Thursday, 29 February 2024 19:44

ዳዊት ድሪምስ ልምዱን በማካፈል ወጣቶችን አነቃቃ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

•  የክ/ከተማው አመራሮች መርሃ ግብሩን አወድሰውታል

"ልምዴን ለወጣቱ" በሚል መሪ ቃል ዛሬ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ሳኦል የኩነቶች አዘጋጅና ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ፣ ከልደታ ክፍለ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የወጣቶች መድረክ ላይ ታዋቂው የህይወትና ስኬት አሰልጣኝና አማካሪው ዳዊት ድሪምስ ልምዱን አካፈለ።

ዳዊት ድሪምስ ከህይወት ተሞክሮውና ከንባብና ጥናቱ ልምዱን ባካፈለበት የልደታ ክፍለ ከተማ አዳራሽ፣ ወጣቶች ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልተውት እንደነበር ተስተውሏል፡፡
   
በዛሬው መርሀ-ግብር ላይ ከዳዊት ድሪምስ ጋር ተገኝተው ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ሲጠበቁ ከነበሩት ታዋቂ ግለሰቦች መካከል መንሱር ጀማል፣ ግራንድ ማስተር ሄኖክ፣ ማስተር በፍቃዱ (ኢሱ)፣ አቶ ሰኢድ፣ ዮኒ ቬጋስ እና ደራሲ መሐመድ ብርሀን ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ በፕሮግራም መደራረብ ምክንያት መገኘት ያለመቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ለወጣቶቹ ልምድ ላከፈሉት ለዳዊት ድሪምስና ለሌሎች አካላትም ከአዘጋጆቹ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

የክፍለ ከተማው አመራሮችም ዝግጅቱን ላሰናዱት ሳኦል የኩነቶች አዘጋጅ እንዲሁም ልምዳቸውን ላካፈሉት ግለሰቦች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ እንዲህ ዓይነቱ ወጣቱን የማነቃቃት ፕሮግራም መዘጋጀቱ ወጣቱን በስነ ልቡና ለማንቃትና ለስራ ለማነሳሳት ስለሚያግዝ በየጊዜው መዘጋጀት አለበት ብለዋል፡፡

“ትልቅ ህልም አለኝ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ያበቃው ዳዊት ድሪምስ፤ “እኔ የህይወትና ስኬት ምስጢሮች ተመራማሪ፣ አማካሪና አሰልጣኝ ነኝ” ሲል ነው ራሱን የሚገልጸው፡፡

ስለ ህልሙ ሲናገርም፤ “የኔ ትልቁ ህልም ለዘመናት የተደበቁ የህይወትና ስኬት ምስጢሮችን በጥልቀት በማጥናት፣ በመጠቀምና በማስተማር ኢትዮጵያንና አፍሪካን መቀየር ነው” ይላል፡፡

በሚሰጣቸው ተከታታይ የስኬትና የሰብአዊ ግንባታ ሥልጠናዎች የበርካቶችን ህይወት እንደቀየረ የሚነገርለት ዳዊት ድሪምስ፤ በጥረታቸውና በትጋታቸው ለድል የበቁ ስኬታማ ሰዎችን እየጋበዘ ልምዳቸውን እንዲያጋሩና ሌሎችን እንዲያነቃቁ በማድረግም ይታወቃል፡፡

ዛሬ ደግሞ እርሱ በተራው በልደታ ክፍለ ከተማ ተገኝቶ ከልምዱ በማካፈል ወጣቶችን አነቃቅቷል፡፡

Read 874 times