Saturday, 23 March 2024 20:27

የአብዮቱ ዳናዎች በአዳም ድርሰቶች

Written by  አብርሃም ገብሬ ደቢ
Rate this item
(1 Vote)

     የየካቲት 1966ቱ የኢትዮጵያ ማህበራዊ አብዮት፣ የኢትዮጵያ ማህበረ-ፖለቲካዊ ሂደት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ታላቅ የዘመን ክስተት ነው፡፡ አዲስ አይነት ማህበራዊ ስርዓትን (social order) ለማነጽ የሞከረ፣ የማህበረ-ፖለቲካዊ ግንኙነታችንን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የለወጠ፣ በማህበረሰቡ የእርስ በእርስ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ እንዲሁም መልከ-ብዙ ቀውሶችን ያስከተለ አብዮት ነው፡፡ ሃምሳ አመቱን የደፈነው የአብዮቱ አያዎ’ኣዊ ‘አሻራዎች፤ በዛሬው ማህበረ-ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸው በመሆኑ የአብዮቱ ጉዳይ እጅግ ወሳኝ ርዕሰ-ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ የ66ቱ አብዮትና አንድምታዎቹን ርዕሰ-ጉዳይ አድርጎ በኪነት አውድ ውስጥ በማምጣትም ሆነ ኩነቱን በመተርጎም በኩል ግን ትልቅ ውስንነት ይታያል፡፡ ለአብነትም በአማርኛ ስነጽሁፍ ውስጥ አብዮቱና አብዮተኞችን ርዕሰ-ጉዳይ በማድረግ የተሰሩ ጥቂት ድርሰቶች ቢኖሩም፣ ከነገሩ ወሳኝነትና ተፅዕኖ አኳያ ግን አብዮቱን መነሻ አድርገው የተደረሱ ድርሰቶች ቁጥር ጥቂት ናቸው፡፡ በተለይ በከያኒያኑ በቀጥታ የተደረሱ ድርሰቶች ደግሞ እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡
በእኔ ንባብ አዳም ረታ አብዮቱንና አብዮተኞችን የድርሰቶቹ ማዕከላዊ ርዕሰ-ጉዳይ በማድረግ፣ አብዮቱን ፍልስፍናዊ (philosophize) በማድረግና መልከ-ብዙ አተረጓጎሞችን (interpretations) በመከሰት ረገድ በፊተኛው ረድፍ የሚቀመጥ ደራሲ ነው፡፡ አዳም አብዮቱን ርዕሰ-ጉዳይ አድርጎ ከመነሳት ባሻገር፣ በአከያየን ስልቱም የተሳካለት፣ በኪናዊ ልህቀቱም የተዋጣለትና የዘመኑን መንፈስ በሚገባ ገልጦ ያሳየ  ደራሲ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ ‘እቴሜቴ የሎሚሽታ’፣ ‘ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’፣ ‘መረቅ’ እና ‘የስንብት ቀለማት’ ያሉ የፈጠራ ስራዎቹ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ግን በዋነኛነት ከ’ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ የቤሳ ኪናዊ ድርሰቶች ስብስብ ውስጥ ራሱ ‘ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ን እና ከረዥም የፈጠራ ድርሰቱ ‘የስንብት ቀለማት’ ውስጥ በጣም ጥቂት ቴክስቶችን (texts) መነሻ በማድረግ፣ አብዮቱ በእነዚህ ድርሰቶች ውስጥ እንዴት እንደቀረበ የራሴን ምልከታ ለማጋራት እሞክራለሁ፡፡
በአዳም የፈጠራ ስራዎች ውስጥ አብዮቱና የአብዮቱ ኩነቶች ከጥቅል ይዘታቸው ይልቅ፣ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ አብዮቱ ያሳደረው መልከ-ብዙ ተጽዕኖ ጎልቶ ይንጸባረቃል፡፡ አብዮቱ የተዋቸው ስነ-ልቦናዊ ጠባሳዎችም (trauma) በገጸ-ባህሪያቱ ሰርካዊ ኑረት ውስጥ የሚስተዋል ህማም ነው፡፡  በተለይ የአብዮቱ ዋነኛ ተዋንያን (ተሳታፊ) የነበሩ ገጸ-ባህሪያት በ”ትግል” እና በ”ነጻነት” ስም የሚሸርቧቸው ሴራዎች፣ የሚቀምሟቸው የተንኮል ድርጊቶች፣ የሚያናቅፏቸው የፍቅር ግንኙነቶች፣ በሀገር ስም የሚፈጽሟቸው የአስመሳይነት ተግባሮች፣ በጥራዝ ነጠቅነት የታጀበ ጮሌነትና የ’እኔ አውቅልሃለሁ’ ድርጊቶች የወል መገለጫቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአብዮቱ የተሳተፉ ብዙኃኑ የዘመኑ ወጣቶች በጥቂት ‘አፈጮሌዎች’ ፕሮፓጋንዳ ሲታለሉ፣ ወጣቶቹ በስሜት ለሆነ የፖለቲካ ድርጅት ወይም የድርጅት መሪዎች ስውር የፖለቲካ ፍላጎት መሳሪያ ሲሆኑ፣ ከዓመታት በኋላም በአብዮቱ ዘመን በሌሎች በመታለል በፈጸሟቸው ድርጊቶች የሚጸጸቱ… ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
በጥቅሉ ገጸ-ባህሪያቱ ስለ ነጻነትና ፍትህ ብዙ ቢለፍፉም በተግባር ግን ነጻነት ነጣቂ ይሆናሉ፡፡ በሀገርና ህዝብ ስም ምለው ቢገዘቱም ከጀርባ ግን በሀገርና በህዝብ ስም ይቆምራሉ፡፡ ገጸ-ባህሪያቱ ታላቅና አስተዋይ ሳይሆን አስመሳይና ጥራዝ-ነጠቅ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሌላው ቀርቶ የአብዮተኞቹ የዘመን ተጋሪ  ሆነው  በአብዮቱ ሂደት መሳተፍ ያልመረጡ ገጸ ባህሪያት ሳይቀሩ፣ አብዮተኞቹን ባላዋቂነትና በተንኮለኝነት ይከሷቸዋል፡፡ አብዮተኞቹ ያነሷቸው ጥያቄዎችና ያቀነቀኗቸው እሳቤዎች ብዙሃኑን አነሳስተው ደጋፊያቸውና የፖለቲካ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ሲሆኑ እናያለን፡፡ በእነዚህ የአዳም ድርሰቶች ውስጥ ከአብዮተኛው ትውልድ አንኳር የፖለቲካ ጥያቄዎች ባሻገር ያሉ ውስብስብ ሴራዎች በአደባባይ ይሰጣሉ፡፡ በዚህም በ’ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ’ እና በ’የስንብት ቀለማት’ ውስጥ በአብዮተኞቹ የተረቀቁና የኋላ ኋላ ተቋማዊ የሆኑ ሃቲቶች (discourses)  የቆሙበት መሰረት ይናወጻል፡፡ የሚናወጸው ደግሞ የአብዮቱ ገናን ተረኮችና ቋሚ የሚመስሉ ሃቲቶችን መልከ-ብዙ የሆነ አተረጓጎም ይሁነኝ ተብሎ በማዋለድ ነው፡፡
በአጠቃላይ ግን የአብዮቱ ዘመን ብዝሃ-መልኮች አዳም ረታ በድርሰቶቹ ይከስታል፣ ይተረጉማልም (interpret ያደርጋል)፡፡ በዣክ ደሪዳ ፍልስፍናዊ እሳቤ መሰረት፤ አብዮተኞቹ የገነቧቸው ሃቲቶችን መሰረታቸውን በመነቅነቅ መልከ-ብዙ ፍች እንዲሰጡ (deconstruct) ያደርጋል፡፡ በዚህ ጽሁፍም አዳም ረታ በድርሰቶቹ ውስጥ የአብዮቱና ከአብዮቱ ጋር የተያያዙ ሃቲቶች እንዲሁም ተረኮች እንዴት ‘ዲኮንስትራክት’ (የዲኮንስትራክሽን እሳቤ ሊሸከም የሚችል አቻ ሀገራዊ ቃል ባለማግኘቴ ቀጥታ እንግሊዝኛውን ለመጠቀም ወስኛለሁ) እንደሚያደርግ በጨረፍታ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
ጥቂት ነጥቦች ስለ ዲኮንስትራክሽን ፍልስፍና
ፈረንሳዊው ፈላስፋ ዣክ ደሪዳ (1930-2004)፤ ከድህረ-መዋቅራዊ (post structuralist) ፈላስፎች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በተለይ ለድህረ-መዋቅራዊነት ፍልስፍና እጅግ ወሳኝ የሆነው የዲኮንስትራክሽን ፍልስፍናዊ ዕሳቤ (philosophy of deconstruction) በማስተዋወቁ በይበልጥ ጎልቶ ይወሳል፡፡ ይኸ የደሪዳን የዲኮንስትራክሽን እሳቤ ደግሞ ቴክስቶችን (texts) የምናነብበት/የምናናብብበት ዘዴ ነው፡፡ በዚህ አውድ ቴክስት ስንል ጽሁፍ (ቋንቋ) ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጽንሰ-ሃሳቦችን፣ ትዕምርቶችን፣ ማህበራዊ አስተማስሎዎችን (representations)…ጭምር እንደሚያካትት ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ደሪዳ የዲኮንስትራክሽን ፍልስፍዊ እሳቤ ለማርቀቅ ምክንያት የሆነው፣ የፍልስፍና ታሪካዊ ጉዞና ዋነኛ የትኩረት ማዕከሉ “ስሁት ነው” ከሚል መነሻ ነው ይላል፤ ግራም ኤለን “Intertextuality” በተሰኘው መጽሐፉ፡፡ ከዚህ አንጻር ደሪዳ፣ ፍልስፍና በዘመናት ጉዞው የለፋውና ብዙ የጣረው ብዙዎችን የሚያስማማ የፍልስፍናዊ እሳቤ መሰረቶችን ለማነጽ ነው ( “…the project of philosophy consists largely in attempting to build foundations for thought”) በሚል መነሻነት ነው ይላል፤ ኤለን በመጽሐፉ፡፡ ይህን ቋሚ ወይም ወጥ መሰረት ለመገንባት ፍልስፍና ባደረገው የታሪክ ጉዞ ውስጥ ደግሞ አንዳንድ ርዕሰ-ጉዳዮችና ጽንሰ-ሃሳቦች ትልቅ ሞገስና ክብር ሲያገኙ ሌሎቹ ደግሞ እንደ አልባሌ ነገር ተቆጥረው ወደ ዳር ተገፍተዋል፡፡ ቦታም ተነፍጓቸዋል፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ አንድ ወጥና ቋሚ ፍልስፍናዊ እሳቤ በማነጽ፣ በአንጻሩ ‘አስፈላጊ አይደሉም’ የሚላቸውን ስለሚያገል ነው፡፡ ለዚህ ይመስላል ደሪዳ ማንኛውም አይነት “philosophical foundationalism” በስራዎቹ ውስጥ ውድቅ የሚያደርገው፡፡
 ትንሽ ርዕሰ-ጉዳዩን ካነሳነው ጭብጥ አውድ አንጻር ሲታይ፣ የዲኮንስትራክሽን ፍልስፍና በማህበረ-ፖለቲካው መድረክ ላይ በሆነ አጋጣሚ ገናን ቦታ የያዙ ሃቲቶችና ተረኮች ማዕከላዊ ሥፍራ ከያዙ በኋላ፣ ማህበራዊም ሆነ ታሪካዊ ጉዳዮችን ጭምር ይበይናሉ፡፡ የያዙትን ስልጣን-ወ-ሃይል (power) ተጠቅመው ማንበር የሚፈልጉትን ማህበረ-ፖለቲካዊ እሳቤ አይጠየቄና ተፈጥሮአዊ አድርገው በብዙሃኑ ዘንድ ያሰርጻሉ፡፡ ይህን እሳቤ ሊቃረኑ የሚችሉ ማህበረ-ፖለቲካዊ እሳቤዎችን ደግሞ እጅግ በረቀቀ ስልት ያጠለሻሉ፣ ከመድረኩም ገለል እንዲል ያደርጋሉ፡፡ በአጭሩ በደሪዳ የዲኮንስትራክሽን ፍልስፍናዊ እሳቤ፣ የአንድን ሃቲትም ሆነ ገናን ተረክ ማዕከልነት መያዝ ማለት የእያንዳንዱ ነገር ምንጭ ወይም መሰረት ተፈጥሮአዊ እውነታን አድርጎ መቀንበብ ነው፡፡
የዲኮንስትራክሽን ፍልስፍናዊ እሳቤ፣ ማዕከላዊ ስፍራን ይዘው እውነታን የሚቀነብቡ ሃቲቶች የተለያዩ አተረጓጎሞች እንዲያዋልዱ ወይም እንዲኖራቸው በማድረግ፣ የቆሙበትን መሰረት ይነቀንቃል፣ ያውካልም፡፡ ተፈጥሮአዊ እንዳልሆኑና ይሁነኝ ተብለው የተቀነበቡ የዘመን ስሪቶች መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ በዚህ ሂደትም ማዕከላዊ ስፍራ የያዙ ገናን ሃቲቶች የከለሏቸው ሌሎች ማህበራዊ እውነታዎች ወደፊት እንዲመጡ በር ይከፍታል፡፡ በሌላ አገላለጽ የደሪዳ የዲኮንስትራክሽን ፍልስፍና ዋነኛ ዓላማው፣ የሆነ ጊዜ የተቀነበቡ ብሎም ማዕከላዊ ስፍራ የያዙ ሃቲቶችና ተረኮችን በማወክ (destabilize በማድረግ) እና ይህን ማዕከላዊ እሳቤ መልከ-ብዙ ፍችዎች እንዲኖራቸው ማስቻል ነው፡፡ ይህ የደሪዳ የዲኮንስትራክሽን እሳቤ፣ በተለይ የስነጽሁፍ ስራዎች ውስጥ ያሉ መልከ-ብዙ ቴክስቶችን ለማንበብና ለመተርጎም እጅግ ጠቃሚ ዘዴ ነው፡፡ አብዮቱን ማዕከል ያደረጉ የአዳም ድርሰቶችም በዚህ መንገድ ሊነበቡና ሊፈከሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
የአብዮቱ ዳናዎች በአዳም ድርሰቶች
በአዳም የፈጠራ ድርሰቶች ውስጥ አብዮቱ ያነጻቸው ማህበረ-ፖለቲካዊ ሃቲቶች ተፈጥሮአዊና አይጠየቄ ሳይሆኑ ይሁነኝ ተብሎ የተዋቀሩ መሆናቸው በገጸ-ባህሪያቱ አማካይነት ይተረካል፣ ይፈከራልም፡፡ ገጸ-ባህሪያቱ፣ የአብዮቱ ዘመን ሃቲቶችና ተረኮች የተለያዩ አተረጓጎሞች እንዲሰጡ በማድረግ ቋሚ ፍች ይዘው እንዳይቀጥሉ አብዮተኞችን ይቀናቀናሉ፡፡ ከእያንዳንዱ ገናን ተረኮች ባሻገር ያሉ ውስብስብ ሴራዎችና ድርጊቶችን ወደፊት በማምጣት፣ እሳቤዎቹ ወጥ የሆነ መሰረት እንዳይዙ ያደርጋሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት በዋነኛነት የአብዮቱ ዘመን ትዕምርቶችና ሃቲቶችን ዲኮንስትራክት በማድረግ ነው፡፡
በ”ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ድርሰት ውስጥ፣ የቀድሞ አብዮተኛ-የ’አሁኑ’ ስደተኛ አለሙ በትውስታ ወደ አብዮቱ ሰሞን ተጉዞ ህይወቱን ይተርክልናል፡፡ አለሙ ትውስታውን የሚተርክልን በአብዮተኛነቱ ጊዜ በ’ኢምፔሪያሊስት’ነት ያወገዛት እንግሊዝ ለንደን ውስጥ ካለው መኝታ ክፍሉ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ አለሙ ስላሳለፈው ጊዜ በጸጸት ይብሰለሰላል፡፡ ስለ ልጅነቱ፣ ስለ ጎረቤቱ፣ ስለ አብዮቱና በአብዮቱ ሰሞን ስለሆኑ ጉዳዮች ውድቀቱን ይናዘዛል፡፡ ሽንፈቱን ያለመሸፋፈን ይናገራል፡፡ ራሱን ደጋግሞ ይወቅሳል፡፡ የዘመን ተጋሪዎቹንም ይሄሳል፡፡ በአጠቃላይ ያለፈባቸውን ሰባቱን ጠመዝማዛ የህይወት መንገዶች፤ ማለትም ከተወለደበት ቤት እስከ በስደት ለንደን ከተማ ላይ እስከተጠለለባት መኝታ ክፍሉ ይተርክልናል፡፡ ከትረካው ይዘትና ድምጸት በመነሳት አለሙ ‘ታገልኩለት’ የሚለው ጉዳይ ሁሉ የነጻነት ትግል ሳይሆን ‘ቅዠት’ እንደነበር በጸጸት ይብሰከሰካል፡፡ አብዮቱ ላይ በራሱ አመዛዝኖ የተሳተፈበት ሳይሆን፣ የብልጣ ብልጥ ፖለቲከኛ አብዮተኞች የፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንደነበር ይናዘዛል፡፡ በእውቁ ስሎቬኒያዊ ፈላስፋ ስላቮይ ዢዤክ አገላለጽ፤ አለሙና የዘመን ተጋሪዎቹ በ”ርዕዮተ-ዓለማዊ ፈንጠዚያ” (Ideological fantasy) ቅንባቤ ውስጥ ገብተው እናገኛቸዋለን፡፡ እስኪ ከ”ይወስዳል መንገድ…” (ገጽ፣ 137) አንድ ሰበዝ እንምዘዝ፤
“ገና የሕይወት አቡጊዳን እንደቆረስኩ፣ የታላላቅ አባቶቼን ድርሰት የሰደብኩት እዚህ [ተወልጄ ያደኩባት መንገድ ላይ] ነው፡፡ ተደነቅሁም፡፡ ማነው ያደነቅኸኝ? ይኼም ባይሆን ልክፍታችንን ይዘን ቅዱስ በቅዠት ጎሳው፣ እኔም በቅዠት ጎሳዬ ወደ ማጥ በድፍረትና በቁጣ ገባን፡፡ ‘ኢንተርናሲዮናል’ በጉርምስናዬ ዘምሬ፣ ሥለ ዓለም አንድ መሆን ሰብኬ ብዙ ሳልቆይ የተመረረ መንደርተኛ የሆንኩት እዚህ ነው…”
አለሙ በአብዮቱ ዘመን ስላሳለፈው ጊዜ ነው እየተረከልን ያለው፡፡ የዘመኑን መንፈስ ገልጦ እያሳየን ጭምር፡፡ ሶሻሊስታዊ ዓለም አቀፋዊነትን በዘመረበት አፉ በፍጥነት ተከርብቶ ወደ ተመረረ “ጎሰኝነት” ሽግግር ማድረጉን እየነገረን ነው፡፡ እንዴት ይሄ ሊሆን ቻለ? ምክንያቱም በዓለም አቀፋዊነትና በጎሰኝነት መካከል ያለው ርቀት እጅግ ሰፊ ነውና፡፡… ያ “ተራራውን ያንቀጠቀጠ ትውልድ”፣ ያ በአንባቢነቱ “አቻ ያልተገኘለት” ትውልድ፣ ያ ለነጻነት እና ለፍትህ፤ ለህዝቦች እኩልነት እና ዴሞክራሲ ውድ ህይወቱን “ሰውቷል” ተብሎ የሚነገርለት ትውልድ… የአባቶቹን ድርሰት “መስደብ”ን የአብዮተኛነት መገለጫ እንዴት ሊያደርገው ቻለ? ቅድመ አብዮት የነበሩ ማህበረሰባዊ እሴቶችን ትንሽ እንኳን ሳይመረምር በጅምላ ውድቅ ለማድረግስ እንዴት ደፈረ?...በአዳም ድርሰቶች ውስጥ የምንተዋወቃቸው አብዮተኛ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የወል መገለጫቸው ይኸው ሃገራዊ የሆነን ነገር ሁሉ ማንቋሸሽና ማጥላላት ነው፡፡
  እውቁ ፈላስፋና ሳይካትሪስቱ ፍራንዝ ፋኖን ‘Black Skin, White Masks’ በተሰኘው መጽሐፉ እንደሚያስገነዝበው፤ የዝቅተኝነት ምስቅልቅሎሻዊ ስሜት (Inferiority complex) ራስን ካለማወቅና ራስን ከመናቅ ይመነጫል፡፡ ይኸ ራስን የመናቅ ሂደትን ደግሞ በተለይ ከአዕምሮ ቅኝ መገዛት ጋር በቀጥታ ያያይዘዋል፡፡  ፋኖን የጥቁሮች የዝቅተኝነት ሥሜት ምንጩ፣ የቅኝ-ግዛታዊ ሃቲት “Colonial discourse” ነው ሲል እንዲህ ይገልጿል፡- ቅኝ-ግዛታዊነት፣ ቅኝ ተገዢውን ማህበረሰብ ወይም ግለሰብ የተፈጥሮ ሃብቱን ከመበዝበዙ ባሻገር ከሰውነት ደረጃ በታች እንደሆነ እንዲያስብ  (Dehumanize) ማድረግና ከቁስ ጋር የሚተካከል ማንነት እንዳለው በተለያዩ ሃቲቶች አማካይነት ማስረጽ ነው፤ (“…colonialism not only exploits but dehumanize and objectifies the colonized subject”)፡፡ ይህን የቅኝ-ግዛታዊነት እሳቤ በተለይ የውጭ ትምህርት፣ ባህልና ርዕዮት ዓለምን ሳያመዛዝኑ እንደወረደ በመቀበል የግለሰቦችን አተያይ ይቀርጻል፡፡ የቅኝ-ግዛታዊ ሃቲት ሰለባ የሆኑ እነዚህን ግለሰቦችም የበቀሉበትን ማህበረሰብ እሴት በቅጡ ሳይመረምሩ በደፈናው ማንቋሸሽና ጥቅም አልባ አድርገው መፈረጁን ተክነውበታል፡፡ ምክንያቱም የቅኝ ግዛታዊ-ሃቲት እንደወረደ ተግተዋልና፡፡ የ’ይወስዳል መንገድ…’ አለሙም ሆነ የአለሙ የትውልድ ተጋሪዎች የዚህ ሰለባ ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም የማህበረሰቡን እሴት ማንቋሸሽና ዋጋ ማሳጣት የሃቀኛ አብዮተኛ መገለጫ እንደነበር የአለሙና ሌሎች የዘመኑ አብዮተኛ ገጸ-ባህሪያት መገለጫ ነውና፡፡
በ’የስንብት ቀለማት’ ድርሰት ውስጥ የባህልና ኪነት ሃያሲ ሆኖ የምናውቀው ገጸ-ባህሪ ዮሀንስ ወላይሶ፣ የአብዮተኛው ትውልድ መንገድ እንዴት አዕምሮው በቅኝ እንደተገዛ ሲገልጽ፤  “ባዴ [ፈረንጅ] የተለየ ብሩህ አይደለም ብለው የነዘነዙኝ በባዴ ቅኝ ገዥዎች ራሳቸውን እንዲጠሉ ጥልቅ ትምህርት የወሰዱና ዛሬም ከእነሱ እግር ስር የማይጠፉ፣ ወገናቸውን ባዴ በቀደደላቸው መንገድ የሚቀረቅቡ ነጋዴዎች ናቸው” (የስንብት ቀለማት፣ 23)፡፡ በእርግጥ አብዮተኛው ትውልድ ከገዛ ማህበረሰባዊ እሴቶቹና እውቀቶች የተነጠለ፣ እያንዳንዱን የማህበረሰቡን ታሪክና ችግሮች በማርክሲዝምና ሌኒኒዝም ርዕዮተ-ዓለም አንጻር በይኖ የሚረዳ፣ የማህበረሰቡን ችግር የሚ’ፈታውም በዚሁ ርዕዮተ-ዓለም ማዕቀፍ ብቻ ነው ብሎ ቢያንስ በጽንሰ-ሃሳብ ደረጃ ያቀነቀነ ትውልድ ነው፡፡ በጽንሰ-ሃሳብ ያልኩት፣ የፍልስፍና ምሁሩ መሳይ ከበደ (ፕ/ር) ‘Radicalism and Cultural Dislocation in Ethiopia, 1960-1974’ በተሰኘው መጽሐፉ፤ ትውልዱ ከማህበረሰቡ እሴትና አስተሳሰብ የራቀ እንደነበር አጽንኦት ይሰጥና ማርክሲዝምና ሌኒኒዝም ግን ስልጣን ለመያዝ እንደ መሳሪያ ለመጠቀም በልሂቃኑ (በአብዮቱ መሪዎች) የሚቀነቀን ርዕዮተ-ዓለም እንደነበረ አስረግጦ ስለሚናገር  ነው፡፡ በኋላ የአብዮቱ ዘመን ልሂቃን ከሶሻሊስታዊ አለምአቀፋዊነት ወደ ዘውጋዊነት ሽግግር ያደረጉትም፣ የዘውግ አደረጃጀት የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ይበልጥ ያግዛል በሚል ስሌት እንደሆነም ያክላል፡፡ እዚህ’ጋ ማስታወስ የሚያስፈልገው አንድ ጉዳይ የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም እሳቤም ምንጩ አውሮፓ፣ ራሱ ርዕዮተ-ዓለሙም ቢሆን አውሮፓ-ተኮር (eurocetric) መሆኑን ነው፡፡
አለሙ ይቀጥላል፤ “ከ’ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል’ ወደ ሆድ ያባውን ንቃት ያወጣዋል የተሸጋገርኩበት …እዚህች መንገድ ጠርዝ ያለች አንዲት አልባሌ [የሰፈሬ] ሱቅ ጀርባ ለጥናት ተጎዝጉዤ ነው፡፡ የፓምፍሌት ደካማ ዕውቀት ከቅራሪ የቀጠነ…እዚህ ነው በጣቶቼ ጠቅሼ የጠባሁት፡፡ ‘ከአስተማርናችሁ አትጨምሩ አትቀንሱ’ የተባልነው፡፡ ወረቀት ቀይ ቀብቼ ለላብአደሩ የጮህኩ እዚህች ቤት መከዳ ላይ ነው፡፡ ሳራ ‘ባንዳ ናት’ የተባልኩት፡፡ ሳራም ‘ከሀዲ ነው’ እንደምትለኝ የሰማሁት…” (ይወስዳል መንገድ…ገጽ 118)፡፡
በአንባቢነቱና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በመረዳት ‘አቻ የለውም’ በሚል ውዳሴ በራሱ በ “ያ ትውልድ” ( ያ ትውልድ ኢህአፓን ብቻ ሳይሆን መኢሶንን፣ ደርግን፣ ህወሃትን፣ ኦነግን፣ ሻዕቢያን፣ ኢጨአትን… ያካትታል) የጎረፈለት አብዮተኛው ትውልድ፤ “በፓምፍሌት ዕውቀት” ነበር አብዮተኛ የሆነው? እንዲሁም “ከአስተማርናችሁ አትጨምሩ አትቀንሱ” በሚለው የድርጅቶቻቸው ‘ቀኖና’ ጭምር ተከታዮቻቸው ይገ’ዙ እንደነበር ዓለሙ ያወጋናል፡፡ ይህም እንደሚባለው አብዮተኛው ትውልድ የወጣበትን ማህበረሰብ ጥንካሬዎችና ድክመቶች በሃገራዊ ርዕዮት ታግዞ ትንሽም ለመመርመር ‘ያልፈቀደ’፣ በፓምፍሌት ዕውቀት ‘ድንገት የነቃ’ እንደነበር ይሁነኝ ተብሎ በአለሙ አማካይነት ዲኮንስትራክት ያደርጋል፡፡
 “በድቅድቅ ሌሊት ‘አምባገነን ፋሽስታዊ የምርጥ መኮንኖችን መንግስት ለመጣል’ የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ላይ ተቃውሞዬን ሰቅያለሁ፡፡ በየቀዳዳው አብራኝ ስላልሆነች የወዳጄን የሳራ ስም አጥፍቼአለሁ…ስሟን ለበላይ ‘የባንዳ ሸርሙጣ’ ብዬ አስተላልፌያለሁ፣ አብሬአቸው ያደግሁት ሁሉ ካሱን [የሳራ ወንድም] ጨምሮ የተቀጪ ስም ዝርዝራቸውን አንብቤያለሁ፡፡ አብሮ ማደግን ፉርሽ አደረግናት፡፡ በልጅነቴ በሰበሰብኩት ዕውቀትና መታመን ገበና በማወቄ…ሳራን አስገድያለሁ፡፡ ካሱን ሰቅዬዋለሁ…’ፍቅር መደባዊ ነው አልኩ…’” (ይወስዳል መንገድ…118)፡፡
ሳራ ለአለሙ ጎረቤቱ ብቻ አልነበረችም፡፡ የልጅነት ትውስታውና እውነቱ ጭምር እንጂ፡፡ “ሳራ ዕውነቴ ነበረች” ይለናል፤ አለሙ በገዛ አንደበቱ፡፡ ምክንያቱም አለሙ በልጅነቱ ሲስቅና ሲጫወት እጎኑ ሳራ ነበረች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴት ጡት ተደብቆ ሲያይ የተለየ ስሜት የተሰማው የሳራን ጡት ያየ ጊዜ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴት እጅ ነክቶ የስሜት መናወጽ ውስጥ የገባው የሳራን እጅ ሲነካ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴት ጉንጭ ስሞ በአዲስ አይነት የስሜት ፀዳል ውስጥ የገባው የሳራን ጉንጭ የሳመ ዕለት ነው፡፡ ታዲያ አለሙ ከዚህች የልጅነት ዕውነቱ፤ የልጅነት ህልሙ’ጋ በአብዮቱ ምክንያት ደም ተቃብቷል፡፡ “የባንዳ ሸርሙጣ ነች” ብሎ አስገድሏታል፡፡ ከትናንት አብዮተኛ ከ’ዛሬ’ው ስደተኛ አለሙ አንደበት የምንሰማው ኑዛዜ፣ አብዮቱ የ”ጀብደኝነት” እና የ”ጀግነነት” ታሪክ ብቻ ሳይሆን የ”ነውረኝነት” እና የእርስ በእርስ “መገዳደል” ታሪክም መሆኑን ነው፡፡ ገናን በሆኑ በአብዮቱ ተረኮች የተሸፈኑ ነውረኛ ድርጊቶችን አለሙ ወደ መድረኩ ያመጣቸዋል፡፡ አብዮተኞቹ ካነሷቸው (ለአብነትም የብሄረሰቦች መብት፣ መሬት ላራሹ፣ ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም…) ጥያቄዎች ባሻገር ያሉ የዘመኑ ሌላኛው መልኮች አለሙ የትረካው አቢይ ማጠንጠኛ ያደርጋቸዋል፡፡     
በተለይ በ’የስንብት ቀለማት’ ኪናዊ ድርሰት ውስጥ የአብዮተኞቹ ልጆች፣ በወላጆቻቸው (በያ ትውልድ) ላይ የሰላ ትችት ያቀርባሉ፡፡ የአብዮተኛው ትውልድ ከፋፋይ እሳቤዎችን ያጠይቃሉ፡፡ በ’የስንብት ቀለማት’ ውስጥ ዲምቢዶሎ ተወልዶ ያደገው ገጸ-ባህሪ ዶ/ር ዮሴፍ ይናገራል፤ “…እኔን ዶክተር ያደረጉኝ ስማቸውንና ፊታቸውን የማላውቃቸው የአገሬ ሰዎች ሁሉ ናቸው፡፡ የድሮ ፊታውራሪዎች በጡት መጠን፣ በባርያ ሽሚያ፣ በከብት ብዛት፣ በጭኮና በጮማ ሲጣሉ ኖሩ እንጂ ዲሞክራሲ ሲያበጁ አልተጣሉም፡፡ ዶክተር ሆኜ ከእነሱ ልነስ እንዴ? ሰው ጨረቃ ላይ ሲወጣ፣ በግስና በተውሳከ ግስ አጠራር ከወገኔ ልለያይ? የታደለ ሐኪም ለብዙ አይነት አስቸጋሪ በሽታዎች መድሃኒት ሲያገኝ፣ እኔ በሽታ ልፍጠር? ማነኝ ሳያዳላና ሳይፈርጀኝ ያበላኝን፣ ያሳደገኝን ገበሬ በቋንቋ የመሸንሸን መብት የሰጠኝ?... በሽታ ቋንቋ የለውም፡፡ ወባ ፍሬንች፣ ጀርመንኛ፣ ዶርዝኛ አትናገርም…” (የስንብት ቀለማት፣238)፤ ሲል አብዮተኛው ትውልድ የነበረውን ማህበረ-ፖለቲካዊ ስርዓትን ያጠይቃል፡፡ እዚህ’ጋ ዘውጋዊ ማንነት የሁሉ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ አድርጎ መበየንን፣ ህዝቡን በዘውጋዊ ማንነቱ ከፋፍሎ የፖለቲካ ማህበረሰብ ማዋቀርን… የአብዮቱ ‘ትሩፋት’ እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ አብዮተኛው ትውልድ የነበረው ይኸ ማህበረ-ፖለቲካዊ ርዕዮት  እንደሚባለው ድሃውን ማህበረሰብ ለመጥቀም ሳይሆን በድሃው ማህበረሰብ ላይ ሌላ ‘በሽታ መፍጠር ነው’ በሚል ጠንከር ባለ ድምጸት ይናገራል፤ ዶ/ር ዮሴፍ የአብዮቱ ሃቲቶች ሌላኛው ገጻቸውን ገልጦ እያሳየን፡፡
በ’የስንብት ቀለማት’ ውስጥ ምኒሊክና ጸጋ ስላለፈው ህይወታቸው ያወራሉ፡፡ ስለ አብዮቱ ጊዜና ስለ ልጅነታቸውም ጭምር ነው የሚጨዋወቱት፡፡ ፀጋ “አብዮተኛ ነበርኩ” ለሚለው ሚኒሊክ እንዲህ በማለት ይወቅሷል፤ “ታሪክህን…ቆፍረው፣ አጥናው፣ በአዕምሮህ አመላልሰው፡፡ ለሚመጣ ትውልድ ጀግና ሳትሆን ኮንዶም እንደነበርክ መንገር አለብህ፡፡ አለበለዚያ ሌላውም እዛ ውስጥ እንደገና ̍ያን ትውልድ ልምሰል̍ ብሎ ይገባል፡፡ ንገረው፡፡ ደፋር ነበርኩ ግን ደግሞ ከብት ነበርኩ ብለህ…” (የስንብት ቀለማት፣ 360)፡፡
በአጠቃላይ በአዳም ድርሰቶች ውስጥ አብዮተኞቹ የገነቡትና እየገነቡት ያለው ገናን ተረክ ውስጡ አየር የሞላው አፉፋ (ፊኛ) መሆኑን ገጸ-ባህሪያቱ ይተርኩልናል፡፡ የአብዮቱ ዘመን ስንክሳሮች የጀግንነት ሳይሆኑ ማህበረሰቡን ያስተሳሰሩ የመተማመን ክሮች ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል እንዲበጠሱ የተደረጉበት፣ በጎረቤታሞች መካከል መጠራጠርና መጠላላት የሚባለው የተንኮል ዘር የተዘራበት፣ ጭቃ አቡክተው ያደጉ አብሮ አደግ ጓደኛሞች ለድርጅታቸው ሲሉ ለመገዳደል ያላመነቱበት፣ የየትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት ርዕዮት የማይጋሩና ዘወትራዊ ህይወታቸውን ለመምራት የሚጥሩትን ግለሰቦች የሆነ ታርጋ ለጥፎ ስማቸውን ማጥፋት እንደታላቅ የፖለቲካ ስልት የተወሰደበት፣ ማጭበርበርና ማታለል የአብዮቱ ማጀቢያ ሙዚቃዎች እንደነበሩ በአዳም ድርሰቶች ውስጥ በስፋት ይንጸባረቃል፡፡
በአንጻሩ የአዳም ድርሰቶች ውስጥ ልሂቃኑ (የአብዮቱ መሪዎች) ‘መንቃት አለበት’፣ ‘እናንቃው’፣ ‘እናስተምረው’ የሚሉት ድሃው “ሰፊው ህዝብ” ሀገርህ ተወረረች ሲሉት የሀገሩን ነጻነት ለማስከበር የማያመነታ፣ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ሃገሩን ለመታደግ ወደ ጦር ግንባር የዘመተው ‘ህዝብ’ ግን መሳለቂያ ሲሆን እናነባለን፡፡ በድርሰቶቹ ውስጥ ድሃው ማህበረሰብ ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን፣ በዘወትር ህይወቱ የቋንቋና የሃይማኖት ድንበር ሳይግደው አብሮ ለመኖር፣ እርስ በእርስ ለመተማመንና ለመረዳዳት ወደ ኋላ የማይል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አሳዛኙ ነገር የዚህ ድሃ ማህበረሰብ የህይወት ዘይቤን በማናቀፍና ድንበር በመከለል ሊያግዱት የሚጥሩት ደግሞ አብዮተኛ ፖለቲከኞች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
በአጠቃላይ በእነዚህ በሁለቱ የአዳም ረታ ድርሰቶች ውስጥ የአብዮቱ ዋነኛ ገናን ተረኮች ይፈተናሉ፣ ይሞገታሉም፡፡ የሚፈተኑትና የሚሞገቱት የአብዮቱ ገናን ተረኮች ይሁነኝ ብለው እንዳይታዩ ወይም እንዲደበዝዙ ያደረጓቸው ድርጊቶችን ወደ ፊት በማምጣት ነው፡፡ ወደ ፊት የመጡት የአብዮቱ ሌላኛው መልኮች ደግሞ የአብዮቱ ማዕከላዊ እሳቤዎችን ያነጽራሉ፣ ያጠይቃሉም፡፡ ይሁነኝ ተብለው የደበዘዙ የዘመኑ ጥዩፍ ድርጊቶች ከጀርባቸው የያዟቸው ሴራዎች ይገለጣሉ፡፡ በዚህ የተነሳ በአብዮቱ ጊዜ የተቀነበቡ ብሎም ማዕከላዊ ስፍራ የያዙ ሃቲቶችና ተረኮች በድርሰቶቹ ውስጥ ይታወካሉ፡፡ አብዮቱ ያነበራቸው ሃቲቶች፣ መልከ-ብዙ ፍችዎች እንዲኖራቸው በማድረግ ዘመኑን ከሌላ ማዕዘን እንድንመለከተው በገጸባህሪያቱ አማካይነት ይነገረናል፡፡


Read 529 times