Sunday, 17 March 2024 20:07

ስለ ትናንሽ አለላዎች፡ የሐበሻ ስንክሳር

Written by  መኮንን ደፍሮ-
Rate this item
(3 votes)

--ዮናስ እንደሚነግረን፣ ሐበሻ በአፉ በታሪኩና አባቶቹ ባጎናፀፉት ነፃነቱ የሚኮራ መሆኑን የሚደሰኩር፤ በገሀድ ግን ኅሊናዉ በፈረንጅ ባሕል ቅኝ የተገዛ ሎሌ ነዉ፡፡ ሐበሻ ድህነቱን ከአድማስ ማዶ ተሰዶ ሊያራግፍ የሚመኝ፣ በአፉ አገሬን እወዳለሁ የሚል፣ በገሀድ ግን እትብቱ የተቀበረበትን አፈር ሽሽት የባሕር ሲሳይ መሆንን የሚመርጥ የሩቅ አገር ናፋቂ ነዉ፡፡ ሐበሻ በድንቁርናዉ ሰበብ የሌላዉ ዓለም ህዝብ ጅራት የሆነ ህዝብ ነዉ፡፡ ድንቁርና ዮናስ ያክላል፣ የብሔራዊ ቁርቁዝናችን (poverty) እና ክሽፈታችን (collapse) ዋናዉ ምክንያት ነዉ፡፡--“

መግቢያ
ስለ ትናንሽ አለላዎች (2011) በዮናስ አድማዉ የተጻፈ ረጅም ልብ ወለድ ነዉ፡፡ ይህ የልብ ወለድ ድርሰት
በአማርኛ ቋንቋ ከተጻፉ በጣት ከሚቆጠሩ ሸጋ የልብ ወለድ ሥራዎች መካከል አንዱ ነዉ፡፡ ዮናስ በቋንቋ መራቀቅን የተካነ፣ በልብ ወለድ የሚፈላሰፍ በሳል ደራሲ ነዉ፡፡ በእዚህም ምክንያት ነዉ ስለ ትናንሽ
አለላዎችን ጠጠር ያሉ ፍልስፍናዎች የተፈከሩበት ሥራ ሆኖ ያገኘነዉ፡፡ ፈላስፋ ልብ ወለድ ደራሲ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ የጋርዮሽ ንፅረተ ዓለም መዋቅሮች (communal belief systems) የመንቀስ (criticizing) አልፎም የመናድ (deconstructing) ክህሎትን የታደለ ነዉ፡፡ ፍልስፍናዊ ልብ ወለድም በተነበበ ቁጥር አዲስ ትርጉምን የሚፈጥር ነዉ፡፡
ዮናስ ተራ የሚመስሉ ጥቃቅን የሕይወት ገጾችንና ኹነቶችን በርቀትና በዝርዝር በሸጋ አተራረክ አጉልቶ በማቅረብ አንባቢ ጉዳዩን ልዩ አፅንኦት ሰጥቶ እንዲመለከተዉ የማድረግ ክህሎት ያለዉ ደራሲ ነዉ፡፡ በሕዉስታ (sensation) የምንቀዳዉን የነገሮችን ቀለም፣ ሽታ፣ ጣዕም፣ ድምፅ፣ ልስላሴና ሻካራነት እና ሙቀትና ቅዝቃዜ ዘርዝሮ መተረክ (detailed narration) የበሳል ደራሲ ሙያዊ ክህሎት ሚዛን ነዉ፡፡
በዮናስ ስለ ትናንሽ አለላዎች ዉስጥ የተዳሰሱ ጭብጦች የጊዜ ህልፈት (change)፣ ፍቅር (love)፣ ሞት (death)፣ ባይተዋርነት (estrangement)፣ ትዝታ (reminiscence)፣ የሕይወት ወለፈንድነት (absurdity)፣ ወረት (faddism)፣ ክህደት (infidelity) እና ይሉኝታ (shame) ናቸዉ፡፡
ይህ ኂሳዊ መጣጥፍ ከላይ በጠቀስሁት የዮናስ አድማዉ የልብወለድ ሥራ ዉስጥ ከተዳሰሱት አያሌ ጭብጦች መካከል ጥቂቶቹን መርጦ የሚዳስስ ነዉ፡፡ እነሱም የሕይወት ከንቱነት፣ የአርነት እና የወሳኛዊነት ተግዳሮት፣ የሐበሻ ማንነት እና ፍቅር ናቸዉ፡ ፩. ሕይወት ወለፈንድ ነዉ
ልክ እንደ ታዋቂዉ ደራሲ እና ፈላስፋ አልበርት ካሙ፣ ለዮናስ የሰዉ ልጅ አንገብጋቢዉ ጥያቄ የሕይወት ትርጉም ነዉ (ዮናስ፣ 2014)፡፡ ካሙም ዘ ሚዝ ኦፍ ሲሲፈስ በተሰኘ የፍልስፍና ሥራዉ እንደ ጻፈዉ፣ ተጨባጭነት ከሌላቸዉ ብሽቅ ጥያቄዎች ይልቅ ፍልስፍና ቅድሚያ ሰጥቶ ሊመልስ የሚገባዉ ወሳኙ ፍልስፍናዊ ተግዳሮት ራስን መግደል ነዉ (ካሙ፣ 1955)፡፡ ራስን መግደል የፍልስፍና አንገብጋቢዉ ጥያቄ ከሆነዉ ከህልዉና ትርጉም ጥያቄ ጋር የተሰናሰለ ነዉ፡፡
ለዮናስ የሰዉ ልጅ ሕይወት ወለፈንድ ነዉ (meaningless) ነዉ፡፡ የእዚህ የዮናስ እሳቤ ዐቢይ ምክንያቱ፣ የሰዉ ልጅ በሞት በቅፅበት እድሜ ትቢያ የሚሆን መዋቲ መሆኑ ነዉ፡፡ ለካሙ፣ ከሞት በተጨማሪ የሕይወት ከንቱነት ምንጩ በድግግሞሽ የተሞላዉ አታካቹ የሰዉ ልጅ ህላዌ ነዉ (ኮፕልስተን፣ 1994)፡፡ ዮናስ የሰዉ ልጅ በሕይወት ከንቱነትና በአታካች የዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ኑረት ሰበብ ራሳችንን ከመግደል የሚታደጉን ብዙ ማባበያና መሸንገያ  ተዉኔቶች አሉን ባይ ነዉ፡፡ በብዙ ጥበብ የተራቀቀዉ “አማልክቱ የሰዉ ልጅ” አይቀሬ ዕጣ ሞት የካበዉን ሁሉ በአንድ ጀንበር የሚንድ ከሆነ፣ የህልዉና ትርጉም እንዴት ናላ የሚያዞር ጥያቄ አይሆን? ሰዉስ ጉያዉ ሸጉጦት በሚራመደዉ ሞት እንደ ጧት ጤዛ በቅፅበት እንደሚረግፍ እያወቀ እንዴት ብሎ በሕይወት ፍቅር ሊወድቅ ይችላል?
ዮናስ ሕይወት ወለፈንድ ነዉ ቢልም ራስን መግደልን ለእዚህ ተግዳሮት መፍትሄ አድርጎ አያዝም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ካሙም ራስን መግደልን አያበረታታም፡፡ ዮናስ ለከንቱነት ስሜት ተግዳሮት ግልፅ መፍትሄን ባይጠቁምም፣ ካሙ ግን ከላይ በተጠቀሰዉ ሥራዉ መፍትሄዉን ጠቁሟል፡፡ በእዚህ ሥራዉ ካሙ እንደሚነግረን፣ የከንቱነት ስሜት መፍትሄዉ ራሱን የወለፈንድነት ስሜትን በፀጋ ተቀብሎ (lucid recognition) እስከ ዕለተ ሞት መዝለቅ ነዉ፡፡
፪. ሰዉ ትናንቱን ነዉ፡ አርነት እና ወሳኛዊነት
የአርነት እና የወሳኛዊነት ተግዳሮት በዮናስ ስለ ትናንሽ አለላዎች የተዳሰሰ ዐቢይ ዲበአካላዊ ርዕሰ ጉዳይ ነዉ፡፡ ዮናስ በእዚህ ሥራው አንደሚነግረን፣ ሰዉ ያለፈ ሕይወቱ ስንክሳር ሥሪት ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የዛሬ ሕይወታችን በትናንት ታሪካችን ግዞት ሥር የወደቀ ነዉ፡፡ ዮናስ ድርሰቱ መግቢያ ላይ የሚከተለዉን አስፍሯል፡-
ሰዉ ትናንቱን ነዉ፡፡ “ወሰን” የተባለዉ ኢትዮጵያዊ ጎረምሳ ከመወለዱ አስቀድሞ፣ ማለት መወለድን የሕይወት መጀመሪያ አጥቅ አድርገን – ሌላ ቀደምት አጥቅ ሊኖር እንደሚችልም ሳንዘነጋ፣ በሚፈጠሩ ተከታታይ የማህበራዊ ክንዋኔዎች መሰናሰል የተፈጠረ ሰብዕና ነዉ፡፡ ቢሞት ምን ይሆናል? አናዉቅም፡፡ ሲኖር ግን ያለፈበት ልጅነቱን ይመስላል (ዮናስ፣ 2014፡ገጽ 8)፡፡
ከላይ የቀረበው የዮናስ አተያይ አንድምታው፣ እኛ እያንዳንዳችን በትናንት ሕይወታችን እግር ብረት የተጠፈርን ነን የሚል ነዉ፡፡ ይህ አይነቱ እሳቤ ለወሳኛዊነት (determinism) ቦታ ይሰጣል፡፡ እዉን ሰዉ የትናንቱ ሎሌ ነዉ? ፈረንሳዊዉ ኤግዚስቴንሻሊስት ፈላስፋ ዠን-ፖል ሳርተር፣ በፍፁም አይደለም ይለናል፡፡ እንደ እሱ እሳቤ፣ ሰዉ ትናንቱን ነዉ የሚለዉ እሳቤ ለአርነት ቦታ የሌለዉ እሳቤ በመሆኑ የተወገዘ ነዉ፡፡ እንደ ሳርተር እሳቤ፣ ሰዉ ትናንት በገነባዉ ማንነቱ ላይ ስልጣን ያለዉ ፍጡር ነዉ (ሳርተር፣ 2018)፡፡ በሌላ አነጋገር፣ እኛ እያንዳንዳችን በራሳችን ላይ አብዮት በማካሄድ የትናንት አሻራ ያረፈበት ማንነታችንን የማፍረስ ሥልጣን አለን፡፡ ይህን ሂደት ሳርተር ሽግግር (transcendence) ብሎ ይጠራዋል፡፡ ካሙ እንደ ሳርተር ሁሉ እያንዳንዱ ግለሰብ ዕጣ ፈንታዉን ለመወሰን ፍፁማዊ አርነትን የተጎናፀፈ ነዉ የሚል አቋም ያለዉ ፈላስፋ ነዉ (ተምኮ እና ሆፍ፣ 2001)፡፡
ከላይ የዳሰስሁትን የሳርተር አተያይ ግብዝነትን (bad faith) የሚቃረን አተያይ ነዉ፡፡ ቡሽ ዠን-ፖል ሳርተር፡ ኪይ ኮንሰፕትስ በተሰኘዉ በስቴቨን ቸርችል እና ጃክ ሬይኖልድስ አርትኦት በተደረገዉ ሥራ ዉስጥ በቀረበዉ ሰልፍ ሜኪንግ ኤንድ አሊኔሽን፡ ፍሮም ባድ ፌዝ ቱ ሪቮሉሽን በተሰኘዉ ሥራዉ እንዳብራራዉ፣ ግብዝነት የሰዉን ልጅ ነባራዊ ሐቆች አርነት (freedom) እና ዚቅ (facticity) በመካድ የሚገለጥ ተግባር ነዉ፡፡ አርነትን የተጎናፀፈዉ ግብ አልቦዉ (contingent) የሰዉ ልጅ ዓለም ዉስጥ እንደ ግዑዝ ባለበት ረግቶ እንዲዘልቅ ያልተፈጠረ፣ በተቃራኒዉ ራሱን እንዲቀርጽና ትልሙን እንዲቀይስ የተኮነነ መሆኑን በይሁንታ የሚቀበል ፍጡር ነዉ (ቡሽ፣ 2013)፡፡
ሰዉ ያለፈ ሕይወቱ ስንክሳር ሥሪት ነዉ የሚለዉ የዮናስ እሳቤ፣ በሃያኛዉ ክፍለ ዘመን የተነሳዉን የኦስትሪያዊዉን የሥነ ልቡና ሊቅ ሲግመንድ ፍሮይድ ፍካሬ፣ ልቡና ነባቢ አእምሮ (Freud’s psychoanalysis) የሚጋራ እሳቤ ነዉ፣ ምንም እንኳ በሳርተር በፅኑ ቢተችም፡፡ ለሳርተር ሰዉ የትናንቱ ዉጤት ነዉ የሚለዉ የዮናስ እና የፍሮይድ እሳቤ ግብዝነት ነዉ፡፡
በግብዝነት ዉስጥ የወደቀ ሰዉ በልዩ ልዩ ኃይሎች ቀድሞ የተበጀ ቋሚ ማንነት (fixed identity) አለኝ ብሎ የሚያስብ ነዉ (ሳርተር፣ 2018፤ በርናስኮኒ፣ 2006)፡፡ በተጨማሪም፣ ሮበርት ሲ. ሶሎሞን ፍሮም ራሽናሊዝም ቱ ኤግዚስቴንሻሊዝም፡ ዘ ኤግዚስቴንሻሊስትስ ኤንድ ዜር ናይንቲንዝ ሴንቸሪ ባግራዉንድስ በተሰኘዉ ሥራዉ እንደ ጻፈዉ፣ ሳርተር ከሥነ ልቡናዊ ተወስኖሻዊነት (psychological determinism) ነባቢ አእምሮዎች (theories) ዉስጥ አንዱ የሆነዉን የፍሮይድን ፍካሬ ልቡና ነባቢ አእምሮ ሚዛን የሚደፋ ምክንያት አቅርቦ ፉርሽ ያደረገ ፈላስፋ ነዉ፡፡
ፍሮይድ ኢ-ንቁ ኅሊና በንቁ ኅሊና ላይ ይሰለጥናል ብሎ ያምናል፡፡ በመሆኑም፣ ነባቢ አእምሮዉ ለሰዉ ልጅ ነፃ ፈቃድ ቦታ የለዉም፡፡ በተቃራኒዉ፣ ለሳርተር፣ እያንዳንዳችን የቀደመ ታሪካችንን በሥልጣናችን የመሻር ኃይሉን የታደልን ነን (ሶሎሞን፣ 2001)፡፡ ለሳርተር፣ ሥነ ልቡናዊ ተወስኖሻዊነት ርትእ ባለመሆኑ በፅኑ የሚወገዝ አንዱ የግብዝነት መገለጫ ጠባይ ነዉ (ሳርተር፣ 2007)፡፡ ሮበርት ሲ. ሶሎሞን (2001) ከላይ በተጠቀሰዉ ሥራዉ እንደ ጻፈዉ፣ አንድ ግለሰብ በቀደመ ባሕሪዉ፣ በቀደመ ኹነቱ፣ በአካባቢዉ ተፅእኖ ታስሬያለሁ የሚል እምነት ከገነባ በግብዝነት ዉስጥ መዉደቁን ያመላክታል፡፡ ለምን ቢባል፣ ያለፈ ስብዕናችን ነጋችንን የመወሰን ኃይል ስለሌለዉ፡፡
ሳርተር ኢ-ንቁ ኅሊና (unconscious mental states) አለ የሚለዉን የፍሮይድ የፍካሬ ልቡና ነባቢ አእምሮ አይቀበልም፡፡ እንደ ሳርተር እሳቤ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ጭቆናዉን (repression) በተመለከተ ደንበኛ ግንዛቤ አለዉ (ስቴቨንሰን እና ሐበርማን፣ 2009)፡፡ የሳርተር የሽንገላ ትወራ የኢ-ንቁ ኅሊናን ቅዠትነት የሚያስረግጥ ነባቢ አእምሮ ነዉ፣ ግብዝነት እዉነታዉን እያወቁ ራስን የመደለል ተግባር ስለሆነ፡፡
፫. የሐበሻ ማንነት
ስለ ትናንሽ አለላዎች ደራሲዉ በመቅድሙ እንደገለፀዉ፤ የሐበሻን ሕይወት ወርድና ቁመት በሳላቸዉ ገፀባሕርያት ዉክልና በጥልቀት የሚፈክር ስንክሳር ነዉ፡፡ ዮናስ እንደሚነግረን፣ ሐበሻ በአፉ በታሪኩና አባቶቹ ባጎናፀፉት ነፃነቱ የሚኮራ መሆኑን የሚደሰኩር፤ በገሀድ ግን ኅሊናዉ በፈረንጅ ባሕል ቅኝ የተገዛ ሎሌ ነዉ፡፡ ሐበሻ ድህነቱን ከአድማስ ማዶ ተሰዶ ሊያራግፍ የሚመኝ፣ በአፉ አገሬን እወዳለሁ የሚል፣ በገሀድ ግን እትብቱ የተቀበረበትን አፈር ሽሽት የባሕር ሲሳይ መሆንን የሚመርጥ የሩቅ አገር ናፋቂ ነዉ፡፡ ሐበሻ በድንቁርናዉ ሰበብ የሌላዉ ዓለም ህዝብ ጅራት የሆነ ህዝብ ነዉ፡፡ ድንቁርና ዮናስ ያክላል፣ የብሔራዊ ቁርቁዝናችን (poverty) እና ክሽፈታችን (collapse) ዋናዉ ምክንያት ነዉ፡፡ ሐበሻ አመፀኛ ነዉ፣ በሦስት ገመድ መሬት የወንድሙን ደም የሚያፈስ፡፡ ሐበሻ ወንድን አምላኪ ሴትን አኮሳሽ
(sexist) ነዉ፡፡ ሐበሻ በተዉኔት መልካም ስሙን የሚገነባ ግብዝ ነዉ፡፡ ሐበሻ ቂመኛ ነዉ፡፡ ሐበሻ የሰዉ ሥጋ እርም የማይል ሐሜተኛ ነዉ፡፡
፬. ፍቅር
ዮናስ እንደሚነግረን፣ ፍቅር የ“ሰዉነት” ልዩ መገለጫ ጠባይ (idiosyncratic essence of man) ነዉ፡፡ ይህ ለሰብአዊ ፍጥረታት የተቸረ ስሜት ሌሎች በሁለንታ ዉስጥ የሚገኙ ፍጥረታት ማለትም እንሰሳት፣ እፅዋት እና አእዋፍት ፈፅመዉ የማያጣጥሙት ልዩ ስሜት ነዉ፡፡ የፍቅር ስሜት፣ ዮናስ ያክላል፣ ቅዱስ ስሜት ነዉ፡፡ ፍቅር እና ናፍቆት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሰብአዊ ስሜቶች በሰዉ ልጅ ልብ ዉስጥ ቤታቸዉን ሰርተዉ ዘመናትን ተሻግረዉ የመጡ እፁብ ስሜቶች ናቸዉ፡፡
፭. የትዉልድ ክሽፈት
ዮናስ በልብ ወለድ ሥራዉ ዉስጥ የሳለዉ ዋና ገጸባሕሪ ወሰን ጫኔ የተባለ ምሁር ወጣት ነዉ፡፡ ይህ ገጸባሕሪ ጭምት፣ አፍቅሮ ያመለካትን ሴት ከንፈር እንኳ ለመሳም ያልበቃ ዐይነ አፋር፣ ጥገኛ (dependant)፣ ሥራ ፈት (unemploy)፣ ባይተዋር (alienated) እና ምኩን (loser) ነዉ፡፡ ወሰን የድህረ ደርግ ትዉልድን የሚወክል ገጸባሕሪ ነዉ፡፡ ወሰን ለምን መከነ? የገጸባሕሪዉ ክሽፈት ሰበቡ የአገሪቱ ክሽፈት ነዉ፡፡ ደራሲዉ በገጸባሕሪዉ ሕይወት ገልጦ የሚያስቃኘን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአገሪቱ ነባራዊ አዉድ ደንቃራነት ወዲያ ወዲህ እንዳይፈናፈን የመጠፈሩንም ሐቅ ነዉ፡፡ እያንዳንዱ ደሃ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች እግር ብረት ተጠፍሮ በገባበት አረንቋ እንዲዳክር የተኮነነ ዜጋ ነዉ፡፡ ማምለጫ የለም፡፡ የአባቶቹ ገፈት ቀማሽ ነዉ፡፡ አባቶቹ የቀናች አገር አላወረሱትም፡፡ ዮናስ የሚከተለዉን ጽፏል፡- የአለፉትን ሶስት አመታት ከአደገበት ቤት ወጥቶ ዩኒቨርሲቲ በጥሶ የእናቱ ጓዳ ሲመለስ የሰዉ ሀገር
ሄዶ ያሳለፋቸዉ ሶስት አመታት፣ የጠቀለለዉ ድግሪና ያፈራቸዉ ጓደኞቹ እንደህልም ቀለም አልባ፣ እንደክረምት አግባ ከንቱ ሆኑበት፡፡ ሲሄድ ትልቅ ሻንጣ ይዞ ሲሸኝ ያስታዉሳል፡፡ በመሐል ብዙ የሚረቡም የማይረቡም ሰዎች እየሄዱ መጥተዋል፡፡ እንደሰመመን ያስታዉሳል፡፡ ቀጥሎ ጥቁር ካባና ቆብ አጥልቋል፡፡ ሊናገር ይፈልጋል – “የት ልንደርስ ነዉ እንዲህ የሚያጣድፉን?” ሊል ይፈልጋል ግንቃላት ከአፉ አይወጡለትም፡፡ በቅጡ በማያዉቀዉ ትምህርት፣ በቅጡ በማያዉቀዉ አኳኋን ተመርቆ ሲወጣ ለክፉም ለደግም የማይነቃ በድን ሆነ (ዮናስ፣ 2014፡ገጽ፣ 26)፡፡ከላይ የቀረበዉ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ፣ የድህረ ደርግ ትዉልድ ራዕየ ቢስ የሆነበት ዐቢይ ሰበብ ነዉ፡፡ በግል ሩጫዉ የትም የማያደርሰዉ ከንቱ ድካም መሆኑን ያዉቃል፡፡ የርትእን መጓደል ጠቅሶ ቢያምፅ፣ አርነት መገፈፉን ቢጠይቅ የጥይት ሲሳይ እንደሚሆን፣ መከራና እንግልት እንደሚደርስበት ጠንቅቆ ያዉቃል፡፡ ታዲያ የእዚህ ትዉልድ ጭላጭ ተስፋ ምንድር ነዉ? የእዚህ ትዉልድ ብቸኛ ተስፋዉ ስደት ነዉ፡፡
ማጠቃለያ
የዮናስ ስለ ትናንሽ አለላዎች፣ ይህ መጣጥፍ ያልዳሰሳቸዉ በርካታ የህልዉና ገፆችና አንኳር ጥያቄዎች (big questions) የተዳሰሱበት ኪናዊ ይዘቱ የላቀ ድርሳን ነዉ፡፡ ይህ ድርሰት ኋላ ላይ በተጻፉ በሌሎች ልብ ወለድ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ርቱዕ ተፅእኖ ማሳረፍ የቻለም ነው፡፡

***

 


       ከአዘጋጁ፡-  መኮንን ደፍሮ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር ድግሪውን በ2009 ዓ.ም፣ የማስተርስ ድግሪዉን ደግሞ በ2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በጅማ፣ በመቐለ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርቷል፡፡ ጸሐፊው አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ መጽሔቶች ግጥሞቹንና የልብ ወለድ ሥራዎቹን አሳትሟል፡፡  መኮንን በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን ጽፏል፡፡


Read 420 times Last modified on Sunday, 17 March 2024 20:39