Saturday, 24 February 2024 20:24

የወንድ የዘር ፍሬ አለመውረድ(አለመኖር)

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ በከረጢት ውስጥ አለመኖርን አስመልክቶ የተዘጋጀ ጽሁፍ ከዚህ ቀደም ለንባብ የቀረበ ሲሆን ይህንንም እትም በድጋሚ ለንባብ እንሆ ብለናል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ100 ወንዶች ውስጥ 4 ወንዶች የዘር ፍሬ ያለመውረድ ችግር ያጋጥማቸዋል። ይህ ችግር በይበልጥ የሚስተዋለው የመወለጃ ጊዜ ሳይደርስ ቀድመው በተወለዱ ህፃናት ላይ ነው። ከ1 እስከ 2 በመቶ የሚሆኑ ወንድ ጨቅላ ህፃናት የዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው። 25በመቶ የሚሆኑ ጊዜያቸው ሳይደርስ የተወለዱ ልጆች የዘር ፍሬ አለመውረድ ችግር ያጋጥማቸዋል።
“የወንድ የዘር ፍሬ በተፈጥሮ ሆድ ውስጥ ነው ያለው” በማለት የተናገሩት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ዩሮሎጂስት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ራምዚ ዩሱፍ ናቸው። የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት የዘር ፍሬ በተፈጥሮ [በጊዜ ሂደት] ከሆድ ወደ እታች በመውረድ የዘር ፍሬ ከረጢት ውስጥ ይገባል።
የዘር ፍሬ አለመውረድ አጋጠመ የሚባለው የዘር ፍሬ ከሆድ ሳይወርድ ወይም ከሆድ ወደ የዘር ፍሬ የሚወርድበት ቱቦ (Inguinal canal) ውስጥ ሲቀር ነው። የዘር ፍሬ ካለመውረድ (በከረጢት ካለመኖር) በተጨማሪ አንዱ የዘር ፍሬ ከወረደ በኋላ የመመለስ ሁኔታ (retractile) ሊያጋጥም ይችላል።
የዘርፍሬ አለመውረድ መንስኤ [ምክንያት]
የመወለጃ ጊዜያቸው ሳይደርስ የተወለዱ ህፃናት (የመወለጃ ጊዜ ሳይደርስ መወለድ)
ህጻናት ሲወለዱ አነስተኛ የክብደት መጠን መኖር
የቴስቴስትሮን እጥረት መኖር
በእርግዝና ወቅት ስትሮጂን መውሰድ
በተለያየ ምክንያት የሚያጋጥም ጉዳት (Vascular injury)
ከጊዜ በኃላ በሚያጋጥም ሰው ሰራሽ ጉዳት
ከቀዶ ጥገና ጋር በተያያዘ ምክንያት የዘር ፍሬ ላይ ጉዳት ሲያጋጥም
ሙቀታማ አከባቢ
ጨረር
የቅርብ ቤተሰብ ላይ የዘር ፍሬ አለመውረድ ችግር ከነበረ(በዘር)
የወንድ የዘር ፍሬ ከረጢት ውስጥ አለመኖር(አለመውረድ) ጊዜያቸው ሳይደርስ የተወለዱ ህፃናት ከሆኑ ሆስፒታል ውስጥ በሚደረግላቸው ክትትል ይታወቃል። እንዲሁም በሌሎች ህፃናት ላይ ወላጆች የዘር ፍሬ በሚዳብሱበት ማወቅ አለመኖሩን ማወቅ ይቻላል። በወንዶች ላይ የዘርፍሬ አለመውረድ በልጅነት ከማጋጠሙ በተጨማሪ ከሁለቱ የዘር ፍሬ ከረጢቶች መካከል በአንዱ ወይም በሁለቱም በተፈጥሮ ሙሉ በሙሉ የዘር ፍሬ አለመኖር ወይም በሰው ሰራሽ ችግር በአንዱ ወይም በሁለቱ የዘር ፍሬ ከረጢት ላይ ችግር ሊያጋጥም ይችላል። በዓለምአቀፍ ደረጃ በልጅነታቸው ህክምና ካላገኙ ከ100 ወንድ ህፃናት መካከል 1 ወንድ ለአቅመአዳም ከደረሰም በኋላ ከችግሩ ጋር እንደሚኖር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተፈጥሮ ወይም በተለያዩ ሰውሰራሽ ምክንያቶች የዘርፍሬ በአንዱ ከረጢት ላይ መኖር ወይም በሁለቱም ላይ ሙሉ በሙሉ አለመኖር፣ በከረጢቱ ላይ ሳይሆን በሌላ የሰውነት ክፍል ላይ መሆን ማለትም አለመውረድ እና መሰል ሁኔታዎች ልጅ ላለመውለድ ችግር እና ለቴስቴስትሮን በሽታ (ካንሰር) ሊያጋልጥ ይችላል።
የወንድ የዘር ፍሬ በአንድ ከረጢት ውስጥ ብቻ ያላቸው ወንዶች ሁለቱም የዘር ፍሬ ከረጢት ላይ የዘር ፍሬ ካላቸው ወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ ልጅ የመውለድ አቅማቸው አነስ ያለ ነው። “አይወለድም ሳይሆን ከሌሎች ወንዶች ጋር ሲነፃፀር የመውለድ እድል ትንሽ ቀነስ ያለ ነው” በማለት ተናግረዋል ዩሮሎጂት ዶ/ር ራምዚ ዩሱፍ። ነገር ግን ያልወረደው የዘር ፍሬ በሆድ ወይም በሌላ የሰውነት ክፍል ውስጥ ካለ ህክምና በማድረግ ልጅ መውለድ የሚቻልበትን እድል ከፍ ማድረግ ይቻላል።
ዶ/ር ራምዚ ዩሱፍ እንደተናገሩት በይበልጥ የዘር ፍሬ ሆድ ውስጥ በሚቀርበት ወቅት ከጊዜ በኋላ ወደ ካንሰርነት የመለውጥ እድል ይኖረዋል። የወንድ የዘር ፍሬ ሙቀት በሆነ አከባቢ ላይ ወደ እታች የመውረድ እና ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ሲሆን ወደ እላይ ከፍ የማለት(የመሰብሰብ) ተፈጥሯዊ ባህሪ አለው። ስለሆነም ይህ የዘር ፍሬ ከሚያስፈልገው ሙቀት በላይ በሆነ ሁኔታ(ሆድ) ውስጥ ለረዥም ዓመታት ሲቆይ ካንሰር የመሆን እድሉ ከፍ ይላል።
የዘር ፍሬ ላይ ችግር ካጋጠማቸው ህፃናት መካከል በመቶበመቶ በሚባል ሁኔታ ህክምና በማግኘታቸው ከችግሩ መላቀቅ ችለዋል። ዶ/ር ራምዚ ዩሱፍ እንደተናገሩት ልጅ በተወለደ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ የዘር ፍሬ ወደ ዘር ከረጢት እንዲገባ ይጠበቃል። ነገር ግን ከ6 ወራት በኋላ ወደ ከረጢቱ ካልገባ ህክምና ያስፈልጋል። ችግሩ ያጋጠማቸው ወንዶች ህክምና እንዲያገኙ የሚመከረው በተወለዱ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ፣ እስከ 13 ወይም 14 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ እና ለአቅመ አዳም ከተደረሰ በኋላ ባለው የትኛውም የእድሜ ክልል ላይ ችግር መኖሩ በታወቀበት ወቅት ላይ ነው።
የዘር ፍሬ አለመውረድ ችግር ሲያጋጥም ቀለል እና ከበድ ያለ ቀዶ ጥገና በማድረግ የዘር ፍሬ በከረጢት ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ የካንሰር ደረጃ ላይ ከደረሰ የዘር ፍሬው ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ የማደረግ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል።
የወንድ የዘር ፍሬ በአንዱ ወይም በሁለቱም ከረጢት ውስጥ በተፈጥሮ አለመኖር የሚረጋገጠው በላፓራስኮፒ ወይም በኤምአርአይ ህክምና አማካኝነት ነው። በዚህም የካንሰር ችግር አለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል። ነገር ግን የዘር ፍሬው በከረጢት ውስጥ አለመኖሩን ብቻ በመመልከት የዘር ፍሬ በተፈጥሮ የለም ማለት አይቻልም። ምክንያቱም በሌላ የሰውነት ክፍል ውስጥ ሊደበቅ[ሊቀመጥ] ይችላል። “የተደበቀ የዘር ፍሬ ወደ ካንሰርነት የመቀየር ሁኔታ አለው” ብለዋል ዩሮሎጂስት ዶ/ር ራምዚ ዩሱፍ።
በተለያየ ምክንያት የሚያጋጥመውን የዘር ፍሬ ያለመውረድ ችግር ለመከላከል ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ለልጆች ትኩረት በመስጠት ችግር ሲያጋጥም ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከልጅነት እድሜ በኋላ ችግሩ እንዳያጋጥም ለማድረግ ደግሞ ከፍተኛ ሙቀት እና ጨረር ማስወገድ ይመከራል። በልጅነት እንዲሁም ከጊዜ በኃላ በተለያየ ምክንያት የዘር ፍሬ በከረጢት ውስጥ አለመኖር ሲያጋጥም በቀላሉ ህክምና ማግኘት ስለሚቻል ችግሩ መኖሩ እንደታወቀ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ወደ የህክምና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ ዩሮሎጂስት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ራምዚ ዩሱፍ ተናግረዋል። 

Read 940 times