም ላከ። ከዚያ ሳየው አንድ አራት አምስት ግጥም አየሁ። አሃ እየሰራሁ ያለሁት ሥራ ምንድነው አልኩኝ። የማላውቀው ሰው ነው ግጥሙን የላከው። አሻግሬ ይባላል። እንዴት ፃፍከው ስለው ትዝ አልከኝ ላኩልህ አለኝ። ዜማውን እኔ ነኝ የሰራሁት። በል አምስት ግጥም አስገብቻለሁ አልኩት፡፡ አፈወርቅ አልሰራሽ እግዜር ነው እንደኔ
    ምነው ባንቺ ብቻ ፅድቅና ኩነኔ ይላል።
ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን አላየኋቸውም ነበርና ልጁ ይህን ሰጠኝ። ሶሚክ "አስቻለ ዘረያዕቆብን ፃፈው" ሲለኝ ጽፌዋሁ አልኩት። አንድ ታሪክ ሰምቻለሁ፡፡ ዘረያዕቆብ የጸሎት መጽሐፍት ፅፎ “ቀይ ቀይ አድርግበት እመቤቴ ላይ ስትደርስ” ይል ነበር የሚል አለኝ።
አሃ አልኩኝና ማታ፡-    ዘረያዕቆብ ፀሎት መፅሀፍ አፅፈው
    እናቱ ላይ ስትደርስ በቀይ አድምቀው
ብዬ ጻፍኩት። ሙዚቃ ሀሳብ ነው። ሀሳብ ከተገኘ ግጥሙ ይመጣል። ለህዝብ ይጠቅማል፤ መሰራት አለበት ብለሽ ካሰብሽ፣ ፈጣሪ አሜሪካ ያለ ሰው ያስፈልገዋል ብሎ ይጠራዋል። እንደዛ ነው የማምነው። ለምሳሌ ካሲናው ጎጃም ላይ እንቅጥቅጥ የምትመታው ትልቋ ሴትዮ ገጠር ነው ያለችው፤ ግን ዘፈን አለ ስትባል መጣች፤ ማንንም አላስጠጋም አለች። አይተሻታል? እንግዚህ ጥሪ ነው፡፡ ከገጠር መጥታ ነው የተቀረፀችው። ብር እንስጥሽ ስትባል "ብራችሁን ወዲያ" ብላ ነው የሄደችው። ስራ ስትሰሪ የሚወርድልሽ ነገር አለ።
ከአንዲት ጓደኛዬ ጋር ቁጭ ብለን "እንገር ወሎ"ን ስናዳምጥ "የአስቼ ድምፅ ከመንዙማውም ከቅዳሴውም የቀላቀለ፤ ሁሉ አይቅርብኝ ያለ ድምፅ ነው" አለችኝ፡፡ በዚህ ትስማማለህ?
እውነቷን ነው። ቻግኒ ሙስሊሞች አሉ፤ አብረናቸው የኖርን፡፡ እንደነገርኩሽ ወልድያ ነበርኩ። የምናውቃቸው ሙስሊሞች ቤት መንዙማ እንሰማለን። ከኢቲቪው ጋዜጠኛና ገጣሚ ጓደኛሽ ጋርም ስንፅፍ መንዙማ እንከፍታለን፤ መንዙማ ትንሽ ከበድ ይላል።
    ከመቃብር በላይ ስም ይውላል ብሎ
    ፍቅርና ጀግንነት ያውቅበታል ወሎ
    ወሎ ልበ ሰፊ መተኛ ድንኳን
    አበጋር ይፈራል እንኳን አምላኩን
ሲል መሰንቆውን ዘለሰኛ አድርገው አልኩት፤ ሁለቱንም ለማመጣጠን።እናንተ በደንብ አድምጣችሁታል።
በሙዚቃ ህይወትህ ፈታኝ የምትለው ወቅት የትኛው ነው?
በሙዚቃ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ህይወቴ በጣም ተፈትኛለሁ። ብዙ ውጣ ውረድ አልፌያለሁ። ይሄ ልጅ ሰው አይሆንም ነበር የምባለው። እዚህ ይደርሳል አልተባለም ነበር። እና ፈተናዎቹን ተቋቁሜ አልፌ አልፌ አምና አቀናባሪዬና ጓደኛዬ እስራኤል ሲያልፍ እጅግ በጣም አዘንኩ። ያው ፈጣሪ የወደደውን አደረገ። ልጁን አሳምሬ አሳድጋለሁ። ያው አላገባሁም፤ ግን አንድ ልጅ አለኝ ነው የምለው።


Read 509 times Last modified on Monday, 05 February 2024 21:46