”--ታዲያ አደገኝነቱ ባያጠራጥርም የመጣው ይምጣ ብለው፤ በድፍረት የሚጠይቁ አልፎ አልፎ ብቅ ይላሉ፡፡ አይነካም የተባለውን የሚነኩ፤ በሩቅ የተሰቀለውን ለማውረድ የሚተጉ፤ ልባም አርቲስቶች፡፡ በአነጋጋሪ
የጥበብ ስራዋ በቀዳሚነት የምንጠቅሳት ኢትዮጵያዊት አርቲስት ደግሞ እንስት ምህረት ከበደ ናት፡፡ ምህረት የተወለደችው በደሴ ከተማ ሲሆን፤ ከስእል በተጨማሪም ገጣሚና የነፃ አርትስ ቪሌጅ መስራች ናት፡፡--“
ቴዎድሮስ ገብሬ በይነ-ዲስፕሊናዊ የሥነ ጽሑፍ ንባብ በተሰኘ መፅሐፉ፤ በሚትዮሎጂ ውስጥ ሴትነት እንደ ጽንሰ ሃሳብ ከሁለት ቋሚ ገፅታዎች ጋር ተዛምዶ ይነሳል ይለናል፡፡ አንደኛው ምክንያተ-ሞት (femme
fatale) ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እናትነት ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁለት የሴትነት መገለጫዎች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ናቸው፡፡ ሴት በእናትነት ስትወከል በአካሏ ድንግል፣ በመንፈሷ ንፅህት ትሆናለች፡፡ ሴትነት
መለመላውን በተለይም ከተቃራኒ ፆታ ጋር ካላት ግንኙነት ጋር ስትያያዝ ደግሞ ሴት አጥፊና አሳሳች ትሆናለች፡፡
ሴትነት አሳሳችነት አሊያም እናትነት ሆኖ የተሳለው በሚቶሎጂ ብቻ ሳይሆን፣ ለብዙ ዘመናት በወንዶች ርእይና ሃሳብ በተሞላው የስነ-ጥበብ አለምም ጭምር ነው፡፡ ኤልሳቤጥ ወ/ጊዮሮጊስ (ፒ. ኤች. ዲ.)
Modernist Art in Ethiopia በተሰኘ ጥናታዊ መፅሐፏ፤ ብዙውን ጊዜ የሴቶች የስነ-ጥበብ ስራዎች እንዲሁ በድንግዝግዙ ደማቅና አነስታይ (warm and feminine) ተብለው እንደሚታለፉ
ትነግረናለች፡፡ ይህ ቅጥያ ታዲያ በተለምዶ ብዙም ጥልቀት ለሌላቸው አበርክቶዎች የምንጠቀመው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በነባሩና በተለመደው የማህበረሰብ ስርአት ውስጥ ሴት የግሏን ስነ-ጥበባዊ አስተዋፅኦ
አበረከተች እንዲባል፤ አንድም ስነ-ጥበቡን እናውቀዋለን የሚሉ ወንድ የስነ-ጥበብ ሰዎች ሊመሰክሩላት ይገባል፤ አሊያም የሴቷ የጥበብ ስራ የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴት የሚያጎለብት ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል፡፡
ዘመናዊ ስነ-ጥበብም ቢሆን ሴትን ከጥበቡ ባለቤትነት ይልቅ የሴትን አካል እንደ አንድ የጥበብ ቁስ (object) ሲቆጥርና ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1975 Laura mulvey የተባለች የፊልም
ሃያሲ፤ ወንድ ሰአሊዎች ሴቶችንና አካላቸውን ለወንድ ተመልካቾች እንዲመች አድርገው የሚስሉበትን መንገድ ለመግለፅ the male gaze የተሰኘ ቃል ቀምራለች፡፡ ይህም ሴት እንጅ ቁራጭ ስአል አይደለሁም፡፡
አካሌም ቢሆን የወንዶች አይን የሚያርፍበት፤ የነሱን ፍላጎት የሚሞላ ቁስ አይደለም የሚል አንድምታ ያለው እንቅስቃሴ እንዲጀመር አስችሏል፡፡
ይህ አይነቱ የተለመደና የአንድን ወገን (የወንድን) የሃይል የታሪክ የባህል እንዲሁም የማንነት አተያይና አረዳድ ብቻ የሚያንፀባርቅ የሴቶች ውክልና፣ በወንድ አርቲስቶች ብቻ ሳይሆን በሴቶች አርቲስቶችም ስራ
ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ ይህም የአንድ ወገን (hegemonic) አተያይ በብዛት በሚንፀባረቅበት የማህበረሰብ ስርአት ውስጥ የብዙሃን ምናብና ማህበራዊ ሀቲትም የአርቲስቷን/ቱን ግላዊ ነፃነት አንቆ አላፈናፍን
ይላል፡፡
ከዚህ ሲያልፍም ሴቶች የጥንት ሚቶሎጂ ላይ እንደተሰጣቸው ውክልና አጥፊና አሳሳች፣ ወደ ሰውነት ማእረግ ከፍ ያላሉ ፍጡራን፣ በአካላቸው ሁሌም ወንድን የሚያጠምዱ፤ ወይም የሚማርኩ ብቻ ሆነው
እንዲቀረፁ ያደርጋል፡፡
****
ታዲያ በዘመናችን (contemporary times) ሃገራችን ያበቀለቻቸው ሴት ጥበበኞች፣ በተለያየ መንገድ ይህን በአባዊ ስርአትና አስተሳሰብ የተቃኘ ሀቲት የሚፈታተን፣ ሲያልፍም ኣማራጭ ቅኝት
የሚያቀርብ ስራ ሲያበረክቱ አይተናል። እንደ አዲስ ግላዊ የፈጠራ ምናብን ሲቀነበብቡም እንዲሁ፡፡ አይተንም ስለ ጥበባዊ ፈጠራና ነፃነት ስንል ሀሴት አድርገናል፡፡ ከነዚህ የዘመናችን መልኮች መሃል ለዛሬ የሦስት
እንስት ሰአሊዎችን ስራና የታሪክ ነገራ ከሴታዊ ማንነት አንፃር ለማየት እንሞክራለን፡፡
የቆምነው የድህረ ዘመናዊ ስነ-ጥብብና አስተሳሰብ በአመዛኙ በሚስተዋልበት ጊዜ ላይ ሲሆን፤ ሲያልፍም የተለያዩ ፆታዊና የማንነት ጥያቄዎች በብዛት በሚነሱበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ምናልባትም ይሄ ከብዙኃኑ
አስተሳሰብ ይልቅ ለግለሰብ ምናብና ሃሳብ ነፃነት ይሰጣል፡፡ ጥቃቅን የሚባሉ ሃሳቦችና ጥያቄዎች፤ የማይረቡ የሚባሉ የጥበብ ስራዎች እንዳይኖሩ ጭምርም ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አርቲስቶቹ
ለውስጣዊ ስሜታቸው ታማኝ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡
የስእል ስራ የመጀመሪያ እርምጃ፣ ራስን ለማወቅ የሚደረግ ጉዞ ነው ትላለች፤ ሶሎሜ ሙላታ፡፡ ሶሎሜ (ይህንን ምልልስ ባደረግንበት ወቅት) የ29 አመት ወጣት ሰአሊ ስትሆን፤ በአቢሲኒያ የፋይን አርት ት/ቤት
እንዲሁም በእንጦጦ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የስእል ትምህርትን ተከታትላለች፡፡ ሶሎሜ የስእል ስራዎቿ ማእከል የሚያደርጉት ሴትነት ላይ ነው፡፡ የሴትነትን አንጓ ይዛ እንደ ሃሳብ ሴት መሆን ምንድን ነው? መሬት ላይ
ያለው የሴት የህይወት ልምድስ ምን ይመስላል? ሴትነት ሃሳብ ሲሆንና በተጨባጭ መኖር ሲሆን፤ እርስ በራሱ የሚያገናኘው ድር ምንድን ነው? ምንስ ያለያየዋል የሚሉ ጥያቄዎችን ታነሳለች፡፡
በአብዛኛው የፖርትሬት ምስሎችን የምትመርጠው ሶሎሜ፤ ዝም ያሉ ፤ አንድ ቦታ ላይ የቆሙ፤ ፊታቸው ሙሉ በሙሉ የሌለ ወይም የተበላሸ የሴቶች ምስልን ትስላለች፡፡ ብዙ ስራዎቿም የተጠቀሱትን መልኮች
ያንፀባርቃሉ፡፡ ውስጠ ሃሳባቸውን፤ ከተፈጥሮና ከአካባቢያቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት፤ እንዲሁም ያንን ግንኙነት ለማሳየት የምከተለው ቴክኒክ ጠቅሞኛል ትላለች፡፡ የሶሎሜ ፊት አልባ ሴቶች፣ ወደ ውስጣቸው
አጥብቀው የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የሴቶቹን ምስል ያየችም ተመልካች ወደ ውስጧ እንድትመለከት የሚገፋ አንዳች ሃይል አላቸው፡፡ ዝም ያሉ፤ ለስላሳና ሰላማዊ ቢመስሉም፣ እምቢተኛና አማፂ መሆናቸው ግን
አያጠራጥርም፡፡ ምናልባት ፊት የሌላቸው፤ ወይ ፊታቸው የተበላሸ ሴቶችን መሳሏ፤ ቀደም ብለን ያነሳነውን የአንድ ወገን፤ ወንዶችን
ብቻ ባለቤት የሚያደርግ ሲልም የሴቶችን አካል መትሮ ለእይታ የሚያቀርበውን ትርክትና ውክልና ለመቃወም የተጠቀመችበት መንገድ ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ይህንን ሆን ብላና አስባበት ላታደርገው
የምትችልበት እድል ሰፊ ቢሆንም፣ ብዙ የጥበብ ስራዎች ንቁ ባልሆነው የአይምሮአችን ክፍል እንደመከናወናቸው መጠን፤ ስእሎቹ ለትንታኔና ለትርጉም ክፍት መሆናቸው ከላይ የተጠቀሱትን ሃሳቦች በነፃነት ለመናገር
ያስችላል።
****
ሴት ሰአሊዎች ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች መካከል፣ ማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው፤ ለውይይት ክፍት ያልሆኑ፤ ለመጠየቅ ያልተፈቀዱ፤ አይነኬ ተብለው በሩቅ የተሰቀሉ አርእስቶች መኖራቸው ዋነኛው ነው፡፡
በተለይ እንደ እኛ ሃገር ባሉ ወግ አጥባቂ ማህበረሰብ ውስጥ ፈተናው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አንድም ቀደምትና አንጋፋ የሚባሉት ባለሙያዎች እንኳ አይነኬ ተብለው የተቀመጡ ሃሳቦችን ደፍረው
ባለመንካታቸው፤ ሲቀጥልም ሙሉ በሙሉ ከአባዊ ስርአትና አስተሳሰብ ባልተላቀቀ ማህበረሰብ ውስጥ ሴቶች ልማድን እንደ አዲስ የሚያሳይ መነጽር ይዘን መጥተናል ይኸውልህ፤ የቆየው አርጅቷል ቢሉ፤ “አካኪ
ዘራፍ እንዴት ሆኖ” መባሉ እሙን ስለሆነ፡፡
ታዲያ አደገኝነቱ ባያጠራጥርም የመጣው ይምጣ ብለው፤ በድፍረት የሚጠይቁ አልፎ አልፎ ብቅ ይላሉ፡፡ አይነካም የተባለውን የሚነኩ፤ በሩቅ የተሰቀለውን ለማውረድ የሚተጉ፤ ልባም አርቲስቶች፡፡ በአነጋጋሪ የጥበብ
ስራዋ በቀዳሚነት የምንጠቅሳት ኢትዮጵያዊት አርቲስት ደግሞ እንስት ምህረት ከበደ ናት፡፡ ምህረት የተወለደችው በደሴ ከተማ ሲሆን፤ ከስእል በተጨማሪም ገጣሚና የነፃ አርትስ ቪሌጅ መስራች ናት፡፡
በተለያዩ ቁሳቁሶችና አዳዲስ ቴክኒኮች በርከት ያሉ የፈጠራ ስራዎችንና ሃሳቦችን መሞከር እወዳለሁ የምትለው ምህረት፤ The red diary በሚለው ስራዋ ብዙ ሰው ያስታውሳታል፡፡ በየ27 ቀናቱ ለሁለት
አመት ያህል የወር አበባዋን በማጠራቀም የተሰራው ይህ ስእል፤ “ለኔ ፍፁም ቅርበት ያለውና ቀጥተኛ መገኘቴ ነው ትላለች”፡፡ ምክንያቱም ሃሳቤ ወይም ስሜቴ ብቻ ሳይሆን፣ እኔም እዛው ውስጥ አለሁና ስትል
ገለፃዋን ትቀጥላለች፡፡ በብዙ የሃይማኖት አስተምህሮቶች መሰረት ብሉይ ኪዳንን ጨምሮ የወር አበባ እንደ ቆሻሻ ደም ይቆጠራል፡፡ አንዲት ሴትም የወር አበባዋን በምታይባቸው ወቅቶች፤ ከአምልኮ ስፍራዎችና
ከመንፈሳዊ ክንውኖች እንድትርቅ ይደረጋል፡፡ ክርስትና የሴቷን መቅደስ ውስጥ መግባት ሲከለክል፤ እስልምና ደግሞ መስጊድ ውስጥ መገኘትን፣ መስገድን እንዲሁም ፆምን ይከለክላል፡፡
በአይሁድ ሃይማኖት አስተምህሮት መሰረት ደግሞ በወር አበባ ጊዜ ሴቷ ፍፁም ከመንፈሳዊና ማህበራዊ ሃላፊነቶች ዘንድ እንድትገለል ይደረጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሴትና በወንድ መካከል ምንም አይነት አካላዊ
ግንኙነት እንዳይኖር ተፅፏል፡፡ ህጉ ባልና ሚስት የተለያየ አልጋ እንዲጠቀሙ ከማስገደዱም በተጨማሪ በወንድና በሴቷ መካከል እቃ እንኳ መቀባበል እንደማይቻል ይደነግጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ታዲያ ሴቷ የወር አበባዋን
ከጨረሰችም በኋላ ሙሉ በሙሉ ከቆሻሻ እስክትነፃ ድረስ ለሚቀጥሉት ሰባት ተከታታይ ቀናት ይቀጥላል፡፡ የፍጥረት መሰረት የሆነችን ሴት ፤የህይወት መነሻ የሆነን ተፈጥሮአዊ ኡደት እንዴት በዚህ ልክ የሚያርቅ
ህግና ባህል ኖረ የሚለውን ጥያቄ ለሌላ ጊዜ እናቆየውና ወደ ምህረት እንመለስ፡፡ The red diary እንዲጠነሰስ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ይኸው ማህበራዊ ተቃርኖ ነው፡፡ በእርግጥ በአዲስ ኪዳን የቆዩት
አስተምህሮቶች በተወሰነ መልኩ የተሻሩ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ የወር አበባ የምታይን ሴት ንፁህ እንዳልሆነች የሚቆጥሩ አማኞች መኖራቸው፤ የወር አበባዋን አጠራቅማ ይህንን ማስታወሻ እንድትሰራ እንደገፋፋት
ትናገራለች፡፡
ምህረት፤ የዚህ ሁሉ ምክንያት አባዊ ስርአት እንደሆነ ታምናለች፡፡ በዋነኛነት አባዊ ስርአቱን እንዲቀጥል የሚያደርገው ደግሞ ሃይማኖት እንደሆነ ትጠቅሳለች፤ “patriarchy manifests itself in
many ways and religion is the core of it and we need to tackle it with an intersectional critical view” ስለዚህ በየጊዜው
የምንፈጥራቸው ባለብዙ መልክ መነጽሮች አስፈላጊ ናቸው፡፡ አሻግረን እንድንመለከት ያግዙናልና፡፡
****
Afro-futuristic የሆኑ የስነ-ጥበብ ስራዎች ላይ ነው ረጅም ጊዜዋን የምታጠፋው፡፡ የጥቁርን ባህልና ማንነት ቀድሞውኑ ካጠፉት ሰዎች ስር ሆነው እየተማሩ እንዴት በዋነኛነት የጥቁሮች ባህል ላይ
የሚያተኩር የጥበብ ስራ መስራት ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ቢያጭርም፤ ባለ ብዙ ወግና ባህል ባለቤት ለሆነችው ጋብሬላ ግን ከተለያዩ ሰዎች ልምድ ለመማር ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረላት ይመስላል፡፡ አንድም
ብዙም የሆኑ ታሪኮችን ለመንገር፡፡
ከጃማይካዊት እናትና ኢትዮጵያዊ አባት የተወለደችው ጋብሬላ ፍረወይኒ ተስፋዬ ሰአሊ፣ የፊልም ባለሙያ፣ እንዲሁም አኒሜተር ስትሆን፤ ብዙ የስእል ስራዎቿ በራሷ ዙሪያ ያጠነጥናሉ፡፡ ውበትም ህመምም እኩል
ለፈጠራ ያነሳሱኛል የምትለው ጋብሬላ፤ “ልናገር የምፈልገው የተወሰነ አንድ ታሪክ የለም፡፡ ይልቁንም በየእለቱ የምደርስበት ጊዜው በተቀየረ ቁጥር አብሮ ቅርፅ የሚቀይር እንጂ” ትላለች፡፡
ገፀ-ባህሪዎቼም እኔ የማልፍበት ስሜትና አለም እኩል ይነካቸዋል የምትለው ጋብሬላ፤ ምናልባት ስራዎቼ ውስጥ ወጥ ቋሚና የማይቀየር ነገር ካለ ሁሌም ረቂቁንና ንፁሁን የኔን ማንነት ለማንፀባረቅ የማደርገው ጥረት
ነው፡፡ “it is a reflection of the purest part of myself. It is my soul. You can tell my work is my work even if you don’t
know me well.” ስትል ታብራራለች፡፡ የጋብሬላ ገፀ-ባህሪያት ሴት ናቸው፡፡ ባለ ቀለም፤ ውሃ የሚመስሉ፤ ጥቁር ሴቶች፡፡ ባለሦስት አይን ፤ባለታቶ እና ባለ ሎቲም ጭምር ልክ እንደ እሷ፡፡ ከሦስት የተለያዩ
ባህሎች መምጣቷም የተለየ ቀለምና እይታ ሰጥቷታል፡፡ ታዲያ አንችን የምትመስል ሴት ገፀ-ባህሪይ በመሳል፤ ከራስሽ የህይወት ልምድ ያለፈ ምን ሃሳብ፤ የቱንስ ታሪክ ለመናገር ትችያለሽ? ብዬ ላነሳሁላት ጥያቄ፣
እንዲህ ስትል ምላሽ ሰጥታኛለች፤ ” I paint mainly women, which is why my work has connected so deeply to many women. Through telling my
story I am also telling her story. There is a human commonality between us and when I express things I have been through
in my art, other woman who have been through the same see themselves in my work and feel an emotional connection. Through
this I have learned that vulnerability is one of my truest strengths and to not let it go, no matter what.” የመሳል ፍላጎቷን
ለማነሳሳት እንዲሁም እንደ ግብአትነት ውሃን በብዙ የምትመርጠው ጋብሬላ፤ ስፋትን ጥልቀትን ድህነትን(redumption) እንዲሁም መንፈሳዊነትን በአንድ ላይ የያዘ መሆኑን አጥብቃ ታምናለች፡፡ ከስእሎቿ
በተጨማሪ ከሁለት አመት በፊት የሰራችው “the water will carry us home” የተሰኘው አጭር አኒሜሽን ፊልም፣ ይህንን በውሃ ዘንድ ያላትን ጥልቅ እምነት የሚያንፀባርቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በፊልሙ ዙሪያ “The Ethiopian Reporter” ላይ ቅኝት ያደረገችው ህይወት አበበ፤ ውሃው ከቅድመ አያቶቿ ጋር ያላትን ትስስር የገለፀችበት መንገድ ነው ትላለች፡፡ ‘the film is her
connection to her ancestors and those that permanently become part of the water as their lives passed underneath’ ፊልሙ ላይ
ውሃ እንደ ዋና ገፀ-ባህሪ ሆኖ ታሪክ የሚናገር ሲሆን፤ አፍሪካዊያን በባርነት የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጠው በግዞት ሲወሰዱ አንድም በነበረው ከባድ የአየር ሁኔታ፣ ሲቀጥልም በበሽታና በረሃብ ጉዞውን ማጠናቀቅ
ሳይችሉ ሲቀር ውቅያኖሱ ላይ ይወረወሩ አንደነበረ ያሳያል፡፡ ታዲያ እነዚህ ውሃ ውስጥ የተወረወሩ አፍሪካዊያን ወደተለያዩ የባህር ውስጥ ፍጡራን ተቀይረዋል ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ ጉዞውን በሰላም
ካጠናቀቁት ውስጥም ውሃው ወደ ቤታችን ይመልሰናል በማለት ራሳቸውን ባህር ውስጥ የወረወሩ አፍሪካውያን ስለመኖራቸው የሚናገሩ የምእራብ አፍሪካ አፈ ታሪኮች አሉ፡፡ ይህን እና መሰል አፍሪካዊ ታሪኮችን ይዛ
ነው፣ እንግዲህ ጋብሬላ፣ ከውሃ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሳየት የምትሞክረው፡፡
****
በአጠቃላይ ጋብሬላ ውቅያኖስን የሚያክል ጥልቀት ይዛ፤ ማንነትን፤ ታሪክን እምነትን ስትተርክ፣ የሴትነትን ነጠላ ይዛ ደግሞ እንዴት ብዙ ነፍሶችን የሚያገናኝ ድር እንደሚሰራ ታሳየናለች፡፡ ድህነት እና ተስፋ፤ ጥያቄ
እና መልስ፤ ለጥበቡ እና ለራስ መታመን፤ ራስን የማወቅ እና ራስን የመቀበል ሂደቶችን፣ በእነዚህ ሦስት እንስት ሰአሊዎች ስራ ውስጥ ለማየት ይቻላል፡፡ በዚያውም ሴታዊ ማንነት እንዴት እንደሚወከል፣
እንደሚገለፅና እንደሚገነባ፡፡
Saturday, 10 February 2024 10:53
ሴታዊ ማንነት እና ሥነ-ጥበብ
Written by -እቴናት አወል-
Published in
ጥበብ