Saturday, 10 February 2024 10:42

ሦስት መዓዘን

Written by  በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(0 votes)

ምዕራፍ 01/2

ከራስ በድን አካል ጋር ፊት ለፊት መተያየት ውስጥ ያለው የድንጋጤ መንፈስ፣ ይህ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲለማመደው የማያውቀው የኬሚካል ዑደት በሰውነቱ ውስጥ ይተራመስበት ጀመር፡፡ ሞትና ስሜት

በአንድ ጊዜ በዚህ ሰው ጭንቅላት ውስጥ በፍጥነት መመላለስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ የትኛው ትክክል እንደሆነ ሊረዳው አልቻለም፡፡
ፊት ለፊቱ እያየው ያለው የገዛ ራሱ አስክሬን አፉ በጅማት የተሰፋ ነው፡፡ ሰውነቱ ሰም በሚመስል ነገር ተጣብቆ ሙሉ ሰውነቱ ያብለጨልጫል፡፡ የራሱ መልክ እንደሆነ ያወቀው ከውስጡ ባለ ልቡሰ ጥላው

ተመርቶ እንጂ መልኩ ምን አይነት እንደሆነ አሁንም አያውቀውም፡፡ የገዛ ራሱን እየተመለከተ ጊዜውን ማባከን አልፈለገም፤ ተነስቶ በጠረጴዛው ላይ ያለውን የወረቀት ክምር ሲያተራምስ አንድ ቀይ ብጫቂ ወረቀት

ላይ አይኖቹ አረፉበት፡፡ ወረቀቱን አንስቶ ተመለከተው፤ በላዩ ላይ ያለው ፅሁፍ እንዲህ ይላል….
“ሦስት ጊዜ ሞተህ ሦስት ጊዜ ትነሳለህ፤ ትዝታህን ከተስፋህ ጋር እየሰፋህ ወደ ፒራሚዱ ጫፍ ለመድረስ የሀሳብ ተረክህን መንገድህ ታደርገዋለህ፤ አታፈቅርም፣ አትወልድም፣ አትታመምም፣ ስሜትህ የራስህ ብቻ

ነው፡፡ በህይወትህ እጣ ፈንታ ውስጥ ሦስት አይነት ልታሳካቸው የሚገቡህ ግቦች ይከሰቱልሀል፡፡ እነሱን ለይተህ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ፡፡ ከሦስቱ ግቦችህ ግን አንዱን ማሳካት ካቃተህ አንተም አልነበርክም፣

ምድርም ከነግሳንግሷ አልተፈጠረችም፡፡
“ይህን ፅሁፍ የፃፍኩት እኔ (አንተ) ነኝ (ነህ)፡፡ ጊዜ እንደ ዥረት ነው፡፡ መንጓለሉ ከፊቱ በሚያጋጥመው እክል ልክ ይቃኛል፡፡ አንድ ወጥ የሆነ የጊዜ ቀመር የለም፡፡ አንተ ነህ የራስህ ጊዜ፡፡ አንተ ነህ ጊዜን

የምትሰራው የምታወድመው፡፡ ስለዚህ ይህን ፅሁፍ መቼ ነው የፃፍኩት ብለህ አትቸገር፡፡ ሁሉም ነገር ቅደም ተከተሉን ጠብቆ እውነቱን በብርሀን ሰበብ ያጋልጠዋል፡፡
“አንተ እውነትም ውሸትም ነህ፣ ነበርክም አትኖርምም፣ ታይተሀል ስውርም ነህ፡፡ ሚስጥራቶች እንደ ጥላህ ይከተሉሀል፡፡ የብዙ ነገራት መፍትሄ ሊያደርግህ ስውሩ የሁለንታ ገመድ ካንተ እጣ ፈንታ ጋር ይጓተታል፡፡

ይሄ ግን ህይወትህ አይደለም፣ ህይወት የለህም፣ ያለህ ሞት ነው…ጉዞህ ከህይወት ወደ ሞት ሳይሆን ከሞት ወደ ህይወት ነው፡፡ በዚህ ሚስጥራዊ የህይወትህ ድርሳን ውስጥ ደራሲው አንተ ልትሆንም ላትሆንም

ትችላለህ፡፡ ፍቃድህ ከዕውናዊው አለም ይልቅ በህልምህ ውስጥ ይሰለጥናል፡፡
“ስምህ ዮሴፍ ነው፡፡
“ሦስት ጊዜ ሞተህ ሦስት ጊዜ ትነሳለህ፡፡
“ትዝታህን ከተስፋህ ጋር እየሰፋህ ወደ ፒራሚዱ ጫፍ ለመድረስ የሀሳብ ተረክህን መንገድህ ታደርገዋለህ፤ አታፈቅርም፣ አትወልድም፣ አትታመምም፣ ስሜትህ የራስህ ብቻ ነው፡፡
“ከዚህ ወረቀት ጀርባ ያለው ቀመር ወደ ግብህ የሚሰድህና አንድ እርምጃ የሚያራምድህ፣ ሚስጥራዊ ስፍራን የሚጠቁምህ አድራሻ ነው፡፡ አንብበህ ድረስበት….ደርሰህም ቀጣዩ ደብዳቤህን (ዬን) አግኘው፡፡”
ፅሁፉ ሲያልቅ ዮሴፍ ጭንቅላት ውስጥ ብዙ ነገሮች መፈጠር ጀመሩ፡፡ ወረቀቱን አዙሮ በጀርባው በኩል ተመለከተው፡፡ በላዩ ላይ የአንድን ስፍራ የሚጠቁም በቁጥር ቀመራት የተበጀ በኬክሮስና ኬንትሮስ ተቀምሞ

የተቀመጠ የአንድ ስፍራ መለያ ኮድ ተመለከተ፡፡ ወደ ሆነ ቦታ ሊሄድ እንደሆነ ገባው፡፡ ማን እና ለምን አሁን ያለበት ንቃቱ ውስጥ እንደዘፈቀው የሚያውቀው ከዚህ በኋላ በሚወስናቸው ውሳኔዎቹ እንደሆነ ተረዳ፡፡

ወረቀቱን አጣጥፎ ወደ ኪሱ ከተተው፡፡ ያንንም የሚያስፈራ የገዛ አስክሬኑን የያዘውን ሳጥን በፍጥነት ተንደርድሮ ዘጋው፡፡ በመቀጠልም ተመልሶ ሲመለከተው ወደነበረው የፎቶ ሰልፍ ጋር ሄዶ ቆመ፡፡ የራሱን መልክ  

በሚያየው በፎቶና በራሱ በድን አካል ማረጋገጥ ችሎ ሳለ…አብራው ያለችውን ሴትና ህፃን ልጅ ግን ሊያስታውሳቸውም ሆነ ሊያውቃቸው አልተቻለውም፡፡
በግድግዳው ላይ ያሉትን ፎቶዎች በሙሉ በአንድ ላይ ሰብስቦ አስቀመጣቸው፡፡ በጠረጴዛው ላይም ተበታትነው የነበሩት ወረቀቶች መልክ መልክ ይዘው ተሰናዱ፡፡ ቢያንስ አንድ ነገር አውቋል…ስሙ ዮሴፍ እንደሆነ፡፡

ሌሎቹ መገለጫዎች ግን በምን አላማና ስለምን ትርጉም ተብለው እንደተፃፉ ምንም ሊረዳ አይችልም፡፡
ዮሴፍ የገዛ ሬሳው ለምን አፉ እንደተሰፋ ሊረዳ አልቻለም፡፡ ያንን ክፍል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመሰናበቱ በፊት የዚህን ጉድ ሚስጥር ሊያረጋግጥ ወሰነ፡፡ በቀስታ ወደ ሳጥኑ ተጠግቶ ከፈተው፡፡ አፍንጫውን ይዞ

እየዘገነነው በአስክሬኑ ከንፈር ላይ የተሰፋውን ክር መበጠስ ጀመረ፡፡ በጥሶ ሲጨርስም በቀስታ የሬሳው ጥርስ ላይ ተንጠልጥላ ያለች ቀጭን ክር ተመለከተ፡፡ ክሯን ስቦ ለማውጣት ሲሞክር የገዛ ጥርሱ በውስጡ

የያዘውን ነገር አላስወጣ አለው፡፡ በሀይል ጨክኖ ቢታገለውም ሊሳካለት አልቻለም፡፡ ያለው አማራጭ አንድ ነው…ጥርሱን ማርገፍ፡፡
ብዙ አስቦበት ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ሳጥኑን በከፈተበት ድንጋይ የሬሳውን ጥርስ ማውደም እንዳለበት እየመረረውም ቢሆን ተረዳ፡፡ ድንጋዩን አንስቶ፣ አይኖቹን ጨፈኖ የሬሳውን ጥርስ በታትኖ ጨረሰው፡፡ አሁን ያቺ

ቀጭን ክር ነፃነት አገኘች፡፡ በተቻለው መጠን ያደረገውን እኩይ ስራ ላለመመልከት ፊቱን አዙሮ ክሯን ብቻ ሳባት፡፡ በክሩ ላይ በላስቲክና በአልሙኒየም የተጠቀለለ ነገር አለበት፡፡ በክፍሉ ውስጥ የተፈጠረውን ሽታ

መቋቋም ስላቃተው የሰበሰባቸውን ንብረቶች ይዞ ክፍሉን ለቆ ወጣ፡፡
እንደወጣም ያንን የተጠቀለለ ነገር እንደምንም ብሎ ፈታቶ ከጨረሰ በኋላ፣ በውስጡ ያለውን ለማየት በአይኖቹ እግሮች እየፈረጠጠ ሄዶ ከአልሙኒየሙ መደብ ጋር ደረሰ፡፡ በአልሙኒየሙ ጥቅል ውስጥ አንድ የዕፅ

ፍሬ ተመለከተ፡፡ ምን እንደሆነ ሊያውቅ አይችልም፡፡ መልሶ ጠቅልሎት ወደ ኪሱ ከተተው፡፡ አይኖቹን አንስቶ መንገዱን ተመለከተ፡፡ ከርቀት በአንድ አስፓልት ላይ የሚራወጡ መኪኖችን ተመለከተ፡፡ በጣም እርቦታል፡፡

እሱን ወደሚመስሉት የሰው ልጆች ሊቀላቀል እንደሆነ አምኖ አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡ የእንባው ባለቤት ግን ደስታው ይሁን ሀዘኑ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በቀዩ ወረቀት ላይ የተከተበውን የካርታ መጠቆሚያ  የቁጥር

ቀመር ለማስታወስ ከሞከረ በኋላ፣ ወደየትም ቢሄድ የሚታዘዘው እግሩን በተስፋ ጅራፍ እየገረፈው የመጀመሪያውን ሚስጥር እንዲያስፈታው አንድ አራመደው…ዮሴፍ፡፡   
         2
ኤልዛቤል በታፋዋ ላይ ያለው ሰው ሳይነቃ በፊት በፍጥነት ከታሰረችበት ነፃ መውጣት እንዳለባት ተረድታለች፡፡ ያላት አማራጭ ከታሰረችበት ካቴና የገዛ ጣቶቿን ቀጭታ ማውጣት ብቻ ነው፡፡ እንደምንም ብላ

ትንፋሿን ሰብስባ ሁለቱን ጣቶቿን ቀጨቻቸው፡፡ ህመሙ እሷን አልፎ ከታፋዋ ላይ ራሱን ስቶ ያለውን ሰው የሚያሳምመው ያህል ነው የተሰማት፡፡ ሆኖም አልጮኸችም፡፡ ሆኖም እንባዋ በስሱ እየተቃኘ በጉንጯ ላይ

ይፈስ ጀመር፡፡ አንዱ እጇ ነፃ ወጣ፡፡ ደግማ የተቀጩትን ጣቶች ወደ ቦታቸው መመለስ አለባትና አሁንም ያንን ስቃይ ተሰቃይተው የተቀጩትን ወደ ቦታቸው መለሰቻቸው፡፡ ኤልዛቤት አሁን ሊያድናት የሚችለው

አጋርዋ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጊዜ እንደ ንፋስ ሳያመልጣትና የወደቀው ሰው ሳይነሳ በፊት በፍጥነት ማድረግ ያለባትን መከወን ውስጥ ገባች፡፡ የተኛውን ሰው ኪስ መበርበር ጀመረች፡፡ የኪስ ቦርሳውን ብቻ ነው ልታገኘው

የቻለችው፡፡ እንደሚጠቅማት ተረድታ ያዘችው፡፡ እንደምንም ቀስ ብላ ከተዘጋባት በር በስተጀርባ ያለውን ድምፅ ለማድመጥ ከበሩ ላይ ጆሮዋን አኖረች፡፡ ምንም አይነት ድምፅ ልትሰማ አልቻለችም፡፡ በቀስታ የበሩን

እጀታ ስትስበው በሩ ወለል ብሎ ተከፈተላት፡፡ እንደምንም ህመሟን እየታገለች ወጣች፡፡ እንደወጣች ከረዥም ኮሪደር ጋር ተገናኘች፡፡ ኮሪደሩን እያለፈች በምትሄድበት ወቅት ላይ ልክ እሷ ታስራበት እንደነበረችበት

አይነት ለእስር የተበጁ የሚመስሉ ክፍሎችን ለመመልከት ቻለች፡፡ ብቻዋን እንዳልሆነች ተረዳች፡፡ ሆኖም አሁን መርዳት የምትችለው ራሷን ብቻ እንደሆነ ታውቀዋለች፡፡
እንደምንም ብላ ኮሪደሩን እንደጨረሰች ከአንድ በር ጋር ተገናኘች፡፡ ነፃነቷን የምታገኝበት በር እንዲሆን ተመኝታ አለት በሚሰነጥቀው ተስፋዋ እየተነዳች፣ ወደ በሩ ቀርባ ልትከፍተው ስትል ድንገት የሰው ድምፅ

ሰምታ የምታደርገውን አቆመች፡፡ ቀስ ብላም ተጠግታ የሚወራውን ነገር ለማድመጥ ሙከራ አደረገች፡፡
“ትዕዛዙ ከበላይ ነው የመጣው ነው እኮ የምልህ….እየሰማኸኝ ነው?”
“ይገባኛል የምትለኝ ነገር …ሆኖም እሷን መግደል ያለውን ጥቅም ብቻ ነው እንድታስረዳኝ የምፈልገው?”
“አንተ ሰውዬ ፍፁምኑ ደነዘዝክ እንዴ…ጭራሽ ብለህ ብለህ የአለቆችህን ሀሳብ መቃወም ውስጥ ገባህ…ወይስ ከልጅቷ ፍቅር ያዘህ?”
“በዚህ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለነው ማናችንም ብንሆን ማፍቀር እንደማንችል ታውቃለህ፡፡ ፍቅር ምንድን ነው?…ፍቅር የምንሞትለት አላማችን ነው፡፡ እኔ ደግሞ ለዚህች ልጅ ልሙትላት እያልኩ ያነሳሁት ሀሳብ ትዝ

አይለኝም፡፡ እኔ አላማዬ ታግሰን ውጤት ማምጣት መቻላችን ላይ ነው የሚያነጣጥረው፡፡” “አጥብቀህ ስማኝ ወንድ መለኮት፡፡ ምድር ላይ ያሉትን ቃላት ሰብስበህ እኔን ልታሳምነኝ ብትሞክር ልረዳህ የሚቻለኝ ነገር

የለኝም፡፡ ትዕዛዝ አለማክበር የሚያመጣውን አሰቃቂ ጣጣ ደግሞ ከኔ በላይ አንተ ታውቃለህ፡፡ ስለዚህ ለአንዲት የሴት ነፍስ ብለህ እስካሁን በትግል ያቆየሀትን ነፍስህን አትገብር፡፡ አሁኑኑ ሄደህ አስወግዳት? ይህን

ካላደረግህ….”
ድንገት ሁሉም ነገር ፀጥ አለ፡፡ ኤልዛቤል አይኖቿ ፈጠው የሞት መልዓክት የሚመለከቱ ይመስላሉ፡፡ በህይወቷና በሞቷ መካከል ያለው ነገር ቢኖር አሁን አፍጣ የምታየው በር ነው፡፡ መለኮት የሚባለው ሰው ይህን

በር ሲከፍተው ህይወት የምድር ርዝማኔዋን ለማስቀጠል መወራጨት ውስጥ ትገባለች፡፡ ስለዚህ ራሷን ልታድንና በህይወት ቆይታ በቀሏን እንድትወጣ መሞት የለባትም፡፡ ከጀርባዋም ጥላቸው የመጣችው የወህኒ ቤቶች

ውስጥ የገዛ ወገኖቿ እንባ አዝለው እንደተቀመጡ ታውቃለች፡፡ ለራሷም ለነሱም ስትል በህይወት መቆየት አለባት፡፡ ከብዙ ደቂቃዎች በኋላ ያ በር በቀስታ መከፈት ጀመረ፡፡ ኤልዛቤልም በፍርሀት ውስጥ ሆና ከበሩ

ትንሽ አፈግፍጋ የሚሆነውን ለመወጣት መጠባበቅ  ውስጥ ገባች፡፡ በሩ ተከፍቶ መለኮት ወደ ውስጥ ሲዘልቅ ከኤልዛቤል ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡ መለኮት በፍጥነት ሽጉጡን አውጥቶ ደቀነባት፡፡ ኤልዛቤል ተስፋ

በመቁረጥ እጆቿን ወደ መሬት አውርዳ በደምና እንባ ቀለም የተሳለው መልኳን መለኮት አይኖች ላይ እንደ ካንቫስ አድርጋ ዘረጋቻቸው፡፡ መለኮት ጥቂት ሲመለከታት ከቆየ በኋላ የጥይቱን ቃታ ሳበው፡፡ የሽጉጡ

ድምፅ በሀይል ጮኸ፡፡ ኤልዛቤል ይህ ሲሆን አይኖቿን ጨፍና ሞቷን እየተጠባበቀች ነበር፡፡ በቀስታ አይኖቿን ስትገልጥ ባለችበት እንደቆመች ተረዳች፡፡ በድንጋጤ መለኮትን ተመለከተችው፡፡ መለኮት ባለበት አይኖቹ

እንደፈጠጡ ሽጉጡን ወድሮባት እየተመለከታት ነው፡፡ እሷ ላይ አልነበረም የተኮሰው፡፡ ማን ላይ እንደተኮሰው ልታረጋግጥ ወደ ጀርባዋ ስትመለከት፣ በእስር ክፍል ውስጥ ምርመራ ሲያደርግባት የነበረው ሰው እንደሆነ

ተመለከተች፡፡ አሁንም የምታየውን ማመን አቅቷት ዞራ መለኮትን ተመለከተችው፡፡ መለኮት ለሽርፍራፊ ሰከንዶች ከገዛ ራሱ ጋር ሲጨቃጨቅ ከቆየ በኋላ፣ በፍጥነት እየተራመደ ወደ ኤልዛቤል በመቅረብ እጁዋን ይዞ

በመጣበት በር በኩል ይዟት ወጣ፡፡ከዚያን ደቂቃ አንስቶ ኤልዛቤል ከራሷ ጋር አልነበረችም፡፡ ከምታየው ነገር ይልቅ ከጀርባዋ በሽጉጥ እሩምታ የሚከተላት ድምፅ ነው ጎልቶ የሚሰማት፡፡
“መለኮት አትሳሳት…መለኮት እንዳትሳሳት….መለኮት…????” 3
ዘካሪያስ ራሱን እጅግ ካማረ የምግብ መመገቢያ ጠረጴዛ ላይ አገኘው፡፡ ከፊት ለፊቱ አንድ ሙሉ ፂሙ ሽበት ብቻ የሆነና ጉንጩ አካባቢ ተለቅ ያለ ጠባሳን የተነቀሰ ሰው ተቀምጦ እያየው ነው፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች

እንግዳ በሆነ መልኩ ይህ ሰው ዘካሪያስ ላይ ሲያፈጥበት ከቆየ በኋላ በሚያስገመግም ድምፅ መናገር ጀመረ….
“ዘካሪያስ…አሁን የምታየው መልክ ከዚህ በኋላ በተደጋጋሚ የምታስበውና የምታየው መልክ ነውና በጥሞና ተመልከተኝ፡፡ በፍፁም ልትረሳኝ የማይገባህ ሰው ነኝ፡፡ ስትተነፍስ ታስታውሰኛለህ፣ ስትተኛ የህልምህን

ምዕራፎች እየከፋፈልኩ አዕምሮህን የግሌ አደርገዋለሁ፡፡ ለዘመናት የምትሻውን ሞትህን የምሰጥህም የምነፍግህም እኔ ነኝ፡፡ ከፈጣሪህ በፊት የምድር እጣ ፈንታህን የሚዘውርልህ የነፍስህ መካኒክ ከኔ ውጭ ማንም

አይኖርህም፡፡ በገዛ እጣ ፈንታህ ላይ ፈጣሪህ ነኝ፡፡ ነፍስህም ለኔ ትገዛለች፡፡”
ዘካርያስ ሰውየውን ፈገግ ብሎ ተመለከተው፡፡ የሰውየው በራስ መተማመን እጅግ አስደማሚ ሆኖ ነው ያገኘው፡፡ የሰውየው አይኖች እውነተኛ ናቸው፤ ተወልደው እሱ ዘንድ እስኪመጡ ድረስ ዋሽተው የሚያውቁ

አይመስሉም፡፡ ሆኖም ይህን ሁሉ ጉድ እንዲያወራ ያደረገውን እርግጠኝነቱን ማወቅ ስለፈለገ እኔነቱ ድረስ ገብቶ ሊመረምረው ወዷልና፣ ከፍርሀት ይልቅ ተረጋግቶ መታየቱን ነው የመረጠው፡፡ ዘካሪያስ መፍራት

ቢችልበት በወደደ ነበር፤ ሆኖም አሁን ምንም አይነት ድንጋጤ ከነፍሱ ጥጋት ስር ተሰዶ ቢመረምር ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በጭንቅላቱ…ለእሱ…እሱ ከሞተ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ ምን ምክንያት ይኑረው ለመፍራት…?
ሰውየው ንግግሩ ቀጠለ….
“የኔ የምትለው ጊዜ የለህም…ጊዜህን የምሰጥህ እኔ ነኝ፡፡ ይህም እኔ አንተ፣ አንተም እኔ እንደሆንን እንድታምን እፈልጋለሁ፡፡ ሆኖም እምነትና ተስፋ እጅግ አደገኛ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህን ከልብህ ውስጥ ይዘህ

ተንቀሳቀስ፡፡ የምትተነፍሰው እኔ ስለፈቀድኩ ብቻ መሆኑን አስበህም ሆነ ኖረህ ትደርስበታለህ፡፡”
ዘካሪያስ በጣም ተገርሞ ነው ሰውየውን የሚያየው፡፡ የሰውየው ቃላት እየተከመሩ በሄዱ ቁጥር የዘካሪያስን ቀልብ እየጠመዘዙ ወደ አንድ ስፍራ…እሱ ራሱ ወዳልተረዳው የስሜት ደለል ይዘውት እየሄዱ ነው፡፡ በቃላት

ብልሀት ተደቁሶ የተበጀው የሰውየው የማሰብ ቅርፅ፣ ከዚህ ቀደም በአዕምሮው ተለማምዶት አያውቅም፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ የሚሰማውን ስሜት አዲስነቱን ለማረጋገጥ ከሰውየው አይኖች ውስጥ ታሪክ መዞ

ለማውጣት መታገል ውስጥ ገባ፡፡ የሰውየው አይኖች ግን ከአለት የጠነከሩ ናቸው፡፡ እሱ ካልፈቀደ በቀር የትኛውም ስነፍጥረት ከህሊናው ከርሞ የውስጡን ሊረዳው እንደማይችል ከአዲሱ እሳቤው ጋር አብሮ አመነበት፡፡

ሆኖም አሁን ላይ ሰውየው እያስፈራራው ይሁን ተስፋ እየሰጠው ሊረዳ አልቻለም፡፡ ሰውየው ከተቀመጠበት ተነስቶ በዝምታ የሚያየውን ዘካሪያስን በትኩረት ሲመለከተው ከቆየ በኋላ፣ ወደ ጀርባው ዞሮ በግድግዳው

ላይ እንደ ብላክ ሆል ተበይዶ ያለውን የቴሌቪዥን መስኮት ከጨለመበት ወደ ብርሀኑ መለሰው፡፡ በእስክሪኑ ላይ የኤልዛቤል መልክ ተከሰተ፡፡ ታስራለች፡፡ ደምታለች፡፡ እያለቀሰች ነው፡፡ ድንገት ንግግር ማድረግ

ጀመረች….የተደቀነባትን ካሜራ አይን አይኑን እያየች፡፡ “አባቴ…ማን እንደሆንክ አላውቅም፡፡ አይቼህ አላውቅም፡፡ ሆኖም አሁን ሊገሉኝ ነው፡፡ ማን እንደሆኑ ሳላውቃቸው፣ ምክንያታቸውን ሳልረዳ፣ ለምን እዚህ

እንደመጣሁ ሳላውቅ ሊገሉኝ ነው፡፡ አባቴ…የምር በህይወት ካለህ ስማኝ?…የሚሉትን አድርገህ ያለሁበት መጥተህ እርዳኝ?  አባቴ ግዴታህ ነው…ያለሁበት መጥተህ እርዳኝ…ግዴታህ ነው…” እስክሪኑ ተመልሶ

ጨለመ፡፡ “ልጄ…ልጄ…ልጄ… የኔ ኤልዛቤል” ዘካሪያስ በተቀመጠበት ሆኖ ጮኸ፡፡
ሰውየውም ጥቂት የዘካሪያስን መልክ ሲመለከት ከቆየ በኋላ….
“በነገው እለት ስራህን ትጀምራለህ…ከመፅሐፈ ሄኖክ ሚስጥራዊ እውቀት ጀምረህ እስከ መፅሐፈ ራዝኤል ድረስ ነፍስህ ከንፋ የምሻውን ትሰጠኛለች፡፡ ፍላጎቴን እውቀትህ ሲሞላው ልጅህን በእጅህ ታስገባለህ…”
ይህን ተናግሮ ሰውየው ከዘካሪያስ አይኖች ተሰወረ፡፡ ዘካሪያስም ድንገት በገጠመው አስፈሪ ገጠመኝ ውስጥ ልቡን ሰብሮ፣ ከእንባው ቀድሞ ልትጨልም ባለችው ነፍሱ ውስጥ ተወርውሮ በመስመጥ ራሱን ከራሱ

ለመሰወር ጥረት ውስጥ ገባ….. ፡፡

Read 409 times