Saturday, 24 February 2024 20:30

በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩት በአቶ ታምራት ላይኔ ባለቤት ፤ ወ/ሮ ሙሉ ግርማይ የተመሰረተው ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ 11ዓመት ሞላው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ/ም ፤ በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ያካሂዳል ።
...
ወ/ሮ ሙሉ ግርማይ ተወልደው ያደጉት በቀድሞው አጠራር በወሎ ክፍለ ሀገር በሰቆጣ ከተማ ነው።  በ 1973 ዓ/ም የቀድሞው ኢህዴን / ብአዴን የአሁኑ አዴፓ ፖለቲካ ድርጅት ተመስርቶ ደርግን ለመጣል የትጥቅ ትግሉን በዋግ አካባቢ ሲጀምር እርሳቸውም እንደ ዘመኑ ወጣቶች የደርግን መንግስት አምርረው ይጠሉ ስለነበር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው በ 1975 ዓ/ም የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከ ጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ሄዶ በ 1983 ዓ/ም የደርግ መንግስት ከስልጣን ሲባረር ቀደም ሲል ከአራት ድርጅቶች ጥምረት ኢህአዴግ ተብሎ በተመሰረተው ድርጅት የበላይነት የሽግግር መንግስት ሲቋቋም ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚንስትር እርሳቸው ደግሞ የአዲስ አበባ ሪጅን ፅ/ቤት የኢህአዴግ ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሆነው እየሰሩ ቆዩ።

እርሳቸው እንደሚሉት በ 1989 ዓ/ም " በስልጣን ያለአግባብ መጠቀም " በሚል የፖለቲካ ሴራ ኢህአዴግ አቶ ታምራትን ለእስር እንዲዳረጉ አደረገ። ይህኔ ታዲያ ወ/ሮ ሙሉ በህይዎቴ ይገጥመኛል ብለው ከማይገምቱት ፈተና ላይ ወደቁ። የአቶ ታምራት ሚስት በመሆናቸው  ከስራ ቦታቸው እና ከሃላፊነታቸው ያለአንዳች ርህራሄ ተባረሩ። በወቅቱ ምንም አይነት ገቢ ወይንም ጥሪት ሳይኖራቸው አራት ዓመት ከሆነው የመጀመሪያ ልጃቸው እና የአንድ ወር ጨቅላ ህፃን ከነበረቸው ሁለተኛ ልጃቸው ጋር ሲኖሩበት ከነበረው የመንግስት ቤትም ሳይቀር እንዲወጡ ተደረገ።

ከእለት ወደ እለት ማወከቦች ፣ የማፈን ሙከራዎች፣  ማስፈራሪያዎችና ልዩ ልዩ ፈተናዎች እየጨመሩባቸው ሲሄዱ በ 1992 ዓ/ም ሁለት ልጆቻቸውንና ታናሽ እህታቸውን ይዘው ወደ ኬንያ በግፍ ተሰደዱ።

ከሦስት ዓመታት የኬንያ አስቸጋሪ የስደት ቆይታ በኋላ በ 1995 ዓ/ም ወደ አሜሪካ በስደት እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው በኮሎራዶ ግዛት ዴንቨር ከተማ መኖር ጀመሩ ። በአሜሪካን ሀገርም ብቻቸውን ሆነው ልጆቻቸውን እንደሚያሳድግ እናት የጋዝ ማደያ ፣ የልብስ መሸጫ መደብርና የመሳሰሉት እየሰሩ ልጆቻቸውን ማሳደግና ማስተማር ቀጠሉ።

በ 2000 ዓ/ም ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ ከእስር ተፍትተው ወደ አሜሪካን ሀገር በመጡበት ወቅት ወ/ሮ ሙሉ ጋዝ ማደያ ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ለ አስራ ሁለት ዓመታት ልጆቻቸውን ያለአባት ማሳደጋቸውና ልጆቻቸውም እነዛን ረጅም ዓመታት ያለ አባት ማደጋቸው እርሳቸው ባለፉበት የመከራ ህይዎት ውስጥ የሚያልፉ ልጆችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችን በተለየ መንገድ እንዲያስቡ አደረጋቸው። በሚወዷቸውና የኔ በሚሏቸው ሰዎች መጠላትና መገለል አሳዛኝ የህይዎት ክስተት መሆኑን ተገነዘቡ ። እናም የተቸገረን ሰው ቀርቦ ማፅናናትና መደገፍ ምንያህል የተቀደሰ ተግባር መሆኑን ከህይዎታቸው ተማሩ።

ከዛም የእርሳቸው እና የቤተሰባቸው የመከራ ውጤት የሆነው እንዲሁም ለችግር የተጋለጡ ፤ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችና መበለቶችን የሚያግዘው ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት በ 2005 ዓ/ም ሊመሰረት ቻለ።

ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ ፤ በአዲስ አበባ ፣ በአማራ ክልል ዋግህምራ ሰቆጣ ከ400 በላይ መበለቶችንና ከ280 ወላጆቻቸውን ያጡ ለችግር የተጋለጡ ልጆችን በመርዳት ላይ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ/ም በከተማችን አዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅቷል ። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በሚችለው ሁሉ አጋር እንዲሆንና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶችና ህፃናትን እንዲያግዝ በማዕከሉ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥሪ ቀርቧል።

Read 457 times