Saturday, 10 February 2024 09:52

ጠ/ሚኒስትሩና የህውሐት አመራሮች በሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ዙሪያ ትናንት ሲመክሩ ዋሉ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና የህውሐት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ተገኝተው ሲመክሩ  ዋሉ።የሁለቱ ወገኖች

ውይይት ለመልሶ ግንባታና በሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ላይ ያተኮረ እንደነበር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ድረ-ገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ጽ/ቤቱ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ጠ/ሚኒስትሩ

ዶ/ር ዐቢይ አህመድና የህውሃቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ የትግራይ  ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በድህረ ግጭት መልሶ ግንባታና በሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉንና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያከናወናቸው ተግባራት ላይ ግምገማ መካሄዱን ምንጮች ጠቁመዋል።
የህውሃቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ  ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ፊት ለፊት ሲገናኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ሲሆን፤ በሁለቱ ወገኖች

መካከል የተደረገው ውይይት በፕሪቶሪያ የተደረገው ሰላም ስምምነት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።
ከፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት በኋላ መሻሻሎች መኖራቸው ቢጠቀስም፣ አሁንም የሚቀሩ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን በሁለቱም ወገኖች በኩል ሲጠቀስ ሰንብቷል።ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በህዝብ

ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደተናገሩት፤ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የፌደራል መንግስቱ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በትብብር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። ለአብነትም ባንኮች

በ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ስራ መጀመራቸውን፣ የ4ጂ የቴሌ ኔትወርክ አገልግሎት መጀመሩና በክልሉ ያሉ አየር ማረፊያዎች ስራ መጀመራቸውን መጥቀሳቸው አይዘነጋም።
ከዚህ በተጨማሪም የፌደራል መንግስቱ የህውሃት ታጣቂዎች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ትጥቃቸውን አለመፍታታቸውን በመግለፁ ቅሬታውን ሲያሰማ ቆይቷል። ይህንኑ ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ

አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን “የፌደራል መንግስት የውጪ ሃይሎችን ከትግራይ ክልል አላስወጣም ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ አላደረገም” የሚል ትችት አቅርበዋል።
በትናትናው ዕለት በጠ/ሚኒስትሩ ፅ/ቤት የተካሄደው የሁለቱ ወገኖች ውይይት ለችግሮቹ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።


Read 1213 times