Sunday, 24 March 2024 00:00

በአፍ አያንግሱ፣ በውል ይደግሱ!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለውለታ፣ Francis Falceto ‹‹About Ethiopian Music(s) and their Heritage›› በተሰኘ መጣጥፉ በሞሐሙድ አሕመድ ‹‹ኧረ መላ መላ›› በሚል ዘፈን አስገዳጅነት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለመውደድ እና ለመገምገም በቃሁ ይልና፤ በሃቲቱ አክሎ በኢትዮጵያ/የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው አካል ሙዚቃን በቅርስነት መመዝገብ እንዳለባቸው ብዙ ይብከነከናል።
ቀጥሎ ይላል ፋልሴቶ በሃቲቱ፣ በፈረንጆቹ April 1985 አዲስ አበባ ተከተትኩ፤ ዋሊያስ ባንድ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ሞሐሙድ አሕመድ እና ሌሎችንም በማስተባበር የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለዓለም ለማስተዋወቅ በቃሁ ይላል።
የሆነው ሆነና፣ በአገራችን የአርካይዥ፣ የቅርስ ጥበቃና ቁጥጥር ክፍተት አለ፤ ሙዚቃ፣ የሙዚቃ ባለሞያዎች እና ሙዚቀኞች ሥራቸው፣ ድርሻቸው፣ አበክሮአቸው፣ ድካማቸው… ወዘተ. ተሰንዶ ቢቀመጥ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፤ መማሪያ ይሆናል፤ ለጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም ለላቀ ሥራ መነሻም ጭምር ነው፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ እና ሙዚቀኞች ባለውለታችን ናቸው…
…በሙዚቃ ተያዥነትና መነሾ የአገር ፍቅር አድሮብናል፣ ጾታዊ ፍቅራችንን ገሃድ ናኝተናል፣ ጀግንነትን ተላብሰናል፣ ጀግኖችን አወድሰናል፣ ሰብዐዊነትን ተቋድሰናል፣ ነገን ወጥነናል፣ ሰው ሰው መሽተትን አንጥረን ወስደናል፤ አገራችንን የመተዋወቅ ዕድሉ የመጣው በሙዚቃ እንጂ ተዟዙሮ በመጎብኘት እንዳልሆነ ማስተባበል አይቻልም፤ ታሪክን ገጥ-በገጥ ቀስመናል፤ ቁምነገር ዘግነናል፤ በግሌ ሳነብ፣ ሳጠና፣ ስመራመር፣ ስወጥን፣ ስደሰት፣ ስበሳጭ፣ ስተክዝ…ወዘተ. አብዛኛውን ጊዜ ከጎኔ የነበረውና የሚኖረው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ነው!
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የጥላሁን ገሠሠን የመኖሪያ ቤት በኃላፊነት ተረክቦ በቅርስነት ቢያስተዳድር ለአገርና ለታሪክ አይተርፍም ነበር? የጥላሁን ገሠሠ ልባሾች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ የእጅ ጽሑፉ፣ ቁሳቁሶቹ፣ የመመገቢያ ዕቃዎቹንና ሌሎች ንብረቶቹን በወጉ ተረክቦ ቢያስተዳድር፣ አንደኛ ጥላሁን ገሠሠን ማክበር ይሆናል፤ ሁለተኛ የጎብኚውንና የጥናትና ምርምር ባለሙያውን መደገፍ ይሆናል፤ ሦስተኛ የአገሪቱን የቱሪዝም መስክና ምጣኔ-ሀብቷን መደጎም ይቻላል፤ አራተኛ በሌሎች ሙዚቀኞች ዘንድ ተነሳሽነትን መፍጠር ይሆናል። ሌላም ሌላም…
…ጥላሁን ገሠሠን የዘፋኞች ሁሉ ንጉስ ብሎ በአፍ ብቻ ማሞገስ ፋይዳው እምን ድረስ ነው? በአንደበታችን የካብነውን ያህል በተግባር ብናሞግሰውና ብናተልቀው እኛው አይደለን ተጠቃሚዎች? ንጉስን ላለማክበር ስለምን በጅምላ ታጨን? አፍና ተግባራችን እንዲሳከሩና እንዲቀባዠሩ የበየነብን አለ ይሆን?...    
…ስለምን አርማዎቻችንን የመግፋት ዳፍንት ውስጥ ሰጠምን? ብንከባከባቸውና ብናመሰግናቸው ምናችን ይጎድላል? አርአያን ያለማወደስ ልምሻ ለምንድር ነው ያደባየን? እንደምንስ ቸርነታቸውንና አበክሮአቸውን ጭልጥ አድርገን የምንውጥ ጭንጫዎች ሆንን? መዘንጋት ዕጣ-ፈንታችን ሊሆን ይገባ ነበር? የበሉበትን ወጬት ሰባሪ መሆን ለትዝብት አይዳርግም? ሙዚቀኞቻችን ፈር አልጠቆሙም? መንገድ አልሰጡንም? በሥራዎቻቸው ሰበብ አፍቅረን አልተፈቀርንም? አልተቋደስንም? አልጀገንንም?...
…ለአብነት ያህል፣ ከየኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ልምድ በመውሰድ ሙዚቃን በቅርስነት መጠበቅ ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ መዛግብትን፣ ጥንታዊ ጽሑፎችን፣ መጻሕፍትንና ሌሎችንም የመረጃ ሀብቶች የማሰባሰብ፣ የማደራጀት፣ የመጠበቅ፣ ለአገልግሎት የማዋልና ለትውልድ ጠብቆ የማስተላለፍ ድርሻን እየተወጣ ይገኛል፡፡
በአገራችን የተከሰቱ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ ማሕበራዊ፣ ምጣኔ-ሀብታዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ስለ ሌሎች ጉዳዮች የሚያትቱ ሰነዶች በድርጅቱ ይገኛሉ። ይኼም ያለፈውን የአገራችንን ታሪክ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍና ጥንታዊዋን አገራችንን ለመገንዘብ ይረዳል።
በድርጅቱ ሥር የተሰባሰቡ መረጃዎችን ተማሪዎች፣ ጥናት አጥኚዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የሚዲያና ኮምኒኬሽን ባለሙያዎች፣ ደራሲያንና ሌሎችም ይጠቀሙበታል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ለተለያዩ አገራዊ፣ ማሕበራዊ፣ የትምህርታዊ መስክና ታሪካዊ ጥናቶች መነሻም ሆነ ግብአት የሚሆኑ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የቆዩ የጽሑፍ ሀብቶች ይገኛሉ፡፡
ታዲያ እንዲህ ያለ ሥራ በሙዚቃው ረገድ ቢከናወን የዚህ ዘመን ሙዚቀኞች አያድጉበትም? አይማሩበትም? ሙዚቀኞቻችንን ለማክበርና ለማወደስ ዕድሉን አናገኝ ይሆን? የማጣቀሻና የመረጃ ምንጭ አይሆንም ነበር? የተለያዩ ለውጦችን ለመፈተሽ ዋቢ አናገኝ ይሆን?    
የአገራችን ሙዚቃ ስንት የመከኑ ቀናቶቼን ወጌሻ ሆኖ ጠግኗቸዋል! ስብራቴን አቅንቷል፤ ደስታዬን አድምቋል፤ በኀዘኔ ወቅት መጽናኛዬ ነው፤ ይኼንን መጣጥፍ ሳዘጋጅም ሙዚቃ እያደመጥኩ ነው! ሥነ-ልቡናው፤ ሕጻናት/ልጆች በረጋ መንፈስ ሰክነው እንዲያድጉ እና ከፍ ሲሉ የማሰላሰል አድማሳቸው እንዲሰፋ ከተፈለገ ለስላሳ ሙዚቃ ማድመጥ እንዳለባቸው ይመክራል።
ሙዚቃ ተውቦ የምንሰማው ከብዙ ፍዳዎች በኋላ ነው፤ የግጥምና የዜማ ደራሲዎቹ ጤናቸው ተስተጓጉሎ፣ ቤተሰባቸውን ገፍተው፣ ማሕበራዊና ምጣኔ-ሀብታዊ ሕይወታቸው ተዛንቆ ነው ወደ እኛ ዘፈንን የሚያደርሷት፤ አቀናባሪውም ቢሆን ብዙ ነገር ጎድሎበት እንደሚያቀናብር ልብ ልንል ይገባል፤ ድምፃዊውም ጭምር በሕይወቱ ላይ ብዙ ውጣ-ውረዶች እንደሚደርሱበት ዕሙን ነው!...
…ወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን ተብሎ ቢሸለልም፣ ሙዚቃው እንጂ ወርቃማ የነበረው ሙዚቀኛው ሕይወቱና ዕጣ-ፈንታው እንደ ወርቅ መቅለጥ ነበር፤ ወርቃቸውን ሙዚቃውና አድማጩ ደመቀበት እንጂ ባለ ወርቆቹ ችግረኞች ነበሩ።
መቼም ደላጎዎች ነን፤ ታሪካችንን እኛ ችላ ብንለውም ነጮቹ ይመዘግቡልናል፤ ጥናትና ምርምር ያካሂዱበታል፤ በእኛ ፈንታ ለዓለም ያስተዋውቁልናል - ‹‹እኔ ሐኪም ቤት፣ መድኀኒቱ ቤቴ›› ዓይነት መደናገር ነው። የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ባይኖሩስ ብዬ አስባለሁ፤ ምን ይውጠን ነበር? መኖራቸው በጀን ወገን!
ቲሞቲ ጆንሰን/Timothy Johnson/ የተባለ ሌላ ጥናት አቅራቢ፤ ‹‹Music Theory: Ethiopian Music›› በሚል መጣጥፍ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ሲያወሳ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ታላቁን ድርሻ የሚይዘው አስገምጋሚና ስርቅርቅ ድምጽ ያለው ሙዚቀኛ ብቻ ሳይሆን፤ የተለያዩ የአዚያዚያም ስልቶችን በሚገባ የሚወጣው ዘፋኝ/ሙዚቀኛ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ አትቷል። እነዚህ ሁሉ ምስጋና ይግባቸው!
የተለያዩ ሙዚቃ ነክ ሰነዶችና ማስረጃዎችን ሰንዶ መጠበቅ ሰነዶቹ በሚይዙት የማጣቀሻና የማስረጃ ፋይዳ ምክንያት በታሪካዊ ማስረጃነት በቅርስነት ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ፣ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ግለሰቦች ለምንጭነት እንዲገለገሉ ማመቻቸት  ይቻላል፤ የአርካይዥና የዶክሜንቴሽን ተቋዋሙ ሙዚቃ ነክ መረጃዎችን በአግባቡ ጥበቃ ቢያደርግ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ ሚናን መጫወት ይችላል፤ በተጨማሪ፣ የትምህርቱን መስክ ለማሻሻል፣ አስፈላጊ መረጃ ለመስጠት፣ ለማሕበራዊ ለውጥና ለሌሎች አገርን ለሚገነቡ ዓላማዎች ማዋል ቀላል ይሆናል።  
የሙዚቀኞች ማሕበር፣ መንግሥትን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ለእንዲህ ያለ ተግባር ሰፊ ግምትና ትኩረትን ሊሰጡ ይገባል፤ በሌሎች የአፍሪካ አገራት እምብዛም ያልተለመደው የመረጃና ሰነድ ማሰባሰብ በአገራችን ትልቅ ደረጃን ይዟል፤ ልብ ሊባል የሚገባው አሳሳቢ ጉዳይ፣ ሃውልቶች፣ ቅርጻ-ቅርጾች፣ ሕንጻዎችና ሌሎች ቅርሶች ቢወድሙ ወይም ቢጎዱ አምሳያቸውን መሥራት ይቻላል…
…ነገር ግን ሙዚቃ ነክም ሆነ ሌላ ማስረጃና ሰነድ ከጠፋ አምሳያውን መሥራት ወይም መተካት ከባድ ነው፤ ስለሆነም፣ የሙዚቃ ሰነድ አያያዝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ አንድ መንግሥት ሰነድ ላይ ማዕከል አድርጎ ሕግና ፖሊሲ መቅረጽና ማርቀቅ ላያዳግተው ይችላል፤ ሰነድ ከዚህ ያለፈ ሚና አለው፤ የበርካታ የአፍሪካ አገራት ታሪክ ተረት ቅልቅል ነው፤ በተረክ ደረጃ እንጂ በተደራጀ መዛግብት ደረጃ የለም፤ በዚህ ምክንያት ማንነታቸውን ለማጥናት፣ ሕግ ለማውጣትና ፖሊሲ ለመቅረጽ ይቸገራሉ፤ ይኼ ዳፋ ለእኛም እንዳይተርፍ የሙዚቃችን ታሪክ፣ ውጣ-ውረዱ፣ ስኬትና ውድቀቱ፣ ባለሙያዎቹና ትጋታቸው ተሰንዶ መቀመጥ አለበት፤ ይኼ ተግባር የአገር ታሪክንና ሀብትን የማሰባሰብና የመጠበቅ የሥራ ድርሻ ነው፤ የባለድርሻ አካሉ፣ ይኼንን ለአገልግሎት ማዋልና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ መቻል አለበት።
በአጠቃላይ፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሙዚቃን አስመልክቶ ለተጠቃሚው ክፍት የሆነ የማጣቀሻ አገልግሎት መስጠት ቢጀምር፣ ለጥናትና ምርምር የሚያገለግሉ የተጨማሪ መረጃዎች፣ መነሻዎች፣ አጋዥ ሰነዶች፣ አጎራባች መዛግብቶች፣ የድምጽ ቅጂዎችንና ሌሎች ጠቃሚ ሰነዶችን የሚያገኝበትን አሠራር ይፈቅዳል። በተለያዩ መስኮች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ፣ ዘገባዎችን የሚሠሩ፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ውስጥ የሚሠሩ፣ የውጭ አገር ጎብኚዎች፣ መዛግብት ፈላጊዎችና ሌሎች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ለሙዚቃ ሞያተኞችም ታላቅ ክብርን ማሳየት ይቻላል፤ ለላቀ ሥራ ተነሳሽነትን ለማሳደግ ይረዳል።
* * *
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።


Read 226 times