Saturday, 10 February 2024 10:22

የጃዝ ንጉሱ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ከአድናቂዎቹ ጋር እራት የሚበላበት ምሽት መዘጋጀቱ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በሃገራችን በጃዝ ሙዚቃ ዘርፍ ከ50 ዓመታት በላይ የሚታወቀው  አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ (የክቡር ዶ/ር)፣ ከአድናቂዎቹ ጋር የሚገናኝበትና እራት የሚበላበት ልዩ ምሽት መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡
የታዋቂ ኤቨንት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል አበራና የጃዝ ንጉስ ሙላቱ አስታጥቄ፣ የእራት ምሽቱን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ላይ እንደተብራራው፤ አርቲስት

ሙላቱ አስታጥቄ፣ የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት፣ በግዮን ሆቴል በሚገኘው አፍሪካ ጃዝ መንደር፣ ከአድናቂዎቹ ጋር ተገናኝቶ ራት እንደሚበላና ፊርማውን እንደሚያኖር ታውቋል፡፡ የፎቶግራፍ መነሳት መርሃ

ግብር እንደሚኖርም ተነግሯል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ተጋባዥ እንግዶችና ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም የአርቲስቱ  አድናቂዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የተለያዩ ኹነቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ታዋቂ ኤቨንት፣ ከዚህ ቀደም አርቲስት ሰላም ተስፋዬን በሸራተን አዲስ ሆቴል ከአድናቂዎቿ ጋር በማገናኘት፣ ራት የመብላትና የፎቶግራፍ መነሳት መርሃ ግብር በስኬት

ማካሄዱ ተመልክቷል፡፡  
በውጭው ዓለም ይህን መሰሉ ዝነኞችን ከአድናቂዎቻቸው ጋር የማገናኘትና አይረሴ ቅጽበቶችንና አጋጣሚዎችን የመፍጠር መርሃ ግብሮች በእጅጉ የተለመዱና የሚዘወተሩ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
የጃዝ ንጉሱ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ በአገሩ ብቻ ሳይሆን፣ በውጭው ዓለም  የሙዚቃ መድረኮችም ከፍተኛ አድናቆትንና ዕውቅናን ያተረፈ አንጋፋ  የሙዚቃ ባለሙያ  ነው፡፡


Read 468 times