መስከንተሪያ፡-
አጭር ልብ-ወለድ ከዕድሜው አንጻር አጭር፣ ከቃላት አጠቃቀሙ ረገድ ቁጥብ፣ በሕዋ ጊዜ ዑደት/space time continuum በኩል የተፋጠነ ነው፤ ከገጸ-ባሕሪይው ይልቅ ለክስተቶቹ/incidents ትኩረት ይሰጥና ሰፊ የፈጠራ ዕድልንና ምናባዊነትን ለደራሲው ያመቻቻል፤ ከዘውግ ይልቅ ገጸ-ሰብ ፈጥረው የመተረክ ምቾት እዚህ አጭር ልብወለድ ውስጥ መሆኑ ዕሙን ነው።
በውል እንደምናውቀው፣ ለደራሲው የፈጠራ ችሎታ ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል፤ በይነ-ዲስፒሊን፣ ሙክርታ/experiment፣ ተውላጠ-ታሪክ፣ የገለጻ ቁጥብነት፣ ፍካሬ፣ ሜቶሎጂ፣ ተውላጠ-ተረት፣ ኤግዚስቴንዣሊዝም፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ቃል፣ ሥነ-ውበት፣ ምናባዊነት፣ ሮማንቲዚም፣ ፋንታሲ እና የትረካ ቴክኒኮች በአጭር ልብ-ወለድ ይቦርቃሉ።
እንዲህ ይሁን…
…አጭር ልብ-ወለድን ዶሮ ወጥ ነው ብለን እንውሰድ፤ አጎራባች ዲሲፒሊኖችን ደግሞ ቅመማ-ቅመም/ንጥረነገሮች ናቸውና ያጣፍጡታል እንበል፤ የዶሮ ሥጋ ብቻውን የዶሮ ወጥ አይሆንምና፣ ታሪክ ለብቻው ዋጋ ቢስ ሊሆን ይችላል እንደማለት ነው። የደራሲው የማሰላሰልና የንባብ ክምችት ወደ ልብ-ወለድነት የሚዘዋወርበት ሂደት ነው አጭር ልብ-ወለድ፤…
…ወደ አሁኔ ልስከንተር…
…ደራሲ ተስፋአብ ተሾመ ‹‹ነገን ፍለጋ›› ብሎ በሰየመው ድርሰት ውስጥ ደራሲው ነገን ይኩላል፤ ነገዎች በዕልፍ ጉድባዎች ውስጥ ተወሽቀዋል እዚህ ድርሰት ውስጥ፤ ተስፈኛ ነገ አለ፤ አስፈሪ ነገም እንዲሁ፤ ወላ አዝናኝ ነገ፤ አስተካዥ እና አስጨባጭ ነገዎች በእየፈርጁ ተተርከዋል። ደራሲው በማሕበራዊ የአኗኗር ይትባሃላችን፣ በአንትሮፖሎጂ፣ በምጣኔ-ሀብት፣ በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ እና በተለያዩ ጉዳዮች ነገአችንን ያስቃኘናል፤ ለምናባዊነቱ ለከት አበጅቶ ሲያበቃ፣ ማሕበረ-ባሕል ውስጥ ተዟዙሮ የእያንዳንዳችንን ቤት ዳስሷል።
ደራሲው ከሚብከነከንባቸው ጉዳዮች አንዱ የኤግዚስቴንሺያል ጥያቄ ነው፤ ፍትሕን መናፈቅ፣ ኑረት፣ ወጥነት እና ሌሎች መጠይቆችና ሙግቶች የገጸ-ባሕሪውን አሁናዊ ሁናቴ ማዕከል በማድረግ ተተርከዋል።
ለምሳሌ ‹‹ቅያሜ›› በተሰኘ ታሪክ ሥር ‹‹ታሪኩ›› የተባለ ገጸ-ባሕሪይ ከተሰነቀረበት የሕይወት ጉድባ እና መንገሽገሽ አንጻር ረጅም ዕድሜ ስጠኝ ሳይሆን ረጅም ዕድሜ ለምን ሰጠኼኝ? በማለት ከፈጣሪው ጋር አታካራ ይገጥማል፤ (ገጽ 5)፤ ከዚህ በዘለለ ከእያንዳንዱ ጎጆ ሥር የሚርመሰመሰው ባተሌ ሕይወት ተቃኝቷል፤ ኑሮን የሚኖሩ ሳይሆኑ ኑሮ የሚኖራቸው ምንዱባኖች የድርሰቱ አካል ሆነው ቀርበዋል።
ሥነ-ውበት ሌላው ጉዳይ ነው፤ ፍካሬ፣ ማስረግ፣ ዘይቤ እና ማነጻጸር በመጠኑም ቢሆን ተንጸባርቀዋል፤ ‹‹ቢላል ለምን ሞተ?›› (ገጽ 31)፣ ‹‹ይህ መንደር በአምላክ ለመረሳት ዓይነተኛ ተምሳሌት ነው›› (ገጽ 203)፣ ‹‹እንጀራ ጋጋሪዋ እንጀራ ጠግባ በልታ አታውቅም፤›› 207፤ ‹‹ሰቆቃ ቀንን ዘልዛላ ያደርጋል፤ ሕይወት ምሬት ሲጫናት የሰዓት አጋማሽ ከአእላፍ ቀናት ይልቅ ይረዝማል፤›› ገጽ 31 እና ሌሎችም ገለጻዎች አንጻራዊነትን ለመተንተን የተጠቀመባቸው ማባያዎች ናቸው።
የኅዋ ጊዜ ዑደትን በተመለከተ አጭር ልብወለድ ከባሕሪው አንጻር፣ ከዕድሜው አንጻር የተካለበ ነው፤ ሕዋ ላይ አይንገዋለልም፤ መቀላጠፍ፣ መፍጠን፣ መስከንተር መገለጫው ነው፤ ዋና ዋና የክስተት አካላትን ነግሮን ያከትማል እንጂ አይዘበዝብም፤ ታዲያ ገጸ-ባሕሪው በመሃል ጣልቃ እየገባ ግብረ መልስ እንዲሰጥ ይደረጋል።
ለምሳሌ ‹‹ቢላል ለምን ሞተ?›› በሚል ታሪክ ገላ ‹‹ቢላል ራሱን አጠፋ›› ካለን በኋላ ዲና መልከመልካሟ፣ ትንሿ አበባ፣ ፍልቅልቋ ኮከብ ከፍ ባለ ድምጽ አለቀሰች፤ ይህ ከሆነ ሳምንት አለፈ፤›› በማለት ተርኮልን ሲበቃ ስለ ቢላል ይነግረናል፤ በመሃል የተቆረጠ የሚመስል ታሪክ ያለ ቢመስልም ተደራሲው የመሙላት ግዴታውን እንዲወጣ ትቶለታል።
ጀስታፖዚንግ የዚህ ድርሰት አንድ ሙክርታ ነው፤ ስለ አንድ ጉዳይ እየነገረን በመሃል ሌላ ተያያዥ ታሪክ ያስገባብናል፤ ስለ አይሻ መጎሳቆል ካስተዋወቀን በኋላ ወረድ ብሎ ምክንያቱን ይነግረናል፤ ከዚያ እናያይዘዋለን፤ መልሶ የአይሻን ነገር ያትታል (ገጽ 31)፤ ሆኖም ሃቲቱ ዋናውን ታሪክ የሚረብሽ አይደለም።
ኒዎ ሂስቶሪሲዝምን አስቃኝቶናል ደራሲው፤ ታሪክ ትልቅም ትንሽም የለውም ብሎ ያምናል ይኼ መስክ፤ ‹‹ትልቁም›› ‹‹ትንሹም›› የማሕረሰብ ክፍል የእራሱ የሆነ ታሪክ አለው፤ ብሎም የእራሱ የሆነ አገራዊና ማሕበረሰባዊ አስተዋእጾ አለው ተብሎ ይታመናል፤ በእነ ሚሼል ፉኮ በኩል፤ ሕጻናትን፣ ሴቶችን፣ የተገለሉ የማሕረሰብ ክፍሎችን፣ የቤት ሰራተኛን፣ ጥበቃን…ወዘተ. የታሪክ አንድ አካል ማድረግ እና ማሳተፍ ነው ቁምነገሩ፤ በመሆኑም ደራሲ ለተገፉ ሞጋች ሆኖ ይቀርባል።
ለአብነት በወላይታ ሕዝቦች ረገድ ‹‹አይሌ›› ስለተባለ ማሕበረሰብ ያወጋናል፤ ባሪያ የተባለ ማሕበረሰብ ነው በድርሰቱ እንደተረዳን፤ ዘለስ ይልና፣ ‹‹ጪነሻ/ፉጋ›› ስለተባሉትና ስለተገፉት የዕድ ጥበብ ባለሙያዎች ይሞግታል፤ በተጨማሪ፣ ደጌላ ስለተባለ ጎሳም ያወሳናል፤ ፋቂ የተባሉ ናቸው፤ የሚገርመው ነገር፣ ሁለቱ የተገፉ ቡድኖች መልሰው ይገፋፋሉ!
በብሔርተኝነት ቦታ ባሕል (ብሔርተኝነት በካልቸሪዝም) እየተተካ እንደሆነ ስጋት ገብቶታል ደራሲው፤ ተራኪዋ ደግሞ ሴት ጋዜጠኛ ናት፤ አንትሮፖሎጂካል አስፔክትን በተመለከተ ‹‹ቦታ ጎዳው›› - አባ ነጮ፤ የነጩ ጌታ ማለት ነው ብሎናል፤ ከፈረስ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ያመላክታል፤ ጉዳዩ ለክብር እንደሚያበቃ መገንዘብ ይቻላል። ተውላጠ ታሪክ በገጽ 80 ላይ ተካቷል፤ ‹‹ዝናው›› የተባለ ገጸ-ሰብ ከመንግስታቱ ድርጅት ደብዳቤ ይደርሰዋል፤ ጓደኛውን ላከበት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት - ምን ብለው? ዝናው የሚያጤሰው ትንባኾ የዐየር ንብረቱን በርዟልና በአፋጣኝ ከድርጊቱ እንዲታቀብ፣ ካልሆነ ካሳ እንዲከፍል/ማዕቀብ ሊጣልበት እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ፤ ምን ያህል ተግቶ አጪያሽ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፤ ጉዳዩ በግለሰብ ደረጃ ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለአንድ አጪያሽ ነው የጣፈው፤ ዝናውም የዋዛ አይደለም ለዓለም ባንክ በግሰብ ደረጃ የብድር ደብዳቤ ይተይባል። ጉዳይን ለማጠንከር ይኼ ሙከራ ጠቃሚ ነውና ደራሲው በቀጣይ ሥራዎቹ አጠንክሮ ይቀጥል ባይ ነኝ።
ደንቃይ አጨራረስ/ሰርፕራይዝ ኢንዲንግ አንዱ ሙከራ ነው፤ ዝናው ለጥፋቱ ተጸጽቶ እያለቀሰ ወላ ይቅርታ ይጠይቃል ብለን ስንጠባበቅ፡-‹‹አረንጓዴ ተክሎች የሚጠፉ ከሆነ ጫትም ይጠፋል ማለት ነው?›› ብሎ ይጠይቃል።
ግሳጼም አለው ድርሰቱ፤ በፖለቲካ የተነጠቀና የተጠለፈ ታሪካችን ምን ያህል የመሰናከያ ጉድባ እንደሆነብን ይተርክልናል፤ ሆኖም ደራሲው ትረካውን ለገጸ-ሰቡ መተው ሲችል ሀቲቱን ራሱ ይዞ ቀርቧል፤ ጫና የማሳደር መልክ አለው፤ ማብራሪዎያችና ገለጻዎች ትረካውን ይረብሻሉ፤ ደራሲው ከሚያትት ገጸ-ሰቡ በቁጭት እየተግለበለበ ቢነግረን መልካም ነው፤ ነጻ ይሆናል፤ ለዚህም ‹‹ታሪክ ወለድ›› የሚል ጽሑፍ ማሳያ ነው።
ተስፋአብ ነገረ-ደራሲ እና ትርጉም ይገደዋል፤ ትርጉም፣ ደራሲ፣ መልክ ማስያዝ፣ መግባባትን መፍጠር፣ መስከንተሪያ መሆን፣ ትርጉም ማበጀት…ያሳስበዋል፤ ገጽ 169 ላይ ማሳያ አለላችሁ። ትርጉምና ሚዛን ሊያበጅ ይውተረተራል።
ከዚህ በተጻራሪ፣ ደራሲው የራሱን ሀሳብ ለመጫን ብዙ ርቀት መጓዝ አልነበረበትም፤ አንዳንዶቹ ታሪኮች ሌጣ ዘገባን ይዘው የቀረቡ ሲሆን፣ በቀጣይ አጎራባች መስኮች፣ ሥነ-ውበት፣ ቋንቋ፣ የተለያዩ የአተራረክ ይትባሃሎች ትኩረት ቢደረግባቸው እላለሁ።
ከዚህ በዘለለ፣ ደራሲው ተስፋ-ቢስ ሮማንቲስምነትን/hopeless romantism የሚያንጸባርቁ ዕልፍ ታሪኮችን ይዞልን ቀርቧል፤ አብዛኞቹ ታሪኮች የቀረቡበት አኳኋን ደግሞ ዋናው ታሪክ ላይ በራዥና በካይ ሃቲቶችን በመጨመር ነው፤ በመሆኑም፣ ትረካውን የሚረብሹና የሚጎረብጡ ሆነውብኛል፤ በአጭሩ ከምናባዊነት ይልቅ የደራሲው ማብራሪያዎች፣ ጭንቀቶች፣ የግል ሀሳቦቹ፣ ምኞቱና ሌሎች ጉዳዮች ድርሰቱን ጨቁነውታል ብዬ አምናለሁ።
የምንፈልገውን ነገ ልናገኝም ላናገኝም እንችላለን፤ ነገር ግን ደራሲ ከተነሳበት ታሪክ ጋር መቃረን የለበትም ባይ ነኝ፤ በመጀመሪያው ታሪክ ድርሰቱ አውቶቡስ፣ ደራሲው ደግሞ ዘዋሪ፣ አንባቢ ተሳፋሪ ሆነና፤ ዘዋሪው መኪናውን እያምዘገዘገ መሃል ደርሶ አንባቢን ለምንም ይተውና ይወርዳል፤ ከትልማችን ያናጠበበት አግባብ ተገቢ አይደለም።
በአጠቃላይ፣ ነገዎች በብዙ መልኩ ተዳስሰዋል፤ የብዙዎቹ ነገ ብሩህ ነው፤ የብዙዎቹ ደግሞ ጽልመት የወረሰው፤ የፈለጉት ነገ እንደጠበቁት ላይሆን የሆነባቸው ዕልፍ ናቸው፤ ሆኖም ደራሲው የራሱን ሀሳብ ጭኖብናል፤ በቀጣይ ሥራዎቹ ለበይነ-ዲስፒሊን፣ ለሙክርታ፣ ለቴክኒኮች፣ ለእንግዳ ክስተቶችና ገጸ-ባሕሪዎች፣ ለቋንቋ መርማሪነት…ትኩረት ይስጥ እላለሁ፤
ሥነ-ጽሑፋችንን እንደ ኹዳዴ በግ ጠሐይ የከካው የሚገራና የሚቆጭ በመመናመኑ እንደሆነ መናዘዝ አለብኝ፤ ሥነ-ጽሑፋችን የደነበሸው ሐያሲያን በእየስርቻው በመደበቃቸው ነው፤ እናም ባለሙያዎች ሰንዳ ሰንዳ ብላችሁ አደባባይ ዋሉ፤ ሥነ-ጽሑፍን አንገዋልሉ፤ ያልተሟሸ ጀበና አያጣፍጥምና፣ ኪነ-ጥበብና ጣዕም እንዳይናጠቡ የአቅማችሁን ያህል ትቡ።
* * *
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡
እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።