Saturday, 09 March 2024 20:12

ምጥ እውነትና እውሸት አለውን ?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

በዚህ እትም ልናስነብባችሁ የወደድነውን የምጥን ሁኔታ ከሐኪሙ ማብራሪያ በፊት የአንዲት እናት ገጠመኝ በቅድሚያ እነሆ እንላለን፡፡
ልጅ ለመውለድ አዲስ አልነበርኩም፡፡ ከዚህኛው ልጅ በፊት የዛሬ ዘጠኝ አመት አንድ ልጅ ወልጃለሁ፡፡ የሚገርመው ነገር በዚያን ጊዜ ስለምጡም ሆነ ስለልጁ ምንም ነገር አስቤ አላውቅም፡፡ እንዲያውም የወለድኩ እለት እኔ በአዳራሽ ውስጥ ቆሜ ስልጠና እየሰጠሁ ነበር፡፡ በድንገት ላፕቶፔን እየነካሁ ነጥቦችን እየተናገርኩ ሳለሁ በድንገት ጫማዬ እስሞላ ድረስ ፈሳሽ ፈሰሰኝ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ ከሰው ፊት ቆሜአለሁ፡፡ የሆንኩት ነገር አልገባኝም፡፡ አጠገቤ ያሉት የስራ ባልደረቦቼ ተጨንቀው ከሰው ፊት ዞር አደረጉኝ፡፡ እኔም ወዲያው ለእናቴ ደወልኩላት፡፡
…..ማም…..እባክሽ ፓንት ገዝተሸ አቀብይኝ…..ነበር ያልኩአት፡፡
እሱዋም….የምን ፓንት…በዚህ ሰአት …የምን ፓንት….የት ነሽ…..አሁን እኮ አምስት ሰአት ነው…..ምን ማለት ነው….ብላ ተቆጣችኝ፡፡፡
አ…አ..ይ…ስልጠና እየሰጠሁ ነበር፡፡ ነገር ግን በድንገት ሽንቴ አምልጦኝ…ፓንቴ በሰበሰ…አልኩአት፡፡
እሱዋም….አረ በስምአብ…የት ነው ያለሽው….በይ መጣሁ…አርፈሽ ተቀመጭ ብላ ….በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ወሰደችኝ፡፡ ..ከዚያም ልጁን ወለድኩ፡፡  በቃ፡፡
ከዘጠኝ አመት በሁዋላ የተረገዘውን ልጅ በተመለከተ ግን እድሜዬም ጨምሮ ወደ ሰላሳ አራት አመት ደርሶአል፡፡ ሁሉንም ነገር መከታተል መጨነቅ ጀመርኩ፡፡ በሁዋላም የቀን አቆጣጠሩ ከሐኪሞቹ ጋር አልገጥም አለኝ፡፡ የእነሱ ቀን አቆጣጠር ከእኔ በአንድ ወር ተለይቶ አረፈ፡፡ እኔ የወገብ ህመም ሲሰማኝ እወልዳለሁ ብዬ ተነስቼ ወደ ሆስፒል ሄድኩ፡፡ ሁለት ቀን አሳድረው የውሸት ምጥ ነው ብለው ወደ ቤቴ መለሱኝ፡፡ ከዚያ በሁዋላ በአንድ ወሩ ነው የወለድኩት፡፡ ያቺን አንድ ወር ግን ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባኝ ቀንና ሌሊት እንደጠበቅሁ…ባለቤቴን …..ቤተሰቤን እንዳስጨነቅሁ ከረምኩ፡፡ የገረመኝ ነገር የእውሸት ምጥ የሚባል ነገር መኖሩ ነው፡፡
ራሔል አየለ…ከመካኒሳ
ምጥን በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ዶ/ር እዮብ አስናቀ ናቸው፡፡ ዶ/ር እዮብ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በአበበች ጎበና የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል በመስራት ላይ ናቸው፡፡
ዶ/ር እዮብ እንደገለጹት ምጥ የሚባለው ነገር የእርግዝናው ጊዜ አብቅቶ ልጁ ከማህጸን ለመውጣት በሚፈልግበት ጊዜ በየተወሰነ ሰአት የማህጸን ወይም የሆድ ቁርጠት የሚመስል ከበድ ያለ ሕመም የሚሰማበት ሲሆን ይህም ልጅ እና የእንግዴ ልጅ እንዲወለድ የማህጸን በር እንዲከፈት የሚያስችል ሂደት ነው ፡፡ ምጥን ትክክለኛ ምጥ ነው ለማለት ቢያንስ በአስር ደቂቃ ውስጥ ሁለት ጊዜ የሚመጣ የቁርጠት ሕመም መኖር አለበት፡፡
የማህጸን በር በተፈጥሮው ወፈር ያለ ነው፡፡ ምናልባትም ከከንፈር ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡ ነገር ግን በምጥ ሰአት የማህጸን በር እየሳሳ እና እየለሰለሰ የወረቀት ያህል ስስ በመሆን እንዲለጠጥ የሚያስችለው ያ የምጥ ስሜት ወይንም ህመሙ ነው፡፡ ህመሙ ልጁ ለመወለድ ግፊት ባደረገ ቁጥር የሚመላስባቸው ደቂቃ ዎቹ እየቀነሱ ግፊ እየበዛ በሄደ ቁጥር የማህጸን በር የበለጠ እየሳሳ እና ልጁን እና የእንግዴ ልጁን ለማሳለፍ ዝግጁ እየሆነ ይመጣል፡፡
ምጥ በትክክል መጣ የሚባለው ከሰባተኛው ወር (ከሀያ ስምንት ሳምንት)ጀምሮ የሚመ ጣውን ሲሆን ከዚያ በፊት ግን ውርጃ ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ጊዜውን የጠበቀ ምጥ የሚባለው ከ37-41 ሳምንት ባለው ጊዜ የሚከሰተው ነው፡፡ ከዚያ በታች ሲሆን ግን ያለጊዜው የመጣ ምጥ ይባላል፡፡
እናቶች እርግዝናቸው የመጀመሪያ ከሆነ እውተኛው ምጥ ከመምጣቱ በፊት የሚሰማ የወ ገብ አካባቢ ህመም ወይም እንደቁርጠት ያለ ስሜት አለ፡፡ ይህ የእውሸት ምጥ ይባላል፡፡ እንዲያውም በአገራችን እናቶች መንገድ ጠረጋ እያሉ ይገልጹታል፡፡ የእርዝናው ጊዜ ወደ ማለቅ ሲቃረብ እንደልብ ወዲያ ወዲህ ለማለት አለመቻል፤በመኝታ ላይ እንደልብ መገላበጥ ማቃት፤ቁጭ ብድግ ሲሉ ጥንቃቄ የመሻት አይነት እና እያለፈ እያለፈም ህመሙ የሚሰማ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ እርጉዝ የሆኑ ሴቶች ይህ ህመም ሲሰማቸው ምጥ ስለሚመስላቸው ወደ ማዋለጃ ሆስፒታል ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን ይህ የእውሸት ምጥ ህመሙ በማስታገሻ የሚተዋቸው እንዲሁም ውስን በሆነ ሰአት የማይመላለስ በመሆኑ ወደቤታቸው እንዲመለሱ ይደረግና ክትትላቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡ በእውነተኛው ምጥ ወደ ሆስፒል ከመም ጣታቸው በፊትም ሁለት ሶስት ጊዜ ወደ ሆስፒል የሚመላለሱ እናቶች አሉ፡፡ እናቶች ሌሎች ተያያዥ እና የቅርብ ክትትል የሚያስፈልገው ህመም (ደም ግፊት..ወዘተ) ካለባቸው ግን ለህክምናው ቅርብ እንዲሆኑ ስለሚያስፈልግ አልጋ እንዲይዙ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌላ የጤና ችግር ከሌለ ግን በቤቷ ሆነ ክትትልዋን እያደረገች ጊዜውን እንድትጠብቅ ይደረጋል፡፡ ይህ እንግዲህ እስከ አንድ ወር እና ከዚያም በላይ ሊደርስ የሚችል ጊዜ ነው፡፡ እውነተኛው ምጣ ሲጀምር በአስር ደቂቃ ውስጥ እስከ ሁለት ጊዜ  ይመላለስ የነበረው ቁርጠት ጊዜው እየደረሰ ሲሄድ ይበልጥ በማፋፋም እስከ ሶስትም አምስት ጊዜም የሚመ ላለስት  እንዲሁም አንዴ ሲመጣ ከአርባ እስከ ሀምሳ ሴኮንድ የሚቆይ ህመም ይኖረዋል ብለዋል ዶ/ር እዮብ፡፡
የሽርት ውሀን በሚመለከት ዶ/ር እዮብ እንደገለጹት በምጥ ወቅት ፈስሶአቸው ወደማ ዋለጃው የሚመጡ እናቶች አሉ፡፡ አፈሳሰሱን ስንመለከት አንዳንድ ጊዜ በድንገት ፏ ብሎ የሚወጣ ብስብስ የሚያደርግ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቀስ እያለ በትንሽ በትንሹ የመ ፍሰስ ባህርይ አለው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ደግሞ ምጡን እንዲያፋጥን ሲባል በሰው ሰራሽ መልኩ በሐኪሞች እርዳታ የሚፈስበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ በሐኪሞች  እንዲፈስ የሚደረገው ሽርት ውሀ በተለይም የመወለጃው ጊዜው ያለፈበት ከሆነ የሽርት ውሃውን ከለር ለማየትም ይረዳል፡፡ በተፈጥሮው የሽርት ውሀ መልኩ ውሀማ ፈሳሽ ሲሆን ልጁ የመወለጃ ጊዜው ካለፈ ግን በማህጸን ውስጥ እያለ ልጁ ካካውን ይለቅና የሽርት ውሀው መልኩንም ቅርጹንም እንዲለቅ ይሆናል፡፡ ይህም በሶስት ደረጃ የሚገለጽ ሲሆን በሶስተኛው ደረጃ የሽርት ውሀው የመወፈር ወይንም ወደ ጭቃነት የመለወጥ ነገር አለው፡፡
 ያንን ጭቃ መሰል የሽርት ውሀ ልጁ ስለሚጠጣው ወደሳንባው የመግባት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ያም የመ ታፈን እና ለሳንባ ኢንፌክሽን የመጋለጥ ሁኔታን ያስከትልበታል፡፡ አንዲት እናት ለመው ለድ በምጥ ላይ ባለችበት ሁኔታ የልጁን የልብ ምት መከታተል ሐኪሞች በኃላፊነት የሚወጡት ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም የልጁ የልብ ምት መጨመር መቀነሱ ከታወቅ በቀጣይ ልጁ በምጥ የወለድ ወይንም በኦፕራሲዮን የሚለውን ለመወሰን ወሳኝ ስለሆነ ነው እንደ ዶ/ር እዮብ ማብራሪያ፡፡  
በምጥ ወቅት በጥንቃቄ መታየት ካለባቸው ነገሮች መካከል የእናትየው የዳሌ መጥበብ አለመጥበብ ነው፡፡ እናትየው ክትትል በምታደርግበት ጊዜ ሁኔታው ይለያል፡፡ የማህጸን ጥበት ስለአለ ልጁ መወለድ አይችልም ወይንም የማህጸን ጥበት የለም መወለድ ይችላል የሚለውን መወሰን ይቻላል፡፡ አንዳንድ ጊጊ ግን መካከል ላይ ሆኖ ጥትም ስፋትም የሚመስል ደረጃ ይገጥማል፡፡ የጽንሱ ጭንቅላት ግጥም ብሎ የተዘጋ ሳይሆን አጥንቱ ክፍት ክፍት ያለው ነው፡፡ በምጡ ወቅት የእናትየው የዳሌ መጥበብ ካለ ጽንሱ በሚወለድበት ጊዜ ጭን ቅላቱ በአይን እንደሚታየው ክብ ሆኖ ሳያስቸግር ማለትም ክፍት ክፍት ስላለው ሞለል ብሎ ወይንም በአንድ በኩል ያለው በሌላ በኩል ካለው ጋር እንደመደራረብ ሆኖ የሚወለድ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ይህ ተፈጥሮአዊ ነገር ካለማንም ጣልቃ ገብነት ልጁ ከተወለደ በሁዋላ በተፈጥሮው ወደትክ ክለኛው የጭንቅላት ቅርጽ ይገባል፡፡
 ከዚህ ሌላ በጥንቃቄ የሚታይ ነገር ደግሞ የጽንሱ ጭንቅላት ማበጥ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የጽንሱ ጭንቅላት በሚያብጥበት ጊዜ የእናትየው የዳሌ አጥንት ሊያሳልፈው ይችላል ወይንስ አይችልም የሚለውን ለመወሰን ይረዳል፡፡ ስለዚህ የተጠቀሱትና ሌሎችም ሁኔታዎችን ለማወቅ ለእናትየው በክትትል ወቅት አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ልጁ ለመወለድ እስከሚደርስበት ጊዜ ድረስ እንዲሁም ከተወለደ በሁዋላ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ አንዲት እናት እርግዝናዋ ሃያ ስምንት ሳምንት ከሆነው ጀምሮ ልጁ እስከሚወለድ ድረስ ባለው ጊዜ የደም መፍሰስ ሲያጋጥም Anti partum haemorrhage (Aph) ይባላል፡፡
ይህም አጋጣሚ እናትንም ጽንሱንም ሊገድል የሚችል አስከፊ ገጠመኝ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል አንዱ ልጅ ከተወለደ በሁዋላ ከማህጸን መላቀቅ ያለበት የእንግዴ ልጅ ልጁ ከመወለዱ በፊት ከማህጸን መላቀቁ ነው፡፡ በእርግጥ የደም ፍሰቱ ጥቂት፤መካከለኛ እና ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ በጥቂቱ ሲሆን በእናትየውም ሆነ በጽንሱ ላይ የሚያስከትለው አደጋ የሌለው ሲሆን ከፍተኛው ሲሆን ግን ከ40-50 በመቶ ያህል ጽንሱ ሊሞት ይችላል፡፡
እናትየውም በከፍተኛ ሁኔታ የደም መፍሰስና ህመም ይኖራታል፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ያለው በሁለቱ መካከል ያለ ነው፡፡ እርግዝናው ወደ 37 ሳምንት ከሆነው እንዲወለድ ሲደረግ ከዚያ በታች ከሆነና የእንግዴ ልጁ መላቀቅ በትንሹ ከሆነ አልጋ ይዛ ጊዜውን እንድትጠብቅ እና እንድትወልድ ይደረጋል፡፡ አልጋ ይዛ የሚለው በቤት ውስጥ ነው ወይንስ በሕክምና ተቋም ለሚለው እንደሁኔታው የሚወሰን ይሆናል ብለዋል ዶ/ር እዮብ አስናቀ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡   

Read 430 times