Sunday, 10 March 2024 00:00

መዓልትና ሌሊት - በቢጣራና ሞክየረር

Written by  -ብርሃነ ዓለሙ ገሣ-
Rate this item
(4 votes)

ሰኞ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ሎሚ ሜዳ ከሚገኘው መጠለያዬ ለጉዞ ዝግጁ ሆንኩ፡፡ ሌሊቱን ለጉዞ የሚያስፈልጉኝን የጽሕፈት፣ የመቅረጸ ድምጽ እንዲሁም የምስለ ፎቶ መሣሪያዎቼን አደራጀሁ፡፡ የጉዞዬ መጀመሪያ አዲስ አበባ ሲሆን፤ የጉዞዬ መዳረሻ ወይም ማጠናቀቂያ ደግሞ የቢጣራና ሞክየረር ናቸው፡፡ ከማለዳው 11፡45 ሰዓት ላይ ጊዜያዊ መጠለያዬን መተው የግድ ሆነ፡፡ ኁልቆ መሳፍርት ከሌለው ሕዝበ ሰራዊት ጋር ለመደባለቅ ወደ አውቶቡስ ተራ ተሳፈርኩ፡፡ አውቶቡስ ተራ ስደርስ ሰዉ ጎርፍ ያመጣው እንጂ ተሳፍሮ የመጣ አይመስልም፡፡ ሰዓት ሳልገድል ከአውቶቡስ ተራ ምዕመናን ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ “ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ፤ አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ” እንዲሉ፡፡
ከየአቅጣጫው የተመመው የሰው ዘር አውቶቡስ ተራ ውጦ አያስቀረውም፡፡ እንደየአመጣጡና እንደ ምዕላዱ ይወጣል፣ ይገባል፡፡ ይመጣል ደግሞም እንደ ሁኔታው ወደ ቅርብ ወይም ወደ ሩቅ አካባቢ ይሄዳል፡፡ የአውቶቡስ ተራ ትዕይንት ሰርክ የተለመደ ነው፡፡ የአውቶቡስ ተራ ነዋሪዎች ነጋዴዎችና ባለደንታዎች ከሚሄደውና ከሚመጣው የዕለት እንጀራቸውን ያገኛሉ፡፡
እኔም አውቶቡስ ተራ እንደደረስኩ የአውቶቡስ ተራ ባሕር ዋጠኝ፡፡ የምፈልገው መስመር አሰለጫ የዌራ በር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዘላቂ ስላልሆንኩ “ሰኽየር” የሚባል ቦታ ላይ እወርዳለሁ፡፡ በቀቡል መኪና ከጧቱ 1፡00 ሰዓት አውቶቡስ ተራ ከሚገኘው መናኸሪያ ወጣሁ፡፡ የዕለቱ ጉዞዬ የቢጣራ ላይ ይጠናቀቃል፡፡ ነገ ደግሞ ሞክየረር፡፡
የጉዞዬ ዋነኛ ዓላማ ዓመታዊው የደሟሚት ክብረ በዓል በሆነው በሰንቸ በዓል ላይ ተገኝቼ  መረጃዎችን ማጠናቀር ነው፡፡ ከሰኽየር ወደ የቢጣራ ለማለፍ ሰኽየር የሚገኘውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አጥር ተከትዬ ወደ ግራ ታጠፍኩ፡፡ መንገድ ላይ ውዬ ቢደክመኝም የዕለቱ አየር ሁኔታ ነፋሻማ ስለነበር ብርታት አገኘሁ፡፡ ያልተበረዘ፣ ያልተከለሰና ያልተበከለ አየር፡፡ የተወሰኑ ደቂቃዎችን እንዳስቆጠርኩ መለስተኛ ጫካ ውስጥ ገባሁ፡፡ የእጅ ስልኬን ወደ አቤቶ ቸር አምላክ ዘንድ ጨቆንኩት፡፡ ምላሻቸው ፈጣን ነበር፡፡ የእንጨት ድልድዩ ጋ መሆኔን ስነግራቸው ከመቅጽበት መንገድ መሪ ላኩልኝ፡፡   የላኩልኝ መሪ በፍጥነት ደርሶ የጉዞ ሻንጣዬን ተቀበለኝ፡፡
ስለ የቢጣራ እያወጋን መንገዱን እንደዘበት ጠቀለልነው፡፡ የቢጣራ ቀበሌ ከነግርማ ሞገሱ ተገለጠ፡፡ በአገርኛና በዕድሜ ጠገብ ዛፎች አጊጦና ተውቦ ልዩ እርካታን ይሰጣል፡፡ የቢጣራ ላይ ሁለት የደሟሚት ሥርአት መከወኛ ገራራዎች ይገኛሉ፡፡ ትልቁ ገራራ በዕድሜ ጠገብ ዛፎች ከማጌጡም በተጨማሪ የዌደማም ቱሪ (የአቤቶ ቸርአምላክ ቅም አያት) ያስተከሏቸው ሶስት ትልልቅ ዝግባዎች ስላሉበት ለአካባቢው ተጨማሪ ውበትን ለግሰውታል፡፡
የቢጣራ የደሟሚት ክብረ በዓል የሚከናወንበት ታሪካዊ ሥፍራ ነው፡፡ የቢጣራ ላይ የተጀመረው ክብረ በዓል ሞክየረር ላይ እልባት ያገኛል፡፡  
የቢጣራ የሰው እጅ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ በራሱ አሰማምሮ ውበት ደፍቶበታል፡፡
ከአካባቢው ለየት ብሎ ጥቅጥቅና ችምችም ባሉ ዛፎች ታጅቦና ግርማ ሞገስን ተላብሶ ለተመለከተው አንዳች ትፍስህትን ይሰጣል፡፡ የካሜራዬን ሌንስ እያስረዘምኩና እያጠበብኩ የቢጣራን ውበት ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ግና የውኑ ዓለምና የካሜራ ውጤት መቶ በመቶ አንድ አይነት ሊሆን አይችልም፡፡ ተፈጥሮ ተፈጥሮ ናትና፡፡
በሥርዓት የተደረደሩት የቢጣራና አካባቢው ዛፎች ቀልብን ብቻ ሳይሆን ልብንም ይገዛሉ፡፡ የቢጣራው የደሟሚት ገራራ በውበት ላይ ውበት ስለተጎናጸፈ ዓይኔን መንቀል ተሳነኝ፡፡   
“ ምነው? ” አሉኝ፤ አቤቶ ቸርአምላክ
“ ምንም-አቤቶ!”  መለሰኩላቸው፤በራሴ ሁኔታ ተገርሜ
 “እንዴት? ”  ጠየቁኝ  
 “ተገርሜ ነው፡፡ በአካባቢው ውበት ነሆለልኩ፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ እስከዛሬ ባለማየቴ በራሴ አዘንኩ”
“ አንዳንዴ አይገጥምም!” አሉኝ
“ አዬ አቤቶ የእኔ ስንፍና ነው፡፡  ከልብ ባስብበት ይህን ያህል ጊዜ የሚወስድ አልነበረም”
“  ግዴለህም! አሁንም አልመሸም፤ ገና ብዙ እንሠራለን፡፡ አይዞህ” አሉኝ
የልብ ልብ ተሰማኝ፡፡ የደስታ ሙቀት በውስጤ ሲቃጣል አስተዋልኩ፡፡ ሰው መርሐ ግብሩን በአግባቡ ከቀመረ ያለጥርጥር ካሰበበት መድረስ ይችላል፡፡
ለጥቆ ያደረግነው የደሟሚት ገራራን ቀሪውን ክፍል መመልከት ነበር፡፡ በምስሉ ላይ የምትመለከቷቸው ሁለት ቤቶች፣ የደሟሚት ሥርአት መከወኛዎች ናቸው፡፡ እዚህ ፈጣሪ ይለመናል፤ ይመሰገናል፤ ለአገር መልካም ምኞት ይተላለፋል፡፡ ደሟሚት መልዕክት ታደርሳለች - ወደ ፈጣሪ፡፡
ገራራውን ጨርሰን ስንወጣ የዌደማም ቱሪ የተከሏቸው ሁለት ዛፎች እናገኛለን፡፡
የመስቀል ደመራ የሚደመረውም እዚሁ ነው፡፡ በየዓመቱ መስቀል የሚካሄድ የራሱ የሆነ ሥርዓት መኖሩን አቤቶ ቸርአምላክ አጫውተውኛል፡፡
በቢጣራ የደሟሚት ሥርዓት ማከናወኛ ሁለት ገራራዎች አሉ፡፡ ትልቁና የኮሽቴ ገራራ ይባላሉ፡፡ የቢጣራ ስንገባ      ትልቁን ገራራ ነው የምናገኘው፡፡ ከገራራው ቀጥሎ ጥቂት ወደፊት አለፍ እንዳልን በቀኝ በኩል የዌደማም (አቤቶ) መኖሪያ ቤት ከፍ ብሎ ይታያል፡፡ በመልክ በመልክ የተደረደሩ፦ ትልቁ ቤት (ጎየ)፣ እልፍኝ (ኸራር) እና ሌሎች የእንግዳ መቀበያ ቤቶች ይገኛሉ፡፡
በቢጣራ ስለ ስንቸ ዓመታዊው የደሟሚት ክብረ በዓል ገለጻ ተደረገልን፡፡
ከገለጻው ቀጥሎ ያደረግነው ወደ ገራራዎቹ በመሄድ ማብራሪያ መስማት ነበር፡፡ ምዕመናን ሲመጡ የተለያዩ ሥርዓቶች እዚህ እንደሚፈጸሙ ተረዳን፡፡
የኅብረተሰቡ አባላት (ምዕመናን) ያጋጠማቸውን ችግር ተናግረው ደሟሚት ፈጣሪ የሰጣትን ስልጣን ተጠቅማ መልዕክት ወደ ፈጣሪ በማድረስ መፍትሄ ታመጣለች፡፡
ወይም እርምጃ ታስወስዳለች፡፡ ልጅ ያማረው ልጅ እንዲያገኝ፣ የተበደለ ካለም መፍትሄ እንዲያገኝ ታደርጋለች - በፈጣሪ አማካይነት፡፡ አቤቶ በመጀመሪያው ገራራ ያለውን ሥርአት በዝርዝር ከነገሩን በኋላ ለሁለተኛው ገራራ ገለጻ ሰው መድበውልን ለጥር 7 ሰንቸ በዓል ዝግጅት ወደ ሞክየረር ተጓዙ፡፡
ደሟሚት በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ ከሚገኙ ሶስቱ ባህላዊ እምነቶች አንዷ ነች፡፡ ደሟሚት የማሕጸንና የልምላሜን ጉዳይ ወክላ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ችግር ወደ ፈጣሪ፣ የፈጣሪን መልዕክት ደግሞ ወደ ኅብረተሰቡ ታደርሳለች ተብሎ ይታመናል፡፡ ደሟሚት ገድሏ ብዙ ነው፡፡    
የደሟሚት ክብረ በዓል ሰንቸ በየዓመቱ በጥር ወር መጀመሪያ ወይም በሁለተኛው ማክሰኞ ይከበራል፡፡ የዘንድሮው ጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ተከብሯል፡፡ ሰንቸ የሚከበረው በቢጠራና ሞክየረር ሲሆን በጥር ወር በይበልጥ በሞክየረር በድምቀት የሚከበር ሲሆን፤ በቢጣራ ደግሞ በግንቦት ወር መሆኑን በቆይታዬ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም በቢጣራ ምሽት የጀመረው ትዕይንት ሌሌቱ ድረስ ዘልቋል፡፡ በደሟሚት ማወደሻ ዜማና ጭፈራ ደምቆ እስከ ሌሊቱን ድረስ በአድናቆት በአግራሞት ተሳትፈናል፤ በክዋኔው ተደምመናል፡፡
በሰንቸ በዓል ላይ የደሟሚት አባል የሆኑ ሴቶች በግንባር ቀደምትነት ይሳተፋሉ - ወንድ የገማ ሞየቶችንም ጨምሮ፡፡ የገማ ሞየቶች ሥርአቱን በመምራት ረገድ ድርሻ አላቸው፡፡ እንደ ሴቶች ሁሉ ወንዶችም በበዓሉ ላይ ይታደማሉ፡፡ የደሟሚትን እንጉርጉሮ በየፊናቸው እያንጎራጎሩ የማኅበረሰቡን አዎንታዊ ተግባራት እንዲቀጥሉ፤ አሉታዊዎቹ ደግሞ እንዲታረሙ እንዲሁም የተበላሹት እንዲስተካከሉ መልዕክት ወደ ፈጣሪ እንዲደርስ ለደሟሚት ማሳሰቢያ ይሰጣታል፡፡ ከማሳሰቡ በተጨማሪ የተማጽዕኖ (የልመና) ጥያቄም ይቀርብላታል፡፡ የደሟሚት እንጉርጉሮ ዋይወቶ በሚል ሥም ይታወቃል፡፡
“አዶተኖ (እናቴ)” ብሎ በመጀመር ልጃገረዶችና ሴቶች ዋይወቶን በኅብረት ያንጎራጉራሉ፡፡
ብሻ ደሞ ዳ ኤናህይ ደሞ
ገረድ ተሰሜ ትተወርድ
ምር አውያም ወረት
 …
ሽማህዮ አት እማቶ
ብሻ ደሟሚቶ
ዋይወቶ ጋሞቶ
ኤቴ ትረብሮ? የቢጣዮ
በቢጣዮ ቤተና ትንቅዮ
 …
ቤቴ ትተፈጠር ደምወት?
በረን ዌራ በር
በተት ቦዠባር …  
የደሟሚት ማሞገሻና ማወደሻ ጥዑመ ዜማዎች ሲዜሙ ጨፋሪዎች ጭፈራቸውን ያሳያሉ፡፡ ከወትሮው ጉራግኛ ጭፈራ ለየት ያለ ስልት ይታያል፡፡ ጨፋሪዎች ሁለት እግሮቻቸውን ከመሬት ብድግ በማድረግ ሁለት እጆቻቸው አየሩን እየቀዘፉ (እጥፍ ዘርጋ እያደረጉ) አንዳንዴም በወገባቸው በኩል አድርገው ይሠሩታል፡፡  
ማክሰኞ ጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም በጧት ከአልጋችን ተፋታን፡፡ ጀምበር የምሥራቁን የአድማስ ጥግ ታክካ እየተገለጠች ነበር፡፡ ማማሚያ! የቢጣራ በውበት ላይ ውበት ደርባለች፡፡ የሚታየው ሁሉ አረንጓዴ ነው፡፡ አረንጓዴ ምንጣፍ፣ አረንጓዴ መንደር፡፡
ጥር 7 ጧት በቢጣራ ከመብላትና ከመጠጣት ውጪ ያደረግነው ነገር የለም፡፡ ቁርስ በልተን እንዳበቃን ወደ ሞክየረር ለመሄድ ተዘጋጀን፡፡ የተለያዩ መንደሮችን አቆራርጠን በባለ ሶስት እግሩ ባጃጅ ወደ ሞክየረር ሮጥን፡፡ ሌላዋ ውብ ቀበሌ ሞክየረር ከእነ ግርማ ሞገስዋ ተሰድራለች፡፡ ሌላው የደሟሚት ሥርዓት መፈጸሚያ ገራራ እዚህ ይገኛል፡፡     
ሞክየረር እንደደረስን ያመራነው አቤቶ ቸርአምላክ ወደ ነበሩበት ገራራ ነበር፡፡ የዌደማም (የደሟሚት ሥርዓት በበላይነት የሚመሩት ናቸው) ስለ ክብረ በዓሉና ሰለደሟሚት ገለጻ የሚያደርጉልን ሰዎች መድበውልን ስለ እያንዳንዱ ክዋኔ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ በምን ጊዜ ምን እንደሚሠራ፣ ምን ምን እንደሚባል ወዘተ. የደሟሚት አባላት ሚናና ተግባራቸውን በዝርዝር አስረድተውናል፡፡  
 ረፋድ ላይ የደሟሚት ዓመታዊ ክብረ በዓል ሰንቸ መከበር ተጀመረ፡፡ የደሟሚት አባላት (ምዕመናን) ልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎች ማቅረቡን ተያያዙት፡፡ ከዚህ ክንዋኔ በተለይ ዱላት በረዳን የመሰለ ድምፀ መረዋ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የዱላት የመቀለጽ ችሎታ ይደንቃል፡፡ ረዥም ዕድሜና ጤንነት ለሁሉም አባላት ለመመኘት ተገደድኩ፡፡ እያንዳንዱን ትዕይንት የተከታተልኩት በስስትና በአድናቆት ነበር፡፡ ይህ በዓል ከዓመታት በፊት በከፍተኛ ድምቀት ይከበር እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ አሁን አሁን አንዳንዶች አይደለም ስለባህሉ ስለራሳቸው እንኳ በቅጡ የማያውቁ በከፈቱት ውዥንብር የታዳሚው ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል ነውና ለባህሉ የሚቆረቆር ሁነኛ የባህል አምባሳደር አልተፈጠረም ነበርና፡፡ በሂደት ግን “እኔ ማን ነኝ? ከየት መጣሁ? ባህሎቼ ምን ምን ነበሩ?” የሚሉ ጠያቂዎችና የባህሉ ተቆርቋሪዎች ሲነሱ ሰንቸ ነፍስ ሊዘራ ችሏል፡፡
እኔ የዚሁ ጽሑፍ አቅራቢ ባህልን በሚመለከት መጣጥፎች ለማዘጋጀት በርካታ ሥፍዎች ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ በባህሎቹ ክዋኔዎች ተደንቄያለሁ፤ ተገርሜያለሁ፡፡
 በቢጣራና በሞክየረር ያየሁት ትዕይንት ግን እጅግ ተለይቶብኛል፡፡ በጣምም አስደስቶኛል፡፡ ነበርን የማያውቅ ነውን ሊረዳ አይችልምና ሰንቸ ሊከበር የሚገባው ትልቅ በዓል ነው፡፡ ሰንቸ፣ ሲከበር በበዓሉ ላይ ለመታደም ቱሪስቶች ይመጣሉ፡፡ አገራዊ እሴቶች አደባባይ ላይ ይወጣሉ፡፡ በዚህም አገር እንደ አገር፣ ዜጎችም እንደ ዜጋ ይጠቀማሉ፡፡
በተለያዩ ዜማዎች የታጀበው የደሟሚት ማወደሻ ጥዑመ ዜማ በሞክየረር ጠፈር ላይ ከቦታ ወደ ቦታ እየናኘ ጆሮ መቆጣጠሩን አላቆመም፡፡
ዜመኞች ዜማቸውን ያሰማሉ፡፡ ተቀባዮች ይቀበላሉ፡፡ በልጅነቴ እሰማቸው የነበሩ የደሟሚት ማወደሻ ዜማዎች ሳይበረዙና ሳይከለሱ እዚህ እንደወረዱ አገኘኋቸው፡፡ ከረዥም ዓመታት ልፋትና ድካም በኋላ፡፡ ለዚህ ተግባር የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት አቤቶ ቸርአምላክ ዘርፉና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ናቸው፡፡ በዕለቱ ያገኘኋቸው የበዓሉ አክባሪዎችና የባህል ተቆርቋሪዎች፣ በጉራጌ ባህል ላይ ይበልጥ እንድሠራ ብርታት፣ ስንቅና ትጥቅ ሆነውልኛልና አመሰግናለሁ ከማለት ሌላ ምን እላለሁ? በቢጣራና በሞክየረር መማር ያለብኝን ተማርኩ፤ ማወቅ ያለብኝን አወቅኩ፡፡
 ለዓመታት ስመኘውና ስናፍቀው የነበረውን የደሟሚት ሥርዓት (ክዋኔ) ሳይበረዝና ሳይከለስ አገኘሁት፡፡ የሞየቶች ዜማ፣ ጭፈራ ወዘተ. ሁሉንም ተራ በተራ ዓይኔ እስኪፈዝ ተመለከትኩ፡፡ በአዕምሮዬም፣ በያዝኩት ካሜራም ምስሎች ቀረጽኩ፤ ድምጾችን ቀዳሁ፡፡ አንዳንድ ብዥ ይሉብኝ የነበሩ ድርጊቶች እስኪገለጡልኝ ተጋሁ፡፡
በመጨረሻም በሕይወቴ ልረሳው የማልችለውን ክዋኔ (ሁነት) በውስጤ አስቀረሁ፡፡
የዕለቱ መርሐ ግብር የተጠቃለለው ሞየቶች ወጥተው የደሟሚት ሥርዓትን ደረጃ በደረጃ ከፈጸሙ በኋላ ነው፡፡ የጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም የደሟሚት ዓመታዊ የሰንቸ ክብረ በዓል የተጠናቀቀው በግብዣ ነው፡፡ የዕለቱ መርሐ ግብር እንዳበቃ ጉዟችንን ወደ እምድብር ከተማ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሆነ፡፡ ለዓመቱ ሰንቸ በሰላም እንዲያደርሰን ተመኝተን ወደ መጣንበት በሰላም ተመለስን፡፡ ሰላም!

Read 513 times