Saturday, 30 March 2024 20:37

ካለፉት 50 ዓመታት ስህተቶቻችን ምን ተማርን!? ለውጥ፣ ሽግግር እና አብዮት

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(3 votes)

የየካቲት 66 ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የተከሰተበት ሃምሳኛ ዓመት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በመታወስ ላይ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ፣ በተለያዩ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚካሄዱት የዳሰሳ ውይይቶችና መጣጥፎች በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። እንዲህ ዓይነት ውይይቶች መካሄዳቸው ዛሬ ላለንበት ሁኔታም ጠቃሚ በመሆኑ ተሳታፊዎቹን  ማመስገን ተገቢ ነው። ይህ ጠቃሚ  ሊሆን የሚችለው ግን ሁሉም ተሳታፊ ወገኖች በቅንነት ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ስህተቶቻችን ለመማር በሚያስችለን ሁኔታ መሳተፍ ሲችሉ ነው። እስካሁን ድረስ የተከታተልኳቸው ውይይቶችና መጣጥፎች ግን ባብዛኛው ባንድ በኩል የትውልድ ውንጀላ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ራስን ነጻ የማውጣት ጥረት የጎላባቸው ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በዚህ ሂደትም ውስጥ ስለ ለውጥ፣ ሽግግርና አብዮት ሊኖረን የሚገባው ግንዛቤ በተውገረገረ መልኩ ሲነሳ ከርሟል። የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ዓላማ እነኚህን መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳቦች ከዘላቂነት ሳይንስ (sustainability science) አኳያ በአጭሩ በማቅረብ ያለውን ብዥታ ለማጥራት መሞከር ነው። ይህንንም በማድረግ ካለፈው የሃምሳ ዓመታት ሃገራዊ ጉዞአችን ለመማርና ካለንበት የፖለቲካ ምስቅልቅል ለመውጣት የሚያስችል ምጥን የዕውቀት ግብዓት ይሰጣል የሚል ተስፋ አለኝ።
የዘላቂነት ሳይንስ፣ በምህዳራዊ አስተሳሰብ ላይ ተመርኩዞ በዘመናችን እየተከሰቱ ያሉትን ውስብስብ ፈተናዎች ለመረዳትና መፍትሄ ለመጠቆም የሚረዳ አዲስ የሳይንስ መስክ ነው። በዚህ ሳይንስ መሰረት፣ ለውጥ በማንኛውም ምህዳር ውስጥ ህልው የሆነና ለየትኛውም ምህዳር በዘላቂነት መቀጠልም ሆነ መጥፋት ወሳኝ ድርሻ ያለው ሂደት ነው። በዚህም መሰረት፣ ከተለዋጭ ሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን ማጣጣም የቻሉ ተፈጥሮአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምህዳሮች እየተሻሻሉና እየዳበሩ ሲሄዱ፣ ያልቻሉት ደግሞ ከዚህ በፊትም ጠፍተዋል ወደፊትም ይጠፋሉ። ለማናቸውም ለውጥ መሰረቱ በነባሩ ወይም አሮጌው ምህዳር ውስጥ የሚበቅሉ አዳዲስ ችግኞችና ባህርያት ናቸው። እነኚህን የለውጥ ዘሮች በሚያስተናግድበት ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ ማንኛውም ምህዳር በሁለት ዓበይት የለውጥ መንገዶች ሊያልፍ ይችላል። የመጀመሪያው፣ ከአዳዲሶቹ ችግኞች ለርሱ ቀጣይነት የሚበጁትን ባህርያት በመለየት በጊዜ ሂደት ከራሱ ማንነትና ምንነት ጋር በማያቋርጥ ሁኔታ የሚያዋህድ የለውጥ ሂደት ይሆናል። ይህ የለውጥ ሂደት ዝግመታዊ ወይም ተደማሪ (evolutionary or incremental) ለውጥ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜ በግልጽ የሚታይ ምህዳራዊ መመሰቃቀል ሳይፈጠር የሚከወን ለውጥ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የለውጥ ሂደት የተፈጥሮአዊው ምህዳር ዋነኛ መገለጫ ነው። ይህንንም ለማሳለጥ ተፈጥሮአዊው ምህዳር በሚሊዮኖች ዓመታት ውስጥ እጅግ አስደናቂ ምህዳራዊ ሂደቶች ማዳበር ችሏል። ይህም፣ በየአንዳንዱ ደቂቃ የሚፈጠሩትን ለቁጥር የሚታክቱ የለውጥ ችግኞችና ባህርያትን ለማስተናገድ አስችሎታል። ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ለውጥ ሰው ሰራሽ በሆኑት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምህዳሮች ውስጥም የሚከሰት ሲሆን፤ ውጤታማነታቸው በየምህዳሮቹ ተመክሮአዊ የመማማር (adaptive learning) አቅም የሚወሰን ይሆናል። በዚህ ረገድ ከተፈጥሮአዊው ምህዳር ልንማራቸው የምንችላቸው በርካታ ትምህርቶች እንዳሉ ይታመናል።
ምንም እንኳን ዝግመታዊ ወይም ተደማሪ ለውጥ በአነስተኛ ዋጋና አለመረጋጋት ወደፊት ለመሄድ የሚያስችል አማራጭ ቢሆንም፣ ማናቸውም ምህዳር ከመሰረታዊ ባህሪው ጋር በተያያዘ እንዲህ አይነቱን ለውጥ የማስተናገድ እድሎቹ ገደብ አለው። በዚህም መሰረት ማንኛውም ምህዳር ወደዚህ ገደብ እየተቃረበ በሚሄድበት ወቅት ተደማሪ ለውጦችን ከማስተናገድ ይልቅ ለውጥን የመገዳደር ባህሪው እየጎላ መታየት ይጀምራል። ይህም የምህዳሩን አለመረጋጋት ለሚያመላክቱ በርካታ ክስተቶች መፈጠር ምክንያት ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ደረጃ ላይ በሚደረስበት ወቅት ምህዳሩ አዳዲስ ለውጦችን ለማስተናገድ ወደሚያስችለው ሁኔታ ለመሸጋገር ዓይነታዊ (transformational) ለውጥ ማካሄድ የግድ ይሆናል። የእንዲህ ዓይነቱ ሽግግር ዋነኛው ትኩረቱ ተደማሪ ለውጦች እንዳይከናወኑ እንቅፋት የሆኑትን ተፈጥሮአዊ፣ አስተሳሰባዊና መዋቅራዊ ሁኔታዎች በማስወገድ ለተከታታይ ተደማሪ ለውጦች አስቻይ የሆኑ ሁኔታዎችን መፍጠር ይሆናል። ይህም ባረጀውና ለመለወጥ ዝግጁ ባልሆነው ምህዳር ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበራቸውን አካላትና ባህርያት በመሰረታዊነት መቀየርን ሊያስከትል ይችላል። እዚህ ላይ በመቀየርና ሙሉ በሙሉ በማጥፋት መካከል ያለን ልዩነት በአግባቡ መገንዘብ ተገቢ ይሆናል። ዛሬ የምንገኝበት ዓለም፣ የጊዜ ምጣኔያቸው የተለያየ ቢሆንም፣ እንዲህ በመሰሉ በርካታ ሽግግሮች ውስጥ ባለፉ ተፈጥሮአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምህዳሮች የተገነባ ነው። በተለምዶ፣ የእርሻና የኢንዱስትሪ አብዮቶች በመባል የሚታወቁትና በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ሂደቶች የእንዲህ ዓይነት አይነታዊ ለውጦችና ሽግግሮች መገለጫዎች ናቸው።
ለውጥና ሽግግር ተፈጥሮአዊ የመሆናቸውን ያህል፣ አልፎ አልፎ ይህንን ተፈጥሮአዊ መርህ በጣሰ መልኩ ነባሩ ሥርዓት ላለመለወጥ በሚያደርጋቸው ጥረቶች የሚፈጠሩ ትንቅንቆች ይከሰታሉ። በተለያየ ደረጃ የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ለእንዲህ ዓይነት ትንቅንቆች መከሰት ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው። በተፈጥሮአዊው ምህዳር ውስጥ እንዲህ ዓይነት ቀውሶች በሚከሰቱበት ጊዜ ሁኔታውን የሚያስተናግድበት የማረጋጋት ዑደት (regulatory function) አለው። ይህም ዑደት በተወሰኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አንዳንድ የተፈጥሮ ምህዳሮችን ሙሉ ለሙሉ እስከማጥፋት (extinction) ድረስ ሊዘልቅ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሊቀር የማይችል ለውጥና ሽግግርን አምርሮ የመገዳደር ሁኔታ በሰው ሰራሽ ምህዳሮች ውስጥ በሚከሰትበት ወቅት ሁኔታውን በአስገዳጅነት ለመቀየር የሚያስገድዱ አብዮታዊ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ከሃገራችን የየካቲት ስልሳ ስድስቱ አብዮት ጋር በተያያዘ ተደጋግመው የሚጠቀሱትና የሶሻሊስቱ አብዮት ዋነኛ መገለጫዎች ተደርገው የሚወሰዱት የፈረንሳዩ ፓሪስ ኮምዩን እና የራሺያው የቦልሾቪክ አብዮቶች በዚሁ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። በሚያሳዝን ሁኔታ እነኚህና ሌሎችም ማህበራዊ አብዮቶች በከፍተኛ የህዝብ እልቂትና ማህበራዊ ክስረት የታጀቡ ሆነው አልፈዋል።
በሃገራችን በኢትዮጵያ ባለፉት ስልሳ ዓመታት የተከሰቱትን የለውጥ አጋጣሚዎች ከላይ በአጭሩ በተቀመጠው የለውጥ፣  ሽግግርና አብዮት ጽንሰ ሃሳቦች መሰረት መፈተሹ ዛሬ ላለንበት አስቸጋሪ ሁኔታም ጠቃሚ እይታ ይሰጣል የሚል ዕምነት አለኝ። በዚሁ መሰረት፣ በቅድሚያ የየካቲት ስልሳ ስድስቱን ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንመልከት። ይህን እንቅስቃሴ፣ አንዳንድ ወገኖች በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ ግራ ዘመም ሃይሎች በቀቢጸ ተስፋ የፈበረኩት አድርገው ሊያቀርቡት ሲሞክሩ፣ ጥቂት ግራ ዘመም ሃይሎችም ይህንን በሚያጠናክር መልኩ ለተማሪው እንቅስቃሴ የማይገባውን የመሪነት ድርሻ ሲሰጡ ይደመጣሉ። ከዘላቂነት ሳይንስ አኳያ ስንመለከተው ግን፣ ለዚህ እንቅስቃሴ በዚያ መልኩ መከሰት ዋነኛው ምክንያት ንጉሳዊው ሥርዓት በተደጋጋሚ የተፈጠሩለትን የተደማሪ ለውጥ ዕድሎች ለመጠቀም አለመቻሉ ነው። ስለሆነም፣ የየካቲቱ ህዝባዊ እንቅስቃሴ በአርሶ አደሩ፣ በሰራተኛው፣ በምሁራኑ፣ በወታደሩ፣ በተማሪውና በሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች እንቅስቃሴ ታጅቦ ሊከሰት ችሏል። ንጉሣዊው ሥርዓት በመጨረሻ እድሜውና  በእንቅስቃሴው የመጀመሪያ ወራቶች፣ ህገ መንግሥት ማሻሻልን ጨምሮ፣ አንዳንድ የለውጥ ማሻሻያዎችን የማድረግ ሙከራ አድርጎ ነበር። ነገር ግን፣ ይህ ሙከራ መሆን ከሚገባው ወቅት እጅግ ዘግይቶ የመጣ ከመሆኑም ባሻገር ባብዛኛው በመንግሥታዊ መርበትበት ውስጥ የሚከናወን በመሆኑና መንግሥታዊ ሥልጣኑን ለመቀማት የተዘጋጀው ሃይል ድጋፉን የነፈገው በመሆኑ ጥረቱ ሁሉ መክኖ ቀርቷል። በዚህም የለውጥና የመለወጥ ዕድሉ ሊከሽፍ ችሏል።
የንጉሡን ከሥልጣን መውረድ ተከትሎ፣ በሃገራችን የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነው የሥርዓት ሽግግር እድል ተፈጥሮ ነበር። ይህ የሽግግር ወቅት፣ መጀመሪያው ላይ አንዳንድ ተስፋ የሚሰጡ የለውጥ እርምጃዎች የታዩበት ነበር። ነገር ግን፣ የተፈጠረው የሽግግር እድል ለሀገራዊው ነባራዊ እውነታና ለዓለም አቀፉ ተጨባጭ ሁኔታ በሚመጥን አዕምሮአዊና ተቋማዊ አደረጃጀት መመራት ባለመቻሉ ሽግግሩ ሊጨናገፍ ችሏል። ይህም በተከታዮቹ የዓብዮት ዓመታት ከፍተኛ ዋጋ ላስከፈሉን ሌሎች ተከታታይ ቀውሶች ሊዳርገን በቅቷል። ለዚህ የሽግግር ዕድል ብክነት ወታደራዊ አገዛዙ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ቢሆንም፤ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የተፈለፈለው የተዓብዮ ፖለቲካ የማይናቅ ድርሻ እንደነበረው መካድ አይቻልም። ለዚህም፣ የዚያ ትውልድ አባላት በሙሉ ሃላፊነት ልንወስድና የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል። የየካቲት ስልሳ ስድስቱን ያህል ባይሆንም፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ በግንቦት 1983 እና በመጋቢት 2010 ዓ.ም. መሰል የሥርዓት ሽግግር ዕድሎች አጋጥመዋታል። ሆኖም ግን፣ ከቀደመው የፖለቲካ ህመማችን ያልተማርንና ያልተፈወስን በመሆናችን፤ የ1983 የለውጥ ዕድል ባክኖ ሲቀር፣ የ2010 የለውጥ ዕድልም ወደዚያው በመንደርደር ላይ ይገኛል። ለዚህም ማሳያ፣ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ጎልተው የሚታዩትን በርካታ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል። በየአካባቢው በሰፊው የሚታየው የሰላም እጦት፣ ግጭትና ጦርነትም የሽግግርን አስፈላጊነት አበክረው የሚያስገነዝቡ ናቸው። ይህንን ዕውነታ አለመረዳት ለወቅቱ አበይት የፖለቲካ ተዋንያንም ሆነ ለሃገራችን የማይበጅ ነው።
ዛሬ ሃገራችን ከምትገኝበት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታ ለመውጣት፣ ከየካቲት ስልሳ ስድስቱም ሆነ እርሱን ተከትለው ከመጡ የለውጥና ሽግግር እድሎችና ክሽፈቶቻቸው ጠቃሚ ትምህርት ልንወስድ ይገባል። ይህም ሲባል ከዚህ ጽሁፍ አኳያ የሚከተሉት በዋነኝነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ማንኛውም ማህበረሰብ ሆነ ሃገር ወደ ተሻለ ደረጃ መጓዝ የሚችለው የሚያጋጥሙትን የለውጥና ሽግግር እድሎች እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ከቀዳሚው የሚወሰደውን አዲስ ከሚተካው ጋር ሊያዋድድ የሚችል አስተሳሰባዊና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ይሆናል።
ይህንንም ለማሳካት፣ የፖለቲካ ልሂቃንና ቡድኖችም ‘እውነት ከእኔ ጋር ብቻ ናት’ ከሚል የተዓብዮ አስተሳሰብ ራሳቸውን በማንጻትና የሁሉም ወገኖች የመደመጥ መብትን በማክበር ለህዝብ ሉዓላዊነት ተገዢ የሆነና ዓይነታዊ ለውጥን የሚያሳልጥ ሃገራዊ ትርክት ለመፍጠር መጣር ይኖርባቸዋል።
ምሁራኖቻችንም ሃገራዊ እውነታን ከዓለም አቀፉ አስተሳሰብ ጋር በማስተሳሰርና ሃገራዊ የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን ጠቃሚ ከሆነው ማህበራዊ እሴቶቻችንና ሃብቶቻችን ጋር በማቀናጀት፣ ለሃገራዊ ልማትና እድገት የሚበጁ ሁለንተናዊ አስተሳሰቦችን ማመንጨትና ማራመድ ይጠበቅባቸዋል።   
አጠቃላይ ማህበረሰቡና በተለይም ወጣቱ ትውልድ በዕውቀት ላይ ካልተመረኮዙና ከሃገራዊ እውነታ ጋር ከማይጣጣሙ ‘የመንጋ አስተሳሰቦች’ ራሳቸውን በማንጻት ሠላማዊ ለሆነ ለውጥና ሽግግር በቁርጠኝነት መሰለፍና ሃይልን እንደዋነኛ የለውጥ መንገድ የሚያራምዱ ማናቸውንም ወገኖች ሃይ ሊሏቸው ይገባል።         
ዛሬ ባለንበት ሁኔታ፣ እነኚህንና ሌሎች መሰል ተመክሮዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የምንገኝበትን አስቸጋሪ የቀውስ ሁነት መቀየር ካልቻልን፣ ወደማይቀረውና ብዙ ዋጋ ሊያስከፍለን ወደሚችለው ‘አብዮታዊ’ ምስቅልቅል’ የምናመራ ይሆናል። ይህ እንዳይሆን የፖለቲካ መሪዎቻችን ራሳቸውን ከዕውነታው ጋር ከማይጣጣመው የጥቁር ወይም ነጭ፣ ብርሃን ወይም ጨለማ ፖለቲካ በማላቀቅ፣ ፊት ለፊታቸው ያለውን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
***
ከአዘጋጁ፡-
ደስታ መብራቱ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ የዘላቂ ሽግግር ማዕከል ፕሮፌሰር ሲሆኑ፤ የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚም አባል ናቸው።        
Read 424 times Last modified on Wednesday, 03 April 2024 21:29