Saturday, 16 March 2024 20:53

ፕላን በማድረግ ሴት ወይንም ወንድ መርጦ መጸነስ ይቻላልን ?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

በርእሱ የተጠቀሰውንና የጽንስን እድገት በሚመለከት ማብራሪያ የሚሰጡን ዶ/ር እዮብ አስናቀ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚሰሩትም በአበበች ጎበና የእናቶችና የህጻናት ሕክምና ማእከል ውስጥ ነው፡፡
ዶ/ር እዮብ ጽንስና ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ሲገልጹት አንዲት ሴት ስትፈጠር በእናትዋ ማህጸን ውስጥ እያለች ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን ይዛ ነው የምትወለደው፡፡ ወደ ጉርምስና እድሜ ሲጠጉ ከእነዚያ ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን ከሚጠጉ እንቁላሎች ውስጥ ወደ አራት መቶ ሺህ ይቀራሉ፡፡ እነዚያን አራት መቶ ሺህ እንቁላሎች በመውለጃ እድሜዋ ውስጥ ትጠቀ ማለች፡፡ በአማካይ በየወሩም ወደ አራት መቶ የሚሆኑ እንቁላሎችን ስለምትለቅ በዚህ ጊዜም እርግዝና ሊፈጠር የሚችልበትን ወቅት ይሆናል ማለት ነው፡፡  የወንድ ልጅን ከዚህ ጋር እናነጻጽር የዘር ፍሬው ከጉርምስና እድሜው ጀምሮ እየተፈጠረ የሚሄድ ነው፡፡ ስለዚህም ጽንስ ተፈጠረ የሚባለው የወንዱና የሴቷ የዘር ፍሬና እንቁላል በማህጸን ቱቦ ውስጥ ሲገናኝ መሆኑ ግልጽ ነው ብለዋል ዶ/ር እዮብ፡፡
ጾታ የሚወሰነው የጽንሰቱ ቀን ነው ብለዋል ዶ/ር፡፡ የሴት እንቁላል የያዘው XX ክሮሞዞም ሲሆን የወንድ የዘር ፍሬ ደግሞ XY ክሮሞዞም ነው፡፡ ስለዚህ ሴት የምታዋጣው X ክሮሞዞም ሲሆን ወንድ ደግሞ X ወይንም Y ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ወንዱ ያዋጣው X ከሆነ ከሴትዋ ጋር ሲዳመር XX ስለሚሆን የሚጸነሰው ሴት ሲሆን ወንዱ ያዋጣው ክሮሞዞም Y ከሆነ ግን X Y ስለሚሆን የሚጸነሰው ወንድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የተጸነሰው ወንድም ይሁን ሴት መለየት የሚቻለው ግን ከአራት እስከ ሰባት ሳምንት ድረስ ባለው ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በሚደረገው ምርመራ መለየት አይቻልም፡፡
ዶ/ር እዮብ እንዳብራሩት ጽንሱ ወንድ የሚሆን ከሆነ ከ Y ክሮሞዞም ላይ  Sex determining region of the Y chromosome (SRY) የሚባል ነገር አለ፡፡ ያ SRY Testis determining facter ያመነጫል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ሂደት ወንድ ሆኖ የመፈጠርን ሂደት የሚወስን ነው፡፡ ከዚያም (Testosterone)  የወንድ ሆርሞኖች ይመነጫሉ፡፡ ከዚያም በሁዋላ የተጸነሰው ወንድ ይሁን ሴት ይለያል፡፡  ሌላው ደግሞ የሴትን የመራቢያ አካል እድገት የሚገታ ኬሚካል የሚያመነጭ ተፈጥሮአዊ ሂደትም አለ፡፡ የእነዚህ ተፈጥሮአዊ ሂደቶች አለመኖር ግን ጽንሱ ሴት እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሴትን ሴት ሆና እንድትፈጠር የሚያደርጋት ወንዶች እንዲፈጠሩ የሚያስችለው የኬሚካል ወይንም (SRY) እንደሚባለው ተፈጥሮአዊ ሂደት ስለሌለ ነው፡፡ ወንድ ለመሆን እንጂ ሴት ለመሆን የተለየ ሆርሞን አያስፈልግም፡፡የወንድ ሆርሞን አለመኖር ብቻ ነው ሴት ልጅ እንድትፈጠር የሚያደርጋት፡፡
ዶ/ር እዮብ እንደሚሉት ሴት ወይንም ወንድ የፈለግሁትን መርጬ መጸነስ ወይንም መው ለድ እችላለሁ የሚል አባባል እንዲሁ ይሰነዘራል እንጂ በሳይንሱ ምንም የተደገፈ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በካላንደር በመደገፍ ወንድ ልጅ ለመውለድ ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን ወይንም ሴትን ልጅ ለመውለድ ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን ድረስ በማለት ወሲብ የሚፈጽሙ አሉ፡፡ ይህ ግን በሳይንስ ምንም አይነት ድጋፍ የሌለው ሲሆን እንዳጋጣሚ ያሰቡት ነገር ቢሳካላቸው እንኩዋን በትክክል እነሱ አቅደው ባደረጉት ነገር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን እን ደማንኛውም ተፈጥሮአው ሂደት ጽንሱ በሚፈጠርበት ወቅት ባለው ተፈጥሮአዊ ሂደት የሚወሰን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጊዜ ሴት እወልዳለሁ ወይንም ወንድ እወልዳለሁ የሚባለው ምኞት በየማህበራዊ ሚድያው ላይ እንደሚየው ሳይሆን በተረጋገጠው ሳይንስ የማይደገፍ እና ምንም አይነት ማረጋገጫ የሌለው ነው፡፡
ጽንሱ ከተፈጠረ ጀምሮ የእድገት ጊዜው ከመቼ እስከመቼ የትኛው አካል ይፈጠራል ብለን ብናስብ የምናገኘው መልስ እንከሚከተለው ነው፡፡
ጽንሽ ከተጸነሰ ጀምሮ ስምንተኛው ሳምንት ካለቀ ጀምሮ በተወሰነ መልኩ የሰው ቅርጽ ይኖ ረዋል፡፡ ሶስት ነገሮች አሉ፡፡ እርሱም ክቶደርም፤ሜዞደርም፤ኤንዶደርም የሚባሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ይፈጠራሉ፡፡
ከኤክቶደርም ጸጉር ፤ጥፍር፤የነርቭ እስትራክቸሮች የመሳሰሉት ይፈጠራሉ፡፡
ከሜዞደርም ልብ፤የደም ስሮች፤አንጀት ፤ጉበት የመሳሰሉት ይፈጠራሉ፡፡
ከኤንዶደርምም የመፈጠሩ የሰውነት ክፍሎ አሉ፡፡
ጽንሱ ከተፈጠረ ስምንተኛው ሳምንት እንዳለፈ በአብዛኛው እንዲያውም ሁሉም የሰውነት ክፍሎች ተሰርተዋል ማለት ነው፡፡ ከመላው የሰውነት ክፍል በተለየ እስከመጨረሻው ማለትም እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ እያደገ የሚሄደው አእምሮ ወይንም አንጎል ነው፡፡ በተረፈ ሌሎቹ የሰውነት አካላት የመጠን መጨመር እና የተግባር መጎልበት ካልሆነ በስተቀር በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ተፈጥረው ያልቃሉ፡፡  ጽንሱ ከተፈጠረ ከሶስት እስከ ስምንት ሳምንት ድረስ አካሉ የሚፈጠርበት ወቅት በመሆኑም በተቻለ መጠን እርጉዝዋ ሴት ምንም አይነት መድሀኒት እንዳትወስድ ይደረጋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ጽንሱ ገና አካሉ በመፈጠር ላይ ስለሆነ ምንም አይነት እክል እንዳይገጥመው ሲባል ነው፡፡ አልፎ አልፎ የሚታዩ የአፈ ጣጠር ችግሮች ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የሚወሰዱ መድሀኒቶች ውጤት ሊሆን እንደ ሚችልም ይገመታል፡፡  
ሌላው ዶ/ር እዮብ አስናቀ እንዲያብራሩ የተጠየቁት ጥያቄ በማህጸን ውስጥ ያለ ጽንስን ባህርይ የሚመለከት ነው፡፡ ጽንሱ ከመወለዱ በፊት አንዳድ ድምጾችን ይሰማል ወይንም ይለያል ይባላል ምን ያህል እውነት ነው ስንላቸው የእሳቸውም መልስ ትክክል ነው የሚል ነበር፡፡  እንደሚከተለውም አብራርተውታል፡፡
ጽንስ ከተጸነሰ ከአራት ወር ጀምሮ በስሱም ቢሆን ለድምጽ ምላሽ የመስጠት ነገር አለው፡፡ ነገር ግን፡-
ጽንሱ ከተጸነሰ ከአስራ ስድስተኛው ሳምንት ወይንም ከአራት ወር ጀምሮ በማህጸን ውስጥ እያለ ለሚሰማው ድምጽ ምላሽ ይሰጣል ይባላል፡፡
ጽንሱ ከተጸነሰ ከ24 ሳምንት ወይንም ከስድስት ወር ጀምሮ ድምጽ ወደሰማበት አቅጣጫ የመዞር ባህርይን ያመጣል፡፡
ጽንሱ ድምጽ በሚሰማበት ጊዜ የልብ ምቱ የመጨመር ፤ወደ ድምጹ ዞር የማለት ነገር እንዲሁም እንቅስቃሴም የመጨመር ነገር መኖሩን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡
በእርግጥ በውጭ የሚሰማውን ድምጽ እንዳለ ሙሉ በሙሉ ጽንሱ አይሰማውም፡፡ ምክንያ ቱም የእናትየው የሆድ ሽፋን አለ፡፡ እንዲሁም ማህጸን ከዚያም የሽርት ውሀ ጭምር ጽንሱን ስለሚሸፍኑት ሊሰማ የሚችለው በዝቅተኛ ደረጃ  በማህጸን ውስጥ እያለ ሊሰማ የሚችለው ለስላሳ ሙዚቃዎችን ነው፡ በጣም ከፍ ያለ ድምጽ በጽንሱ የአእምሮ እድገት ላይ ተጽእኖ ሊያመጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን ጽንሱ በማህጸን ውስጥ እያለ ከ29 ነኛው ሳምንት ጀምሮ ትልቅ ሰው የሚሰማውን ድምጽ መስማት ይጀምራል፡፡        
ወላጆች በተለይም እናቶች ምንም እንኩዋን የሚናገሩትን ነገር በትክክል ይረዳል ብለው ባያስቡም ነገር ግን ጽንሱ በማህጸናቸው ውስጥ እያለ ያነጋግሩታል፡፡ እንደምን አደርክ፤ አይዞሽ፤አሁን እንተኛ፤አሁን እንብላ፤ወደፊት ጥሩ ሕይወት ይኖረናል፤ ካንቺ በላይ የም ወደው ነገር የለኝም፤የወደፊት ተስፋዬ ነህ…..ወዘተ የጽንሱን ምንነት ካወቁ በሁዋላ በየ ፈርጁ ለወንዱም ለሴትዋም የሚፈልጉትን፤የሚመኙትን፤የሚጠብቁትን ነገር ሁሉ ያወ ራሉ፡፡ ጽንሱ በማጸን ውስጥ እያለ በተለይም የእናቶችን ድምጽ ሊለይ በሚችልበት ደረጃ የሚያደምጥ እና ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን ከዚያ በተጨማሪም ሁልጊዜ በቅርበት የሚገኘውን የአባትየውን ድምጽ ጭምር ያውቃል፡፡ የእናቱን ድምጽ በሚመለከት በተለየ ሁኔታ እንዲያውቅ የሚረዳው እናትየው በምታወራበት ጊዜ በድምጽ ቧንቧ በኩል የሚኖረው እርግብግቢት ወደልጁም ስለሚደርስ ያንን ድምጽ ለማዳመጥ ቀላል ስለሚልለት ከሁሉም በላይ ለእናቱ ድምጽ ቀረቤታ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህም በሚወለድበት ጊዜ የእናቱን ድምጽ ከማንም በላይ ያውቀዋል፡፡ ህጻናቱ ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ በመጀመሪያ ደረጃ በማህጸን ውስጥ እያለ ይሰማው ለነበረው የእናቱ ድምጽ ቀረቤታ ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም እናቱን ሲሰማ የመረጋጋት ነገር ይኖረዋል፡፡
አልፎ አልፎ የተለየ ምልክት በሰውታቸው ላይ ይዘው የሚወለዱ ልጆች አሉ፡፡ እሱም በአገራችን በተለምዶ ሽታ እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህም እናትየው እርጉዝ እያለች አንዳንድ የምግብ አይነቶች ሲሸቷት በአጋጣሚ ከምትነካው የሰውነት ክፍልዋ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የጽንሱ የሰውነት ክፍል ላይ የሚወጣ ምልክት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ እትየው በምትናደድት ወቅት የምትነካው የሰውነት ክፍል ጋር ተመሳሳይ በሆነው የጽንስ የሰውነት ክፍል ላይ የሚታይ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ይህ በሳይንሱ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል ዶ/ር አዮብ፡፡ በተለምዶ ሽታ የሚባለው ምልክት በጥቁር መልክ ወይንም በቀይ መልክ በልጁ ቆዳ ላይ የሚታይ ምልክት ነው፡፡ ይህም ከሽታ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ቆዳን ጥቁር የሚያደርጉ ሴሎች አንድ ቦታ ብዝት ብለው ሲፈጠሩ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ በተጨማሪም የደም ስሮቹ ለየት ያለ አፈጣጠር በሚኖርት ጊዜ ቀላ ያለ ምልክት ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ምልክት ከአምስት ቦታ በላይ በሚወጣበት ጊዘ ከነርቭ ጋር የተያያዘ ችግር ሊኖረው ይችላል፡፡ ስለዚህ ከምግብ አምሮት ወይንም ከብስጭት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከአፈጣጠር ጋር የሚገናኝ ነው ብለዋል ዶ/ር እዮብ አስናቀ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡

Read 559 times