Saturday, 23 March 2024 20:34

ልብ ወለድ እና ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች

Written by  -መኮንን ደፍሮ-
Rate this item
(1 Vote)

መግቢያ
     ይህ ኂሳዊ መጣጥፍ ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ (2012) በተሰኘ በእሱባለዉ አበራ ንጉሤ የተጻፈ ረጅም ልብ ወለድ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይኸ ሥራ በርካታ ጠጣር የህልዉና ጉዳዮች በጥልቀት የተዳሰሱበት፣ የደራሲዉንም በሳልነት የመሰከረ ሸጋ ሥራ ነዉ፡፡ በእዚህ ሥራ እሱባለዉ በሥነ ጽሑፍ እና በፍልስፍና መካከል ያለዉ መስመር ቀጭን መሆኑን አሳይቷል፡፡  
እሱባለዉ በይነቴክስታዊነት (intertextuality) (የአማርኛ ፍቺዉ የአቶ ቴዎድሮስ ገብሬ ነዉ) የተሰኘዉን የልብ ወለድ አጻጻፍ ይትባህሎች በሥራዉ ዉስጥ ተግባራዊ ያደረገ ደራሲ ነዉ፡፡ በይነቴክስታዊነት ከድህረ ዘመናዊ የልብወለድ አጻጻፍ ይትባህሎች መካከል እንዱ ነዉ፡፡ በይነቴክስታዊነት ቬርዶንክ (2002)፣ ካርተር (2006) እና ኒኮል (2009) እንደ ጻፋት፣ ቀድመዉ የተሠሩ የጥበብ ሥራዎችን በድርሰት ሥራ ዉስጥ ሰንጎ ማቅረብ ነዉ፡፡
ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ በዘዉጉ አስማተ ዓለም (magical realism) ልብ ወለድ ነዉ፡፡ ይህ ሥራ ሕይወት የተባለ የሰዉ ልጅ መከራ (agony) በጥልቀት የተቃኘበት ድርሳን ሲሆን፤ ኢ-ርቱዕ (nonlinearity) በሆነ የአተራረክ ዑደት የሚፈስ፣ በአንደኛ መደብ እና በሦስተኛ መደብ ሁሉን አወቅ የትረካ አንጻር የቀረበ ነዉ፡፡
ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ በአማርኛ ቋንቋ ከተጻፉ በጣት ከሚቆጠሩ ፍልስፍናዊ ልብወለዶች (philosophical novels) መካከል አንዱ ነዉ፡፡ ደራሲዉ በእዚህ ሥራ ዉስጥ በጥልቀት የፈከራቸዉ ዐቢይ ጭብጦች ትዝታ፣ ወለፈንድ፣ ቀቢፀ ተስፋ፣ ወረት፣ የሕይወት ቋሚ ትርጉም አልባነት እና ፍቅር ሲሆኑ ይኸ ኂሳዊ መጣጥፍም በእነዚህ ጭብጦች ላይ ያተኮረ ነዉ፡፡
፩. ትዝታ
የእሱባለዉ ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ከሌሎች የሀገራችን ደራሲያን የድርሰት ሥራዎች በተለየ የትዝታን (remaincence) ፅንሰ ሐሳብ በጥልቀት የመረመረ ሥራ ነዉ፡፡ እሱባለዉ እንደሚነግረን፣ ሰዉ ትናንቱን እየዘከረ እንዲኖርና እንዲናፍቅ ተኮንኗል፡፡ በመሆኑም፣ ትናንቱን መርሳት አይችልም (እሱባለዉ፣ 2012)፡፡ ትዝታ ትናንት ብለን የምንጠራዉ የጊዜ ምዕራፍ ነዉ፡፡ እንደ እሱባለዉ አተያይ፣ ትናንት ከዛሬ እኛ ቢርቅም ረጅም እጁን ሰዶ ሕይወታችንን የመዘወር ኃይል አለዉ፡፡ ትናንት ዛሬያችን ላይ የሚፈጥረዉ ተፅእኖ ኃያል ነዉ፡፡ ዘመን ሲያልፍ የኋሊት ይርቃል እንጂ አይሞትም፣ ህያዉ ነዉ፡፡ እሱባለዉ መለያየት ንዑስ ርእስ እኮ ልብን አንዴት ይገስጿል? የተሰኘ ርዕስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ የሚከተለዉን ጽፏል፦  
በሥራ አጋጣሚ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የማዉቃትን ልጅ አገኘኋት፡፡ ‘ኤል’ ትባላለች፡፡ በልጅነት አፈቅራት ነበር፡፡ ሻይ ቡና ተባባልን፡፡ በጨዋታ በጨዋታ ስናወራ ‘ያኔ’ የጻፍኩላት ደብዳቤዎች ዛሬም በቤቷ እንዳሉ ነገረችኝ፡፡ አልረሳችኝም፡፡ በእሷም ትላንትና ዛሬ ዉስጥ ዋጋ እንደተሰጠኝ በክብር አለሁ፡፡ የተጠፋፋነዉ ድንገት ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ያለፈ ሕይወቴን በትዝታ ስበረብር ትላንቴ ዉስጥ ያልተመለሰች ጥያቄ ሆና የማገኛት እሷን ነዉ፡፡ ‘ያ’ ያላለቀ ፍቅር ይከነክነኝ ነበር፡፡ እና ጊዜ አልፎ ‘ኤል’ን በአካል ሳገኛት ‘አሁኔን’ ጥያቄ ዉስጥ ከተትኩ፡፡ ትላንቴ ዉስጥ የነበረች አንዲት ትዝታ የተረጋጋ ዛሬዬን ትፈትነዋለች ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ የጀመርኩት ግን ያልጨረስኩት የልጅነት ፍቅር ይጠራኛል፡፡ እንዴት ብዬ ልቤን መገሰጽ እችላለሁ? ኤል ምኞቴ ነበረች፡፡ ምኞቴን የመኖር ዕድል ሲገጥመኝ እንዴት ረግጬ አልፋለሁ? (እሱባለዉ፣ 2012፣ገጽ 107-108)፡፡
ትዝታ የሚወለደዉ ከቁስ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ካለን ጥብቅ ቁርኝት ነዉ፡፡ የትዝታ ድንገተኝነት እሱባለዉ እንደሚነግረን፣ ልክ እንደ ትንታ ነዉ፡፡ በመሆኑም፣ የትኛዉም ኩነት በየትኛዉም ጊዜና ቦታ ትዝታን ቀስቅሶ ትካዜ ዉስጥ ሊከተን አልያም በናፍቆት ሊያንሰፈስፈን ይችላል፣ መከሰቻ መንገዱ ዉስብስብ ነዉ፡፡ እሱባለዉ ሕዋ ንዑስ ርእስ የጠፈር ባይተዋር የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ የሚከተለዉን ጽፏል፦        
የትዝታን ፈረስ በምን ‘ቼ’ ይሉታል? ወዲህ ወዲያ ሲዋልል የምናዉ አሮጌ በር ‘ቼ’ አያስብልም? ዝገቱና ንቅናቄዉ ከሕይወታችን አንዱ ሰበዝ ጋር በሆነ መንገድ ቢዛመድስ? የአሮጌ በር መቀርቀሪያ … ማስታወስ ከማንፈልገዉ የክፉ ሰዉ ትዝታ ጋር ቢዛነቅስ? እንዲያዉ በባዶ ሜዳ ‘እህህ’ እያልን መቅረታችን አይደለምን? በዚህ ትዝታ ስንረታ ለስንተኛና ጊዜ ነዉ? በልጅነት የቀመስናቸዉ ኩርኩሞች በጉልምስናችን ሲታወሱን… መች ሳሳ ይላሉ? የትላንቱ ጥንካሬያቸዉ ዛሬም ባለበት አይደል?  
ማንን በምን እናስታዉሳለን? የእንቅስቃሴዎች፣ የጠረኖች፣ የቀለማቶች፣ የድምፆች፣ የግዑዛን ቅርጾች ዉልብታ ጣፋጭ ወይም መራራ ትዝታን ይቀሰቅስብናል፡፡ ትዝታ ከየት እንደሚነሳ በዉል እንደማናዉቀዉ ነፋስ ነዉ፡፡ ሲደርስብን እንደ ስጥ እንበተናለን፣ እንተራመሳለን፣ እንረበሻለን፡፡ ለትዝታዎቻችን ያለን ስሜት እንደምናስታዉሰዉ ነገር ይወሰናል፡፡ ምናልባት እንፈግጋለን፣ እንኳሻለን፣ እንተክዛለን፣ እንናፍቃለን፣ እናለቅሳለን፣ እንቆጣለን፣ እንመረራለን፡፡ ያማረ ትላንት ለሌለዉ ሰዉ ትዝታ ምንድር ነዉ? የሚያጥወለዉል፣ እንቅልፍ የሚያሳጣ፣ ልብን የሚያከብድ፣ ኀዘን ላይ የሚጥል በሽታ አይደለምን? (እሱባለዉ፣ 2012፣ገጽ 13-14)፡፡
ትዝታ ግለሰቦች ኩነቶችን የተረጎሙበትን ዉስብስብ መንገድ መሠረት ያደረገ በመሆኑ አሉታዊ ወይም አወንታዊ ገጠመኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ለኩነቶች ያለን ሥነ ልቡናዊ አተያይ በአብዛኛዉ ግላዊ ነዉ፡፡
፪. ወለፈንድ
የህልዉና ወለፈንድነት (the absurdity of human existence) እሱባለዉ በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ዉስጥ የዳሰሰዉ የአብዘርዲዝም ፍልስፍና ጭብጥ ነዉ፡፡ የወለፈንድን ጽንሰ ሐሳብ በጥልቀት በመፈከር በስፋት የሚታወቀዉ ፈረንሳዊዉ ፈላስፋ እና ደራሲ አልበርት ካሙ ነዉ፡፡ ካሙ እንደሚነግረን፣ ሕይወት ከንቱ ነዉ (ፖጅማን፣ 2006)፡፡ የህልዉና ከንቱነት ስሜት አንዱ መንስኤ በሰዉ ልጅ ፍላጎትና ለሰዉ ልጅ ፍላጎት መልስ አልባ በሆነዉ ደንታ ቢሱ ሁለንታ መካከል ያለ ግጭት ነዉ (ካሙ፣ 1955፤ ቤኔት፣ 2001፤ ፎለይ፣ 2008)፡፡ በተመሳሳይ እሱባለዉ እንደሚነግረን፣ ጨረቃና ከዋክብት ኅሊና ቢስና ባዳ ፍጥረታት በመሆናቸዉ የሰዉን ልጅ ሐዘንና ደስታ አይጋሩም፡፡ ባዳዋ ጨረቃ የሰዉን ልጅ ዕንባ አታብስም፣ ባይተዋሮቹ ከዋክብት ጠፈር ላይ በመንቦግቦግ ፈንታ ጥልቅ ሐዘናችንን ተጋርተዉ ከል መምሰልን አያዉቁም፡፡ እሱባለዉ መዲናና ዘለሰኛ ንዑስ ርእስ እኔ መች መረጥኩኝ ለብቻዬ እንጉርጉሮ? የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ የሚከተለዉን ጽፏል፦        
የነፍሴን ስርቅታ በጉያዬ ታቅፌ ኅብረ ሰማይ እመለከታለሁ፡፡ እንደ ጥቁር ግምጃ በተንጣለለዉ ሰማይ ላይ ከዋክብት ፈስሰዋል፡፡ በእኔና በከዋክብቱ መካከል በሚልየን የሚቆጠሩ የብርሃን ዓመታት ይዋልላሉ፡፡ የማያልቅ ሰማይ፣ ብትን ከዋክብት፣ ሽራፊ ጨረቃ ለከፋዉ ሰዉ ምንድር ናቸዉ? ማማር እንጂ ማሰብ በዉስጣቸዉ የለም፡፡ ከዋክብት የታከተን ገላ አያቅፉም፡፡ አመድ ለብሶ የተረሳን ከንፈር ‘እፍፍ’ ብለዉ ትቢያዉን አራግፈዉ በፍቅር አይስሙም፡፡ ዉስጡ በሐሳብ ስርዝ ድልዝ የተሞላን የራስ ጠጉር በጣቶቻቸዉ አያሻሹም፡፡ ደረቅ ሃቅ ነዉ – ጨረቃ አንጎል የላትም፡፡ ከከዋክብትም እንደ አንዱ አይደለሁም፡፡ ሕይወቴ ብርሃን የለዉም፡፡ ወደ ወስጤ ስመለከት ድቅድቅ ጨለማን አያለሁ፡፡ ያልታከተኝ ዉበት ምንድር ነዉ? (እሱባለዉ፣ 2012፡ገጽ 21)፡፡                       
፫. ወረት
እሱባላዉ በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ዉስጥ በጥልቀት ከዳሰሳቸዉ ጭብጦች መካከል አንዱ ወረት ነዉ፡፡ ወረት የጊዜ ህልፈት ወይም ለዉጥ ነዉ፡፡ በእዚህ ወሰን አልባ ሁለንታ ዉስጥ ያለ ነገር ሁሉ የለዉጥ ሕግ ተገዢ ነዉ፡፡ ሄራቅሊጠስ የተባለ የጥንት የግሪክ ፈላስፋ እንደሚነግረን፣ ሁሉም ነገር ኃላፊ ነዉ፡፡ በተመሳሳይ፣ እሱባለዉ በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ዉስጥ እንደ ጻፈዉ፣ በእዚህ ተለዋጭ ዓለም ፀንቶ የሚዘልቅ ነገር የለም፣ ፍቅር ነጥፎ ጥላቻ ይነግሳል፣ ወዳጅነትም ይቀዘቅዛል፣ ዉበትም እንደ ጧት ጤዛ አመሻሽ ላይ ይረግፋል (እሱባለዉ፣ 2012)፡፡
እሱባለዉ እንደሚነግረን፣ የሰዉ ልጅ በዕድሜዉ የከወነዉ እያንዳንዱ ተግባር በወረት እንዳልነበር ይሆናል፡፡ ጠዋት ባለፍንበት የሕይወት መንገድ ማታ ብናልፍ ከትዝታ በቀር በቦታዉ ያሳረፍነዉን ዳና አናገኝም፡፡ እሱባለዉ ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ንዑስ ርእስ መንገዳችን የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ የሚከተለዉን ጽፏል፦        
ኮቴያችን በድን መሬት ላይ ያርፋል፡፡ ዳናችን በነፋስ እየተጠረገ ከዐይን ይሠወራል፡፡ መንገዱን አቋርጠን እንዳልመጣን ያሳረፍነዉ አሻራ በዋዛ ይጠፋል፡፡ ጊዜ አልፎ እኛም እዚህ መንገድ ላይ አንድ ሰሞን ነበርን ብንል ማን ያምነናል? ጎዳናዉ ላይ ከነበርን ያሳረፍናቸዉ ዳናዎቻችን የታሉ? ከሌለንስ ‘ያንን መንገድ’ ሳናቋርጥ በምን ተአምር እዚህ እንዴት ደረስን? በምድር ላይ የማይጠፋ አሻራ ማሳረፍ ከባድ ነዉ፡፡ ተልከን ከሄድንበት ስንመጣ ከላኩን ሰዎች አፍ መሬት ላይ የተተፉት ምራቆች ደርቀዉ ይጠብቁናል፡፡ የምናገኘዉ ሽልማት የለም፡፡ ከመኖር የምናተርፈዉ ትዝታ ብቻ ነዉ፡፡ መንገዳችን እንደ ትዝታ ነዉ፡፡ አንዴ ብናልፈዉም አንረሳዉም፡፡ በትዉስታዎቻችን ምሪት ደጋግመን እንመላለስበታለን (እሱባለዉ፣ 2012፡ገጽ 88)፡፡
እሱባለዉ ከላይ እንደነገረን፣ በእዚህ ዓለም ዉስጥ ያለ ነገር ሁሉ ተለዋጭ በመሆኑ ባለበት ፀንቶ የሚቆይ አንዳች ነገር የለም፡፡ ለእሱባለዉ ወረት ከሚሰለጥንባቸዉ ነገሮች አንዱ ፍቅር ነዉ፡፡ ደራሲዉ ይህን እሳቤዉን የሚያሳየን ሥራዉ ዉስጥ በሳላቸዉ ገጸባሕሪያት ‘ሰ’ እና ‘ዘ’ ሕይወት ዉስጥ ነዉ፡፡ ‘ሰ’ እና ‘ዘ’ ባል እና ሚስት ሲሆኑ ‘ዲ’ የተባለች ሴት ልጅ ለመዉለድ በቅተዋል፡፡ ‘ዲ’ ‘ገ’ የተባለዉ የልብወለዱ ዋና ገጸባሕሪ ፍቅረኛ ናት፡፡  
እሱባለዉ መለያየት ንዑስ ርእስ እኮ ልብን እንዴት ይገስጿል? የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ እንደሚነግረን፣ ‘ሰ’ እና ‘ዘ’ ፍቅር ያሞቀዉ ጎጇቸዉ በወረት ሳይፈታ በፊት ደስተኛ ሕይወት የነበራቸዉ ጥንዶች ነበሩ፡፡ ጊዜ ኃያል ነዉና የ’ዘ’ ልብ ፍቅርን የማያፈልቅ ጭንጫ ሆነ፣ አቅፎት ያደረዉን የሚስቱን ዉብ ገላ ሰለቸ፣ ልቡም ሌላን ሰዉ አምልኮ ኮበለለ (እሱባለዉ፣ 2012)፡፡
፬. የሕይወት ትርጉም ደራሲዉ ሰዉ ነዉ
እሱባለዉ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና መሠረታዊ የህልዉና ጥያቄዎችን በልብ ወለድ ሥራዉ ዉስጥ የፈከረ ልብ ወለድ ጸሐፊ ነዉ፡፡ ደራሲዉ በልብ ወለድ ሥራዉ ዉስጥ አፅንኦት ሰጥቶ ከዳሰሳቸዉ የኤግዚስቴንሻሊዝም ዐቢይ ጥያቄዎች አንዱ ሕይወት በራሱ ቋሚ ትርጉም (intrinsic meaning) አለዉ ወይስ የለዉም? የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ እሱባለዉ በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ እንደሚነግረን፣ ሕይወት በራሱ ቋሚ ትርጉም የለዉም፡፡ የሕይወት ትርጉም ደራሲዉ ሰዉ ነዉ፡፡ እሱባለዉ መዲናና ዘለሰኛ ንዑስ ርእስ እኔ መች መረጥኩኝ ለብቻዬ እንጉርጉሮ? የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ የሚከተለዉን ጽፏል፦
ሰዎች በሚያነቡት ምንባብ፣ በሚያዩት ቅርጽ፣ በሚያደምጡት ድምፀት ዉስጥ የማያቋርጥ የትርጉም ኀሰሳን ያደርጋሉ፡፡ ምክንያታዊነትን ይጠይቃሉ፡፡ ሕይወት ላይ ግን ‘ለምን እንዲህ ሆነ? ለምንስ እንዲያ አልሆነም?’ ብለን መጠየቅ አንችልም፡፡ ከአልተመለሱልን ጥያቄዎች ጋር እንጓዛለን፡፡ ምክንያቱም ምድር ላይ የያዝነዉ ሕይወት እንጂ ተዉኔት አይደለም፡፡ የተሰጠን ቃለ ተዉኔት የለም፡፡ ወደዚህ ምድር ስንመጣ የሕይወትን ትርጉም የያዘ ክታብ በአንገታችን አሥረን አልተወለድንም (እሱባለዉ፣ 2012፡ገጽ 24-25)፡፡  
የሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ታላቁ ፈላስፋ ዠን-ፖል ሳርተር ይህን የእሱባለዉ አተያይ ይጋራል፡፡ ሳርተር ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም በተሰኘ የፍልስፍና ሥራዉ እንደሚነግረን፣ የሰዉ ልጅ ወደ መኖር ከመምጣቱ ቀድሞ የተበጀ የሕይወት ትርጉም የለም (ሳርተር፣ 2007)፡፡ ምክንያቱም፣ የሰዉ ልጅ ወደ መኖር መጥቶ ማንነቱን ከመፍጠሩ በፊት ምንም ነበርና (ሳርተር፣ 2007)፡፡ ለሳርተር፣ የሕይወት ትርጉም ፈጣሪዉ ህልዉናዉ ከንጥረ ባሕርይዉ ወይም ማንነቱ የሚቀድመዉ የሰዉ ልጅ ነዉ፡፡
፭. ቀቢፀ ተስፋ
ቀቢፀ ተስፋ (despair) ከትዝታ፣ የሕይወት ወለፈንድነት፣ ወረት እና የሕይወት ቋሚ ትርጉም አልባነት በተጨማሪ በእሱባለዉ ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ዉስጥ የተዳሰሰ ጭብጥ ነዉ፡፡ እሱባለዉ ይህን ጭብጥ የዳሰሰዉ ሥራዉ ዉስጥ በሳለዉ ‘ገ’ በተባለ እንግዳ ገጸባሕሪ አማካኝነት ነዉ፡፡ ደራሲዉ እንደሚነግረን፣ ‘ገ’ ነፍሱ በቀቢፀ ተስፋ ሰማይ የተከበበ፣ ለሕይወትም ለሞትም ግድ የሌለዉ ጭምትና እጅግ ቀዝቃዛ ወጣት ነዉ፣ ገና በለጋ እድሜዉ የአገሩ ልጆች ከሐረጋቸዉ ባለመመዘዙ ጠልተዉት በካራ ወግተዉ የገደሉት፡፡ ‘ገ’ ሞትን እስኪናፍቅ ድረስ ጥልቅ ቀቢፀ ተስፋ ዉስጥ የወደቀዉ ሊኖርበት በማይፈልገዉ ዓለም ዉስጥ በመፈጠሩ ምክንያት ነዉ፡፡ እሱባለዉ ዘጠኝ ሞት ንዑስ ርእስ ሞት ሳይሞቱት ነዉ እሚለመድ? የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ የሚከተለዉን ጽፏል፦
ከተወለድኩበት ቀን አንስቶ በተሳሳተ ዓለም እንደ ተፈጠርኩ ይሰማኝ ነበር፡፡ የልጅነት ሕልሜ በወጣትነት መሞት ነበር፡፡ ጉርምስና አይቀርምና – በቀጠሮዉ መጣ፡፡ እኔ ግን ሳልሞት በሕይወት ቆየሁ፡፡ ለምን? (እሱባለዉ፣ 2012፡ገጽ 50)፡፡
ገጸባሕሪዉ መኖር ኢምንት ትርጉም ካልሰጠዉ ለምን ታዲያ ራሱን አላጠፋም? ገጸባሕሪዉ እንደሚተርክልን፣ ለመሞት የነበረዉን ብርቱ ምኞት ከልቡናዉ ሰሌዳ ላይ እንዲፍቅ ያደረገችዉ በፈቃዱ ሊሞት ቀጠሮ በያዘበት ዕለት የተዋወቃት ‘ዲ’ የተባለች ሴት ናት፡፡ እሱባለዉ ጽድቅና ኩነኔ ንዑስ ርእስ መሆን አለመሆን የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ የሚከተለዉን ጽፏል፦ “እናም ራሴን ላጠፋ በምችልበት አንድ ዉብ ምሽት ከ ‘ዲ’ ጋር ተዋወቅኩኝ፡፡ ከሞት ያስቆመኝ ብቸኛ ምክንያት – ያ ነበር” (እሱባለዉ፣ 2012፡ገጽ 64)፡፡ አብዘርዲስቱ ፈላስፋ ካሙ እንደሚነግረን፣ ከፈቃድ ሞት የሚታደጉን ፍፁማዊና ዘላለማዊ መሆን የማያሻቸዉ ሌሎች የትርጉም ምንጮች አሉ (ዊክ፣ 2003)፡፡           
፮. ፍቅር
 እሱባላዉ በትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ዉስጥ በጥልቀት የዳሰሰዉ ሌላኛዉ ጭብጥ ፍቅር ነዉ፡፡ ፍቅር እሱባለዉ እንደሚነግረን፣ ተመጦ እንደሚያልቅ ከረሜላ ያልቃል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ልባችን ለተንበረከከለት ሰዉ ያለን ፍቅር ጊዜዉን ጠብቆ ከልባችን ይነጥፋል፡፡ እሱባለዉ ወደድንም ጠላንም ይህን ደረቅ ሐቅ መሸሽ አንችልም ይለናል፡፡ ደራሲዉ በሥራዉ ዉስጥ እንዳሳየን፣ ‘ዘ’ የተሰኘዉ ገጸባሕሪ የትዳር አጋሩን ‘ሰ’ን የፈታዉ ለእሷ ያለዉ ፍቅር ከልቡ ተንጠፍጥፎ አልቆ ነዉ (እሱባለዉ፣ 2012)፡፡ ለመሆኑ ልባቸዉ እስኪቃጠል ያፈቅሩን የነበሩ ሰዎች ለእኛ የነበራቸዉ የወትሮዉ ፍቅር ከልባቸዉ የሚነጥፍበት ዐቢይ ምክንያት ምንድር ነዉ? የእሱባለዉ ምላሽ ሌሎችን ከልክ በላይ ማፍቀር ነዉ የሚል ነዉ፡፡ ደራሲዉ የእሳት እራት ንዑስ ርእስ ራት እና መብራት የተሰኘ ርእስ በተሰጠዉ ትረካ ዉስጥ በሳላት በ‘ዲ’ አያት አማካኝነት እንደነገረን፣ ‘ዘ’ የልጁን እናት ‘ሰ’ን ሰልችቶ ጀርባዉን ሊሰጣት የበቃዉ ከልክ በላይ ራሷን አሳልፋ በመስጠቷ ምክንያት ነዉ (እሱባለዉ፣ 2012)፡፡
እሱባለዉ እንደነገረን፣ ከልክ በላይ ሌሎችን ማፍቀራችን ጀርባ የሚያሰጠን ከሆነ በምን መንገድ ፍቅር ዘላቂ ሊሆን ይችላል? እሱባለዉ እንደሚመልስልን በፍቅር የተጣመሩ ጥንዶችን ፍቅር ዘላቂ የሚያደርገዉ ሚዛናዊ ፍቅር ነዉ፡፡ ፍቅር ሚዛናዊ ከሆነ ሌሎችን ገሸሽ አድርገን ከልክ በላይ ራሳችንን አናፈቅርም፤ ራሳችንንም ረስተን ከልክ በላይ ሌሎችን አናፈቅርም፡፡ ሚዛናዊ ፍቅር በእሱባለዉ የፍቅር ፍልስፍና ዉስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህ አይነቱ ፍቅር ከምንወደዉ ሰዉ ጋር እስከ መቃብር ያዘልቀናል፡፡ በተቃራኒዉ ከልክ በላይ ራስን ማፍቀርና ከልክ በላይ ሌላዉን ማፍቀር ያፈቅሩን የነበሩ ሰዎች ገሸሽ እንዲያደርጉን የሚጋብዙ፣ በእዚህም ሰበብ ፍቅርን የመሰለ ታላቅ ፀጋ ከሕይወታችን ስለሚሰልቡ ተቀባይነት የላቸዉም፡፡ እሱባለዉ ከላይ በተጠቀሰዉ ትረካ የሚከትለዉን ጽፏል፣  
ከራሳችን በላይ ሌላዉን ስንወድድ ራሳችንን እንበድላለን፡፡ በሕይወታችን ዉስጥ ላሉ ሌሎች ሰዎች ከትንሿ ልባችን ላይ ቆራርሰን የሰጠነዉ ስፍራ ብዙ ነዉ፡፡ ስለዚህም በእኛ ዓለም ዉስጥ ለእኛ የሚሆን ቦታ አጥተናል፡፡ በልባችን የወደድነዉ ሌላዉን ሰዉ ብቻ እንጂ የገዛ ራሳችንን አይደለም፡፡ የገዛ ራሳችንን እንዴት መዉደድ እንዳለብን አናዉቅም፡፡ አልተማርንምም፡፡     
ከሌሎች በላይ ራሳችንን አስበልጠን ስንወድድ ሌላዉን እንበድላለን፡፡ ራሳችንን ስንወድ ለሌላዉ ሰዉ የሚሆን ቦታ በልባችን አንተዉም፡፡ ስለዚህም በእኛ ዓለም ዉስጥ ሌሎች ሰዎች ስፍራ ያጣሉ፡፡ በልባችን አብዝተን የወደድነዉ ራሳችንን ብቻ እንጂ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ጭምር አይደለም፡፡ ሌሎችን ሰዎች እንዴት መዉደድ እንዳለብን አናዉቅም፡፡ አልተማርንምም (እሱባለዉ፣ 2012፡ገጽ 119)፡፡
ማጠቃለያ
ትዝታሽን ለእኔ፣ ትዝታዬ ለአንቺ ጊዜ የማይሽራቸዉ በርካታ ህልዉናዊ ርእሰ ጉዳዮች በነጠረ ቋንቋ የቀረቡበት፣ በሥነ ዉበት ይዘታቸዉ ከላቁ የልብወለድ ሥራዎች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ሥራ ነዉ፡፡ በተጨማሪም፣ ይህ ሥራ የሃያ አንደኛዉ ክፍል ዘመን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እድገት አንድ እርምጃ ወደ ፊት መራመዱን ማስረገጫ  አድርገን ከምንጠቅሳቸዉ ማለፊያ ሥራዎች መካከል አንዱ ነዉ፡፡   
 ***
ከአዘጋጁ፡-
መኮንን ደፍሮ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር ድግሪውን በ2009 ዓ.ም፣ የማስተርስ ድግሪዉን ደግሞ በ2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በጅማ፣ በመቐለ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርቷል፡፡ ጸሐፊው አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ መጽሔቶች ግጥሞቹንና የልብ ወለድ ሥራዎቹን አሳትሟል፡፡      መኮንን በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን ጽፏል፡፡

Read 274 times