Sunday, 03 March 2024 20:55

የሃብታሙ አለባቸው “ጉልጥምት ኢትዮጵያ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ማንይንገረው ሸንቁጥ

ሀብታሙ አለባቸው ቀደም ባሉ ጊዜያት አውሮራ፣ የሱፍ አበባ፣ የቄሳር እንባ፣ አንፋሮ፣ ህንፍሽፍሽ የተባሉ የአገራችን ታሪክና ፖለቲካ ላይ ያጠነጠኑ ልብ ወለድ መጻሕፍትን አበርክቶልናል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም “ታላቁ ተቃርኖ” በሚል ርዕስ አንድ ኢ-ልብወለዳዊ መጽሐፍ ለገበያ አቅርቧል፡፡ በዚህ ኢ-ልብወለዳዊ መጽሐፉ ውስጥ የሚከተሉት ሃሳቦች ይገኙበታል፡፡
““ብሔር ግንባታ”  ከሐገረ መንግሥት ምሥረታ  የሚቀጥል የተለየ ሌላ ሂደት ወይም ተግባር ነው፡፡……… ከሐገረ መንግሥት ምሥረታው ተግባር መጠናቀቅ በኋላ ወዲያውኑ ተከትሎ የሚመጣና ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል ተግባር ነው፡፡ የዚህኛው ተግባር ቀጥተኛ ዒላማ፣ የአገር ግዛትና ሉዓላዊነት ሳይሆን ህዝቡ ነው፡፡ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የአካባቢ ወይም የመልክዓ ምድር፣ የሐብትና ገቢ መጠን ወይም ሌላ ልዩነት ተመልሶ ለሐገረ መንግሥቱ ህልውና አደገኛ እንዳይሆን አድርጎ ማስተሳሰር ግቡ ነው፡፡” (ገፅ 43) ”የብሔር ግንባታ የትም ዓለም ላይ በበርካታ ምክንያቶች አስቸጋሪ ተግባር ነው፡፡ የሚፈልገው የጥንቃቄ ደረጃም ከፍተኛ ነው፡፡ በየትኛውም መንገድና ዘዴ የተመሠረተ ሐገረ-መንግሥት በብሔር ግንባታ ሂደት ወቅት በሚሠራ ሥህተት ተመልሶ ሊፈርስ ይችላል፡፡”(ገፅ 135) በማለት ይቀጥልና ወረድ ብሎ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ የጋራ ቅርስና ስለ ቅርሱ የተያዘ የጋራ “ጥሩ ወይም መጥፎ ትዝታ” የተፈጠረበት አገራዊ ወይም ብሔራዊ ሁኔታ ለብሔር ግንባታ ወሳኝ ስለመሆኑ ከምሁራን ጽሑፍ ያጣቅሳል፡፡ ይህ የጋራ ቅርስና ትዝታም በትውልዶች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል የቀደመ ጊዜ የጋራ ስኬት ወይም ውድቀት ታሪክ ሊሆን እንደሚችልና ይህንን መሰል ታሪካዊ የትስስር ስኬት ወይም ውድቀት ያለበትን ትዝታና ቅርስ ምሁራን ”ዘ ፎረም ሮማነም“ ብለው ማተታቸውን ይነግረናል፡፡  ቅርሶቹ በህዝቦች መካከል የነበረውን ፍቅር ብቻ ሳይሆን ግጭቶቻቸውንም የሚያስታውሱ በመሆናቸው፣ ስለቅርሶቹ ምንነት እየጠየቀና እየተረዳ ያደገ ህጻን፣ የቆየ ግጭትን ከቂም በቀል በራቀ መልኩ በማስተዋል፣ ግጭትን እየፈቱና እየተማማሩ አብሮ መኖርን እሴት አድርጎ እንዲወርሰው ምክንያት እንደሚሆንለት ያብራራል፡፡
ይህንኑ ሃሳብ ወደኛ ያመጣውና “ዘ ፎረም ኢትዮጵያነም” ብለን ልንሰይመው እንደምንችል ጠቅሶ አቻ ትርጉሙን፣ “አጥንትና ጉልጥምት ኢትዮጵያ” በማለት አሥፍሮታል፡፡ “ስያሜውና አተረጓጎሙ አንድ ህዝብና ግለሰብ አባላቱ እንዴት በተቃራኒ መንገዶች አልፈው ለዛሬው አብሮነታቸው እንደደረሱ የሚናገርና በልዩ ልዩ መንገዶች የሚገለጽ ታሪካዊ የቅርሶችና የትዝታዎች ሰነድ ነው” ይለናል በገፅ 136፡፡
ለእኛ አገር ሁኔታ ጽንሰ ሃሳቡን ስንጠቀም መጠንቀቅ እንደሚገባን እያስጠነቀቀ፣ ”ጉልጥምት ኢትዮጵያ“ በርካታ ልዩነት ፈጥረው ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ የፖሊሲና አስተዳደራዊ ስህተቶችን ተሻግሮ፣ ከፍ ባለ የማጣመርና ማቀናጀት ብቃቱ፣ የተለያዩ ፍላጎቶችንና ግፊቶችን የሚያስተሳስር ውጤታማ መረብ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ከዚህ አለፍ ብሎም፣ “አጥንትና ጉልጥምት ኢትዮጵያ” ትናንት ስለመሠራቱ ብንጠራጠር እንኳን፣ ቁርጠኝነቱ ካለ ዛሬና አሁን መፍጠር እንደሚቻልም ይነግረናል፡፡  ”የብሔረ- ኢትዮጵያ ግንባታ“ ማለትም ከዚህ የተለየ ትርጉም እንደሌለው በአፅንዖት አሥፍሯል፡፡ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ደራሲው በኢ-ልብወለድ መጽሐፉ በግልፅ ያስቀመጠውን የ”አጥንትና ጉልጥምት“ ፅንሰ ሃሳብ፣ ለዚህ ልብወለዱ ዋነኛ ጭብጥ አድርጎ ብቅ ብሏል፡፡ ”አጥንትና ጉልጥምት“ ከሚለው ፅንሰ ሃሳብ የተቀዳው፣“ጉልጥምት ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የተሰናዳው ልብወለድ፣ በገፀ ባህርያት ሥጋን ተላብሶ በመቅረቡ፣ ፅንሰ ሃሳቡን የዕለት ተለት ኑሮዋችን ውስጥ እንድንፈልገው፣ እንድናሰላስለው ይጎተጉተናል፡፡ ሴራውን በደህንነት መሥሪያ ቤት ክንውን ውስጥ ማዋቀሩ፣ የአገር ጉዳይ ከሥርዓት ባሻገር መታየቱን ያጎላል፡፡ አለፍ ሲልም፣ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ወቅታዊ ቅራኔዎቻችንና እነሱን ልንፈታ የምንዳክርበት መንገድ፣ ምን ያህል ከትልቁ ስዕል የራቀ ስለመሆኑ እንድናስብ ምክንያት ለማግኘት ያግዘናል፡፡
እርግጥ ነው፣ ታሪኩ ልባችንን አንጠልጥሎ በውብ ቃላት ይፈሳል፡፡ ሁነቶችና ምናባዊ ቦታዎችን የሚገልጹት ቃላት ምስል ከሳች ናቸው፡፡ እንደዚያ ብቻ ግን አይደለም፣ በገፀባህሪያቱ በኩል በድፍረት የሚነሱት ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ታሪክ ነክ ሃሳቦች ቆም ብለን እንድናሰላስል የሚያስገድዱን ናቸው፡፡ ደራሲው፣ ሀብታሙ አለባቸው  ሃሳብ የማይነጥፍበት ደፋር ደራሲ መሆኑን በዚህም ድርሰቱ አስመስክሯል፡፡
ፖለቲካን ያለሙያ እንደልባቸው ‘የሚተነትኑ ጎበዛዝት’ በበዙበት ዘመን፣ የፖለቲካ ምሁሩ ሀብታሙ አለባቸው፣ ፖለቲካና  ታሪካችንን በልብወለድ መልክ ማስኮምኮሙን የተጋበት ምስጢር ምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ፣ አንድ ዘመን አይሽሬ ግሪካዊ ጸሐፊ ፊታችን መጥቶ ድቅን ይላል - ኒኮስ ካዛንታዝኪስ።
የሕይወት ትርጉም ለጠፋበት፣ ተቅበዝባዥ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ሰው፣ አዲስ አለም ሊፈጥሩለት ተፍተፍ ይሉ በነበሩት ማርክሲስቶች ሃሳብ፣ ካዛንታዝኪስ ተማረከ። የጦፈ ወዳጅነትም መሠረተ። ቭላድሚር ኤሊች ሌኒንንም፣ ከሰማይ እንደወረደ መና ቆጠረው።  ትግሉን ለማገዝም አራት ያህል ጊዜ ወደ ሶቪየት ህብረት ተመላለሰ። በመጨረሻ ጉዞው የሶቪየት ህብረት መንግሥት ዕድል ሰጥቶት፣ አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ ዞሮ በመጎብኘት ስለ አዲሱ መሲህ/አዳኝ- ኮሚኒዝም፣ ሊጽፍ ተነሳሳ። ጉብኝቱን ሲያጠናቅቅ ግን ያየውንና የሰማውን ሁሉ በፕሮፓጋንዳ መልክ መጻፍ እርባና እንደሌለው ተገለጠለት። በተመስጦ የተቀበለው ማርክሲዝም ብቻውን፣ የሰው ልጆችን መንፈሳዊ ጉድለት ለመሙላት በቂ እንዳልሆነ ተገነዘበ። እናም የፈጠራ ድርሰትን ሙጥኝ አለ።
የኛው ደራሲ ሀብታሙ አለባቸውስ?
የፖለቲካ ሳይንስ ተምሯል፣ አስተምሯል። በመስኩ የተለያዩ ጽሑፎችንና መጽሐፍም አበርክቷል። አለፍ ሲልም ከፍተኛ በሚባል የመንግሥት አስተዳደር ባለሥልጣን ሆኖ አገልግሏል።
“በሙያህ የፖለቲካ ጽሑፎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ለምን ወደ ፈጠራ ድርሰት አጋደልክ?” ብለው ጋዜጠኞች እንዳይጠይቁት፣ እስካሁን ለሚዲያ ቅርብ እንዳልሆነ አውቀናል። የግሪኩን ጠሃፊ ቀደም ብለን የጠቀስነው አመሳስሎ ለመገመት እንዲመቸን ስለሆነ፣ ሀብታሙ አደባባይ ወጥቶ፣ የራሱን ሃቅ እስኪያጋራን ድረስ፣ እንደፈረደብን እንገምታለን -  ”የፈጠራ ድርሰት “ጉልጥምት ኢትዮጵያን” ለማጠናከር ትልቁ መሣሪያዬ ነው” የሚል ይመስለኛል። ቢልም ያምርበታል!!!


Read 425 times