Saturday, 30 March 2024 20:41

እኛም ተደነጋግረናል!!

Written by  ብርሃነ ዓለሙ ገሣ
Rate this item
(1 Vote)

 “በአገራችን የፖለቲካ ውጥረት፣ በአገራችን የዋጋ ንረት … ያልተደነጋገረ ካለ እርሱ በጣም ዕድለኛ ነው፡፡  በስልጥኛ የሚነገር አንድ ምሣሌያዊ አባባል አለ፡፡ “ለአዲ ፍቼ፣ ለአዲ ብቼ” ይላል፡፡ ሲተረጎም፣ የአንዱ ፋሲካ፣ ለሌላው ልቅሶ - እንደማለት ነው፡፡ በዚህ በኩል የማፈርሰው ለልማት ነው ሲል፤ በሌላኛው ወገን ደግሞ ለጥፋት ነው ይላል፡፡”
አንድ ቢያጆ እንቅልፍ አገባድጄ ነቃሁ። አዎ የሞት ታናሽ ወንድም የተባለለት ኃያሉ እንቅልፍን ድል ነስቼ ዓይኔን ገለጥኩ፡፡ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው የጊዜ ቆጣሪ፣ ከሌሊቱ 7፡40 ሰዓት እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ለማረጋገጥ የእጅ ሰዓቴን አየሁት፡፡ 7፡36 ሰዓት ይላል፡፡ ማንን ልመን? የግድግዳውን ወይስ የእጅ ሰዓቴን? ለማረጋገጥ ብዬ መደወል ወይም መልዕክት መላክ አልፈለግኩም፡፡ እንደተወዛገብኩና እንደተደነጋገርኩ መኝታ ቤታችን ውስጥ ለጥቂት ደቂቃዎች ዝምታ ነገሠ፡፡ የትዳር አጋሬ ለሽ ብላለች፡፡ የሰላም እንቅልፍ፡፡ ፊያሜታን መሰለችኝ፡፡ ትንሽ ነበልባል፡፡ ሰሜናዊት ጽብቕቲ - አሥመሪና፡፡
መለስ አልኩ፡፡ ነፍሴ ሙዚቃ አሰኛት፡፡ ከፊት ለፊቴ ከተሰደረው ማጫወቻ የዝነኛዋ ኤርትራዊት ድምጻዊ ሔለን መለሰን፣ “ተደናጊረ” እንዲጀምር ማጫወቻውን ጨቆንኩት። እየተስረቀረቀች ስታወርደው ነፍሴ ክፉኛ ተወራጨች፡፡ ምናለ ሞት ባይኖር? ስንኝ በስንኝ ለመተርጎም አቅም አጠረኝ፡፡ ጭራሽ ባይተዋር ግን አልሆንኩም፡፡ ሴሜቲክ ለሴሜቲክ ስለሆነ ሙቀት ተሰማኝ፡፡ “ሔለንን በአካል አግኝቻት በኢንተርቪው ብታፍታታልኝ?” ብዬ ተመኘሁ። የእርሷን ሙዚቃዎች ሳዳምጥ አንዳች ውርር የሚያደርግ ነገር ይሰማኛል፡፡ ለዚህ ነው በክፉ ጊዜ ላይ ሆነን እንኳ፣ “ሔለን! አንድ ቀን አንቺ መድረክ ላይ የመድረክ ንግሥት ሆነሽ፤ እኔ ደግሞ ታዳሚ ሆኔ ሳጨበጭብልሽ ይታየኛል።” ያልኳት፡፡
የአሥመራ ትዝታ፣ የሰሜናዊት ኮከብ ፍቅር፣ ጓል አሥመራ፣ በዘንባባዎች ጥላ ሥር … እንዲህ ነው እንዲያ ብል ማንስ ያምነኛል? በነገራችን ላይ የአገራችን የአማርኛ፣ የትግርኛ፣ የኦሮምኛ፣ ጉራግኛ ወዘተ. ከውጪ ደግሞ የሱዳን ዘፈኖች ጉዳዬ ብዬ አዳምጣለሁ፡፡ ይህ እኮ በእኔ አልተጀመረም፡፡ ብዙዎች አሉ፡፡ ብዙዎቻችን ለጥበብ እንገዛለን፤ እንሸነፋለን፡፡ በዚያው መጠን የሚቃወም ባይጠፋም፡፡
አዎ የሔለንን “ተደናጊረ” ደግሜ ተመስጬ አዳመጥኩት፡፡ አልበቃኝም - ሰለስኩት። ሰሜናዊቷ ኮከብ አሥመራ ላይ ሆና እንደተደናገረችው ሁሉ እኛም ተደነጋግረናል። እኛ ዘንድ የሚያደነጋግር ነገር ይበዛልና። የግድግዳና የእጅ ሰዓቴ ቢያደነጋግሩኝ መላ ይኖራቸዋል፡፡ እኛን ያሰቃየን፣ መላ የጠፋለትና መላ የሌለውን ነው፡፡ የቀኝ ፍሬቻ አብርቶ ወደ ግራ የሚታጠፈው የትየለሌ ነው፡፡ ግሪካዊው ፈላስፋ ሶቅራጥስ፣ ሶስት ነገሮች ሲከወኑ ቢዋሽም ክፋት እንደሌለው ተናግሯል ይባላል። የተጣላን ለማስታረቅ፣ ፍቅረኛን ለማግባባትና አገር ስትወረር የፕሮፓጋንዳ ሥራ ለመሥራት፡፡ እኛ አገር ግን ውሸት ልክና መጠን ወይም ዳር ድንበር የለውም፡፡ ከምናምነው የማናምነው አይበልጥምን?
የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ዜና ሲያውጅ ሙድ እንይዝበታለን፡፡ ምክንያት? ቅሸባ የታጨቀበት ዜና ስለሚበዛ፡፡ የሚተላለፈው ዜናና በውኑ ዓለም ላይ ሆኖ የምናየው ለየቅል ሲሆንብን ሁሌም እንደነጋገራለን፡፡ እንወዛገባለን፤ እንጭበረበራለን … ፡፡
ቴሌቪዥናችን አደግን ተመነደግን ብሎን ደቂቃዎች ሳይቆጠሩ፣ የሌላው ዓለም - አቀፍ መረጃ አቀባይ “የምን ማደግ? - አትልፉ፣ ወፍ የለም” ይለናል፡፡ ሞታችን፣ ሐዘን፣ ደስታችን፣ ማግኘት - ማጣታችን ወዘተ. እንዲሁ እንዳወዛገበና እንዳደነጋገረን ይኸው አለን፡፡ “በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በኢትዮጵያ ታሪክና መረጃ እኔ ተደነጋግሬ አላውቅም” የሚል ካለ እርሱ ከማርስ የተገኘ መሆን አለበት፡፡ አለሁ የሚል ከተገኘም ልምዱን ሊያካፍለን ይገባል፡፡ ወዲህ ነኝ ይበለን፡፡
በቅርቡ በአንድ ኤፍ.ኤም ራድዮ፣ በቀጥታ ስርጭት ለሚተላለፍ ፕሮግራም ስለ ድርሰት ሥራዬና ተያያዥ ጉዳዮች አስተያየት ለመስጠት ተጠይቄ ተገኝቼ ነበር፡፡ ፕሮግራሙ የቀጥታ ስርጭት ስለሆነ ለሚቀርቡልኝ የአድማጭ ጥያቄዎች - ራሴን ኤዲት እያደረግኩ ነበር መልስ የምሰጠው፡፡ አድማጮች ለጠየቁኝ ሁሉ ምላሽ ስሰጥ ቆየሁ፡፡
ለመሰናበቻ አዘጋጆቹ ድርሰትና የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታን በሚመለከት አስተያየት እንድሰጥ ጋበዙኝ፡፡ የአቅሜን ያህል በዚያ ውስን ሰዓት ማለት የምችለውን አልኩ፡፡ የእኛ አገር ከሌሎች ለየት እንደምትል ለማብራራት ማሳያዎችን ጠቀስኩ፡፡ በአገራችን ሥም፣ በአገራችን ባንዲራ፣ በአገራችን ታሪክ፣ በአገራችን የሥራ ቋንቋ … ውዝግብ እንዳለና አንድ እንዳልሆንን ገለጽኩ፡፡ ይኼኔ አንድ አድማጭ ጣልቃ ገቡ፡፡ በአንዳንድ ጋዜጠኞችና እንግዳ ተደርገው በሚቀርቡ ሰዎች ዘንድ ስህተት እንደሚሠራ በእርግጠኝነት ተናገሩ። ”እኔ በአገሬ ሥም፣ አንድነት፣ ባንዲራ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ተወዛግቤ አላውቅም፡፡ ጥቂቶች ስላልፈለጉ ልዩነት ተብሎ መወሰድ የለበትም … የማይደግፈው ማን ቆጥሮት ነው ልዩነት  አለ የሚባለው?” በማለት ደስ ያላቸውን ከቁጣ ጋር አወረዱብን፡፡ እኔም ጠብቄ መልስ ልሰጥ ተዘጋጀሁ፡፡ የተሰማኝንና የማምንበትን በጥቂቱም ቢሆን ተናገርኩ፡፡
“እርስዎ የራስዎ አቋም እንዳለዎ ሁሉ እኛም አለን፡፡ ጥያቄ እንጠይቅ ከተባለ ማንም ለመጠየቅ አይሰንፍም፡፡  አገራችንን በሚመለከት መሬት ላይ ያለውን እውነት እንሸፋፍን ካልን፣ ‘አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ’ ነው የሚሆነው፡፡ እናንተ ለመበየን የተነሳችሁ ማን ናችሁ? ላሉት እርስዎስ ማን ነዎት? አውቀን እንዳላወቅን ማለፉስ ተገቢ ነው ወይ፡፡ በአገር ሥም፣ በባንዲራ፣ በታሪክና በቋንቋ እንግባባለን ወይ?” አልኳቸው፡፡
የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር ይላሉ አበው፡፡ እዚህ አገር ቅሸባ ይበዛል፡፡ አስተያየት ይቀሸባል፤ ሪፖርት ይቀሸባል፡፡ ደፍረን እውነትን የምናወራ፣ ለእውነት የምንጋፈጥ ስንቶቻችን ነን? አለቃ ፊት ሌላ፣ ከአለቃ ፊት ገለል ስንል ሌላ የምንሆን እጅግ በርካቶች ነን፡፡ ለማለት ቀላል ለመሥራት ግን ከባድ የሆነባት የምትገርም አገር - ኢትዮጵያ!
የረዥም ዘመን ታሪካችንን ለጊዜው እናቆየውና በኃይለሥላሴ፣ በደርግና በኢሕአዴግ አሁን ደግሞ በብልጽግና ስንት ነገር ተብሎ ስንቱ ተፈጸመ? የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዘገብን ብለን በቁጥር ጫወታ ተጠምደን እያለ፣ “ይህን ያህል ወገኖች ተራቡ፣ ተጠሙ፣ ታረዙ … ” እንባላለን፡፡ አንዳንዴ የገዛ ጆሯችንን እንጠራጠራለን፡፡ የሚባለው ሌላ፤ የሚተገበረው ሌላ፡፡ ባለፉት ሥርአቶች የተሠራ በጎ ነገር የለም ባይባልም ጥፋትም ተሠርቷል። ሰው በግፍ የተሰቀለባት፣ ሰው በግፍ በጅምላ የተረሸነባት፤ በጅምላ ተገድሎ በስካቫተር ታፍሶ የተቀበረባት፣ ሰውን ያህል ክቡር የእግዚአብሔር ፍጡር የተዋረደበት… ተቋም እንደ ተቋም፣ መንግሥት እንደ መንግሥት አጥፍቶ ይቅርታ የማይጠየቅባት አገር - ኢትዮጵያ ናት፡፡ ሕግ ባለበት አገር፣ ሕዝብን በግልጽ የሚሳደብ፣ ዋሽቶ ማስታረቅ ሲገባው ዋሽቶ የሚያጋድል፣ ተማረ የተባለው በርካታ ቁጥር ያለው ትውልድ እንቅፋት የሚሆንበት፣ ቁጭ ብሎ መነጋገር ዳገት የሚሆንበትና ከእኔ በላይ ለአሳር የሚል ወልካፋ አእምሮ የያዘ ጀብራሬ ይበዛል፡፡
በአገራችን የፖለቲካ ውጥረት፣ በአገራችን የዋጋ ንረት … ያልተደነጋገረ ካለ እርሱ በጣም ዕድለኛ ነው፡፡  በስልጥኛ የሚነገር አንድ ምሣሌያዊ አባባል አለ፡፡ “ለአዲ ፍቼ፣ ለአዲ ብቼ” ይላል፡፡ ሲተረጎም፣ የአንዱ ፋሲካ፣ ለሌላው ልቅሶ - እንደማለት ነው፡፡ በዚህ በኩል የማፈርሰው ለልማት ነው ሲል፤ በሌላኛው ወገን ደግሞ ለጥፋት ነው ይላል፡፡ ማን ነው እውነት ላይ የቆመው? ጊዜ መስተዋት ነውና ወደፊት ሀቅ መውጣቱ የማይቀር ነው፡፡ አጥፍቶ ገነት የሚገባስ ይኖራልን? እኛ ያልተደነጋገርንበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ በኃይማኖት፣ በዘር፣ በጎሣ … ከእኛ በላይ የተደነጋገረ ማን ይሆን?
ለማንኛውም ግን ተስፋ አንቆርጥም፡፡ በዓሉ ግርማ “ኦሮማይ” በተሰኘው መጽሐፉ፣ “ሰው ያለ ተስፋ ምንድነው? ተስፋ በልባችን ማሳደር አለብን፤ ተስፋ በሌለበት ቦታም ቢሆን፡፡” ይላል፡፡ የመጽሐፉ መሪ ገጸ ባህሪ ጸጋዬ ኃይለማርያምስ ቢሆን በሁለቱ እንስቶች (በሮማን ኅልተወርቅና በፊያሜታ ጊላይ) ፍቅር ተደነጋግሮ አልነበረምን? ለመውጫ ይኸው፦
“እንባ እንባ ይለኛል፣
ይተናነቀኛል
ግን እንባ ከየት አባቱ?
ደርቋል ከረጢቱ
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እያለቀሰች
መከረኛ ነፍሴ፡፡”
(በዓሉ ግርማ፣ ኦሮማይ)   

Read 862 times