Monday, 05 February 2024 15:43

“‘የዘመን ቃናዎች ፩’ን የሰራሁት ነባር አርቲስቶችን ለማክበርና ለማመስገን ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

-ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ-
በአንጋፋዎቹ የአገራችን ድምፃውያን አሰፋ አባተ፣ ጥላሁን ገሰሰ እና እሳቱ ተሰማ ከዘመናት በፊት የተቀነቀኑና ከአድማጭ ጆሮ እርቀው የኖሩ ሦስት ተወዳጅ ሙዚቃዎች በወጣቱ ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ ዳግም ተቀንቅነው፣ “የዘመን ቃናዎች ፩” በሚል ስያሜ የሙዚቃ ቪዲዮዎች እንደተሰራላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ትላንትና አርብ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ሥራዎቹ በራሱ ዳዊት ፅጌ ዩቲዩብ እንደሚለቀቁ ተነግሯል፡፡
“የዘመን ቃናዎች ፩” የሙዚቃ ቪዲዮዎችን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ  ረፋዱ ላይ ድምፃዊ ዳዊት ፅጌና አንጋፋው የሙዚቃ አቀናባሪ አበጋዙ ክብረወርቅ ሺዎታን ጨምሮ ሌሎች በሙዚቃ ሥራዎቹ የተሳተፉ ባለሙያዎችና የቀድሞ አርቲስቶች ቤተሰቦች  በተገኙበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫው በጥያቄና መልስ፤ በማብራሪያና አስተያየት የታጀበና ከወትሮው በተለየ መልኩ ቁምነገር የሚያስጨብጥና ጥበብ ጥበብ የሚሸት እንደነበር ታዳሚዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መድረኩን በጥበብና በዕውቀት የመራው የመድረኩ ሞገስ  ተዋናይ ግሩም ዘነበ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ብዙዎች መሥክረዋል፡፡
 


ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ የራሱን ዘፈኖችና አልበም ከመሥራት ይልቅ ለምን የነባር አርቲስቶችን ሙዚቃዎች በድጋሚ ለማቀንቀን እንደመረጠና ዓላማውንም ሲያስረዳ፤ “ትውልድ የራሱን ቀለም አስቀምጦ ማለፍ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላውም እንዲሁ እንዲያደርግ እመክራለሁ፡፡ የዘመን ቃናዎች ቀደምት አርቲስቶችን የማክበር መንገድ--- መድረክ  መፍጠር ነው ዓላማው፡፡” ብሏል፡፡
የራሱንም ሙሉ አልበም ሰርቶ በማጠናቀቅ ላይ እንደሆነ የጠቆመው ድምጻዊው፤ በቅርቡ ለአድማጭ ጆሮ እንደሚደርስም በይፋ ቃል ገብቷል፡፡
አንጋፋው የሙዚቃ ሰው አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ የሙዚቃዎቹን ዳግም ማቀናበር አስመልክቶ ሲናገር፤ “እነዚህን ሥራዎች የተቀበልኩበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የአስቴር አወቀንና የጥላሁን ገሰሰን ሥራዎች ተቀብዬ በድጋሚ ስለሰራሁ ነው፡፡ ሦስቱም ዳዊት ፅጌ የተጫወታቸው ሙዚቃዎች መሰረታዊው ጉዳይ ሳይነካ ወይም ሳይለወጥ ነው በድጋሚ የተቀናበረው፤ እኔ ብዙ የጨመርኩት ነገር የለም” ብሏል - ትህትና በተጫነው ድምፀት፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከታደሙት ብዙዎቹ ግን በዚህ ትህትና በእጅጉ በተጫነው አስተያየቱ ጨርሶ አይስማሙም፡፡ ለዚህ ደግሞ በመግለጫው መጨረሻ ላይ ታዳሚው የተጋበዘውን ዳግም የተቀነቀነና የተቀናበረ ሥራ ይጠቅሳሉ፡፡ ልዩነቱ በግልጽ የሚታይ ነው ይላሉ - አስተያየት ሰጪዎች፡፡
የሙዚቃ ቪዲዮዎቹ የተቀረፁት ከትላንት በስቲያ ጋዜጣዊ መግለጫው በተሰጠበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስ መኮንን አዳራሽ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ይሄ ደግሞ ግጥምጥሞሽ ሳይሆን በዕቅድ ታስቦበትና ታልሞበት የተከወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከሰሩ አይቀር እንዲህ ነው - ጥንቅቅ አድርጎ፡፡
የመድረኩ አጋፋሪ አርቲስት ግሩም ዘነበ በበኩሉ፤ የዘመን ቃናዎች ፩ የተሰራበትን ምክንያት  ሲያብራራ፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ አርቲስቶች ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ለከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋ ለመስጠትና ለማክበር የተሰራ የሙዚቃ ስብስብ መሆኑን በአፅንኦት የገለፀ ሲሆን፤ ሌላው ምክንያት ደግሞ እነዚህን ሙዚቃዎች ሌላ ከፍታ በመጨመር አቀናብሮ ለዘመኑ  ጆሮ በሚጣጣም መልኩ ለአድማጭ ለማቅረብ ነውም ብሏል፡፡
የዘመን ቃናዎች ቀጣይ ክፍሎች ወደፊትም እንደሚወጡ በመግለጫው ላይ የተጠቆመ ሲሆን፤ ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰነዘረው አስተያየት፤ “ቀጣዮቹን ክፍሎች እኔም ላልጫወታቸው እችላለሁ፤ ግን ብዙ ሥራዎች አሉ፤ በቀጣይ  የሚወጡ፡፡” ሲል ጠቁሟል፡፡
“የዘመን ቃናዎች ፩” የሙዚቃ ቪዲዮዎች የህግና የሞራል ግዴታዎችን በአግባቡ ተወጥተው መሰራታቸውም በመግለጫው ላይ ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ ተወዳጁ ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ በጋዜጣዊ መግለጫው መደምደሚያ ላይ ለአርቲስቶቹ ቤተሰቦች በሙሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ “የእናንተ ፈቃድ ባይኖር ኖሮ ሙዚቃዎቹን መሥራት አንችልም ነበር” ብሏል - ዳዊት ፅጌ፡፡


ድምፃዊው በሙዚቃ ስራዎቹ ላይ ለተሳተፉት ባለሙያዎችም ምስጋናውን ከመድረክ አቅርቧል - በይፋ፡


የጋዜጣዊ መግለጫውን ኹነት ያዘጋጀው የተለያዩ ኤቨንቶችን በማዘጋጀትና በመምራት የሚታወቀው አንጋፋው የህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ኢምር አድቨርታይዚንግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 446 times