Thursday, 21 March 2024 21:03

ንግድ ባንክ ገንዘቡን እስከ ቅዳሜ የማይመልሱ ሰዎችን ፎቶና ማንነት በሚዲያ ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባጋጠመው የሲስተም ችግር ወቅት ገንዘብ የወሰዱ ወይም ያስተላለፉ ግለሰቦች እስከ መጪው ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ካልመለሱ ፎቷቸውንና ማንነታቸውን በመገናኛ ብዙኃን ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ባንኩ ገንዘቡን ተመላሽ በማያደርጉ ሰዎች ላይ በሕጋዊ ሂደቱ ተገቢ ውሳኔ እስኪገኝ ድረስ ፎቶግራፋቸውንና ዝርዝር ማንነታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች “ባንኩ በመረጠው የብዙኃን መገናኛ መንገድ ለሕዝብ ይፋ አደርጋለሁ” ሲል አሳስቧል።

ገንዘብ የወሰዱ ወይም ወደተለያዩ ሂሳቦች ያስተላለፉ ግለሰቦች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች በመቅረብ እንዲመልሱም የመጨረሻ ጥሪውንው ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስተላልፏል።

ነገር ግን ይህ ሳይሆን ገንዘቡን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ተመላሽ የማያደርጉ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቋል።

የሚወስዳቸው እርምጃዎች ደረጃ በደረጃና በተከታታይ ጠንከር ያሉ እንደሚሆኑ የገለጸው ባንኩ፤ ለሕግ አካላት ማሳወቅ አንዱ እንደሚሆንም አስታውቋል።

“ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር የግለሰቦችን ስም ዝርዝር በየቅርንጫፎችና እንደሁኔታው ግለሰቦቹ ሊታወቁ በሚችሉበት አካባቢ ይፋ በማድረግ ቀጣይ ሕጋዊ እርምጃዎችን” እንደሚከተሉ አስታውቋል።

በተጨማሪም “ከፍትህ አካላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተገቢውን የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚያደርግም” አሳስቧል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ፣ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞች እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ካልመለሱ ማንነታቸውን ለፖሊስ እንደሚያሳውቁ ተናግረው ነበር።

Read 810 times