Friday, 29 March 2024 21:08

ሠዓሊ ባልሆን ኖሮ የሬዲዮ ጋዜጠኛ እሆን ነበር” ሠዓሊ ዮሴፍ በቀለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በተፈጥሮ አካል ጉዳተኛ የሆነው ዮሴፍ በቀለ በሙያው  ሠዓሊ ሲሆን፤ የሚስለው ደግሞ  በአፉና በእግሩ ነው፡፡ ስዕል  የጀመረውም በልጅነቱ ለእንቁጣጣሽ አበባ በመሣል እንደሆነ ያስታውሳል፡፡ አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም ሠርቶ መብላት ይቻላል የሚለው ሠዓሊው፤ ሆኖም ሥዕሎቹ እየተሸጡለት አለመሆኑን  ይናገራል፡፡  የአዲስ አድማስ ልዩ ዘጋቢ መልካሙ ተክሌ ከሠዓሊ ዮሴፍ በቀለ ጋር ካዛንቺስ በሚገኘው ስቱዲዮው ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡
**
ሥዕል የምትሰራው በእጅህ አይደለም ---?
አዎ፤ እኔ ሥዕል የምሥለው ለየት ባለ ሁኔታ ነው፡፡ በእጄ መሥራት ስለማችል በአፌ ነው የምሥለው፡፡ እጅ የሚያስፈልገውን መመገብንና መልበስን ጨምሮ ሌላ ነገር ሁሉ በሌላ ሰው እገዛ ነው የማከናውነው፡፡ እግዚአብሔር በኪነጥበቡ ስላደለኝ በእግሬም በአፌም እሥላለሁ፡፡ በአፌ ሥዬ ስዕሎቼን ሸጬ እስከመጠቀምም ደርሻለሁ፡፡
መቼ ነው ሥዕል የጀመርከው?
ሥዕል የጀመርኩት በልጅነቴ  ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደነገርኩህ በእግሬ ነው ፊደል መጻፍ የጀመርኩት፡፡ ያየሁትን ነገር በእርሳስ እስል ነበር፡፡ እንደዚያ እያደረግሁ ነው የተለማመድኩት፡፡ ሥዕል በጣም ጠቃሚነት እንዳለው ያወቅኩት ደግሞ ለእንቁጣጣሽ ለልጆች ሥሥል ነው፡፡ ራሴ ለበዓሉ እያዞርኩ የምሠጠውን እንዲሁም ለሰፈር ልጆችም እሥል ነበር፡፡ በእግሬ እየሣልኩላቸው በአጋጣሚ ደግሞ በአፌ መሣል ጀመርኩኝ፡፡ በእግሬ እንደምሠራው በአፌ እችላለሁ እንዴ ብዬ? ብሩሼን በአፌ አንሥቼ ሥሞክር ሠራሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሥዕል ትምህርት ቤት እንኳ እንዳለ ያወቅሁት፡፡ በአሜሪካ ሀገር እንደኔ በተፈጥሮ  ሳይሆን  ከጊዜ በኋላ አካል ጉዳተኛ  የሆነች ሴት በአፏ ሥላ፣ ራሷንና አሜሪካን እንዳስጠራች ሰማሁ፡፡ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚያስተላልፈው “ብሩህ ተስፋ” የሚባል የሬዲዮ ዝግጅት ነበረ፡፡ እዛ ላይ ነው የሰማሁት፡፡  እሱን ሰምቼ የሥዕል ትምህርት ቤት አለ እንዴ ብዬ ስጠይቅ፣ እንዳለ ነገሩኝ፡፡ አቢሲኒያ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ገባሁኝ፡፡ የቀለም ትምህርትም በእግሬ እየጻፍኩ ተምሬአለሁ፡፡ በቅድስት ማርያም የቋንቋ ትምህርት ቤት ደግሞ እንግሊዝኛ ተምሬአለሁ፡፡
አሁን እንደ ስቱዲዮ የምትጠቀምበትን ቤት እንዴት አገኘህ?
እዚህ ሥዕል የምሥልበት ጋለሪ በአካል ጉዳተኝነቴ ሥም የሰጠኝ ወረዳው ነው (ቂርቆስ ወረዳ 8)፡፡ ሆኖም የቤት ኪራይ፣ የጥበቃ ወዘተ እከፍላለሁ፡፡ ግብርም እገብራለሁ፡፡ ሥራ ግን ብዙ የለም፡፡ በፊት የተሰጠን ባሕላዊ ልብስ ለመነገድ ነበር፡፡ ሦስት አራት ዓመት ያህል ያንን ብቻ ካልሠራችሁ ተብለን ተቸግረን ነበር፡፡ ሌሎቹ አስረክበው ወጥተዋል፡፡ እኔ መሔጃ ስለሌለኝ፣ የምሰራውም ስለሌለ እንደምታየው በአቧራ በተሸፈነ በማያመች ቦታ ነው እየሠራሁ ያለሁት፡፡ ልብሶቼን እንኳ ሰው ስለሚያለብስ ስለሚያወልቅልኝ፣ ከሥራዬ ጋር አይመቸኝም ብዬ ማመልከቻ አስገባሁ፡፡ አመልክቼ ሥዕል መሣሉን ቀጠልኩበት፡፡  ሥዕል ብዙ የሚገዛ ስለሌለ ግን በሥዕል መተዳደር አልቻልኩም፡፡ ባለቤቴ እዚህ ወረዳ 8 (ቂርቆስ ክፍለከተማ) ነው የምትሠራው፡፡ በሷ እየተደጎምኩ ነው - ሥዕሎቹ ቢሸጡ ግን እንኳን ለባለቤቴና ሦስት ልጆቼ ለሌላም እተርፋለሁ፡፡
ዐውደ ርእይስ አሳይተሃል?
ከሌሎች ጋር ሆኜ አሳይቼአለሁ፡፡ እዚያም ተመልካቾች ያዩና አይዞህ በርታ ይሉሃል፡፡ ነገር ግን ብዙ ሲገዙ አይታይም፡፡ ቆንጆ ናቸው በርታ ይሉህና፣ ከሌላ ሰው ይገዛሉ፡፡ የሥዕል ገዢዎች አሉ፡፡ ሆኖም ሽያጩ የሚከናወነው በደጋፊ ብዛት (በቲፎዞ) ስለሆነ ብዙም ገዢ አላገኘሁም፡፡
የሠዓሊያን ማኅበር አባል ነህ?
የማኅበሩ አባል አይደለሁም፡፡ ለዚያም አንደኛው ምክንያት የአባልነት ክፍያው ከፍተኛነት ነው፡፡ ሌላው የቲፎዞ ጉዳይ ነው፡፡ ለወደፊት ምን አልባት አባል እሆን ይሆናል፡፡ የማኅበር አባል ስትሆን ሙያህ እንዲጎለብት፣ ልምድ እንድትለዋወጥ፣ ሥራዎችህ እንዲጎበኙና እንዲሸጡ መታገዝ አለብህ፡፡
ቀደም ሲል የጠቀስካት አሜሪካዊት ሰዓሊ እንዳነቃቃችህ ተረድቻለሁ፡፡ አርአያዬ የምትለው ሠዓሊስ አለ?
አዎ፤ በትክክል አለ፡፡ አንጋፋው ሰዓሊ ወርቁ ማሞ በአቢሲኒያ አስተማሪዬ ነበሩ፡፡ እርሳቸው አርአያ ሆነውኛል፡፡ በራስ ሆቴል ሥንመረቅ የተገኙት ደግሞ ሠዓሊ ለማ ጉያ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ከአንጋፋዎቹ ብዙ ተምሬአለሁ ማለት ይቻላል፡፡
አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን ከራስህ ሕይወት ተሞክሮ ተነስተህ ልታስረዳኝ ትችላለህ?
በሚገባ፡፡ ሰው ወዶ አይለምንም፡፡ የሚለምን ሁሉ ግን መለመን ነበረበት ብዬ አላምንም፡፡ በተፈጥሮም ሆነ በአደጋ ለአካል ጉዳተኝነት እንጋለጣለን፡፡ በተቻለን መጠን ግን ከአካል ጉዳታችን ጋር የሚጣጣም ሥራ መሥራት አለብን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ምንም የአካል ጉዳት ወይም በጣም አናሳ የአካል ጉዳት ኖሮባቸው ሲለምኑ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ አጋጣሚው እስከፈቀደ ድረስ መሥራት እየቻሉ  መለመን ግን ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ አኔ ተጣጥሬ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡ የአካል ጉዳቴ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት በተፈጥሮ ስለሆነ፣ በልጅነቴ ለልመና በጣም የተጋለጥኩ ነበርኩ፡፡ ያንን ግን አልፌ እግዚአብሔር ይመስገን ከዚህ ደርሻለሁ፡፡ የወደፊቱንም እሱ ያውቃል፡፡ እኔ እየሠራሁ እቀጥላለሁ፡፡
ባለፈው የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ለቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስትያን የንግሥት ዘውዲቱን ሥዕል አበርከተሃል፡፡ የተለየ ምክንያት አለህ?
ንግሥት ዘውዲቱ ቤተ ክርስትያኑን በዚህ መልኩ ስላሠሩ መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ ነው ሥዕሉን ያበረከትኩት፡፡ እድሳቱ ሳይጀመር ሌላ ሥዕል አበርክቼ ነበር፤ ለረዥም ዓመታት ተሰቅሎ በእድሳቱ ምክንያት ወርዷል፡፡ ቤተ ክርስትያኑ ታድሶ በተጠቀሰው ቀን ስለተጠናቀቀ፣ ለክብረ በዓሉም ጭምር ነው የንግሥት ዘውዲቱን ሥዕል ያበረከትኩት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቅዱስ ዑራዔል ጠበል ስለተፈወስኩኝ፣ ቅዱስ ዑራኤልን ለማመስገንም ነው፡፡
ሥዕሎችህን እስካሁን በምን ያህል ዋጋ ሸጠሃል?
ዝቅተኛውን በሰባት ሺህ ብር፣ ከፍተኛውን ደግሞ በዐሥር ሺህ ብር ሸጫለሁ፡፡ ሥዕል ከገዙኝ መካከል የብሪታንያ ኤምባሲ፣ የኢሊሌ እና የጁፒተር ሆቴሎች  ባለቤቶች ይገኙበታል፡፡ የሆቴል ባለቤቶች በርካታ ሥዕሎች ገዝተውኛል፡፡ ሆኖም አሁን ሥዕል  ከሸጥኩ ዐራት ዓመት ሆኖኛል፡፡ ሥዕሎቼ እየተሸጡ አይደለም፡፡
ሠዓሊ ባትሆን ኖሮ ምን ትሆን ነበር?
ሠዓሊ ባልሆንማ ኖሮ፣ የሬዲዮ ጋዜጠኛ ነበር መሆን የምፈልገው፤ እንደ ሰፈሬ ልጅ ጌታቸው ማንጉዳይ፣ ነፍሱን ይማርና እንደ ጎርፍነህ ይመር እሆን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቅዳሜ መዝናኛ ዝግጅትን በጣም ነበር የማደምጠው፡፡
የት ነው ትውልድህና ዕድገትህ?
የተወለድኩት እዚሁ ካዛንቺስ ቅዱስ ዑራዔል ቤተ ክርስትያን ጀርባ ነው፡፡ ቄስ ሰፈር ይባላል፡፡ የአካል ጉዳተኝነቴ በተፈጥሮ ስለነበር በእግሬም አልሔድም ነበር፣ ከጊዜ በኋላ ነው መሄድ የጀመርኩት፡፡ ከሰባት ዓመቴ በፊት ቤተሰቦቼ እያዘሉኝ ነበር የምንቀሳቀሰው፡፡ ከፊደል እስከ ዳዊት ድረስ ቄስ ትምህርት ቤት ስማር ወንድሞቼና እህቶቼ እያዘሉኝ ነበር፡፡ ከስምንት ከዘጠኝ ዓመቴ በኋላ ነበር፣ በቅዱስ ዑራዔል ጸበል ተጠምቄ መራመድ የጀመርኩት፡፡ እናቴ ሐኪም ቤት እየወሰደችኝም የሕክምና ድጋፍ አገኝ ነበር፡፡ እንድድንላት እናቴ ብዙ ለፍታለች፡፡
***

ከዝግጅት ክፍሉ፡- የሠዓሊውን ስዕሎች መግዛት የምትፈልጉ ወይም ሠዓሊውን መደገፍና ማበረታታት የምትሹ በ0902567909 ወይም 0913569353  ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡

Read 669 times