Monday, 05 February 2024 22:04

አንድ ታጣቂ ቡድን ዓለምን የሚያስጨንቅበት - የድሮኖችና የሮኬቶች ዘመን!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

የቀይ ባሕር የጭነት ማመላለሻ መርከቦች እንቅስቃሴ ከአምና ካቻምና ጋር ሲነጻጸር፣ ከግማሽ በታች ወርዶ ወደ ሩብ እየተጠጋ እንደሆነ ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ይገልጻል።
ከመላው ዓለም የምርቶች ንግድ ውስጥ 10 በመቶ ያህሉ በቀይ ባሕር በኩል ያልፍ ነበር። ቀላል አይደለም። የዓለም ዓመታዊ የባሕር ንግድ 11 ቢሊዮን ቶን (110 ቢሊዮን ኩንታል) ገደማ ነው። ከዚህ ውስጥ 11 ቢሊዮን ኩንታል በቀይ ባሕር በኩል ያልፋል።ዛሬ ግን፣ ወደ 3 ቢሊዮን ኩንታል ቀንሷል።
ጉዳቱ ደግሞ የዚያኑ ያህል ጨምሯል። ዓለምን ሁሉ የሚነካ ሆኗል።
በኢራን መንግሥት ድጋፍ የየመን የሁቲ ታጣቂ ቡድን የፈጠረው የቀይ ባሕር ነውጥ፣ በአንድ አካባቢ ላይ የተፈጸመ ቢሆንም፣ የአንድ አካባቢ ጉዳት አይደለም።
በእርግጥ፣ ከቅርበታቸው የተነሳ ለአፍሪካና ለአረብ አገራት ትልቅ ራስ ምታት ሊሆንባቸው ይችላል። ምነዋ ድምጻቸው ብዙም አልተሰማም? ጥሩ ጥያቄ ነው። የአፍሪካ መንግሥታት፣ "ምንም ብንጮኽ ማንም አይሰማንም፤ ዓቅምም የለንም" ብለው ተስፋ ካልቆረጡ በቀር እንዴት ዝም ይላሉ?
የአረብ አገራትስ?
የፖለቲካ ነገር ጠመዝማዛ ነው። ግን፣ የጠመዘዙት ነገር ተመልሶ ራሳቸውን እስረኛ ያደርጋቸዋል። የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት፣ በደፈናው "የእስራኤልና የአረብ ጦርነት ነው" ተብሎ ሲሰየም ወይም እንደ ሃይማኖት ቅራኔ ተደርጎ ሲቆጠር፣ በአረብ አገራት ላይ ምንም መዘዝ የማያመጣ ይመስላል። ግን ያመጣል።
“እስራኤል ላይ ተጠምጥሞ ይጥላታል” ተብሎ የተቋጠረ የፕሮፓጋንዳ ገመድ፣ የአረብ አገራትንም ጠልፎ የሚይዝ ሆኗል። የኢራን መንግሥትና የሁቲ ታጣቂ ቡድን፣ የቀይ ባሕር ጉዳይ ከእስራኤልና ከሐማስ ጦርነት ጋር አዛምደውታል። ታዲያ የአረብ መንግሥታት እንዴት ደፍረው ይናገሩ?
እናም፣ የቀይ ባሕር ነውጥ፣ የአፍሪካና የአረብ አገራት ጭንቀት ቢሆንም፣ ዝም ብለው የሚያዩ ተመልካቾች ሆነዋል - የአፍሪካ መንግስታት በዓቅም ዕጦት፣ የአረብ መንግሥታት በፕሮፓጋንዳ ተገዝተው ተሸብበው።
እንዲህ ሲባል ግን፣ የቀይ ባህል ነውጥ የአፍሪካና የአረብ አገራት ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን በመርሳት አይደለም።
የዓለም ጭንቀት ነው። ጉዳቱም፣ ዓለምን ሁሉ ያዳርሳል።
የአንዱ ጉዳት ከሌላው ሊብስ ይችላል እንጂ ያልተነካ አገር የለም። የአውሮፓ የኢኮኖሚ ዕድገት ቀድሞውንም ደካማ ቢሆንም፣ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ፣ "ትንጥየዋ" ዕድገት በሩብ ያህል ትቀንሳለች ብሏል - አይኤምኤፍ። የአውሮፓ የኢኮኖሚ ዕድገት ዘንድሮ 1 በመቶ እንደማይሞላ ነው የተገመተው።
የቻይና የውጭ ንግድም አደጋ ገጥሞታል። የቻይና ባለሥልጣናት በቀጥታ ባይሆንም በኢራን መንግሥት በኩል ቅሬታቸውን ወይም ቁጣቸውን ገልጸዋል።  መቆጣት ሲያንሳቸው ነው፡፡ የባሕር ንግድ ከተረበሸ፣ የቻይና ኢኮኖሚ ይቃወሳል። አለምክንያት አይደለም።
የዓለም የንግድ መርከቦች በዓመት 450 ሺ ጊዜ ወደ ወደብ ጎራ ይላሉ - ለመጫንና ለማራገፍ። ከዚህ ውስጥ 80 ሺ ያህሉ ከቻይና ለመጫንና ወደ ቻይና ለማራገፍ ነው።
ታዲያ፣ የሁቲ ታጣቂ ቡድን በሚሳዬልና በድሮን በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ሳቢያ የባሕር ንግድ ሲረበሽ ቻይና እንዴት ዝም ትበል? ከቻይና ወደ አውሮፓና ወደ አሜሪካ በየዕለቱ የሚካሄደው የምርቶች ንግድ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል። በዓመት ከ700 ቢሊዮን ዶላር በላይ።
ኧረ ያልተነካ አገር የለም፡፡
በእርግጥ ቀዳሚዋ ተጎጂ ለጊዜው ግብፅ ናት። በዓመት በስዊዝ ቦይ መተላለፊያ "ለኮቴ" በማስከፈል 9 ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች።
ዘንድሮ ግን፣ ገና የቀይ ባሕር ችግር በተፈጠረ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ የስዊዝ ቦይ ገቢ 40 በመቶ አሽቆልቁሏል። ከዚያ ወዲህም እየተባባሰ ነው። የመርከቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነውና። በሌላ አነጋገር የግብፅ ኪሳራ በቢሊዮን ዶላሮች ይሆናል ማለት ነው።
ዎል ስትሪት ጆርናል በበኩሉ፣ የጭነት ማጓጓዣ ወጪ በቀይ ባሕር በኩል ለሚመላለሱ መርከቦች ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር ወደ አራት ዕጥፍ እንደናረ ዘግቧል - በሐሙስ ዕለት ዕትሙ።
በኮረና ጊዜ ካልሆነ በቀር፣ ለወትሮ ከቻይና ሻንጋይ ወደ አውሮፓ የባሕር ማጓጓዣ ዋጋ ለአንድ ኮንተይነት 1000 ዶላር አይሞላም። የቀይ ባሕር መተላለፊያ ስለተረበሸ፣ የመርከቦች ጉዞ በደቡብ አፍሪካ በኩል ዞረው ወደ አውሮፓ ሲጓዙ ግን የጭነት ዋጋው ከ2000 ዶላር በላይ ይሆናል። የቀይ ባሕር ሰላም፣ ለቻይና መንግሥት ከባድ ራስ ምታት ነው። እስካሁን፣ የቻይና መንግሥት ቁጣውን ለመቆጣጠር እየሞከረ ይመስላል። ቁጣ ያንሰዋል ማለት ግን አይደለም። የማጓጓዣ ዋጋ እጅግ የናረው፣ ከቻይና ወደ አውሮፓ ባለው የባሕር መስመር ላይ ነው።
ከቻይና ወደ አውሮፓ፣ በቀይ ባሕር በኩል የ35 ቀን ጉዞ ነው - 15 ኪሎሜትር ገደማ። በደቡብ አፍሪካ በኩል ዞረው ሲሄዱ ግን፣ 45 ቀን ይፈጃል። ከ21 ኪሎሜትር ይበልጣል የባሕር ጉዞው። የቻይና ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም።
በአማካይ የአንድ ኮንቴይነር ማጓጓዣ ዋጋ 2000 ዶላር ገደማ ደርሷል። በዓመት ደግሞ ከ160 ሚሊዮን በላይ ኮንቴይነር ይጓጓዛል። ለኮንቴይነር ጭነቶች ብቻ 320 ቢሊዮን ዶላር ነው የጭነት ዋጋው። የማጓጓዣ ዋጋ በግማሽ መጨመሩና መቀነሱ፣በዶላር ሲመነዘር  ለቻይና ከባድ ነው። ብዙ የምታስጭን አገር ናትና። ከኮንቴይነር ጭነቶች በላይ ደግሞ፣ የነዳጅ፣ የማዕድን፣ የብረታ ብረትና የእህል ጭነቶችን ለማጓጓዝ ሌላ የዋጋ ንረት ጨምሩበት። ታዲያ የቻይና ባለሥልጣናት እንደሚናደዱ መገመት ይከብዳል? እስከመቼ ንዴታቸውን ውጠው እንደሚቆዩ መገመት ነው አስቸጋሪው ነገር።
ያው የብዙ አገራት ተስፋ፣ "አሜሪካ የሆነ ነገር ማድረጓ አይቀርም" የሚል ስሜት ላይ የተንጠለጠለ ተስፋ ነው። መቼም አሜሪካ ዝም አትልም… ብለው ያስባሉ - ጉዳዩ ያሳሰባቸው የአፍሪካና የአረብ አገራት። አፍ አውጥተው ባይናገሩትም፣ ተስፋ ያደርጋሉ። በይፋ በአደባባይ ግን አይናገሩም፡፡ አሜሪካ ሚሳዬል መተኮስና የጦር አውሮፕላኖችን ማብረር ስትጀምር፣ አንዳንዶቹ ወደ መቃወም ሊያዘነብሉ ይችላሉ። ሲቃወሙም ግን፣ አሜሪካ የሁቲ ታጣቂዎችን እንድታስታግስላቸው ከመመኘት ጋር ነው።
በእርግጥም፣ ምኞታቸውና ተስፋቸው ለከንቱ አይደለም። እስካሁን፣ አሜሪካ ብቻ ናት፣ የቀይ ባሕር ነውጠኞችን አደብ ለማስገዛት የሞከረችው - በእንግሊዝ አጃቢነት።
ግን እየተሳካላት አይመስልም። አንደኛ ነገር፣ የግብር ይውጣ የሚመስል ነገር ነው - የአሜሪካ የቀይ ባሕር ዘመቻ። ሁለተኛ ነገር፣ አሳማኝ ባልሆነ የመፍትሔ ሐሳብ ነው አጀማመሩ። የንግድ መርከቦችን በጦር መርከቦች አጅቦ ማሳለፍ አስተማማኝ መፍትሔ አይደለም። ለዘመኑም አይመጥንም። ድሮን እና ሚሳዬል በየአገሩ የተዛመተበት ዘመን ላይ ነን። ታጣቂና አማፂ ቡድኖች ሳይቀሩ ድሮኖችን የሚያሰማሩ፣ ሚሳዬሎችን የሚያዘንቡ ሆነዋል።
በዚያ ላይ፤ ከርቀት ሆኖ ባሕርና ምድር ላይ ሰላም ማስፈን ከባድ ቢሆንም፣ ለመረበሽና ለመበጥበጥ ግን፣ ዘመኑና ቴክኖሎጂው ይመቻል።
 ታጣቂና አማፂ ቡድኖች የራሳቸው ሳተላይት ላይኖራቸው ይችላል። ግን፣ የሳተላይት መረጃ የሚሰጣቸው፣ ድሮኖችን የሚለግሳቸው፣ ሚሳዬሎችን የሚያስታጥቃቸው፣ የሮኬት መገጣጠሚያ መሣሪያዎችን የሚተክልላቸው፣ በአጠቃላይ ከርቀት ሆኖ የሚደግፋቸው አጋዥ መንግሥት ካገኙ፣ አካባቢያቸውን ማናወጥ አያቅታቸውም። ከርቀት ሆኖ መበጥበጥ እጅግ ቀላል የሆነበት ዘመን ላይ ነው ያለነው።
ታዲያ፣ የንግድ መርከቦችን በጦር መርከብ እያጀብኩ አሳልፋለሁ የሚል መፍትሔ አስተማማኝ ነው? አስተማማኝ እንዳልሆነማ በተግባር እያየነው ነው።
የአሜሪካ ችግር ይህ ብቻ አይደለም።
የሁቲ ታጣቂዎች፣ የመቶ ሺ ዶላር ሚሳዬል ሲተኩሱ ወይም የ10 ሺ ዶላር ድሮን ሲልኩ፣ የሚሊዮን ዶላር ሚሳዬሎችን በመተኮስ ማክሸፍ፣… ምን ተብሎ ይጠራል? አዎ ከአጣዳፊ የፍንዳታ አደጋ ያድናል። ነገር ግን፣ ትልቅ ኪሳራ ነው። አያዋጣም። ቢያዋጣ እንኳ አያዛልቅም። ሚሳዬልና ሮኬት መወራወር ለሁቲ ታጣቂዎችና ለኢራን ሊያዋጣቸው ይችላል። ለአሜሪካ ግን አያዋጣም፣ አያዛልቅም።
የቀይ ባሕር ነውጥ እየባሰበት ከሄደና የሚሳዬል ውርወራና የሮኬት ቅብብሎቹ ከተቀጣጠለ ግን፣ ለኢራንና ለሁቲ ታጣቂዎችም የሚያዋጣ አይሆንም። የለየለት ጦርነት፣ ኪሳራው ብዙ ዕጥፍ ይከፋል።
በእርግጥ የለየለት ጦርነት ለአሜሪካም አስቸጋሪ ነው። የኢራቅና የአፍጋኒስታን ጦርነትን መድገም ለአሜሪካ የሚታሰብ አይደለም። የኢራን ጦርነት ደግሞ እጅግ የባሰ ሊሆን ይችላል።
እና የቀይ ባሕር ነውጥ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው?
የነውጥ የሽፍታ ቦታ ሆኖ ይቀራል?
ወይስ የሚማረሩ አገራት እየበረከቱ ንዴታቸው ይገነፍላል?
ወይስ፣ ሚሳዬልና ሮኬት ከመወራወር የተለየ፣ ወደለየለት ጦርነትም የማይገባ ሌላ "መካከለኛ የጦርነት አማራጭ" ይኖራል?
የነገውን ለመገመት ሊያስቸግር ቢችልም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ለከርሞ እንደማይዘልቅ መናገር ግን የሚከብድ አይመስልም። ነገርዬው፣ የብዙ መቶ ቢሊዮን ዶላሮች ጉዳይ ነውና።
የአረብና የአፍሪካ አገራት ግን፣ ኢትዮጵያም ጭምር፣ የሚሆነው ሁሉን ከዳር ሆነው ከመመልከት ውጭ ለጊዜው ሌላ አማራጭ የላቸውም። ወይ አማራጭ እንዳይኖራቸው አድርገዋል። ወይ የዓቅም ጉዳይ ሆኖባቸዋል።

Read 564 times