Tuesday, 12 March 2024 00:00

መቋጫ ያጣው የመጠፋፋት አባዜ! (ከትላንት እስከ ዛሬ)

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

እንደ ኢየሩሳሌም ቅጥር ፈርሶብን ሳንጠግነው፣ የዝማሬ መሠንቋችን ደርቆ፣ የኤርምያስን ሠቆቃ እንድናላዝን፣ሙሿችንን እንድናሟሽ ያደረጉን የታሪክ መዘዞች ብዙ ቢሆኑም፣ በሩቅ ሳይሆን በቅርብ የምናያት ሀገራችን የተስፋዋ ቋንጣ ተዘልዝሎ ከተሰቀለበት ለማውረድ ተንጠራርተን የምንደርስ አልመስል እያለን ስንባትት ዘመናት ቆጥረናል።
አበባችን ለፍሬ ሳይበቃ፣ረግፎ ከአፈር የተቀላቀለው በጣም ብዙ ጊዜ ስለሆነ፣አሁን የምናሸተው የተስፋ አበባ አፍንጫችን ሥር የለም። ይልቅስ ያረረ ፍሬ፣የከሰለ መልክ ማየት ከጀመርን ዘመናትን ቆጥረናል።
ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት እያልን ሠርክ ብናቅራራም፤ ጀግንነቷ ግን የራሷን ችግር በማሸነፍ አልተረጋገጠም። ምክንያቱም ሁሌ ራሷን የምትበላው ራሷ ናት። ጀግኖቿና አዋቂዎቿ ባብዛኛው የተበላሉት እርስ በርሳቸው ነው። ለምሳሌ ራሳችንን በራሳችን በመጎተታችን የከፈልናቸው ዋጋዎች ብዙ ናቸው።...በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት መግባባት አቅቶን፣ አንዳችን ለአንዳችን እንቅፋት እየሆንን፣በስተመጨረሻ የጠላት መፈንጫ ሆነናል። በዚያም ምክንያት የተጸነሱ ሕልሞች ጨንግፈው፣የተጀመሩ እርምጃዎች ተቋርጠዋል።
ይህ እርስ በርስ የመበላላት ችግር ከዚያም በኋላ ሳያበቃ፣በዐፄ ዮሐንስ ዘመን ቀጥሎ ከውጭ ጠላት ጋር የሚደረጉ ውጊያዎች እስከመጨረሻው በድል እንዳይደመደሙ እንቅፋት ሆኗል። ገና በልጅነታቸው ባሩድ አሽትተው፣ጀግንነት ተጠምተው፣በቄስ ትምህርት ቤት ከአጎታቸው ጋር ዒላማ የለመዱት ራስ አሉላ እንኳ ከአካባቢያቸው ተወላጆች ሳይቀር የገጠማቸው ፈተና ቀላል አልነበረም።...ከእነ ራስ ሐጎስና  መሰል ሰዎች የሚሰነዘርባቸው ጥላቻ በኋላ በጥይት እስከመመታት አድርሷቸው፣ የደረሰው የእርስ በርስ መጠፋፋት ቀላል ዋጋ አላስከፈለም።
በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ብዙ ሽኩቻና የእርስ በርስ ጥፋት ደርሷል። በአንድ በኩል የሀገረ መንግሥት ምሥረታ፣በሌላ በኩል የየሠፈር ሽፍትነት አቅማችንንና ኀይላችንን ከፋፍሎት መራራ ዋጋ አስከፍሎናል።
የትኛውም የዛሬ ሥልጡን ሀገር ትናንት በሄደበት ዓይነት ሻካራ የሀገር ግንባታ መንገድ ብንሄድም፣ለአካሄዱ የተሰጡት ትርጓሜዎችና በተለይ የውጭ ኀይሎች በሃይማኖት ሰበብ ገብተው የዘሩት ክፉ ዘር እንደ ጉሮሮ አጥንት ተሰንቅሮ ምራቅ አላስውጥ፣አላላውስ ብሎን ቀጥሏል። በጦር ግንባር የተሸነፉ የነጭ አክራሪዎች በሃይማኖት ሽንቁር ተጠቅመው እሳት ለኩሰዋል፤ሕዝብን ከሕዝብ፣ ወገንን ከወገን የማቆራረጥ ሴራ ሸርበዋል።
ከዚህ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በዐፄ ኀይለሥላሴ ዘመን፣ በዐፄ ምኒልክ ኅልፈት ምክንያት የተፈጠሩት ሽኩቻዎችና ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዙፋኑን ተረክበው፣ኅይለሥላሴ ባለሙሉ ሥልጣን አልጋወራሽ ከመሆናቸው በፊትና ከአቤቶ ኢያሱ ጋር በፈጠሩት ግጭት፣በራስ ሚካኤል በሚመራው የወሎ መኳንንትና በሸዋ መኳንንት መካከል በተካሄደው የሠገሌ ጦርነት፣ ከሁለቱ ወገን የፈሰሰው ደምና የደረሰው እልቂ፣የወደመው የሀገር ሀብት እጅግ የሚሰቀጥጥ ነበር። በጊዜው...የሞተው የተዋጊ ቁጥር ብቻ ሳይሆን የወሰደው የመንግሥት ትኩረት፣የወደመው የጦር ወሣሪያ፣ የፈሰሰው መዋዕለ-ንዋይ ቀላል አልነበረም። ምናልባት እዚያ ጦርነት ላይ የፈሰሰ ሀብትና የሰው ኀይል ቢኖር ኖሮ፣በኋላ ከሞሶሎኒ በኩል የተደረገው ወረራ በጠነከረና በተሟላ ዝግጅት የድሉን አቅጣጫ መቀየር ይቻል ይሆናል ብሎ መገመት አይከብድም።
የማይጨው ጦርነት ሽንፈት፣ የጠቀስኩት ሁነትና በኋላም በጦርነቱ ወቅት ወገን ከወገኑ የመበላላት አባዜና በመንግሥት ላይ ቅሬታ የነበራቸው ወገኖች በነበራቸው የአሰላለፍ ልዩነት የተፈጠረ፣አሳዛኝ የታሪካችን መልክ ነው።
ጥሎብን ወይም መርጠነው፣የኛ ነገር በግጭት ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ዐመታትን ቆጥረን እስከ መበቃቀልም የሚከፋ ቁርሾ ስለምንይዝ እስከ አጥንታችን ዘልቆ መራራ ዋጋ የሚያስከፍልና በድኽነታችን እንድንተከል አድርጎ  ዋጋ የሚያስከፍለን ሆኖ በየዘመናቱ ቀጥሏል።...የቋጠርናቸው  የቂም ከረጢቶች የበቀል ስልቻ እየሆኑ፣የጥፋታችን ፉርጎ እየረዘመ እነሆ ቀጥሏል።
በኢያሱና በንጉሡ መካከል የነበረው ልዩነትም ለረዥም ጊዜ ያመጣው መዘዝ ቀላል አለመሆኑና ንጉሡ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የሥርዐታቸውን ብልሽት በመቃወም መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት፣ገርማሜ ንዋይና መንግሥቱ ንዋይ በሞከሩት መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት፣በኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ ታሪክ ውስጥ ያመጣው ክስረትና ደም መፋሰስ እጅግ አሳዛኝና የታሪካችን ትውስታ እምብርት የሚጠዘጥዝ ቁስል ነው። ክስረቱና ጉዳቱ  ደግሞ በአንድ በኩል ብቻ ሣይሆን፤በሁለቱም አቅጣጫ ስለነበር ያጣናቸው ሰዎችና የቤት ሥራ ሆኖ የቆየው እርስ በርስ መነቋቆርና መጠፋፋት እንደ ቀላል የምናየው አልነበረም።
እነ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ ተልዕኳቸው አለመሳካቱን ሲያውቁ፣የገደሏቸው ትልልቅ ሰዎች በሀገሪቱ በቀላሉ የማይተኩ ሲሆኑ፣ በእነ መንግሥቱ ንዋይ በኩል ደግሞ እጥፍ ድርብ በሚባል ደረጃ ሀገሪቱ የነበሯትን ዕንቁዎች ያጣችበት አጋጣሚ ነበር። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑን በኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት አወቃቀርና ዘመናዊነት ላይ ልዩ የለውጥ ምዕራፍና የተቀላጠፈ እርምጃ የፈጠሩት የፖሊስ ሠራዊት አዛዡ ሜጀር ጄነራል ጽጌ ዲቡ፣ ራሱ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋነኛ ጠንሳሽ የነበረውና በዘመኑ የተማረ ሰው ብርቅ በነበረበት ዘመን በውጭ ሀገር የማስተርስ ዲግሪውን ሠርቶ፣በተለያዩ የሀገሪቱ ጠቅላይ ግዛቶች ተመድቦ፣ልዩነት ያመጣ ሥራ በመሥራት ላይ የነበረው ገርማሜ ንዋይም ሌላኛው የሀገሪቱ ስብራት ነበር።
በጦር አካዳሚ ሠልጥኖ፣በጠላት ወረራ ዘመን ከታላላቅ አርበኞች ጋር ሆኖ ለነጻነት የታገለውና በስተመጨረሻም የክብር ዘቡ አዛዥ የነበረው ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ፤ ለሀገራቸው የጎመራ የፍሬ ዛፍ ነበሩ። የደኅንነት ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁም ስለነበሩበት ደረጃና የሀገሪቱ የዐይን ብሌንነት ጃንሆይ በጊዜው ከተናገሯቸው ንግግሮች መረዳት ይቻላል።
የዚህ ዐይነት ሀገርን የሀገሪቱ ኅሩያን ቄራ ማድረግና ለአዋቂዎች የሚከፈል አምሓ ሞት ሲሆን ማየት በሀገራችን በየትውልዱ ሲደረግ የነበረና በታሪክና በየዘመኑ አንጓ የተለመደ ክስተት ሆኖ ኖሯል።
ይህ የታሪክ ምዕራፍ፣ኢትዮጵያ በተሻለ የታሪክ ቁመናና የዘመናዊነት ደጅ ቆማ በር ታንኳኳለች በተባለበት ጊዜ የተፈጸመ በመሆኑ የጭንገፋን ያህል የሚያም የታሪክ ቁስል ነው። በዚህም በሀገሪቱ የተሻለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር ተስፋ አላቸው ተብለው፣ፍሬያቸውን እንደያዙ የወደቁት ታላላቆች ሲወድቁ እነርሱ ውስጥ የነበሩት ሕልሞች መጨንገፋቸውና ለፍሬ የታሰቡት አበቦች መርገፋቸው እጅግ የሚያምም ቁስልና በታሪክ ውስጥ የሚቆይ ጥዝጣዜ ነው።
ይህ ጥዝጣዜ ደግሞ በወቅቱ በነበረው ሁነት ላይ ፈንድቶና ነድዶ ያበቃ አልነበረም። ነገሩ ውሎ አድሮ ያስከተለው መዘዝ፣ በመለዮ ለባሹ መካከል ጥርጣሬ ፈጥሮ፣ በእርስ በእርስ ውጊያ የወደቁትን የጦር ሠራዊትና የክብር ዘበኛ አባላት ከበላ በኋላ፣በሴራው ውስጥ ይኖራሉ የተባሉትንና የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ነው ያሉትን የክብር ዘብ የጦር ክፍል በማሳደድ በቀሉ ቀጥሎ ከባድ ጉዳት አድርሶ ነበር።
በዚህም መፈንቅለ መንግሥት ሰበብ በኋላ በደርጉ አብዮት ማግሥት “የመጀመሪያው የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጀኔራል” የተባሉትን በሳሉ ጀኔራል መርዕድ ንጉሤን ጨምሮ በርካታ የጦር መኮንኖች መራራ የሥቃይ ጽዋ ተጎንጭተዋል። ሥራቸውንም እንደሚገባ እንዳይሠሩ ተሠነካክለዋል። ይህ መሠነካከል ደግሞ ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን፤ የሀገር ዕድገትና እርምጃ የሚያዘገይ እንቅፋት ሆኗል።
በአብዛኛው የሀገራችን ታሪክ ከሀ እስከ ፐ እርስ በርስ የመጠላለፍና የመጠፋፋት መሆኑ ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ሳይሆን፣በታሪክ ገጾች ላይ ፊት ለፊት ያሉ ሐተታዎችን በማየት የምንረዳቸውና የምንቆጭባቸው ግልጽ ጸጸቶች ናቸው። በኋላም ይህንኑ ሁነት ተከትሎ ወይም መነሻ አድርጎ እንደተጠነሰሰ የሚገመተውና ለተማሪዎች አመጽ ፍም አዳፍኖ ካለፈው መፈንቅለ መንግሥት ቀጥሎ የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዐት አቅጣጫ የቀየረ ክስተት የተባለው የ1966 ቱ አብዮት፤ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔና ዕድገት መገታት ይዞ የመጣው መዘዝ ቀላል አልነበረም። እንደዋዛ “ያለምንም ደም፣እንከኗ ይውደም!” ተብሎ የተዘመረለትና በብዙ ዜማዎች የተሽሞነሞነው አብዮት፤ የሀገሪቱን የተመረጡ ምሁራን ከየአቅጣጫው ስብስቦ በብዙ ቄራዎች ላይ እርድ የፈጸመ፣ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ያደርጋሉ የተባሉ ምሁራንንና የጦር ኀይላችንን በዐለም ተወዳዳሪ ያደርጋሉ የተባሉ ጀግኖችን የበላ ሌላው የታሪካችን ወልጋዳ መንገድ ነበር ማለት ይቻላል። ገና ሀ ብሎ ሲጀምር፣በደርጉ የአቅም ማነስና ፍርሃት የተነሳ ሁሉንም ነገር በራሳቸው አቅምና መጠነ ርዕይ  ልክ ለማድረግ፣ በችሎታና በዕውቀት ከእነርሱ ዘለግ ብለው ያገኙዋቸውን ሁሉ መንጥረው መቃብር መክተታቸው እስከ ዛሬ ድረስ የሀገሪቱን ጉልበት ያላላና ታሪኳን ያጎበጠ ውጤት አምጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ በትምህርት ዝግጅትና ብቃት ብቻ ሳይሆን፣ ከምኒልክ ቀጥሎ ሀገሪቱ አሁን ያላትን ቅርጽ እንድትይዝ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ዋነኛውና በታሪካችን ውስጥ የግፍ ሥራ የተሠራባቸው፣ባጎረሱ የተነከሱ የሀገር ክብርና ጌጥ  ናቸው።
ከእርሳቸውም ሌላ ኢትዮጵያዊው አርበኛ ራስ መስፍን ስለሺ፣የመከላከያ ሚንስትሩ ሌተና ጀኔራል ከበደ ገብሬ፣ሌሎችም የሀገሪቱ ታላላቅ የጦር መኮንኖችና ምሁራን ያለ ፍርድ እጅ በማውጣት ሲገደሉ፣ሀገሪቱን ለውጭ ጠላት በሚያጋልጥ ሁኔታ በበርካታ ዐመታት ሥልጠናና ትምህርት የተገኙትን መኮንኖች አጥታለች። ይህ ሲደረግ፣በቀል እንጂ ነገ ሀገሪቱ ላይ ስለሚፈጥረው ክፍተት ያሰበም፣የተጨነቀም አልነበረሞ።
ነገሩ በዚህ ብቻ አላበቃም። ከራሱ ከደርጉ ውስጥ የተለየ አመለካከትና የፖለቲካ አቋም ያላቸው በሙሉ የጥይት ሲሳይ ከመሆን አላመለጡም። ቤተ መንግሥቱ የጦር ሜዳ እስኪመስል ድረስ ደም ፈሰሰበት። ፖለቲካው እየጦዘ መጥቶ ሀገሪቱ የሶሻሊስት ሥርዐተ ማኅበር ተከታይ መሆኗን በይፋ ካበሠረች  በኋላ ሌላ ጎራ ተፈጥሮ፣አሁንም ሌላ ፍጅት ብቅ አለ። በአዲሱ የአብዮት መንገድ ላይ ለየት ያለ አቋም የነበራቸው ሁሉ ተመንጥረው ሲያበቃ፣በሁለቱም ወገን እንደተለመደው ብዙ ሰዎች በጥይት ታጭደዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ሻለቃ አጥናፉ አባተ፣ብርጋዲየር ጀኔራል ተፈሪ በንቲና ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጀኔራል አማን አምዶም ይገኙበታል።
 ለማሳጠር ያህል ብለን ነው እንጂ ስማቸውን ብንዘረዝር ጭንቅላታችንን የሚያስይዘን አሳዛኝ ታሪክ ነው።
እንግዲህ ደርጉ ለአብዮታዊው ጉዞው የራሱን ቡድን አባላት ጨምሮ ብዙ ከሸኘ በኋላ እርሱም እረፍት አላገኘም። እረፍት ያጣውም በውጭ ጠላቶች ብቻ አልነበረም። በአብዛኛው ከራሱ ወገኖች ነበር።
 በሠፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርምና፣ ንጉሡን በተቸባቸው ነገሮች ተራውን መተቸቱ ብቻ ሳይሆን፣ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ የሀገር ልጆች መተናፈሻ አሳጡት። በዚህም መሐል መተላለቅ ሆነ፤ከሁለቱም ወገን የሀገር ጀግኖች እንደ ቅጠል ረገፉ። ለውጭ ጠላት ማስፈራሪያና ለወገን መከታ የሚሆኑ ጀግኖች በአማጺውና በመንግሥት ወገን ተቀጠፉ። እጅን በእጅ መብላት ከዚህ የተለየ ትርጉም ያለው አይመስለኝም። እርስ በርስ ተጫረስን።
 በኋላም አንደኛው ወገን አሸንፎ መንበረ ሥልጣኑን ያዘ። ከሥልጣን በኋላ ትንሽ ጋብ ያለ ቢመስልም፣የደርጉ ሰዎች በሠፈሩት ቁና ተሠፈሩ። ኢሕአዴግ ትንሽ ፋታ አግኝቶ ሲተነፍስ፣ሀገሪቱም ትንሽ ተንፍሳለች። በአንጻራዊነት ለተወሰኑ ዐመታት ሞት ጋብ አለ። ቀጣዩ እርስ በርስ መገዳደልና መጠፋፋት የመጣው በቅርብ ዐመታት ነበር። ይሁን እንጂ ከቀደሙት በከፋ መልኩ ተበላላን፤አሁንም እየተናከስን ነው።ይህ ደግሞ የኛ ቀለም ሆኖ እስኪታይ ድረስ በታሪካችን መዝገብ ላይ የሰፈረ አሳፋሪ ታሪክ ነው። በሚገርም ሁኔታ ዛሬም የዘፈን መሠንቋችንን አውርደን መቀኘት የምንችልበት ደረጃ ላይ ሳንሆን፣እርስ በርስ እየተቆሳሰልን  ሙሾ በየቤታችን እያሟሸን ነው። መሠንቋችንን ከተሰቀለበት ለማውረድ፣የተጨበጠ ነገር ባይኖርም በመስኮታችን በምትገባው ጨረር ትንሽ ተስፋ አለች።...መበላላት መቋጫ ይኖረው ይሆን?
***    
ከአዘጋጁ፡-
 ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡
 በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ  ለአንባቢያን አድርሷል፡፡



Read 565 times