Saturday, 16 March 2024 20:40

ቁጥራችን እየተተኮሰ ነው - (ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከዓለም 10ኛ አገር)

Written by  ዩሃስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

እንጀራችንስ እየሰፋ እየበረከተ ነው?
የእህል ምርት ምን ያህል ወረደ? ምን ያህል ተሻሻለ?


የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር፣ ዘንድሮ ከጃፓን በተጨማሪ ከሜክሲኮም በልጦ፣ ከዓለም ዐሥረኛ ደረጃ ላይ እንደሚቀመጥ የዩኤን መረጃዎች ይነግሩናል።
ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ፣ ከራሺያም አልፈን እንሄዳለን። ይሄ አስቀድሞ የታወቀና ያለቀለት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። ገና ያልታወቀው ጉዳይ፣ እህል ውኃችንስ፣ ኑሮና ሕይወታችንስ እንዴት ይሆናል የሚለው ጥያቄ ነው?ከዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን እንጀምራለን።የዛሬ ኀምሣ ዓመት በንጉሡ ላይ ዐመፅ ተነሥቶባቸው ደርግ ሥልጣን የያዘበትን ዘመን እንቃኛለን።
የኢሕአዴግ ሠላሳ ዓመታትንም በታሪክ ተመልሰን እንጓዛለን።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ አምስት ዓመታትንም እንደምራለን።ብዙ ዓመታትን ነው የምንመለከተው። ለካ፣ በረዥሙ ሲታይ አገሪቱ ሌላ ሆናለች።  በ1956 ዓ.ም የሕዝቡ ቁጥር 24 ሚሊዮን ነበረ። ዛሬ 130 ሚሊዮን? ከዓለም ዐሥረኛ? ታዲያ ከዚህ ጋር የእህል ውኃ ነገር እንዴት እየበረከተላት ይሆን ብለን መጠየቃችን የግድ ነው። እርሻውና የከብት እርባታው በዚሁ ረዥም ዘመን፣ ዕጥፍ ድርብ እየጨመረ ካልገሠገሠ፣ ያ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ ምን በልቶ ያድራል? እና ምን ትላላችሁ?
እንግዲህ፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዓመታዊ የእርሻና የእንስሳት እርባታ መረጃዎችን ለመቃኘት እንሞክራለን። የየዓመቱን እየለቀምን ለማስላትና ለማነጻጸር በጣም ከባድ ቢሆንብንም፣ ሌላ ምን አማራጭ አለ? በእርግጥ፣ ከስታትስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የምናገኛቸው ዓመታዊ የጥናት ሪፖርቶች፣ ቢበዛ የሠላሳ ዓመት ርቀት ቢያስኬዱን ነው።ተጨማሪ መረጃዎችን ከተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እናፈላልጋለን። የቀድሞ ዘመን መረጃዎችን እየመዘዝን እናመጣለን። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም፣ ዕድገትንና ውድቀትን ሁሉ ከዓመት ዓመት ለማሳየት የሚያገለግሉ ቁጥሮችን እንደ ሰንሰለት አያይዘን እናነጻጽራለን።
በዚህ መኻል፣ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከመስከረም እስከ ነሐሴ መሆኑ…
የበጀት ዓመት ደግሞ ከሐምሌ እስከ ሰኔ መዘርጋቱ…
የአውሮፓውያን አቆጣጠር በፊናው ከጥር እስከ ታሕሳስ መዞሩ…
የመረጃዎች አጠቃቀማችንን እንዳያምታታብን ማሰባችንና መጠንቀቃችን አልቀረም። ቢሆንም ግን ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም።  በእርግጥ፣… የመኸር አዝመራ፣ የበልግ እርሻ እያለ ለየብቻው እየተንጠባጠበ ሲመጣ መረጃዎቻችንን እንዳያዝረከርክብን ከተጠነቀቅን ነው ድምር ውጤቶችን ቀለል አድረገንና አሳጥረን ማቅረብ የምንችለው።
የዘንድሮው በልግ፣ ከሚቀጥለው ዓመት የክረምት አዝመራ ጋር ነው የሚቆጠረው ወይስ ከዘንድሮው? አሁን ደግሞ የበጋ የስንዴ እርሻ ተጨምሮበታል።
በዛሬ ቅኝታችን ከምናያቸው የቅርብ ዓመታት መረጃዎች ውስጥ፣ ጎላ ያለ የዕድገት ለውጥ የምናገኘው በስንዴ ምርት ላይ ነው። በሌሎች ላይ ግን ውጣውረድ እየተቀላቀለ፣ የአንዱ ዕድገት በሌላኛው ድክመት እየተጣፋ ሲያዘግም እናያለን። በእርግጥ፣ በግጭትና በጦርነት መኻል ኢኮኖሚው አለመፍረክረኩና የእርሻ ምርት አለመውረዱም ትልቅ ቁምነገር ነው። ግን ምን ዋጋ አለው? ኢኮኖሚው ባያሽቆለቁልም በፍጥነት አለማደጉ፣ ለኢትዮጵያ እጅግ ብርቱ ፈተና ነው። ከድኽነት ጥግ ያልተላቀቀ አገር፣ ከረሐብ አደጋ አጠገብ ያልራቀ ሕዝብ፣ ትንሽ እንቅፋት ይበቃዋል።
የዩኤን ተቋማትና ለጋሽ አገራት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ የሚያዘጋጁት ዓመታዊ የእርዳታ ጥሪ ማየት ትችላላችሁ። ዘንድሮ ከ14 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ባለፉት ሳምንታት የተሰራጨው የእርዳታ ጥሪ ይመሰክራል። ለእህል እርዳታ ብቻ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሏል። አስቸጋሪ ነው። ግን ከአምናው ይሻላል። አምና ከ20 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ነበር።
የዘንድሮው አዝመራ ከባለፈው የተሻለ ስለሆነ ነው የተረጂው ቁጥር የቀነሰው።
ጥቂት ነው ማለት ግን አይደለም። የእርሻ ውጤት እየጨመረ ቢሄድ እንኳ፣ ለረሐብ የሚጋለጡ በርካታ ሚሊዮን ሰዎች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። በድኽነት ውስጥ የተነከረ አገር፣ በቀላሉ ከረግረጉ አይወጣም። ከዚህ ጎን ለጎን የሕዝብ ብዛት በፍጥነት ሲገሠግሥ፣ እንዲህ ዐይነት አደጋዎች እየገዘፉ እንዳይሄዱ ያስፈራል። አያስፈራም?
የከፋ ድርቅ አይምጣ እንጂ፣ የረሐብ አደጋውስ ሲያስቡት ያንቀጠቅጣል። ሠላሳ ሚሊዮን ሰው ተርቦ፣ በቂ እርዳታ ከዓለም ዙሪያ እንደልብ ቢሰባሰብ እንኳ፣ በየትኛው የባሕር በርና በየትኛው ትራንስፖርት ይገባል? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህን ሥጋት ነበር “ከባሕር በር አስፈላጊነት” ጋር አያይዘው ያነሡት። ትክክለኛና አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ከሕዝብ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ሳይሆን፣ ዕጥፍ ድርብ የእህል ምርትና የእንስሳት እርባታ ማስፈለጉም፣ የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ ሁላችንም ልብ ብለን ብናስብበት ይሻላል።
የስድሳ ዓመታት መረጃዎችን ጠቅለል ጨመቅ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራሉ። አብረን የአገራችንንና የራሳችንን አዝማሚያ በቅጡ እንመልከት።
የዛሬ ስድሳ ዓመት፣ በ1955 ዓ.ም ግድም የእርሻ ምርት በየዓመቱ እያደገ እንደነበር የፋኦ መረጃዎች ያሳያሉ። ነገር ግን የሕዝብ ቁጥርም በዚያው ፍጥነት እየጨመረ ነበር። እናም “ለአንድ ሰው በአማካይ ስንት ይደርሰዋል?‹ ብለን ብናሰላው፣ ከዓመት ዓመት ብዙም የእህል ምርት ለውጥ አይታይም ነበር ማለት ይቻላል።
ግን በጣምም አታማርሩ፣ በደርግ ዘመን የባሰ ጉድ ይመጣል።
የእህል ምርት በኃይለሥላሴ ዘመን
በ1955 የአገሪቱ ጠቅላላ የበቆሎ ምርት፣ በአማካይ ለአንድ ሰው በዓመት 32 ኪሎ ይደርሰው እንደነበር የዘመኑ መረጃዎች ይነግሩናል። እስከ 1965 ዓ.ም ድረስም፣ የበቆሎ ምርት ከሕዝብ ቁጥር ጋር በእኩል ፍጥነት ነበር የሚያድገው። እናም አማካይ የአንድ ሰው ድርሻ፣ ብዙም አልተለወጠም።
የስንዴ ምርት በአማካይ ለአንድ ሰው 28 ወይም 29 ኪሎ ነበር።
ጤፍ ለአንድ ሰው በአማካይ ከ46 እስከ 51 ኪሎ የሚደርስ ምርት ይገኝ ነበር።
ማሽላ ከ30 እስከ 35 ኪሎ።
ገብስ ከ28 እስከ 33 ኪሎ።
ዳጉሳ ከ5 እስከ 6 ኪሎ።
እነዚሁ ናቸው ዋና ዋናዎቹ የእህል ምርቶች።
በአጠቃላይ ለአንድ ሰው በአማካይ ከ180 እስከ 190 ኪሎ የሚደርስ እህል በየዓመቱ ይመረት ነበር።
ይሄ፣ ከ1954 እስከ 1964 ዓ.ም ባሉት ዐሥር ዓመታት ነው።
በደርግ ዘመን የእህል ምርት ወደ ምድር?
በደርግ ዓመታት ውስጥ በበቆሎ ምርት ላይ ከታየው ዕድገት በስተቀር በሌሎቹ የእህል ምርቶች ላይ አሳዛኝ ውድቀት እንጂ የመሻሻል ምልክት አልታየም።
በቆሎ ለአንድ ሰው በአማካይ ከ30 እስከ 44 ኪሎ ድረስ የተመረተባቸው ዓመታት በርካታ ናቸው።
የስንዴ ምርት ግን፣ ከኃይለሥላሴ ዘመን ጋር ሲነጻጸር፣ በደርግ ዘመን የታየው ምርት ወደ ግማሽ የወረደ ነው። ለአንድ ሰው በአማካይ ከ28 ኪሎ በላይ ሲመረት እንዳልነበረ፣ ከ1967 በኋላ በነበሩት ዓመታት ወደ 18 ኪሎ ወርዷል። አንዳንዴም ወደ 15 ኪሎ። ለአንድ ሰው በአማካይ ከ40 እስከ 50 ኪሎ ጤፍ ሲመረት እንዳልነበረ፣ በደርግ ዘመን ወደ 30 ኪሎ ከዚያም ወደ 20 ኪሎ ሲወርድ ታይቷል።
ማሽላና ገብስም እንዲሁ፣ ከ30 እና ከ35 ኪሎ እያሽቆለቆለ ወደ 20 ወደ 25 ኪሎ ወርዷል።
በአጠቃላይ፣ ከ1967 ዓ.ም በኋላ ባሉት ዓመታት ጠቅላላ የእህል ምርት በአማካይ ለአንድ ሰው፣ ከ180 ኪሎ በላይ እንዳልነበረ፣ ወደ 130 ወደ 120 ኪሎ ቀንሷል። እንደዚያ ዐይነት ውድቀት በጭራሽ ታይቶ አይታወቅም።
ወደፊትም ተመልሶ የሚመጣ አይመስልም። ከመጣ ግን አገሪቱ በሰላም ትተርፍ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል። ከሕዝቡ ውስጥ ሩብ ያህል በረሐብ ከተያዘ ምን ማድረግ ይቻላል?
ለማንኛውም፣ ወደ ኢሕአዴግ ዘመን እንሻገርና በአጭሩ እንቃኘው።
በመጀመሪያዎቹ ዐሥር የኢሕአዴግ ዓመታት፣ ብዙም የዕድገት ለውጥ አልታየም።
የቀድሞውን የማሽቆልቆል ጉዞ መግታት ችሏል ካልተባለ በቀር፣ አማካይ የእህል ምርት በአንድ ሰው ሲሰላ ከ120 እስከ 130 ኪሎ ገደማ ነው የነበረው። ከደርግ ዘመን ጋር ይቀራረባል።
በ1997 ዓ.ም ግን በፍጥነት ማደግ ጀመረ። ወደ 160 ኪሎ ዐደገ። በ2002 ደግሞ 190 ኪሎ ደረሰ። በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን እንደነበረው ማለት ነው። ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ ለማደግ፣ ከ35 ዓመታት በላይ ፈጅቷል ማለት እንደሆነ አስቡት። የሆነ ሆኖ፣ በተለይ በበቆሎ፣ እንዲሁም፣ በስንዴ፣ በጤፍና በማሽላ ምርቶች ላይ ጥሩ ዕድገት ታይቷል።
ጠቅላላ የእህል ምርት በአማካይ ለአንድ ሰው ስናሰላው፣ እንዲህ ይመጣል።
በ2003 ዓ.ም    205 ኪሎ
በ2004 ዓ.ም    210 ኪሎ
በ2005 ዓ.ም    215 ኪሎ
በ2006 ዓ.ም    230 ኪሎ
በ2007 ዓ.ም    243 ኪሎ
በ2008 ዓ.ም    252 ኪሎ
በ2009 ዓ.ም    250 ኪሎ

ከኢሕአዴግ በኋላ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ስንሸጋገርስ ምን እናገኛለን።
ጠቅላላ የእህል ምርት በአማካይ ለአንድ ሰው ሲሰላ ስንት ኪሎ ሆነ?
    የእህል ምርት በኪሎ (በአማካይ ለአንድ ሰው)
2010    266
2011    255
2012    260
2013    258
2014    254
2015    256

 
የለውጥ ጊዜ በብዙ ውጥንቅጥ የተሞላ ቢሆንም፣  በርካታ ግጭቶችና ጦርነቶች ቢከሰቱም፣ የእህል ምርት ብዙ አለማሽቆልቆሉ “ተመስጌን” ነው። የመጀመሪያ የለውጥ ዓመታት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆኑ ከታሪካችን አላያችሁም?
እንዲያም ሆኖ ግን፣ “አላሽቆለቆለም” ብለን እንዝናና ማለት አይደለም። ዕልል እንበል አያሠኝም። ከሕዝብ ቁጥር ዕድገት የላቀ ፈጣን የእህል ምርት ዕድገት አልታየም። ይሄ በጊዜ ካልተሻሻለ አሳሳቢ ነው።
በእርግጥ፣ በስንዴ ምርት ላይ፣ ፈጣን ለውጥ እንደታየ የፋኦ መረጃ ያሳያል።
ለአንድ ሰው በአማካይ ከ40 እስከ 45 ኪሎ ድረስ ነበር የሚመረተው። ባለፉት ዓመታት የስንዴ ምርት፣ በአማካይ ከ46 ተነስቶ እየጨመረ በ2015 ዓ.ም ወደ 56 ኪሎ ደርሷል። ጥሩ ነው። በስንዴም ሆነ በሌሎቹ የእህል ምርቶች ላይ ፈጣን ዕድገት ያስፈልጋል።
የእንስሳት እርባታና የሥጋ ውጤቶችስ?
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን    ከ1954-64
በአማካይ
ለአንድ ሰው    ከ14 እስከ 18
ኪሎ ሥጋ በዓመት
በደርጉ ዘመን    ከ1970-80
በአማካይ
ለአንድ ሰው    ከ13 እስከ
 18 ኪሎ ሥጋ
በዓመት
በኢሕአዴግ እና በብልጽግና ዘመን    ከ1983-2015
በአማካይ
 ለአንድ ሰው    ከ6 እስከ 8
 ኪሎ ሥጋ በዓመት

የሥጋ ምግብ በጭራሽ ማንሰራራት የሚችል አይመስልም። በኃይለሥላሴ ዘመን ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ በግማሽ ቀንሷል።
ኢሕአዴግ በጭራሽ አልሆነለትም። አሁን ላለው መንግሥትም ትልቅ ፈተና ነው። የእንስሳት እርባታን ማሻሻልና የሥጋ ውጤቶችን በፍጥነት ማሳደግ ይቅርና፣ በትንሽ በትንሹስ ፎቀቅ ማድረግ ይቻላል ወይ? ከባድ ጥያቄ ነው።
 እስካሁን ላለፉት 50 ዓመታት ሲያሽቆለቁል እንጂ ሲሻሻል አልታየም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ማሻሻል ይቻላል እያሉ ነው። ይቅናቸው። ቢሳካ ነው ለሁላችንም የሚበጀው።

Read 700 times