Saturday, 10 February 2024 10:03

ሶሻሊዝም በደበበ ሰይፉ እና በበዕውቀቱ ሥዩም ብዕር

Written by  (ዮናስ ታምሩ ገብሬ)
Rate this item
(3 votes)

አይሁዳዊው ግና በቀድሞዋ ፕሩሺያ በአሁኗ ጀርመን መሰንበቻውን ያደረገው አቶ ማርክስ (ለአቤቶ ኤንጂልስ ‹ወዳጄ ልቤ የድንች መግዣ አጠረኝ፤ በሞቴ ርዝራዥ ፍራንክ ስደድልኝ› ሲል የተማጸነው፤ በሚወደው

ትንባሆ ሕይወቱን ያጣው ሶሲዮሎጂስታዋይ ፖትላኪ)፡- ካፒታሊስቶች የጭቁኑን ሕዝብ ደም የሚመጡ ጭራቆች ናቸው/Capitalists are vampires; they suck the blood of

proletarians ሲል ጎፈላ፤ የእንግሊዝ ባላባት ልጅ የሆነው ኤንጂልስ (የእኛው ደበበ ሰይፉ) ካፌ ውስጥ እንደ ቆላ ፍየል ከአንዲት ጥጋት ጭብጥ ብሎ በራድ እየማገ ሳለ ይኼንን ሰው ያገኘውና ‹‹እንዲያ

ያለ ሀሳብም አለ! አንዳንዱ ሰው እንዴት ሸጋ አሳቢ ነው እቴ!›› በማለት እጁን በአፉ በጫነ ቅጽበት ይኼንን አብዮት ተቀላቀለ፤ ያ ሀባብ ራስ ሌኒን ደግሞ ሶቭየት ሕብረታዋይ የሕግ ባለሞያ፣ ፖትላኪና

የአመጻ ሰው ነበር፤ ሌኒንስም ይሉት ሶሲያሊስታዊ/ተግባቦታዊ ይትባሃል በሶቭየት ሕብረት እንዲንሰራፋ ምክንያት ሆነ፡፡ ጭቁኑን ሕዝብ የመሬት፣ የቤት፣ የመብት… ባለቤት እናደርጋለን በማለት ብዙ ተጓዙ።
….ወደ አሁኔ ልስከንተር….    ….በእኛ አገር፣ ደርግ (ወታደራዊ ፓርቲ) የተገበረው ሶሻሊዝም ብዙዎችን ያግባባል፤ በርካቶችን ደግሞ አያግባባም፤ አንድን ፖለቲካዊ ርዕዮተ-ዓለም፣ ኀልዮት፣ ፍልስፍና…ወዘተ.

ለማራመድ በቂ የሆነ ቅድመ-ዝግጅት መኖር እንዳለበት መደንገግ የማያከራክር ነው፤ ሶሻሊዝም ግቡ ጦርነትን አቁሞ፣ ፊውዳላዊ ሥርዐትን ገትቶ፣ ገበሬውን የመሬት፣ የቤት፣ የባለንብረት ባለቤት ማድረግ ነው፤

የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ ሚዛን እንዲኖረው እንደማስቻል ዓይነት ትጋትን ይጠይቃል፤ ለዚህ ደግሞ ፋብሪካዎች፣ ግብዐትና ጤናማ የሥራ ቦታ ሊኖር ይገባል።
ወታደራዊ መንግሥት ጭቁኑን ሕዝብ እንዳንበሻበሸ መካድ ከባድ ነው፤ ድሃውን ሕዝብ የቤትና የመሬት ባለቤት አድርጓል፤ ግና ምን ያደርጋል! በእርስ-በርስ ጦርነትና በከተማ ውስጥ ግጭት እንዲረግፉ ሆነ እንጂ፤

ዘመቻውና ሽኩቻው ሲፋፋም በተሰፈረለት ቤትና ቦታ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ ማረፊያው መቃብር ሆነ። ድፍረት ይሁንብኝና፣ ደርግም፣ ኢሕአፓም፣ ወያኔም፣ ሻዕቢያም… ግብታዊዎች ነበሩ፤ ለአገሪቱ መቆርቆዝ ታሪክ

ይፋረዳቸዋል።
ኪነ-ጥበብ ማሕበራዊ፣ ምጣኔ-ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ኩነቶችን ማንፀባረቂያ ነው፤ ሥነ-ግጥም ማሕበራዊ ኩነቶችን እንዲነቅስ ይታመናል፤ ሥነ-ግጥም ዛሬ ላይ አይቸነከርም፤ ነገን ያስሳል፤ አንድ እርምጃ

ቀዳማይ እንዲሆን ዕሙን ነው።
ሥነ-ግጥም አንድ እርምጃ ይቀድማል የሚባለው ለዚህ ነው፤ ተንባይ ነው፤ ጠቋሚ፤ ሕዝቡ ካለበት የሞራል፣ የዕሴት፣ የፍልስፋና፣ የአገዛዝ፣ የታሪክ…ወዘተ ውጥንቅጥ ውስጥ ዕውነትን መርምሮ የሚያገኝበትንና

የሚያፈተልክበትን መንገድ ያሳያል፤ ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚያደርስ ዓይነተኛ ጥበብ ነው፤ ዕውነትን እንድንጠነቅቅ ሥነ-ግጥም ታስገድዳለች፤ ሥነ-ግጥም መንገድ ጠራጊ ነው፤ ከኋላ እየተንጦለጦለ

አይንቶሳቶስም፤ ይልቅ አቅጣጫ ይጠቁማል እንጂ።
ለዛሬ የወታደራዊ መንግሥት የአሠራር ይትባሃልን፣ ውለታውን፣ መውሰድ የነበረበትን ቅድመ ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮችን በደበበ ሰይፉ እና በበዕውቀቱ ሥዩም ግጥሞች አስታከን እንመልከት፡-     
ደበበ ሰይፉ እንደ ኤንጂልስ የባላባት ልጅ ነበር፤ መሬት አልባው ሕዝብ መሬት ያግኝ በማለት ቤተሰቡን ጣጥሎ የወታደራዊ መንግሥትን ርዕዮተ-ዓለም ተቀላቀለ፤ ስለ ርዕዮተ-ዓለሙ ጥንካሬ፣ ዓላማ፣ ትርፍ…

ይኼንን አለ፡-
‹‹የክረምት ማገዶች››
እንዲህ ተጫጭሰን፤
እንዲህ ተጨናብሰን፤
ውሃ እንዳለዘዘን፤
ከውሃ ተዋግተን…ተዋግተን…ተዋግተን
ውሃን አሸንፈን፤
እሳትን ፀንሰን፤
እሳትንም ወልደን፤
እሳትንም ሆነን፤
    /የክረምት ማገዶች/
ካጨለጨልንለት፣ የድሃውን ጎጆ፣ ቀሣ ከል ጭራሮ፤ ካበሰልንለት ዘንድ፣ የአርሶ አደሩን ንፍሮ፤
የሰርቶ አደሩን ሕዝብ፣ ለሰስ ያለ ሽሮ፤
ታሪክ ይዘምረው፣ የኛን እንጉርጉሮ፤
ዘመን ይመስክረው፣ የኛን ውጣውረድ፣
የእንግልት ኑሮ፤
(ከ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፤ የብርሃን ፍቅር፣ ቅጽ 2)
በዚህ ግጥም ደበበ ሰይፉ የሶሻሊዝምን ፋይዳ ይናገራል፤ ስለ ርዕዮተ-ዓለሙ ውለታ፣ አበክሮና መልካም ጎኖች ምናልባት ካለፈ በኋላ መስካሪ እንደሚመጣ በልበ-ሙሉነት ያወጋል፤ ወታደራዊ አገዛዝ የድሃውን ሕዝብ

ጎጆ እንዳቀናና መናውን እንደጋገረለት ይመሰክራል፤ በአጠቃላይ፣ ወታደራዊ መንግሥት ጠብ እርግፍ ብሎ ሕዝቡን እንዳገለገለ ደበበ ሰይፉ ቃሉን ሰጥቷል፤ አጉል መታበይ እና ፉከራ ነው ብለን እንዳናልፍ ቤተሰቡን

ያስተወውን ዓላማ መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፤ በሹማምንት ቤት ሆኖ የሞቀ ኑሮውን ማፋፋም ይችል ነበር ደቤ፤ ግና ይቅርብኝ ብሎ ጭቁኑን ሕዝብ ተቀላቅሏል።
መሸንገል ባይሆንም፣ ወታደራዊ መንግሥት መልካም ዓላማ ነበረው፤ ሕዝቡን የመሬትና የቤት ባለንብረትም አድርጎ ነበር፤ መልሶ ገደለው እንጂ፤ ማን ይረስ? ማን ይኑርበት? ከዚህ በዘለለ፣ የደርግ መንግሥት

በውሪዎች ታውኮ ነበር፤ በኢሕአፓ፣ በወያኔ፣ በሻዕቢያ፣ በመኢሶን… እና በሌሎች፤ እነዚህ የተጠቀሱ ሁላ ዩኒዬኒስት ነን ቢሉም አገር መከፋፈል ዋንኛ ዓላማቸው ነበር፤ ወታደራዊ መንግሥት ከእነዚህ ጋር እልህ

በመጋባት አገር የማቅናት ዓላማው ተጨናግፎ አገር አቆርቁዟል። በሁለቱም ወገኖች ክፍተት አለ ብለን ማለፍ ያግባባል።
ወደ በዕውቀቱ ሥዩም ግጥም እንምጣ፡-‹‹ኀሠሣ ሰላም››
ማጭድ ይሆነን ዘንድ፣ ምንሽር ቀለጠ፤
ዳሩ ብረት እንጂ፣ ልብ አልተለወጠ፤
ለሣር ያልነው ስለት፣ እልፍ አንገት ቆረጠ፤
ይለናል፤ (ከ‹‹ስብስብ ግጥሞች›› መድበል)
በዚህ ግጥም፣ የአብዮቱን ግብታዊነት ነው የሚተቸው በዕውቀቱ፤ ውጥኑ ከግብ እንዲደርስ በቅድሚያ መሠራት የነበረበት የቤት ሥራ ተዘሏል ነው የሚለን፤ ጦርነት ይቁም፣ ወደ ሥራ እንግባ ለማለት ቅድመ-

ሁኔታዎችን መደልደል ተገቢ ነበር ባይ ነው፤ ይኼንን የሚያሳካው የሰው ልጅ ጭንቅላት ላይ በቅድሚያ ሥሩበት ነው መልዕክቱ፤ ለነገሩ ሠላም፣ መተማመን፣ መቻቻል፣ ፋብሪካ… ሳይኖር ሕዝቡ ምን ይሥራ?

በስተመጨረሻ ለልማት በታለመ መሣሪያ ተገዳደለ፤ በጊዜው የነበረ ነዋሪ ስለ ርዕዮተ-ዓለሙ በቂ ግንዛቤ ነበረው ማለት ይከብዳል፤ በርዕዮት ላይ ርዕዮት የተደራረበበት ሕዝብ ነው፤ አንዱን ሳይለምድ አንዱ

ይተካል፤ የአንዱ ቁስል ሳይሽር ሌላ ቁስል ያርፍበታል፤ ወታደራዊ መንግሥት ግንዛቤ የማስጨበጥ ክፍተት ነበረበት፤ ዓላማው መልካም ቢሆንም የሕዝቡን አስተሳሰብ መቀየር ነበረበት፤ ለመሆኑ መላው የኢትዮጵያ

ሕዝብ የወታደራዊ መንግሥትን ዓላማ ያውቅ ነበርን? ወታደራዊ መንግሥትስ ዓላማውንና ሊወሰዱ በሚገቡ ቅድመ-ሁኔታዎች ላይ በአጥጋቢው ሠርቷል? ይኼም አንድ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ሆኖ ይኖራል፤….
….ደበበ ሰይፉ ስለ የሚመጣው መስካሪ ሀሳብ ነው የሚያትተው፤ ወታደራዊ መንግሥት ዓላማው ምን እንደነበርም ያወሳናል፤ በዕውቀቱ ሥዩም ደግሞ ስላለፈው ነው የሚነግረን፤ በዋናነት ስለ ቅድመ-ሁኔታው

አስፈላጊነት።  

Read 524 times Last modified on Saturday, 10 February 2024 21:08