Monday, 25 March 2024 08:15

አላዋቂነት ላይ መመስከር፤ አዋቂነትን ማጽደቅ!

Written by  ባዩልኝ አያሌው-
Rate this item
(1 Vote)

 “Empty vessels make the most noise” የሚል የቻይናዎች ምሳሌያዊ አነጋገር አለ፡፡ ንግግሩ ምሳሌያዊ ነውና የሚያወራው ባዶዋቸውን ስለሆኑ፣ በውስጣቸው አንዳችም ስለሌለ ሳጥኖች አይደለም፡፡ ዕውቀት አልባ የሆኑ ባዶዎች ስላላቸው ስሙኝ ባይነት፣ አሻግሮም አዋቂዎቹ ስላላቸው ትሁት ዝምታ ነው፡፡ አዋቂዎችም ከእነ ትሁት ዝምታቸው፣ መሐይማኑም ከእነ ይዘት አልባ ጩኸታቸው በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ክፍለዓለም አሉና ይህንኑ የሚመሰክር ምሳሌያዊ አነጋገር በእኛም ቋንቋ ውስጥ አለ- “የሚጮኸው ባዶው ጋን ነው”!
“ሁሉን የሚያውቅ የሚመስለው አንዱንም አያውቅም፡፡” የሚል መቼና የት እንዳነበብኩት ያላስታወስኩት ጥዑም አገላለጽ አለ፡፡ ምንጩን በቅጡ አለማስታወሴ የነገሩን ልክነት አያደበዝዘውምና ይህንኑ የነገሬ መሰንዘሪያ አድርጌ ልቀጥል፡፡
አንድ ሰው ምን ቢረቅ፣ ምን ቢመጥቅ ሁሉን ሊያውቅ ሁሉን ሊጠነቅቅ አይችልም፡፡ ይህም ለሰው አይቻለውም ብቻ ሳይሆን፣ እስከአሁን በአንድም ሆነ በብዙ የዓለማችንን  መልክና ውጥን፣ አሠራርም ቢሉ ቃኝተዋል ለምንላቸው ለየትኞቹም ታድሎ አልተመለከትንም፤ አልሰማንም፡፡ እነሱም ጥራዝ ነጠቅ ተመኪ አይደሉምና “ነን” ሲሉ አልተሰሙም፡፡ ይልቁንም የምር አዋቂዎች ናቸውና፣ ጠልቀው ስላወቁትም ነገር ያላቸው እርግጠኝነት “ይመስለኛል” ከማለት ትሁት ቃል የሚዘል አይደለም፡፡
ነገሬን ካሰናኘልኝ፣ አንድ የራቀ ትውስታዬን ላውሳ፡፡ ጊዜው በ1990ዎቹ አጋማሽ ግድም ነው፡፡ ሚክሎል የተባለው የስዩም ገብረ ሕይወት ድንቅ ልቦለድ አንባቢያን እጅ የገባበት አካባቢ፡፡ ወደ አንድ ጉዳዬ እያቀናሁ ይመስለኛል፡፡ በአጋጣሚም የጠቀስኩትን መጽሐፍ (የመነበብ ተራው ሆኖ) በእጄ ይዣለሁ፡፡ የመንገዱን ዳር ይዤ ስጣደፍ፣ ሊቁና የሁልጊዜ ጠያቂው፣ የንባብና ግዕዝ መምህራችን የኔታ ዘውገ ዶሰኛው (አፈሩ ይቅለላቸውና) ከመንገድ ላይ አገኙኝ፡፡ ለመምህር የሚገባውን እጅ መንሳት ከውኜ ቀና ስል፣ ሊቁ መምህሬ ዐይናቸውን ብብቴ ሥር በሸጎጥኩት መጽሐፍ ላይ አተኩረዋል፡፡
“ምን ይዘሀል እንቶኔ?” አሉኝ በእጃቸው ወደ መጽሐፉ እያመለከቱ፡፡ እጅግ የሚያቀርቡትን ተማሪያቸውን እንቶኔ ብለው ነው የሚጠሩት፡፡
“መጽሐፍ ነው የንታ” ቀጥለው ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ራሴን እያዘጋጀሁ መጽሐፉን አቀበልኳቸው፡፡ ቢያንስ “መጽሐፉ ስለምንድን ነው የሚናገረው?.... ምን የተለየ ዕውቀት ተማርክበት?” የሚሉት ጥያቄዎች አይቀሩልኝም፡፡
መጽሐፉን ተቀብለውኝ ርዕሱ ላይ ዐይናቸውን አጠበቡ፡፡ ከዛም አተኩረው ቃሉን እየጠሩ ማልጎምጎም ያዙ፡፡
“ሚክሎል… ሚክሎል... ምን ማለት ነው?” ቀና ብለው ተመለከቱኝ፡፡ ነቃ አልኩ፡፡
የኔታ ዘውገ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ የግዕዝ፣ የቅኔና የአንድምታ ትርጓሜ መምህራን ከፊት ተርታ ከሚጠሩት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ደራሲው ደግሞ ቃሉ የግዕዝ ቃል መሆኑን፣ ትርጉሙም (የዘነጋሁት አይመስለኝም) “ፍጹም ጌጥ፣ ፍጹም ክብር፣ ፍጹም ሽልማት…” መሆኑን ገልጿል፡፡ እኔ ይህንን ፈልጌ ባለማግኘቴ፣ እርግጡን የማወቅ አጋጣሚ እንደተፈጠረልኝ በመቁጠር ምላሻቸውን በጉጉት ጠበቅሁ፡፡
የኔታ ማሰላሰሉና ማልጎምጎሙ ባሰባቸው፡፡ ቃሉን ደጋግመውና አስረግጠው እየጠሩ ጥቂት እርምጃዎች ከእኔ ፈንጠር ብለው ተብሰለሰሉ፡፡
“ሚክሎል... ሚክሎል... ምን ከሚለው ግስ የወጣ ነው?…. ሚክሎል…..?” ወዲህ ቃሉ ምን ከሚለው ግስ የወጣ ይሆን? በሚለው ጥያቄ፣ ወዲህ ደግሞ ትርጉሙን ለማወቅ በጓጓ ስሜት ውስጥ ሆነው ወደ እኔ ተመለሱ፡፡
“እንቶኔ እና አንተ አገኘኸው?”
የንታ እንዲህ ናቸው፡፡ አዛውንቱ መምህር ትንሹን ተማሪያቸውን ይህንን ያህል ነው የሚያከብሩት፡፡ የዕውቀቱ ባለቤትና መምህር እሳቸው ያላወቁትን፣ በዕድሜም በዕውቀትም፣ እጅግ ትንሹ ተማሪያቸው ሊያውቀው ይችላል ብለው ያስባሉ፡፡ ከእሱ ሊረዱ እሱኑ ይጠይቃሉ፡፡
መልስ ሰጠሁ፡፡ “እረ አላገኘሁትም የንታ” ድምጼ ውስጥ ለእርግጠኝነት ጥቂት ፈሪ ድምጸት ይስተዋላል፡፡ ያደረኩትን ጥረት አስከተልኩ፡፡ የእሳቸው አቻ የሆኑትን የሌላኛውን መምህራችንን ስም ጠቅሼ እሳቸውም “ግዕዝ ውስጥ እንዲህ የሚባል ቃል የለም” እንዳሉኝ ገለጽኩ፡፡ ፍጹም ያልጠበኩት ተፈጠረ፡፡ የኔታ ቦግ አሉ፡፡ ቀይ ፀዐዳ ፊታቸው በርበሬ መሰለ፡፡ ሲቆጡ እንደሚሆነው ሁሉ አንደበታቸው ጠነከረ፡፡ ሲቆጡ የራሳቸውን ስም አስቀድመው ነው የሚናገሩት፡፡
“እንዲህ ናትና ዘውገ!…. የለም?!… እንዴት እንዲህ ይባላል?!…. እኛ የማናውቀው ነገር ሁሉ የለም ማለት ነው?” የራሳቸውን ሊቅነት አሳንሰው ለደራሲው ይመሰክሩ ያዙ፡፡
“እኛ ሳናውቀው ቀርተን እንጂ፣ ደራሲን ያህል ባለታላቅ አእምሮ የሌለን ቃል ያውም የመጽሐፍ ርዕስ አያደርግም” በቁጣ ተርገፈገፉ፡፡ በእዛች እለት ዕድሜዬን ሁሉ የማልዘነጋቸውን ሁለት ነገሮች አስተዋልኩ፡፡ አንድ፡- ሌላውን የማክበርና ለሥራው ዋጋ የሰጠን መስካሪነት፡፡ ሁለት፡- ተራቀንበታል፣ መጥቀንበታል በምንለው መስክ ውስጥ እንኳን ጠያቂና ተማሪ የመሆንን ትህትና፡፡
“የዕውቀት የመጨረሻው መድረሻ ትህትና ነው ይላል!” አንድ ወዳጄ፡፡
አንብበን ወይም ጠይቀን ባልተገነዘብነው፣ አጥንተን እና መርምረን ባልደረስንበት ነገር ላይ አይደለም፤ አንድ ቀን ሰምተነው በማናውቀው ጉዳይ ላይ ያለን እርግጠኝነት፣ ያለን የአዋቂነት መተማመን ያስደነግጣል፡፡ “አላውቀውም፤ እርግጠኛ አይደለሁም” የሚሉትን ቃላት የእኛን ያህል የሚፈራው ያለ አይመስልም፡፡ አላዋቂ ያሰኘናል ብለን በምናደርገው ድፍረት ይበልጥኑ ባዶነታችንን እንገልጣለን፡፡
እስቲ ትውስታችንን ጥቂት እንገላልጥ፡፡ የሆነ አቅጣጫ፣ ወይም ቦታ፣ ቤት ወይም የሆነ ያጣችሁትን ነገር ሰዎችን ስትጠይቁ ምን ይመልሱላችኋል? ምን ያህል ሰው ነው ስለማያውቀው “አላውቀውም” የሚላችሁ? ሳያውቀው “በዚህ ጋ መሰለኝ…. ወደዛ ጋ ስትደርሱ እንዲህ መሰለኝ… እዛ ጋ  መሰለኝ” የሚላችሁ ምን ያህሉ ነው?
በሕይወታችሁ ስለተቸገራችሁባቸው፣ መልስ ስለምትፈልጉባቸው ነገሮች ጠይቃችሁት “እኔ ስለዚህ ነገር አላውቅም ወይም እዚህ ላይ በቂ መረጃ የለኝም ወይም እኔ ለዚህ ጉዳይ ሩቅ ነኝ፤ ሌላ ሰው ብትጠይቅ” ያላችሁ ሰው ገጥሟችኋል? ምን ያህል?   
ገጠመኞቻችንን ለመቀስቀስ ይህንን አነሳሁ እንጂ፣ ችግሩና ጦሱ ከዚህ ያይላል፡፡ በጉዳዩ ላይ አንድም ዕውቀትና መረጃ የሌለው ሰው፣ በፍጹም የእርግጠኝነት ስሜት እመኑኝ፣ ተቀበሉኝ ላስተምራችሁ ሲል ትመለከታላችሁ፡፡ ይህ ሰው ደግሞ ወይ ፖለቲከኛ ሆኖ ሊወስን፣ ሊያዝ ስልጣን ይዟል፤ ወይ “አንቂ” (ከእነ ግብሩ “አናቂ” የሚመስለኝ ቃል) ነኝ ብሎ ሺዎችን ሰብስቦ መድረክ ላይ ወጥቷል፡፡ እናም ከምንም ስለምንም ያህላል ብለው በማይገልጹት ድፍረት ይናገራል፤ “ይተነትናል”፡፡ ሺዎችን ያስጨበጭባል፡፡
ዛሬ ስለ አንድ መስክ ራሱን ሊቅ አድርጎ በእርግጠኝነት መፏለል ሲደሰኩር የሰማችሁት ሰው፣ ነገ ደግሞ ከዛሬው ፍጹም ሩቅ በሆነ መስክ ላይ አሁንም በእርግጠኝነት ሲንደቀደቅ ትሰሙታላችሁ፡፡ እሱን አይደላችሁምና እናንተ ለእሱ ተሳቃችሁ መደበቂያ ጥግ ትፈልጋላችሁ፡፡ ግን ደግሞ እውነታው እንደሚነግረን “በአንዱ መስክ አዋቂ የሆነ ሰው፣ በሌላ መስክ መሐይም ነው፡፡”
ለማወቅ ሳይሆን፣ አዋቂ አክሎና መስሎ ለመታየት ያለው ግፊያና ሽቅድምድም አስፈሪ ነው፡፡ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የትኛውም የማህበረሰብ ክፍል በሚያስፈራ ሁኔታ፣ ሁሉም በሁሉም ጉዳይ “ተንታኝ” የሆነበት እጅን በግርምት አፍ ላይ የሚያስጭን ዘመን ነው፡፡ በስመ “አንቂነት” ቢሉ “ታዋቂነት” ማንም በምንም ጉዳይ ላይ የፈለገውን ለማለት የደፈረበት፣ ጽንሰሐሳቦች የተወናገሩበት፣ ቲዎሪዎች የተልከሰከሱበት፣ የተጠየቅ ህጸጾች ጽድቅ ሆነው ያላስጨነቁበት የዚህ ዓይነቱ የክስረት ጊዜ በታሪካችን የነበረ አይመስልም፡፡
በእኛዋ ሀገር አዋቂነት ድፍረት፤ አላዋቂነት ትህትና እና ዝምታ ከሆነ ውሎ አደረ፡፡ አላዋቂዎች በድፍረትና ቅጥ ባጣ ዋልጌነት በአደባባዩ ላይ የመንቧቸራቸውን ያህል አዋቂዎችና አሰላሳዮች ይህንን ተጠይፈው ዳር ይዘዋል፡፡ ይህም በሀገርና በትውልድ ላይ የሚያርፈውን የጥፋት በትር ሁለት ያደርገዋል፡፡ አንደኛው በትር ያለአዋቂዎቹ ከሳይንስም፣ ከሃይማኖትም፣ ከሞራልም ፍጹም የተፋታ ዲስኩር ሰለባ መሆን ሲሆን፣ ሁለተኛው በትር ደግሞ ይህንን መዝቀጥ ተጠይፈው ዳር የያዙትን የአዋቂዎቹን ትውልድን እና ሀገርን ሊያቀና የሚችል ዕውቀትን ማጣት ነው፡፡  
እንደ ሀገር ዕውቀት ተገፍቶና አፍሮ ድንቁርና የሰለጠነበትና አዛዥ ናዛዥ የሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡ እነሆ ዝግ እያለ መንገዳችንን የቀየደው ያለአዋቂነት ወጀብ፣ ሰልቶና ሰብቶ ወደፈለገበት አንደርድሮን ከቁልቁለቱ ጫፍ ያደረሰን ይመስላል፡፡ ከአዘቅቱ መዳኛው አንድ መንገድ ብቻ ይመስለኛል፡፡ አላዋቂነት ላይ መመስከር! አዋቂነትን ማጽደቅ! ያን ጊዜ ሳይገባቸው (ባ ጠብቆም ላልቶም ይነበብ) አደባባዩን ያጨቀዩት ሁሉ ወይ ለማወቅ፣ አሊያም ጥንትም መክሊታቸው አልነበረምና ከመድረኩ ይወርዳሉ፡፡ ያንጊዜ ያነበቡ፣ የተወያዩ፣ የመረመሩና ያሰላሰሉቱ ወደ አደባባዩ ይመጣሉ፡፡ ያንጊዜ ሀገርም ትውልድም በተፈተነ ዕውቀት ይገለጣል፡፡  ቸር እንሰንብት!
  ***
ከአዘጋጁ፡-
ባዩልኝ አያሌው በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነጽሑፍ መምህር ሲሆኑ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የኪነጥበብ መድረኮች ላይ በሚያቀርቧቸው ግጥሞችና አዲስ አድማስን ጨምሮ በሌሎች የሕትመት ውጤቶች ባስነበቧቸው ሥነጽሑፋዊ ሂሶቻቸው ይታወቃሉ፡፡

Read 805 times