Saturday, 23 March 2024 20:24

ላም ባንድ ጎኗ አትሰባ፤ ባንድ ጎኗ ጉፋያ አትሆን

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ የጣሊያን አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል።
አንድ የታወቀ ክራክ የሚባል ሌባ ነበር ይባላል። ይህንን ሌባ ማንም ሊይዘው አልቻለም። ይህ ክራክ የተባለው ሌባ ደግሞ ክሩክ የሚባለውን ሌላ ሌባ ለማግኘት ከፍተኛ ምኞት ነበረው።
አንድ ቀን ክራክ ምሳውን ሊበላ አንድ ሆቴል ገብቶ፣ ከአንድ ሌላ ተመጋቢ ራቅ ብሎ ይቀመጣል። ሰዓት ለማየት ወደ እጁ  ሲመለከት ሰዓቱ ተሰርቆበታል።
“እኔ ሳላውቅ ሰዓቴን ከእጄ ላይ አውልቆ ሊወስድ የሚችል ክሩክ መሆን አለበት” አለ በሆዱ።
በዚህ ቁጭት ብድግ ይልና ግራና ቀኝ ዘወር ዘወር ብሎ ምግብ እየበላ ወዳለው ሰው ተጠግቶ በከባድ ቅልጥፍና የሰውዬውን ቦርሳ ይመነትፈዋል።
እንግዳው ተመጋቢ ሂሳብ ሊከፍል ኪሱ ሲገባ ቦርሳው የለም። ያለምንም ማመንታት ወደ ክራክ ዘወር ብሎ፤
“አንተ ክራክ መሆን አለብህ” አለ።
“ትክክል ነህ” መለሰለት።
“እንግዲያው አብረን እንስራ?” አለው።
“መልካም” አለ ክሩክ።
ጊዜ ሳይፈጅባቸው ተስማሙና አብረው ወደ ከተማ አመሩ። ከዚያም ወደ ንጉሡ ሀብት ማከማቻ ካዝና ሄዱ። ካዝናው በበርካታ ዘቦች ተከቧል። ያም ሆኖ ሌቦቹ ምድር ለምድር መግቢያ ጎርጉረው ገቡ። ያለውን ሀብት ሁሉ ሰርቀው ወጡ።
ንጉሡ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው። ሌቦቹ እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ችግሯቸው ሰነበቱና ቀጥታ ወደ እስር ቤት አመሩ። አንድ በሌብነት የታሰረ ሰው ጋር ሄዱና፤
“ማን እንደሰረቀኝ ከነገርከኝ በነፃ እንድትለቀቅ አደርጋለሁ” አሉት።
እስረኛውም፤ “ያለጥርጥር  ወይ ክራክ ወይም ክሩክ ወይም ሁለቱም መሆን አለባቸው። እንዴት ሊይዟቸው እንደሚችሉ እነግርዎታለሁ። የስጋ ዋጋ ከዛሬ ጀምሮ በኪሎ 100 ብር ገብቷል ይበሉና ያውጁ። ያንን ከፍሎ የሚገዛ ያ የእርስዎ ሌባ ነው።”
ንጉሡ የሥጋ ዋጋ 100 ብር አስገቡ። ሥጋ የሚገዛ ሰው ጠፋ። ሲረፋፍድ ግን አንድ ቄስ እንደገዛ ወሬው ተሰማ።
ይሄኔ እስረኛው፤ ”በቃ ወይ ክራክ ወይ ክሩክ በቄስ ተመስለው ሥጋ ገዙ ማለት ነው። አሁን እኔ እንዳልታወቅ ተሸፋፍኜ በየቤቱ እየዞርኩ እለምናለሁ። ሥጋ የሚሰጠኝ ሰው ካገኘሁ በሩ ላይ ቀይ ምልክት አደርጋለሁ። የእርስዎ ዘቦች እንግዲህ ተከትለው ሌቦቹን ማሰር ነው” አለ።
እስረኛው በዘዴ ተጠቀመ። እንዳለው በክራክ ቤት ላይ ቀይ ቀለም ምልክት አደረገ። ዳሩ ምን ያደርጋል፤ ሌባው ክራክ ምልክቱን አየውና በከተማው ባሉ ቤቶች በሮች ላይ ሁሉ ቀይ ምልክት አደረገባቸው። በመካያው የክራክና የክሩክ መኖሪያ ቤት የት እንደሆነ ሳይታወቅ ቀረ።
እስረኛው አሁንም ሌላ ዘዴ ዘየደ። “እነዚህ ሌቦች መቸገራቸው አይቀርም። ስለዚህ እንደገና የእርስዎን ሀብት ሊሰርቁ መምጣታቸው አይቀርም። ከደረጃው ግርጌ የሚፈላ ውሃ ያስቀምጡ። ሌቦቹ በጨለማ ወደ ምድር ቤት እንወርዳለን ሲሉ ውሃ ውስጥ ይገባሉ” አላቸው።
ንጉሡ እንደተባለው አደረጉ።
ሌቦቹ እውነትም ሲቸግራቸው ወደ ንጉሡ ካዝና መጡ። ክሩክ ቀድሞ ገባ። ጨለማ ስለነበረ በቀጥታ የፈላ ውሃ ካለበት በርሜል ውስጥ ጥልቅ አለ። ጓደኛው ሊያወጣው ሲሞክር አልተሳካለትም። ስለዚህ የክሩክን አንገት ቆርጦ እዛው ሬሳውን ጥሎት ሄደ።
ንጉሡ በነጋታው ሄደው ሌባው መያዙን አዩ። ግን ጭንቅላቱ ተቆርጦ ስለተወሰደ ማንነቱ የማይለይ ሆነ። አሁንም እስረኛው ሌላ ዘዴ ነገራቸው። “ሬሳውን በከተማ መሃል በፈረሶች ያስጎትቱት። ሬሳውን አይቶ የሚያለቅስ ሰው ከሰሙ የሌባው ቤት እዛ ነው ማለት ነው።”
እውነትም የክሩክ ሚስት ሬሳውን ስታይ ጮኸች። ሆኖም ይሄ አደገኛ መሆኑን የተገነዘበው ክራክ፤ ሰሀንና የቤት እቃ እየወረወረ  ሴትየዋን እየደበደበ ቆየ። ዘቦቹ ድምጽ ወደሰሙበት ቤት ገቡ። ያገኙት ግን ሚስቱ የቤት እቃ በመስበሯ ምክንያት የሚደበድብ ባል ብቻ ነው።
በመጨረሻ፤ ንጉሡ ሲጨንቃቸው፤ ሀብቴን የዘረፈውን ሌባ እምረዋለሁ። ግን አንድ ነገር ማድረግ ከቻለ ነው። ይኸውም የምተኛበትን አንሶላ ከሰረቀ ነው። ክራክ ፊት ለፊት መጥቶ ”እኔ እችላለሁ፤” አለ።
ያን ማታ ንጉሡ ሽጉጣቸውን ይዘው አልጋቸው ውስጥ ገቡ። ክራክ ከመቃብር ቆፋሪዎች ዘንድ ሬሳ ይዞ መጣ። የራሱን ልብስ አልብሶ ቤተ-መንግስቱ ጣራ ላይ አንጠለጠለው። እኩለ-ሌሊት ከጣራው ወደ ንጉሡ መኝታ ቤት መስኮት ሬሳውን ላከው። ንጉሡ ክራክ ነው ብለው ሬሳውን ደበደቡት። መሬት ወደቀ። ተነስተው ከፎቅ ወርደው የወደቀውን የክራክ ሬሳ ሊያዩ ሄዱ። ይሄኔ ክራክ በመስኮቱ ገብቶ የንጉሡን አንሶላ ጠቅልሎ ውልቅ አለ።
ንጉሡ ምህረት አደረጉለት። ልጃቸውንም ዳሩለት። ክራክም ሁለተኛ ላይሰርቅ ቃል ገባ!
***
ሌቦች በችሎታ የሚፎካከሩባት ሀገር ያልታደለች ናት። ሌባ ለመፈለግ ሌባ ማማከር እርግማን ነው። ሌባውን ካገኘህልኝ በነጻ እለቅሃለሁ ማለት ደግሞ የከፋ እርግማን ነው። በየበሩ ላይ ቀይ ምልክት ከሚያደርግ ሌባ ይሰውረን። ጭንቅላቱ ተቆርጦ ማንነቱ የማይለይ  ሌባ አይጣልብን፡፡ የምንተኛበትን አንሶላ ጭምር ለሚሰርቅ ሌባ እድል የሚሰጥ አዋጅ፤ መመሪያ፣ ፖሊሲ አያምጣብን። ሌቦቻችንን መያዝ ከባድ ነው። ታክቲክ እየለዋወጡ ሌብነት የሚያጧጡፉ ሌቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ትልቅ ተግባር ነው። ሌብነትና አያሌ መልኮቹ የጥቅል ስማቸው ሙስና ነው። ዛሬም እንደ ትላንት እግር እስኪነቃ ሲሄዱ ቢውሉ በዚህም ሆነ በዚያ ዘዴ በሀገራችን ይህ አባዜ ያልተጠናወተው መ/ቤትና ተቋም አይገኝም፤ ብንል ከሀቁ አንርቅም። በተናጽሮ ሲታይ ጥንት “ደሞዙን 250፣ የሚኖረው ቪላ ቤት፣ የሚነዳው ውድ ውድ መኪና!” በሚል ምጸታዊ መፈክር ሙስናን ለመዋጋት፤ ይሳካም አይሳካም መሞከሩ አይዘነጋም። ዛሬም መሰል መፈክር ማስገር የሚያስፈልግበት ደረጃ የደረስን ይመስላል። ጥንትም የነበረው ችግር ዛሬም እንዴት ሊኖር ቻለ? “በሥራው አጋጣሚ በእጁ የገባውን የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ የዘረፈው” የሚለው አባባል ትላንት ነበር፤ ዛሬም አለ። ነገሩ እንግሊዞች “Who judges the judges?” “ዳኞቹን ማን ይዳኛቸው?” የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ዙሪያ ያጠነጠነ ነው። ተቆጣጣሪውን ማን ይቆጣጠረው? ገምጋሚውን ማን ይገምግመው? እንደማለት ነው። ሌላው መነሳት ያለበት አባባል፤ They shout at most against the vices they themselves are guilty of የሚለው ነው፡፡ በአማርኛ ሲታሰብ፤  “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” የሚል የሼክስፒር አባባል መሆኑ ነው።
ዛሬ አዲስ የሚሾሙ ባለስልጣኖች ስለማናቸውም ጉዳዮች ሲጠየቁ፤ “ከጥንት የወረስነው አሰራር”፣ “ያለፈው ስርዓት የጣለብን እዳ”፣ “ባለፈው ጊዜ የነበረው አሰራር ዝርክርክነት” ወዘተ የሚል ነው፤ የመልሳቸው መነሻ ሃረግ። ከቶውንም እንደ ሰንሰለት ተሳስሮ ባለው የቢሮክራሲ አውታር፣ ሰው የሰውን ኪስ እንደራሱ በሚያውቅበት የእከክልኝ ልከክልህ አገር፣ ከጎኑ አንድ ባለስልጣን ሲነሳ ወዲያውኑ “ያለፈው አሰራር፣ ያለፈው ስርዓት” የሚባለው እንዴት ነው? ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚባለውን የቁርጥ ቀን ተረት አንርሳ እንጅ!
ሹም ሽረት በተደረገ ቁጥር አሮጌውን መኮነንና አዲሱን ጻድቅ ማድረግ የተለመደው የአገራችን ፈሊጥ ነው። ከዚህ መጠንቀቅ አለብን። ከዜሮ የሚጀምር ልማት የለም። መልካም ፍሬ ያላፈሩ፣ ውጤት ያላስመዘገቡ፣ ድርብ ስራ የሚሰሩና የተዘጉ፣ ብቃትና ስኬት የሌላቸው ወዘተ… የሚሉ ግምገማዎች ስንል ፈጠው የወጡትን ጉድለቶች አብሮ መመርመርና በአግባቡ መገምገም  ይኖርባቸዋል። ማመን ብቻ ሳይሆን መተማመን ያስፈልጋል። አሁንም ሙያ፤ ስነ-ምግባርና ልምድ ወሳኝ መሆን አለባቸው።
ዝውውሮች በተፈተሸ አቅም የተጤኑ፣ ከአንዱ ኃላፊነት ገለል ብሎ ይሂድ ብቻ የማይባልባቸው መሆን አለባቸው። የሁሉ መ/ቤቶችና ተቋማት ጤና የአገሪቱ አጠቃላይ ጤና ነው። የሰራ-አከላቷ በትክክል መንቀሳቀስ ነው ለደህንነቷ ዋስትና የሚሆነው። አለበለዚያ ቴዎድሮስ እንዳለው፤
“መች ትተርፊያለሽ ኢትዮጵያ፤ ህዋስሽ አብሮኝ ካልሰራ
አንገትሽ ብቻ መቅደላ፣ አፋፍ ወጥታ ብትበራ…”
(የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ)
ማለት እንዳይሆን የመጨረሻ ቃላችን፤ መጠንቀቅ ተገቢ ነው። “ላም ባንድ ጎኗ አትሰባ፤ ባንድ ጎኗ ጉፋያ አትሆን” ይሏል ይሄው ነው።

Read 1330 times