Monday, 19 February 2024 08:26

‹‹መዝገቡ ዱባለ›› የመዘገባቸው ሕጸጾች

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

አዳም ረታ ብዙነህ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› በተሰኘ ልብ ወለድ ድርሰት ዕውቀቱን፣ ትዝብቱን፣ ንባቡን፣ ነቀፌታውን፣ ብስጭቱን፣ ጣመኑን፣ ድባቴውንና ሌሎች ጉዳዮችን በዋናው ገጸ-ባሕሪይ በ‹‹በመዝገቡ ዱባለ›› አንደበት አድሮ ተናዟል፤ በዚህ ድርሰት አዳም መቅኔውን አሟጥጦ ግልጋሎት ላይ አውሏል ብዬ አምናለሁ፤ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› የአዳም ረታ ታላቁ ሥራ እንዲሆን ዕሙን ነው፤ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች››ን እንደ ድፍን ፍራንክ እንውሰደውና፣ ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ደግሞ የ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› ዝርዝሮች ናቸው እንበል!
የዋናው ገጸ-ባሕሪይ፣ የ‹‹መዝገቡ›› ጠረን በቀጣዮቹ ድርሰቶች እየተስረቀረቀ ሲናኝ እናስተውላለን፤ ድባቴው ድባቴአቸው ይሆናል፤ ጣመኑ ጣመናቸው ነው፤ ‹‹መዝገቡ›› ላለማጣጣም ያፈገፈገበትን ወለፈንዲ እና መሪር የሕይወት ጽዋ ሌሎች የአዳም ገጸ-ሰቦች ሲንገሸገሹ እናስተውላለን። በመታከት ጉም ወሳንሳ ተሰቅዘው ተይዘው ሲናውዙ ይኖራሉ፤ ዘለስ ሲል፣ ጥልቃ-ጥልቅ የሥነ-ልቡና ጣጣ ውስጥ ተዘፍቀው ሠርክ ሲነኾልሉና ከማሕበረ-ባሕላዊ ዕሴቶች/ anthropological aspects ጋር በውል ሲናቸፉ ይስተዋላሉ፤ አታካራ መግጠም ልማዳቸው ነው፤ እንደ መልካም መብል ነጻነታቸው ያምራቸዋል፤ መናጆያውን ተጠይፈው ንጡልነትን ያበጃጃሉ፤ የሥነ-ልቡናው መስክ የሚያወራ ግለሰብ ጤናማ እንደሆነ ቢደነግግም፣ አዳማዊ ገጸ-ሰቦች አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች ንግግር የተንገሸገሹ ናቸው፤ ኋላ ቆይቶ፣ ቆይቶ የራሳቸውን መንገድ ይጓዛሉ፤ ይሸሻሉም።   
አንጣር-በአንጣር እንየው ከተባለ፣ አዳም ረታ በ‹‹መረቅ›› ያመጣቸው ‹‹አላዛር›› እና ‹‹ተባረኪ›› የ‹‹መዝገቡ ዱባለ›› አምሳዮች ናቸው፤ ድካምና መታከት፤ ንጡልነትና መጓዝን በመጠኑም ቢሆን ከ‹‹መዝገቡ›› ወርሰዋል፤ ከዚህ በዘለለ፣ ‹‹አለንጋና ምሥር›› ላይ ትናንሽ ገጸ-ባሕሪዎች የ‹‹መዝገቡ››ን መሳይ ከሕይወት ድካም ለመላቀቅና ከማሕበረሰቡ ቅየዳ ለማምለጥ ሠርክ የሚፋጭሩ መሆናቸውን ታዝበናል፤ በእርግጥ በዚህ ጉዳይ እነ ቴዎድሮስ ገብሬ (ፒ.ኤች.ዲ) ከአዳም ረታ ድርሰቶች መካከል ‹‹ማሕሌት››ን እንደ መነሾ ይጠቅሳሉ፤ በመጠኑም ቢሆን ከዚያ እንደተንደረደረ መገመት ባይከብድም፣ ግና አብዛኞቹ ድርሰቶች የ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› ርዝራዦች እንደሆኑ መገርገር ከዚያ አልፎ ማረጋገጥ ሕጸጹ እምብዛም ነው። በሌሎች ድርሰቶቹ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› እንደ ጨው ወይም እንደ ቅመማ ቅመም በእየቦታው በመጠኑም ቢሆን እየተዶለ ትረካዎችን ለማጣፈጥ በቅቷል…
…ወደ አሁኔ ልስከንተር…
…‹‹መዝገቡ ዱባለ›› ይመዘግባል - ጥቃቅን ነጥቦችን፤ መዝግቦ ሲያበቃ ትርጉም ያበጃል፤ ወደላበት ሁኔታና ዐውድ ስቦ ከትቶ በሚስማማው መልክ ይከረክማል፤ ፌዝ የሚመስሉ ነገሮችና ሁነቶች ለ‹‹መዝገቡ›› የገዘፈ ትርጉም አላቸው፡፡ በሁኔታዎች ወይም በሙዶች/moods ላይ ተንተርሶ ወደ ታላቅ ጉዳይ ይደርሳል፤ ጉዞው ሥነ-ልቡናዊ ዳራ ያለው፣ በጥምዝ ሥነ-ልቡና የታሹ፣ በሂስ መልክ የተበጁ፣ ሜቶሎጂካል ይዘቶችን ያቀፉ፣ ተውላጠ ታሪክ ልውሶች፣ ተውላጠ ተረትና ምሳሌ ነኮች እና ሌሎች ጉዳዮችን ያካትታል፤ Every little scenarios and incidents potentially constitute to the Mezgebu’s makeup of reality…
…እንሆኝ ኑዛዜ…
…አንዳንዴ እሰክራለሁ፤ ከዚያ ‹‹መዝገቡ›› የተባለው ማሽንክ መዝጋቢ አዳም ረታ ነው እላለሁ፤ ንውዝ ሆኜ በስክርክር ሥሜት፤ ቅያሜ አልነበረም ታዲያ፤ እንደ ማጣቀስ ወይም እንደ መገርገር ዓይነት ጮሌነት ነው፤ ‹ከሲግመንድ ፍሮይድ ጋር ትንባሆ በአፋቸው ዶለው ጥስ ምገው እየተፉ ሲያወጉ› ዓይነት ጥርጣሬ ንውዝ ልቤን ይጎበኛታል…
…ታዲያ አዳም ረታ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› በተሰኘ ድርሰቱ የቀረጸው የምውት ልጅ፣ ንጡል፣ ጉቤው (ባለ ጉብታው)፣ ባዶውን የሕይወት ኪስ በውል የሚዘረግፈው፣ መንታላ ወ ነኹላላ… ‹‹መዝገቡ›› የሥነ-ልቡና ጣጣዎች ባለቤት ነው ስል ደመደምኩ!
ደግ አደረኩ!
የማሕበራዊ ፍንገጣ፣ የልቡና መታገል፣ የአስተዳደግ ንጥፈትና ግንትሮሽ/fixation ብሎም በባሕላዊ ዕሴቶች የታከተ እና የሌሎች ማሕበረሰብ ተኮር ጉዳዮች ሰለባ ነው ‹‹መዝገቡ››፤ የዚህ መንስኤ ምናልባትም በማሕበረ-ባሕላዊና ግብረ-ገባዊ እሴቶች በመንገሽገሽ የሚፈጠር ደመ-ነፍሳዊ መጻረር ሊሆን ይችላል፤ ከሚኖርበት ማሕበረሰብ (ንፋስ መውጫ) ወደ እሱ የተወረወሩ እሴቶች፣ የጎበኙት ማሕበራዊ መገለጫዎች፣ ባሕል እና ተያያዥ ነገሮች ሥሜትና ዕውነቱን ማዕከል አላደረጉም ይሆናል፤ ይኼ ባለመሆኑ ‹‹መዝገቡ›› በውል ሲጻረራቸው ይኖራል፤ ያለበት ማሕበረሰብ ለእሱ የሚሆን ምቹ ሁናቴ አላበጃጀም፤ ስለዚህ በእያንዳንዱ ክስተት ብቅ እያለ ሲተችና ሲነቅስ ይስተዋላል።  
በማሕበረሰቡ ላይ የሚያሳየው መታከት ወዲያው ደግሞ ወደ ውርክብ/ንውዘት/trauma ዓይነት ጣጣ ሊያድግና ሊመዘን ይችላል፤ በመሆኑም ‹‹መዝገቡ›› ይወራከባል፤ ዕውኑ ከቅዠቱ ተባርዞበት ይላተማል፤ ተወራክቦም አልቀረ ወላ ይሸሻል ይነጠላል - a travelling character, he travels to somewhere comforting him፤ ‹‹ሲሰለቸኝ ወንዝ ወርጄ መታጠብ ጀመርኩ፤ ቆንጆ ልጆች መታጠብ አለባቸው›› ይለናል በገጽ [99]። ብሎም፣ ራሱን ችሎ አዲስ አበባ ተከትቶ ሥራውንና ትዳሩን ሲያቀና እናያለን።
ሥነ-ልቡናዊ ቀውስ ሰቅዞ ይዞታል፤ ‹‹መዝገቡ››ን፤ እናም ማሕበረ-ባሕላዊ ጭቆናን ለማፈንገጥ ሲል እንደ ምስ ፍሮይዳዊ ሳይኮሴክሽዋል (psychosexual) ቅንዝርነትን ሲያከናውን ይገኛል፤ ‹‹የወንዝ ጉዞ›› በሚል ትረካ ስር ‹‹ጉብታዬ ከፈረሰች በኋላ ስፈልግ ዋናው ቤት፣ አለበለዚያ ወንዝ እወርዳለሁ፤ ወደ ወንዝ የምወርደው የዋና ፍቅር ይዞኝ ሳይሆን ብዙ ራቁታቸውን የሚታጠቡ ሴቶች ስለማይ ነበር፤ ገለል ያለ ኮካ መሬት መርጬ እቀመጥና አያለሁ፤ በሕሊናዬ ብርሃኑ ዘሪሁን እንደዚህ ዓይነት ሴቶች ካየ በኋላ ይሆን ጨረቃ ስትወጣን የጻፈው? እላለሁ፤ የብዙዎቹ ሴቶች ጡቶች ትልልቆች ናቸው፤ መጻሕፏ ውስጥ ጨረቃንም ባልሰጥሽ እስከዚህም ድረስ ኑሯችን መጥፎ አይሆንም ብሎ በቀለ የሚናገርላቸው እነዚህ ጡተ ትላልቆች ለመታጠብ አያፍሩም፤ ጣቶቻቸውን ሳሙና ተቀብተው ግራና ቀኝ እያወናጨፉ፣ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው፣ በፀሐይ እየተንቃቁ…. (ጋኔንም አይፈሩም?)... ልጃገረዶቹም ይታጠባሉ፤ ልጃገረዶቹ ሚስጢር ቦታ ፈልገው ይታጠቡ ነበር፤ መሬት ውስጥ መግባት እስኪቀራቸው፤ እኔ እናደዳለሁ፤ በጨረፍታ የልጃገረዶቹን ጠንቃቃነት አምልጦ የሚታይ የጡት ስር፣ የጡት ጫፍ፣ ሆድ፣ ሽንጥ፣ ጀርባ በሕሊናዬ እየገጣጠምኩ ራሴን አስገርም ነበር፤›› ገጽ [171] በማለት የማሕበረሰቡን መንገድ ንዶ በራሱ መንገድ ደስታውን እያጣጣመ እንደሆነ ነግሮናል፤ ይኼንን ካለን በኋላ ‹‹ሻፋዳ ነበርኩ?›› በማለት ከእራሱ ጋር ይነጋገራል።
የተነፈገው የወሲብ ፍላጎት አለ፤ ማሕበረሰቡ ውግዝ አድርጎበታል፤ ሰማይ ጠቀስ የወሲብ ፍላጎት ውስጥ እንደሆነ የሚያሳብቁ ሃቲቶች በእየቦታው ይገኛሉ፤ ስግመንድ ፍሮድ being unsatisfied at any particular stage can result in fixation እንዲል ገጸ-ሰቡ በማንኛውም ነገር ርካታን ባለማግኘቱ የተነሳ መጠነ ሰፊ ግንትሮሽ ገንትሮታል። ክልክሉን የሴት ልጆች ገላ ኮካ መሬት መርጦ አድብቶ ሲኮመኩም ይኖራል። ክልክል ነገሮችን ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም፤ ገና ከጅማሮ ገጽ [19] ላይ ‹‹ቲቸር ኃይለኛው›› የጣላትን የትንባሆ ኩርማን አንስቶ ይምጋል፤ ፍሮይድ እንደሚለን ከሆነ፣ ‹‹መዝገቡ›› በማሕበረሰቡ ዕሴቶች በመሸበቡ ምክንያት ደስታው እንደ ባቢሎን ፈራርሶና እንቅልፉ ነጥፎ እንደ ቃኤል ተቅበዝባዥ እንደሆነ እንገነዘባለን።               
‹‹መዝገቡ›› ሰልፍ ጠል ነው፤ ደራሲው በአንድ ወቅት በመንገዱ የገጠመው፣ ከአዕምሮው የተመሰገ የአብዮት ወይም የሰልፍ ጠልነት ወለል ብሎ ይታያል፤ ላይሞቅ ጎጆ በመናጆ የፈጀናቸው የመሰለፍ ጊዜያት ዛሬም ደርሰው ያብከነክኑታል፤ ደግሞ የተማሪዎች አብዮት ተማሪውን እንዲፈጅ ዕሙን ነው፤ አንድ ነገር ፋይዳ እስካላመጣ፣ አገር ብቻ ካተራመሰ ስለምን ይደረጋል፣ ይደጋገማል? ሰልፍና ተቃውሞ ዕጣ-ፈንታ እንዳልሆኑ ይታወቃል፤ ግና የዘመኑ መገለጫዎች ሆነው ቆይተዋል፤ አዳም ረታ ሰነፎች እንደሚሰለፉ አዟዙሮ ይነግረናል፤ ‹‹ትምህርት ቤት መሄድ የምጠላበት ምክንያት አንዱና ዋንኛው ሰልፍ ስለሚመስለኝ ነበር፤ ምናልባት ብቻዬን መማር ብችል ጎበዝ እሆን ነበር›› ገጽ [97] ላይ ይለናል፡፡ እዚህ ውስጥ የአጀብ ነገር እንደማይጥመው ማወቅ ይቻላል።
በተጨማሪ፣ ‹‹ተማሪው ከተረጋጋ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ከገበያው መሃል ተሰልፈው ሲወጡ ሰልፉ ፊት ለፊት በረዥም ጣውላ ላይ ያን ወራሪ ልጅ መፈክር ተሸክሞ አየሁት፤ በጉብታዋ በኩል ሲያልፍ ቀና ብሎ አየኝ። ይስቃል። ምን ያስቀዋል? ሰልፉ ያስቃል? የሚያስቅ ነገር አለው? ሰልፉን ለምሳሌ እንደ ወሰንየለሽ ቆንጆ ነው ማለት እንችላለን?›› ገጽ [97] እያለ ከሚያስበልጠው ነገር ጋር ሲያነጻጽር ተመልክተናል፤ ‹‹መዝገቡ›› በማይሆን፣ ባልቆነጀ ባልበጀ ነገር ጊዜያቸውን በብላሽ በሚያጠፉ ሰዎች ይበሽቃል፤ ማሕበራዊ ሂስ ነው ይኼ።      
ወረድ ይልና፣ ‹‹ወራሪው ለሰላምታ እጁን አነሳልኝ፤ ዝም አልኩት… እንድመጣ በዓይኑ ጠራኝ፤ አልሄድኩም፤ ተቀምጬ እንደማላይ ሆኜ አየዋለሁ…፤›› ገጽ [97] ሲል ግብረ መልስ ሰጥቷል፤ በዚህ ትረካ ደክሞ እንዳያደክሙት ይሸሻቸዋል፤ የአገሬ ሰው ብቻውን አይቃወምም፤ ባልተጠራበት ድግስ ይጠራሃል፤ መግተልተል ነው ከዚያ፤ ያለቦታህ ስትሆን እንደ ኹዳዴ በግ ማንም ዘወር ብሎ አይመለከትህም፤ ከዚህ ግብረ-መልስ ለማየት እንደተሞከረው ሌሎች ተጽእኖ አሳድረውበታል፤ አብሯቸው እንዲግተለተል አነሳስተውታል፤ እሱ ግን እንቢተኛነቱን አሳይቷል፤ ነቀፌታ ብቻ ሳይሆን አነጻጻሪ ዘይቤን በመገልገል ለነገሮች የተለየ ፍቺ ይሰጣል፤ ለገጸ-ባሕሪው ነገሮች ርባና ያገኙ እና እንዲወዳቸው ዘንድ ለሕይወቱ ትርጉም ካለው ነገር ጋር ያወዳድራል። በዚህ መሃል ፍላጎቱ ምን እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
ያለ ቦታቸው የሚውሉ ሰዎች ጉዳይ ብዙ ያትከነክነዋል፤ ‹‹የምሄድበት ባጣ ሙስጠፋ ቤት ሄድኩ፤ መስጠፋ ሽርኬ በነጻ በራድ ቀዳልኝ፤ መስጠፋ በዕድሜ ብዙ ይበልጠኛል… ግን ሽርኬ ነበር… አራዳ በዕድሜው ጉራ አይነፋም፤ አንዳንድ አዋቂ ነን ባዮች (ምን እንደሚያውቁ ባይገባኝም) ግን የሰው መዝናኛ፣ ማረፊያ እያበላሹ አሪፍ ነን በስለናል ለማለት ሲሞክሩና ሲሆንላቸው አይቼአለሁ፤›› ገጽ [106] ላይ ሲል ተሰምቷል፤ በአካባቢያቸው ትንሽ የሆነው ‹‹ሙስጠፋ›› ከትላልቆቹ እንዲሻል ዕሙን ነው፡፡   
‹‹መዝገቡ›› የሚጻረረው ከማሕበረሰቡ ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ተረትና ምሳሌ ጋርም ጭምር ነው፤ እሱን ማዕከል እስካላደረጉ ያበሽቁታልና በእራሱ ስልት ይከረክማቸዋል፤ ‹‹የምርጥ መኮንኖችና የባንዳዎች እጅና ጓንት መሆን›› ይሉት ብሒል ምኑም ስላይደለ ተክኖ ሲያበቃ፣ ‹‹እኔ ብጠየቅ፣ በድርጊት የሚስማሙ ሁለት ነገሮችን ጥቀስ ተብዬ ብጠየቅ ሳልፈራ ‹የምርጥ መኮንኖችና ባንዳዎች እንጀራና ሽሮ መሆን› እል ነበር፤ ምክንያቱም እንጀራና ሽሮ የትም ናቸው›› ገጽ [170] ይለናል፤ በሥነ-ልቡና ሂልዮት መሠረት ብዝኀ-ዕውነት እንዳለና ይኼም ዕውነት ባመቸን መልኩ የሚደነገግ እንደሆነ ዕሙን ነው። በተጨማሪ፣   
አፍ ያለው ይቆላል፣ ይለኛል አገሬ፤
እኔን የሰለቸኝ፣ ቆሎ ጥራጥሬ፤
ወግድልኝ ባላፍ፣ ጥሬም አይቆላ፤
ሥጋ ቅባቅቤ፣ ጤፍ እንጀራ እንብላ፤ ገጽ [106]፤ ‹‹መዝገቡ›› በዚህ ግጥሙ በፊት የምናውቀውን አባባል ወዳለበት ዐውድ ቀይሮ በማስገባት ስሜቱን አማክሎ በጥቅም ላይ አውሏል።  ‹‹በቅርብ ደሞ የለውጥ ሐዋሪያ የሚባል ሰው ለከተማው ሕዝብ ንግግር እንዲያደርግ ተጠርቶ ካልጠፋ ቦታ የት ይቆማል? ጉብታዬ ላይ። ላንድሮቨሩን ጉብታዬ ላይ አውጥቶ እሱ ላንድሮቨሩ ላይ ቆሞ ብዙ ለፈለፈ። ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› ብለው ደግሞ ባለአንድ ዓይን መኪናቸው ላይ ስዕል ስለዋል። አንድ ዓይን? ለምን ሦስት አልሆነም? ላንድሮቨራቸው ሰባራ ነበር መሰለኝ ከሔዱ በሁዋላ ጉብታዬ በሙሉ በፍሬን ዘይት፣ በግራሶ፣ በነዳጅና በአክታ ተበላሽታ መቀመጥ አልቻልኩም።›› ገጽ [104]። ‹‹አዋቂ የተባሉ ሰዎች ለምን ማበላሸት እንደሚወዱ አላውቅም፤›› ገጽ [105]። አርአያ መሆን የሚገባቸው ሰዎች ካለ ቦታቸው ሲገኙ ይበሽቃል፤ ከሚያከናውኑት ግብር በመነሳት የትልቅነት ዳሩ እስከምን ድረስ መሆን እንደነበረበት ይደነግጋል።
ሕጻናት የአዳም ረታ በትሮች ናቸው፤ መገፋትን፣ ማሕበረ-ባሕላዊ ጭቆናን እና ፍንገጣን የሚዋጋባቸው ሁነኛ መገልገያዎቹ ሆነዋል፤ ከመዝገቡ ዱባለ ፊት የተጋረጡ እልፍ ጉድባዎች አሉ፤ ደላጎ አይደለም፤ እፊቱ ከተሰናዳ ገመድ ገብቶ አይንጠለጠልም፤ አተካራ ይይዛል፣ ታንቲራ ይገጥማል እንጂ፤ ኤግዚስቴንሺያል ጥያቄዎችን ይወረውራል፤ አዳም ረታ ታዲያ ምርጥ ማባያዎችን በባሕል፣ በአፈ-ታሪክና በማይቶሎጂ አጥቆች እየሰገሰገ ሥነ-ልቡናዊ ኅልዮቶች ነፍስ እንዲዘሩ እስትንፋስ እንካችሁ ይለናል!
***
ከአዘጋጁ፡-
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛ እና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፤ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

Read 295 times