Saturday, 10 February 2024 10:30

የንባብ ለሕይወት ”ተማሪ ፌስት” ዛሬና ነገ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሕፃናት ጸሐፍት ዛሬ መጻሕፍቶቻቸውን በጋራ ያስመርቃሉ



በከተማችን በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው ንባብ ለሕይወት ለተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው የሚያዘጋጀው ”ተማሪ ፌስት” የተሰኘ ትምህርታዊና አዝናኝ ፌስቲቫል ዛሬና ነገ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
“ተማሪ ፌስት” የተለያዩ ገፅታ ያላቸው ፕሮግራሞች ተቀናጅተው በአንድ መድረክ የሚቀርቡበት የቤተሰብ መርሃ ግብር ሲሆን፤ ከፕሮግራሞቹም መካከል የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ከወዲሁ በቂ የሥነ-ልቦና ዝግጅት

እንዲኖራቸው የሚያግዝ ገለፃ በመስኩ ባለሙያዎች እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው፡፡  
ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎችም “ልዩ ተሰጥኦ ያሸልማል” በሚል መሪ ቃል ነፃ የትምህርት ዕድልና የተለያዩ ሽልማቶች የሚያስገኙ የተሰጥኦ ማሳያ ልዩ መድረክ እንደሚጠብቃቸው ለማወቅ

ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በዚህ ዛሬ በሚከፈተው የተማሪዎች ፌስቲቫል ላይ ሰባት ሕፃናት ያዘጋጇቸውን ሰባት መጻሕፍት በጋራ እንደሚያስመርቁ ተጠቁሟል፡፡
ሰባቱ ሕፃናት ጸሐፍት የ“ማርካን እና ሪማስ” ደራሲ የ7 ዓመቷ የማርያም ብሩክ፣ የ“ሁለቱ ጓደኛሞች እና ቤተሰብ” ታሪክ ደራሲ የ10 ዓመቷ አሜን ልዑልሰገድ፣ የ“ቅቤ እና ቋንጣ” ደራሲ የ10 ዓመቷ

ሔመን ብሩክ፣ የ“ሁለቱ” መጽሐፍ ደራሲ የ11 ዓመቱ ቢኒያም መለሰ፣ የ“እርሳስ እና እስኪርብቶ” ደራሲ የ12 ዓመቱ ዮናታን ልዑልሰገድ፣ የ“ሳራ እና ቢታንያ” ደራሲ የ 11 ዓመቷ ፈርደውስ ሡልጣን እና የ

“ላሊበላ” ደራሲ የ14 ዓመቱ ዮሴፍ መለሰ ናቸው፡፡
ዛሬ ቅዳሜና ነገ እሁድ  ከጠዋቱ 4፡00 እስከ ምሽት 1፡00 በሚቆየው ፌስቲቫል ላይ ስመጥር ምሁራንና ተወዳጅ አንባቢያን እውቀትና ልምዳቸውን ለታዳሚያን የሚያጋሩ ሲሆን፤ ከዚሁ ጎን ለጎን በርካታ

የቤተሰብ ጨዋታዎች፤ የልደት ፕሮግራሞችና ቤተሰብን ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳትፉ ልዩ ልዩ አዝናኝ ዝግጅቶች መሰናዳታቸው ተነግሯል፡፡
ንባብ ለሕይወት ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው በዚህ የተማሪዎች ፌስቲቫል ላይ ቤተሰቦች በተመጣጣኝ የመግቢያ ዋጋ ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ አክብሮታዊ ግብዣውን

አቅርቧል።

Read 1043 times