Saturday, 30 March 2024 20:57

ማንበብ ከሞትም ያድናል!

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(2 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
  የጦር መሳሪያ ድምፅ  ሞቅ  ደመቅ ብሎ መሰማት ጀመረ። ባህር ኃይል መደብ ውስጥ ምድር ሰማዩን የሚያናውጥ ድምፅ ተሰማ። በባህር ኃይል መደቡ የሚገኙ መርከበኞች በፍጥነት የመከላከያ መሳሪያቸውን ከግምጃ ቤት አንስተው በየምሽጋቸው  አደፈጡ። የጦር መርከቦች ሁሉ ወደ አውላላው ባህር ቀዝፈው ፊታቸውን ወደ ወደቡ አዙረው በተጠንቀቅ ቆሙ። ጓደኛዬ እራቱን በልቶ እንዳጠናቀቀ ነበር የክተቱ አላርም’ የተሰማው። ጓደኛዬ መሳሪያውን ከቅርብ ግምጃ ቤት አውጥቶ በመታጠቅ ከሆስፒታሉ ምዕራብ አቅጣጫ የደፈጣ ስፍራውን ያዘ። ይህ ስፍራ በሦስት አቅጣጫ የጦርነቱን ሂደት ቁልጭ አድርጎ  የሚያይበት ስፍራ ነበር። ከፊት የስድስተኛ ክፍለ ጦር አባሎች ወደ ኋላ አፈግፍገው የህዳጋን የሙጥኝ ብለው እየተፋለሙ ነው። ድልድዩን አማፂያኑ  አልፈው እንዳይገቡ መራር መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡  አማጺያን ድልድዩን ለመሻገር ግንባራቸውን ሆነ ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው እየተላለቁ ነበር። ይህንን ድልድይ አልፈው ከገቡ የምጽዋ ወደብ ኢትዮጵያዊነት ለዘለዓለሙ ያከትማል።
መድፍ ያጓራል። ቢኤም ያስገመግማል። መትረየስ እንደ ማዕበል እያጓራ ከፊቱ ያለውን ያጭዳል። ኤኬ እንደ ፈንድሻ ይንጣጣል። ነብስ ግቢ፣ ነብስ ውጪ ሆነ። ሁሉም “ልብ አይታመንም እንኳን ባልንጀራ” ዘንድ የደረሱ ነው የሚመስለው፡፡ የስፍራው ወሳኝነት  ለሁለቱም ሀይል ገብቷቸው መተላለቁን በጸጋ የተቀበሉት ይመስላል። ድልድዩ በምርጥ ባለሙያ ታስቦ የተገነባ በመሆኑ፣ በከባድ መሳሪያ ቢቀጠቅጡት እንኳ  ከመፈንከት በቀር ንቅንቅ አይልም፡፡ አሸናፊው እንዲሻገርበት የተመቻቸ ይመስላል። በዚህ ሁሉ  አሸባሪ ድምጽ  መካከል የላቀ አሸባሪ ድምጽ ድንገት ተሰማ። ጓደኛዬ ቁጢጥ  ባለበት ራደ። ድምጹ የአየር ኃይል ጀት ነበር። አይኖቹ ፈጥጠው ቀሩ። ጀቷ እንዴት ያንን  የአቧራ ጉም ገልጣ ገብታ በፍጥነት ኢላማዋን መትታ፣ ሽቅብ ወደ ደቡብ ቀይ ባህር  አቧራውን በርቅሳ ተፈተለከች!
ሰውዬው እናቱ ሞታ አርጂው አቀበት ላይ ቆሞ፤ “አያ እገሌ እናትህ ሞታለችና ቶሎ ድረስ !” ይሉታል።
ሰውዬው ባለበት ደንግጦ ቆሞ፤ “ምን ሆና ሞተች ?!” ሲል ይጠይቃል።
 “መብረቅ መቷት!”
“ውይ እንዴት ትደንግጥ !” አለ አሉ።
ይህን አባባል ጓደኛዬ እውነት ነው ያለው የጀቷን ድምፅ እንደሰማ  ነው። በተከታታይ ይህንን ከባድ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ጀብዱ የአየር ኃይል ጀቶች ፈጸሙ። “ይህ ፍልሚያ ካሚካዚ ነው !” አለ ጓደኛዬ በልቡ።  ካሚካዚ የጃፓንኛ ቃል ነው። ጃፓኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጠላትን አውሮፕላን ፣ መርከብና ፐርል ሀርበር ባህር ኃይል መደብ ለመደምሰስ ይወስናሉ። በዚህ እቅድም የጃፓን አየር ኃይል አባላት  ጀታቸውን አብረው  ከእነታጠቁት ቦንብ  በጠላት ንብረት  ላይ በመፈጥፈጥ የጠላትን ኃይል አውድመው አብረው ይወድማሉ።
ካሚካዚ ላይ የሚዋጉት የአየር ኃይል አባላት  ልክ ተመልምለው ለግዳጅ ሲሰማሩ ለአንድ ለአገሪቱ ታላቅ ጀግና የሚገባው ክብር፣ ኒሻን በቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ አውደ ውጊያው ውስጥ ለገቡ ከዚህች ዓለም በሞት ቀድሞ እንደተሰናበቱ ይታመናል።(በነገራችን ላይ በካሚካዚ እንዲሰው ግዳጅ ተሰጥቷቸው የታዘዙትን ወታደራዊ ትእዛዝ ፈጽመው በህይወት የተረፉ አብራሪዎች ነበሩ። ግዳጃቸውን ስለሚያውቁ በመትረፋቸው ተቆጭተው፣ ሀይለኛ የስነልቦና መዘበራረቅ ደርሶባቸዋል።)
ይህ የየካቲት አንድ ቀን 1982 ዓ.ም የአየር ኃይል ውጊያ ቁርጥ ካሚካዚን ሆነ። ጀቷ ተፈጠፈጠች ብሎ ተንጠራርቶ ሲመለከት፣ ምድርን የመሳም ያክል ዝቅ ብላ አለቀላት ብሎ ልቡ ስቅል ሲል፣ የታጠቀችውን መሳሪያ ወርውራ የሚፈጥረውን እልቂት ማየት የዘገነናት ይመስል ሽቅብ አፍንጫዋን ቀልብሳ ትምዘገዘጋለች። ፀረ አየር መቃወሚያ  ሽቅብ ይንጣጣባታል። ለጀቷ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዲሉት ዓይነት ይሆናል። ድምፅዋም እንደተለመደው የሰራ አከላትን ይነዝራል።
ይህንን መስዋእትነት ለመፈጸም አየር ኃይሉ ከሦስት አቅጣጫ ትእዛዝ እንደሚቀበል ጓደኛዬ ገመተ።  ይህ ትእዛዝ 1ኛው ከፕሬዚዳንቱ ቢሮ የሚተላለፍ ሲሆን ፤ 2ኛው ከአስመራ ሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት ቢሮ ከሚገኙ ከፍተኛ ኃላፊዎች ነው፡፡ 3ኛው ጦርነቱን ከሚመሩት ወሳኝ መኮንኖች ሲሆን፤ ይህንን ድልድይ ከሚያልፍ አብሮ መመታቱን ይቀበሉታል።  ለአገርና ለወገን ደህንነት ሲባል ይህንን አይነት መራር ጽዋን የሚጎነጭ መኮንንን “አብረህ ምታን!” ብለው ያዛሉ። አየር ኃይል ይህንን ዘግናኝ ትእዛዝ ተቀብሎ ‘ካሚካዚ ‘ ሲፈጽም ጓደኛዬ የአይን ምስክር ሆነ። ይህን ትእዛዝ የሚፈጽመው አብራሪው  መኮንን፤ ምን ያስብ ይሆን? ምን ያህልስ ይዘገንነው ይሆን? ቆዘመበት ።
ከሲያድ ባሬ ጦር ጋር በተደረገው ፍልሚያ የዘመኑ የኢትዮጵያ  አየር ኃይል ተአምር መስራቱ  የዓለም መነጋገሪያ መሆኑን አስታወሰ። ይህንን  አቧራን ገልጦ  ማደባየቱን ቢመለከቱ ምን ይሉ ይሆን? ሲል ጓደኛዬ በአያሌው አብሰለሰለ።
 “ይሄኔ ደጀን ጦር  ከአስመራ እየተንቀሳቀሰ ነው።” አለ በሀሳቡ ጓደኛዬ። ሻዕቢያ  ደግሞ ደጀን ጦር ከደረሰ ሳንድዊች እንደሚያደርጉት ስለሚገባው ከቀረበ ንፋሲት ከተማ ላይ፣ ከራቀም  ጊንዳዕ ከተማ ላይ   ሲገታው በሃሳቡ ታይቶት በትካዜ አቀረቀረ። የገመተው ትክክል ነበር።
በሌላኛው ግንባር ከጨው በረሃ  በግራር ሰርጥን አልፎ  ባህር ኃይል መደብ ለመግባት የሚገሰግሰውን የአማጺ ሠራዊት ለመግታት የተደረገው ፍልሚያ  ዘግናኝ  ነበር። አንድ የሻዕቢያ ታንክ ከሚካኤል ቤተ ክርስትያን አቅጣጫ ታየች። ግራር ሰርጽ ላይ ያለው ከባድ መሳሪያ ይዘንብባት ጀመር። ታንኳን ተገን አድርጎ ወደፊት ለሚተመው የጠላት ጦር፣ እያንዳንዷን እርምጃ መዝለቅ በጣም መራር ነበር። የሻዕቢያ ሠራዊት እንደ ቅጠል እየረገፈ ወደፊት ገፋ። የወደቀን ማንሳት ብሎ ነገር አይታሰብም፡፡ ወዳቂው ሲደፋ እያየ ከኋላ የሚከተለው  አንድ እርምጃ ይጨምርና እርሱም ይወድቃል። ... ስፍራው አውላላ ሜዳ ነው፡፡ በ180 ዲግሪ አንድም ተገን የሚያደርጉት ከለላ  የለም። ሰው ግንብ ፣ ሰው ከለላ እየሆነ አንድ እርምጃ ለመጨመር ሺህ እየወደቁ ወደ ግራር ተጠጉ። የምድር ጦር፣ የባህር ኃይል ማሪኖች፣ መርከበኞች መራሩን ፍልሚያ አጧጧፉት። አያሌ ጀግኖች ወደቁ።
ሦስተኛው የሻዕቢያ ኃይል የሚመጣው በጉርጉሱም መዝናኛ ስፍራ ነው። ይህ ስፍራ በየብስ ከባህር ኃይል መደብ ጋር ስለሚገናኝ “ከሊዲንግ ሲማን ኳርተር” ጀርባ ባለው የብስ ላይ ፈንጂ ተቀብሮበት ነበር። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ወደ እዚያ አካባቢ ዝር የሚሉ ውሾች ለአሳዛኝ አደጋ ይጋለጣሉ። ፈንጂው ፈንድቶ ለህልፈት ይዳርጋቸዋል። ይህ ፈንጂ ነበር መደቡን በሰሜን አቅጣጫ የሚጠብቀው። ጦርነቱ ሊካሄድ ወራት ሲቀረው ‘ፈንጂው  ኤክስፓየርድ ‘ አድርጓል በሚል ሰበብ ስለተጠረገ፣ ያለምንም አደናቃፊ ሻዕቢያ ሰተት ብሎ የሚገባበት ስፍራ መሆኑን ጓደኛዬ አሰበ። ይህ ከሆነ እርሱ ከግቢው ጋር ያለው ግንኙነት እንደሚቋረጥ ገባው። ያለበትን ሁኔታ ገመገመ ፣ ማንም አጠገቡ የለም። “እዚህች ሰንደቅ ዓላማ ስር ነው የምንሞተው!” እያለ ደጋግሞ ይናገር የነበረ አለቃው፣ በስፍራው የለም። ከፊት ለፊቱ ዘገው በሚባል መሳሪያ ላይ ሚሊሻዎች ድፍት ብለው ይታዩታል። ከማዶ ትጥቅና ስንቅ በመኪና  ሲያቀርብ የነበረው ሾፌር በአልሞ ተኳሾች ተመትቶ የድረሱልኝ ድምፅ ያሰማል። ጠቅላይ መምሪያው በጠላት ተመትቷል። ስለዚህ ከፍተኛ መኮንኖች ሁሉ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ታጥቀው ፍልሚያ መግባታቸውን ጓደኛዬ ሰማ። አሁን ስፍራ በመቀየር ካገኛቸው ጓዶች ጋር ተቀላቅሎ ለመፋለም ሞከረ። ይህ ፍልሚያ  ለ96 ሰዓታት፣ ወይም ለአራት ቀናት ቀጠለ። በእነዚህ ቀናት ውሃ አልጠጣም ፣ ምግብ አልበላም፣ እንቅልፍ  በአይኖቹ አልዞሩም። ይህ ሁሉ ትውስ ብሎ ባሰቡት ለመከወን ሰላም ወሳኝ ነው። አለበለዚያ ትውስ የማይል ጉዳይ ነው። በማንኛውም ሰዓት በጠላት ሊገደልም፣ሊገድልም ይችላል። በእንዲህ አይነቱ  ፍልሚያ ላይ ያለ ወታደር ምንስ ብሎ እራበኝ ፣ ጠማኝ ይላል። በሰላሙ ጊዜ ምግብ በተትረፈረፈበት ወቅትም ሲመገብ መጥኖ መሆኑ በዚህ ክፉ ጊዜ ችግሩን እንዲቋቋም ረድቶታል።
ጓደኛዬ በዚህ በተጧጧፈ ጦርነት ውስጥ ቢሆንም፣ 100% እራሱን ማዳን እንደሚችል ይሰማዋል። ጦርነቱ ለድል ተስፋን የሚሰጥ አልነበረም። ስድስተኛ ክፍለጦር በሁለት አቅጣጫ ተፈቶ እያፈገፈገ ነበር። ሻዕቢያ ደግሞ በዚህ  እየተከታተለ በማጥቃት ላይ ነው። ሠራዊቱ ዓመታት በፈጀው ጦርነት ተሰላችቷል። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ምርጥ ምርጥ መሪ ጄኔራሎቹን በመፈንቅለ ሰበቡ ተረሽነውበታል። በዚህም የውጊያ ሞራሉ የደከመ  በመሆኑ ጠላት በአውደ ውጊያው የበላይነት ይታይበታል። ከ12 አመታት በፊት ጠላት ከጨው በረሃ አላለፈም ነበር። እዚያ ዘንድ ወጥረው ይዘው ነበር ፣ የኋሊት እንዲያፈገፍግ ያደረጉት። አሁን ግን ያንን ቅጥር ጥሶ ጠላት ወደፊት እየገሰገሰ ነው። ከዚህ በኋላ እራሱን ማዳን እንዳለበት ወስኖ እንቅስቃሴውን መጀመር እንዳለበት ገባው።  ጓደኛውን ሊዲንግ ሲማን ገላዬ ጮንቄን አሰበው። የት ይሆን?
ሻእቢያ ሰራዊቱ መራር መስዋዕትነት እየከፈለ ጨው በረሃን አቋርጦ ግራር ሰርጥ ደረሰ። መራሩ ፍልሚያ እንደቀጠለ ነው። አናቱን ዝቅ አድርጎ እየሮጠ እያለ  ሆስፒታል አካባቢ ገላዬን አየው። ጮክ ብሎ ተጣራ፤ እንደመታደል ገላዬ ሰማውና ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ። ከኋላው አጅበውት አንድ ስድስት የምድር ጦር አባላት አብረውት መጡ። ጓደኛዬ እንደገመተው ገላዬ ግቢውን ስለሚያውቅ እንደ ጎበዝ አለቃ ሆኖ እየመራቸው ነው። ይህ ድርጊቱ በመደቡ ውስጥ አመራር እንደሌለ አስገነዘበው።
“ምን ታስባለህ?” አለ ጓደኛዬ።
“አታይም ሻዕቢያ እየተግተለተለ ግቢ ለመግባት ሲንደረደር። ወደፊት እንሂድና ተፋልመን እንሙት !” አለ ገላዬ።
“ይሻላል !” አለና ጓደኛዬ አውጠነጠነ። ከተናገረ የማሳመን አቅሙን ያውቀዋል። አሁን ግን ቦታው አይደለም፤ ሃሳብ ለማስለወጥ ጥረት ቢያደርግ አንዱ አናቱን እንደ አንፖል ያፈነዳዋል። ስለሆነም መራሩን ትእዛዝ ለመተግበር ሲንቀሳቀስ ከፊት ገላዬ ሲመራ፣ ከኋላ ወታደሮቹ ሲከተሉት በዚያው ቅጽበት ከኋላቸው ያለው ሆስፒታል በመድፍ ተመታ። ሁሉም ተዘረሩ። ጓደኛዬ ሸብረክ እንዳደረገው ቆሟል። ሬሳ ባንዴ ምድሯን ሞላው። ገላዬን በዩኒፎርሙ ለመለየት ሞከረ።አላገኘውም፤ እዚያ መሀል የለም።
ሞት ሞጭለፍ ሊያደርገው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መሆኑን አውጠነጠነና ደመነብሱን መሮጥ  ጀመረ። በሃሳቡ ገላዬ መጣበት። ገላዬ በአፈቀራት ወጣት ሰበብ እዚህ አውደ ውጊያ ላይ ተገኘ እንጂ  ያ መዘዘኛ ፍቅር በህይወቱ በቅርቡ  ባይከሰት ኖሮ ይህንን መአት ያልፈው ነበር።
 ነገሩ እንዲህ ነው። በ1980 ዓ.ም ገላዬ የሙያ ስልጠና ለመውሰድ ከጓደኛዬ ጋር አስመራ በሚገኘው ባህር ኃይል ማሰልጠኛ ገብቶ መሰልጠን ነበረበት። አሁን ጓደኛዬ ጉዳዩን በማያውቀው ምክንያት በወቅቱ ስልጠናውን አልወሰደም። ስለሆነም በ1982 ዓ.ም አስመራ ተጉዞ የሙያ ስልጠናውን እንዲወስድ ትእዛዝ ከጠቅላይ መምሪያ ደረሰው። ገላዬ ግን በወቅቱ ድንገተኛ ፍቅር ይዞት ስለነበር በሰበብ ባስባቡ አስመራ ተገኝቶ ሳያመለክት ቀረ። ከዚህች ልጅም ጋር የተገናኙብት አጋጣሚ ‘ድራማ ‘ ይመስላል። ይህ መዘዘኛ ጦርነት ሊፈነዳ ወራት ሲቀረው ከእለታቱ በአንዱ ቀን ‘ሊዲንግ ሲማን ኳርተው ‘ የሚገኘው ስልክ ጮኸ፤ አጠገቡ ገላዬ ስለነበር አነሳና፤ “ሊዲንግ ሲማን ገላዬ ጮንቄ ይመልሳል፤ ማንን ፈልግው ነው !?” ይላል። ከማዶ ደዋይዋ “አንተን ፈልጌ ነው ፣ ስምህን ድገምልኝ።”
“ሊዲንግ ሲማን ገላዬ ጮንቄ ቴንቶ !” አላት፤ የአያቱን ስም ጨምሮ።
“ድገምልኝ !”
ደገመላት፡፡ ሰለሰላት፡፡ ጨዋታው ደርቶ የእለቱ እለት ተቀጣጠሩ።  አገኛት፡፡ ግራር በምትገኘው ሰላማዊና  ጸጥተኛ ሆቴል ሲደሰቱ አደሩ። ይህ አጋጣሚ አይደለም የሙያ ስልጠና፣ የፈለገውን መስዋዕትነት እንዲቀበሉ አያደርግም?! በኋላ እንዳጣራው እርሱም ልጅቱም በዚህ ዘግናኝ ጦርነት ተሰውተዋል።
ጓደኛዬ በሶምሶማ እየሮጠ ወጥቤቱ ዘንድ ደረሰ። ወደ ውስጥ ገባ፣ ቧንቧውን ከፈተው፣ ውሃ አለ። ፍል ውሃ ነው። ውሃ መኖሩ እየገረመው አፉን ተጉመጠመጠ። የተከደነች ሳህን አየና ገለጥ አደረጋት፤ ፓስታ በስጎ ነች። ስጎውን ፓስታዋ ምጥጥ አድርጋው ሽቦ ሆናለች። ከእለታት በፊት  አንዷ ወጥ ቤት ልትበላት ያሰናዳቻት  ሳትሆን አትቀርም። መርከበኞች የተመገቡበትን ሳህን፣ ሹካ፣ ማንኪያ ወዘተ አጣጥቤ በኋላ እበላታለሁ ብላ  አስቀምጣት ይህ መዘዘኛ ጦርነት እንዳትቀምሳት  አደረጋት።  ሳህኗን መልሶ ከድኗት ወጥቶ ወደ ባህሩ ዳር ለመድረስ  መሮጥ ጀመረ።
“ከሊዲንግ ሲማን ኳርተር” ጀርባ ሞቅ ያለ ተኩስ እየተሰማ ነው። “ ቁም !” አለ አንድ ድምፅ። ጓደኛዬ ዞሮ አየው፤ ንፁህ ዩኒፎርም የለበሰ ወታደር ነው ያዘዘው።  “እንዳትመታ ነው፤ አንዴ ቆይ!” አለው። ተኩሱ በረድ ሲል “አሁን እለፍ!” ሲለው አመስግኖ በሩጫ ከአካባቢው ራቀ። ያ ወታደር ባያስቆመው ኖሮ በጥይት ተመትቶ  ወንፊት ይሆን ነበር። ከዚያ በኋላ ተኩስ በሰማ ጥቁር እስኪበርድ እየጠበቀ  ያሳልፋል።
ረዥሙን ታሪክ እናሳጥረው። ጓደኛዬ በሶምሶማ እየሮጠ ቀይ ባህር ዘንድ ደረሰ። እዚያው ባህሩ ዳር ሲማን ሪኩሪት እሸቱን አገኘው። በሰላሙ ጊዜ ፎቶግራፍ ክፍል ባልደረባ ሆነው አብረው  ሰርተዋል። ስለዚህ ይህንን ወጣት ለማዳን በማሰብ አብሮት እንዲዋኝ ጠየቀው። እሸቱም፤ “አንድ እግሬ ላይ ተመትቻለሁ። ደም እየፈሰሰኝ ስለሆነ ለሻርክ አደጋ ያጋልጠኛል። ሁለተኛ ዋና ደግሞ በቅጡ አልችልም !” ሲለው ጓደኛዬ በጣም አዝኖ  ተጨባብጠው ተለያዩ ።
 “ጆኒ!” ጓደኛዬ አንድ ድምጽ ሰማ። እርሱን ነው። ጠሪው የጦር ሠራዊት አባል ነው።
 “አቤት!”
“ዋና ትችያለሽ ?”
“አዎን እችላለሁ!”
“እኔን ተሸከሚኝና አብረን እንሂድ”
“ሃሳብህ ጥሩ ነው። እኔ ግን አራት ቀን ውሃ አልጠጣሁም፣ ምግብ አልበላሁም፣ እንቅልፍ አልተኛሁም፤ ስለዚህ በቂ አቅም ስለሌለኝ ዋናውን እንደጀመርን  አብረን ነው የምንሰጥመው፤ ይልቅ ከዚህ በኋላ ስለማታስፈልገኝ ይህቺን ጃኬት ማስታወሻ ልስጥህ !” አለና ጓደኛዬ የባህር ኃይል ጃኬቱን አውልቆ ሰጠው። እንዳለው ሲዋኝ ስለሚከብደው ከዚህ በኋላ ጃኬቱ አያስፈልገውም።
 ወታደሩ ሲምጋት የነበረችውን ቁራጭ ሲጋራ ወዲያ ጣለና ጃኬቱን በደስታ ተቀብሎ ለብሶዋት ሲለካ፣ ጓደኛዬ መሳሪያውን ወደ ባህር ጥሎ ዋና ጀመረ። በእንዲህ አይነት ወቅት ዳር ያለ ጠላትም ሆነ ራሱን ያላዘጋጀ ወገን በዋና እራሱን ለማዳን የሚጥርን ሰው  ጥይት ተኩሰው ይማታሉ ተብሎ ሲነገር ሰምቷል። ስለዚህ ራሱን ለመከላከል መጀመሪያ በጥልቀት ወደ ገላጣማው ባህር በፍጥነት ዋኘ። የክላሽንኮቭ ጥይት እስከ 300 ሜትር ውጤታማ ምት ይመታል። በርቀት ግን እስከ 700 ሜትር ድረስ ይወነጨፋል። ስለዚህ ከእንዲህ አይነቱ አደጋ ለመትረፍ ግፋ ቢል እስከ 1000 ሜትር ድረስ ወደ ገላጣማው ባህር ክልል መዋኘት ከጥቃቱ ለመራቅ መልካም አማራጭ ነው። በዚያ ርቀት መሬት ላይ ቆመው ሲያዩት የሰው ጭንቅላት የቡሽን ያህል አንሳ ነው የምትታየው። ስለሆነም ጓደኛዬ በረዥሙ ከዋኘ በኋላ ‘ በ ‘ ቅርጽ እጥፍ ብሎ ወደ ምጽዋ ወደብ መዳረሻ ወደሆነው ርእሰ ምድር መዋኘት ጀመረ። ይሄኔ አካሉ መዛል ጀመረ። ዩኒፎርሙን እንደለበሰ ነው። ጫማውን አውልቆ ጣለ።
ቀለል አለው፤ ጥቂት ወደፊት ቀዘፈ። ተስፋውን ያውጠነጥናል። “አዲስ አበባ እመለሳለሁ። እናቴን እንደገና አገኛታለሁ! የማፈቅራትን ልጅ ‘እጠብሳለሁ’ ! ዘሬም ከአዱ ገነት ይቀጥላል !”
እያለ ይዋኛል። ቀስ በቀስ አካሉ እየዛለ እየዛለ ሄደ። ‘ሆድን በጎመን ቢደልሉት አካል በዳገት ይለግማል’ እንዲሉት እየሆነ ነው። አካሉን በባዶ ሆዱ ቢደልለው ሰውነቱ  በሂደት በጣም እየደከመ ሄደ። እርሱ ግን መጣሩን  አልተወም። በእጁ ውሃውን በጭረቅ ያደርግና “ትንሽ ቀረኝ!” ይላል ለራሱ። አሁንም በጭረቅ “ጨረስኩ !” ...
ቀይ ባህር በጣም ጨዋማ ውሃ ነው።  ላወቀበት ሲዋኝ በጣም ቀላል ነው። ያ ግን የሚሆነው በበላ እንጀት ነው። ጓደኛዬ የምር ቢፍጭረጨርም  መዳረሻው ርእሰ ምድር አፍንጫው ስር ሆና የዘላለምን ያህል ራቀችበት። እግሩም የአእምሮውን ትእዛዝ መቀል አቆመ። በእጁ ብቻ ላመል ያህል ተፍጨረጨረ። እጆቹም ዛሉ። የሚችለውን ያህል ለመዳን ቢሞክርም አልቻለም። “ለካንስ ሲሞቱ እንዲህ ቀላል ነው?!” አለ በልቡ፤ ቀስ እያለ መስጠም ጀመረ። “ሀዘን መራር የሚሆነው ለቋሚ እንጂ ለሟች ለካ እንዲህ በቀላሉ ነው የሚሰናበተው። ይብላኝ ለቋሚዎቹ። ሀዘናቸውን እንዴት መራር ነው!?” እያለ ቀስ በቀስ መስጠም ጀመረ። “አይደረግም እኖራለሁ፣ እናቴን እንደገና አገኛታለሁ! ፍቅሬስ!? ...”በጭረቅ አደረገ ውሃውን ...። ይህ የመጨረሻ ጉልበቱ ነበር።
እሯጮች ብርርር ብለው ድፍት ሲሉ 100% ጉልበታቸውን ጨርሰው ነው። ጓደኛዬም ልክ እንደ እሯጮቹ ጉልበቱን ጨረና መስመጥ ግድ ሆነ። እግሮቹ ቁልቁል ሲሰጥሙ እይኖቹን ገርበብ አድርጎ ቁልቁል ወረደ። ተአምር ተፈጠረ፤ እግሮቹ  መሬት እረገጡ።
“ተመስገን!” አለ። ለካንስ ጥልቀት አልባው ባህር ክልል ደርሷል። እንደማይሰጥም እርግጠኛ ሆነ። እግሮቹ  መቆም አልቻለም ፣  መሬቱ  ተዳፋት ስለሆነ ተጋደመበት። የሚገርምው አንዲት የማትቆረቁር ድንጋይ ትራስ ሆነችው። በህይወቱ በሙሉ የማይረሳውን ረዥም ትንፋሽ ተነፈሰ። “አለሁ እናቴንም ፣ ታናናሾቼንም፣ ፍቅረኛዬንም አገኛቸዋለሁ !” አለ ለራሱ ያህል።
ጦርነቱ እንደ ቀጠለ ነው። ... ይህ የጓደኛዬ የህይወት ታሪክ አንዱ ምእራፍ ነው። ያቺን የጆን ኤፍ ኬኔዲን ታሪክ ባያነባት ኖሮ ይህ አይነቱ ጽናት ኖርት እዚህ  ይደርስ ነበር? አይመስለኝም። እንዳለው “ማንበብ ከሞትም ያድናል!” ሌሎች ወሳኝ  መራር ምእራፎችን አልፎ እንዳለው የመጨረሻውን ጦርነት ተካፍሎ “በድል አድራጊነት” አዲስ አበባ ገባ። ይህ ባለታሪክ ማን መሰላችሁ? ፒቲ ኦፊሰር ዘነበ ወላ ነው።
ሰላም በምድራችን ላይ ይስፈን !


 

 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 190 times Last modified on Monday, 01 April 2024 06:46