Saturday, 02 March 2024 21:19

32 ዓመታትን በስነተዋልዶ ጤና ላይ.

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሐኪሞች ማኅበር 32ኛ ዓመታዊ ጉባኤ የካቲት 11 እና 12 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል። ጉባኤው ለሁለት ቀናት የተካሄደው “አመራርነት በሴቶች ጤና ላይ” [Leadership in woman health] በሚል መሪ ቃል ነው። በጉባኤው ላይ የተገኙት የዓለም አቀፉ የፅንስ እና ማህፀን ሐኪሞች ፌዴሬሽን (FIGO) ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አኔ ኪሃራ በኢትዮጵያ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ዋነኛ ጉዳዮች ውስጥ የእናቶች እና የህፃናት ጤና አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። ከእዚህም መካከል የጤና ኤክስቴንሽን ማጠናከር፣ ግንዛቤ ማሳደግ፣ ለእናቶች የመጓጓዣ (ትራንስፖርት) አገልግሎት ማመቻቸት እና የህክምና ተቋማትን ጥራት ማሻሻል ይጠቀሳል። “የኢትዮጵያ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር በሀገር ላይ ያለው አሻራ በጣም ብዙ ነው” ብለዋል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ። የኢትዮጵያ የፅንስ እና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልፈታህ አብዱልቃድር እንደተናገሩት ማኅበሩ ላለፉት 32 ዓመታት በስነተዋልዶ ጤና ላይ ብዙ ስራዎች ሰርቷል። የስነተዋልዶ ጤና መመሪያ (Sexual and reproductive health Guideline) እንዲዘጋጅ በማድረግ በዋናነት ይጠቀሳል። የእናቶች እና የህፃናት ጤና ለመጠበቅ ዘርፉን በብቃት መምራት የሚችል የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚስፈልግ የዓለም አቀፉ የፅንስ እና ማህፀን ሐኪሞች ፌዴሬሽን(FIGO) ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አኔ ኪሃራ ተናግረዋል። በተመሳሳይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ የተናገሩት የእናቶች እና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡት ሙያዊ አገልግሎት ብቻ በቂ አለመሆኑን ነው። ስለሆነም በአመራርነት መሳተፍ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በፅንስ እና ማህፀን ህክምና ውስጥ ለሚገኙ 6 የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስቶች እውቅና ተሰቷል። የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እውቅና ከተሰጣቸው የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ባለሙያዎች ውስጥ እንዷ ናቸው። ዶ/ር ሊያ ወደ ጤና ሙያ ለመግባት አባታቸው የኢንቶሞሎጂስ ስራ ላይ መሰማራታቸው የህክምና ሙያ ለመቀላቀል መሰረት ሆኗቸዋል። የሕክምና ትምህርታቸውን የተከታተሉት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻላይዝድ አድርገዋል። ዶ/ር ሊያ ታደሰ የሴቶች እና የህጻናትን ጤና ላይ የተለያዩ ስራዎችን ሰርተዋል። የህክምና ተቋማት ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ የትምህርት ተቋም በማቋቋም፣ በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለጤና ስርዓት ማጠናከር አስተዋፅኦ በማበርከት ፣የስነ ተዋልዶ ጤና እና ለጤና አጠባበቅ ጥራት መሻሻል እንዲሁም ጥናት እና ምርምር በማድረግ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የበኩላቸውን አበርክተዋል። የጤና ሚንስቴር ከሆኑ በኋላ እኤአ በ2020 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የነበራቸው ተምሳሌት የሚሆን የአመራር ብቃት ጎልቶ ታይቷል። በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የስነ ተዋልዶ ጤና ማሰልጠኛ ማዕከል (CIRHT) ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። በመላው አፍሪካ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል በሰሩት ስራ “የአፍሪካ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር” የሚል ቅጽል ስም ተሰቷቸዋል።
ሌላኛው በጉባኤው ላይ እውቅና የተሰጣቸው የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ታደሰ ቂጢላ ናቸው። ዶ/ር ታደሰ ቂጢላ በ1957 ዓ.ም በነቀምት የነርሲንግ ትምህርት ቤት ተማሩ። በዚህም ወቅት በማታ የትምህርት መርሐ ግብር የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ወስደው አለፋ። ዶ/ር ታደሰ ከ1962 እስከ 1971 ዓ.ም በነበረው ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በህክምና ትምህርት የላቀ ውጤት በማስመዝገባቸው ከጀርመን መንግስት የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተዋል። ከ1971 እስከ 1974 ድረስ ዶ/ር ታደሰ በወሎ ህጻናት ህክምና ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር እና ሀኪም በመሆን አገልግለዋል። ከዛም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1975 እስከ 1978 ዓም በጽንስና ማህፀን ህክምና ክፍል አገልግለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቆዩበት ጊዜ ከ1978 እስከ 1996 የቀጠለ ነበር። የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል። ዶ/ር ታደሰ በናይሮቢ፣ ስዊድን፣ ጄኔቫ እና ደቡብ አፍሪካ በመካንነት አያያዝ የአጭር ጊዜ ስልጠና ወስደዋል። ዶ/ር ታደሰ በጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከሙያቸው በጡረታ ተገለው ይገኛሉ። ዶ/ር ታደሰ ቂጢላ በ1971 ዓም ከሟች ባለቤታቸው ከዶ/ር መስታወት እጅጉ ጋር ትዳር መስርተው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።
በተመሳሳይ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፈቃደ ደነቀ በማህበሩ እውቅና የተሰጣቸው የህክምና ባለሙያ ናቸው። በ1980 ዓ.ም የህክምና የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በ1988 ዓም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጽንስና ማህጸን ሕክምና ስፔሻላይዝድ አድርገዋል። ዶ/ር ፈቃደ በናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ እና በአሜሪካ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በተለያዩ ትምህርቶች ላይ አጫጭር ኮርሶችን ወስደዋል። የዶ/ር ፈቃደ ሙያዊ ጉዞ የተጀመረው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ሲሆን በጠቅላላ ሀኪምነት አገልግለዋል። ግብረሰናይ ድርጅቶች ውስጥ በአመራርነት አገልግለዋል። ከዚህ ውስጥም የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የሀረርጌ ቅርንጫፍ፣ ቀይ መስቀል ድሬዳዋ ኢሳ እና ጉርጉራ አውራጃን ጨምሮ በሚገኙ ቦታዎች ማገልገላቸው ተጠቃሽ ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ዶ/ር ፈቀደ ደነቀ ከብርሃናዊት የሺ ጥላ ጋር ትዳር የመሰረቱ እና የ3 ልጆች አባት ናቸው።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር አሸብር ጌታቸው እውቅና ካገኙ ባለሙያዎች ውስጥ ሲሆኑ በማህበረሰብ ጤና አገልግሎት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ አገልግለዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጽንስና ማህጸን ሕክምና እንዲሁም በሥነ ተዋልዶ ኢንዶክሪኖሎጂ እና መካንነት የስፔሻሊቲ ዲግሪ አግኝተዋል። ዶ/ር አሸብር በስነ-ተዋልዶ ጤና ፕላኒንግ ፖሊሲ እና የፕሮግራም ትንተና ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ፣ በጾታዊ፣ ስነ ተዋልዶ ጤና እና መብቶች ከሉንድ ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማ እንዲሁም ህንድ ከሚገኘው ኖቫ [NOVA] የወሊድ ማእከል በአይቪኤፍ [IVF] ህክምና ስልጠና ወስደዋል። ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ዶ/ር አሸብር የማህፀንና የማህፀን ህክምና በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል አገልግለዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን ሰርተዋል። ዶ/ር አሸብር በኢትዮጵያ የጽንስና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ውስጥ ለአምስት ዓመታት በፀሐፊነት አገልግለዋል። ዶ/ር አሸብር በርካታ የእናቶች እና የስነ ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክቶችን በመምራት በኢትዮጵያ የእናቶች ሞት ዋነኛ መንስኤ የሆነውን የድህረ ወሊድ ደም መፍሰስን ለመቀነስ ሰርተዋል።
ሌላኛው እውቅና የተሰጣቸው የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ኮከብ መሀመድ ናቸው። ዶ/ር ኮከብ በጤናው ዘርፍ 35 ዓመታትን አስቆጥረዋል። በአሁኑ ወቅት በሐረር አጠቃላይ ሆስፒታል እና አዋሽ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ እያገለገሉ ይገኛሉ። ዶ/ር ኮከብ በምስራቅ ሀረርጌ ደደር ሆስፒታል፣ ህይወት ፋና ሆስፒታል፣ ጁገል ሆስፒታል እና ሌሎችን ጨምሮ በተለያዩ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግለዋል። ዶ/ር ኮከብ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ነው የተማሩት። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻላይዝድ አድርገዋል። በደደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፣ በህይወት ፋና ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍል ኃላፊ፣ በሐረር አጠቃላይ ሆስፒታል የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና የምስራቅ ሐረርጌ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ሀላፊ በመሆን በጤና ተቋማት አስተዳደር ላይ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ዶ/ር ኮከብ እንደ የኢትዮጵያ የጽንስ እና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር በመሳሰሉ የሙያ ድርጅቶች ውስጥ ተሳታፊ ናቸው።
ፕሮፌሰር ድልአየሁ በቀለ በስነ ተዋልዶ ጤና ላላቸው አመራርነት፣ በኢትዮጵያ ህክምና ጥናት እና ምርምር ላይ ላበረከቱት አስተዋፅዖ የኢትዮጵያ የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር እውቅና ሰቷቸዋል። ፕሮፌሰር ድላየሁ የስነ ተዋልዶ ጤና መስክን በማሳደግ እና የኢትዮጵያን የስነተዋልዶ ጤና ጆርናል (Ethiopian journal of reproductive health) በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን እንዲያገኝ ትልቅ ሚና አበርክተዋል። እንዲሁም በኢትዮጵያ የእናቶች እና ህፃናት ጤናን ለማሻሻል ስራዎችን ሰርተዋል። የፕሮፌሰር ድልአየሁ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ምርምር እና አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማሰራጨት የሚያስችል ጠንካራ መድረክ እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ የኢትዮጵያን የስነተዋልዶ ጤና ጆርናል በስፋት ተደራሽ እንዲሆን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ይህም ስራዎች እና የምርምር ውጤቶች በፍጥነት እንዲሰራጭ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በምሁራን እና በባለሙያዎች መካከል ትብብር እና የእውቀት ልውውጥ እንዲኖር አድርጓል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ “ህክምና የብዙ ባለሙያዎች ስብስብ ነው፤ ልክ እንደ እግር ሷስ ቡድን የተለያየ ሚና ያላቸው ግን ለአንድ ዓላማ የሚሄዱበት ነው” በማለት የህክምና ባለሙያዎች በተለያየ ዘርፍ በሚገኙ የአመራርነት ቦታዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አድርገዋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ የፅንስ እና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልፈታህ አብዱልቃድር የህክምና ባለሙያዎች በአመራርነት ላይ ተሳትፎ በማድረግ የእናቶች እና የህጻናት ጤና ላይ እንዲሰሩ መልእክት አስተላልፈዋል።

Read 569 times