Sunday, 31 March 2024 19:52

የዘበት ከተማ!

Written by  ሲራክ ወንድሙ
Rate this item
(1 Vote)

የሰው ልጅን የከባቢያዊ ጠባይ ተቆጣጣሪ (master) ነው በሚል ከአንደኛው የአለም ጦርነት በኋላ በጣልያንና የግሪክ ፈላስፎች የተጀመረው Environmental Determinism ፍልስፍናን የተከተለ በሚመስል ሁኔታ “የሲኦል ገበሬ” ከምትል ስብስብ የልቦለድ መፅሐፍ ውስጥ እንዲህ የምትል ቦታ ትዝ አለችኝ : -
«...ድንገት የሚያጓራ የመኪና ድምፅ ተሰማው። ወደ ሰማበት አቅጣጫ ሲዞር ከፊት ለፊቱ ረጃጅም የተቆረጡ የዛፍ ግንዶችን የተሸከመ ግዙፍ መኪና እያቃሰተ በአውራው ጎዳና ላይ ወደ ፊት ይተማል። ሾፌሩና አጠገቡ የተቀመጠው ጎልማሳ በእጃቸው የጨበጡትን የቢራ ጠርሙስ ወደ አፋቸው አስጠግተው እየጠቡ ያሽካካሉ።
መኪናውን ተከትሎ የተለያዩ ቀለም ያላቸው የወፍ ዝርያዎች መኪናውን ተከትለው ይበራሉ።  ወፎቹ በተቆረጡት ዛፎች ላይ ትዝታ አላቸው። እንጨት ቆራጮቹ ዛፎቹን ቆርጠው ሲወስዱ ወፎቹን አልወሰዷቸውም። ቤትም አልሰጧቸዎም።
ወፎቹ የዛፉን ብቻ ሳይሆን የትዝታቸውን ጠረን እያሸተቱ ነው የሚበሩት። አንዳንዶቹ ከዛፎቹ ጋር ሳያረጁ አልቀሩም። ምናልባትም ከዛፎቹ ቅርንጫፎች ላይ በተሰራ የወፍ ጎጆ ውስጥ እድሜ ዘመናቸውን ኖረውም ሊሆን ይችላል። ማረፊያቸውን የተነጠቁ ወፎች።.....¹ »
ከዛፋቸው ተላምደው አንድ ማለዳ ዛፋቸውን በማጣታቸው ስደት ስለወጡ ቀለማም ወፎች የሚተርክ ጅማሮ ነው። ዛፍ ቆራጩ ስለትዝታቸው ቦታ የለውም። እነዚያ ከርታታ ወፎች ግን የትዝታቸውን ጠረን እየማጉ የዛፉን ግንድ ተከትለው ይነጉዳሉ። የት ደረሱ? የቀረውን ከደራሲውና ከመፅሐፉ ውረሱ!
ሰው ሀገሩን መንደሩን ይመስላል። ጠባዩ ከኑረቱ የእለት ተእለት መማፀን ውስጥ ይቀዳል፤ ይባላል። (ባይባልም እኛ እንላለን።)  በመንደር የተደገሰ ታሪክ በአንዲት ከተማ ውስጥ ይጎለምሳል። እሱን ተከትሎ ማህበራዊ የስነ ልቦና ዳራው ከተለያዩ የከተማነት መልክ ጋር ይጋመዳል።
ከተማ ሰው ነው። ከትዝታው ሀያል ስበት ጀርባ እንስፍስፍነትን ያቀፈ ጨቅላ ነው። ከተማ መፅሐፍ ነው፤ ሊያውም አሮጌ። በፊት የገፁ ወሰን ጥቂት መልኮችን አቅርቦ ቀሪውን በሰፊው የገፆቹ ማሳ የወከለ ድጉስ!
ምናልባት ከተማ እኔ ነኝ። ቃሎቼ ፣ ወዞቼ ፣ ፌዝና  ምሮቼ ነክተው የተነሱት ገፅ አለ።
በአይኖቼ መንደሩን ገንብቷል። በጥርሶቼ ውክቢያውን አለምልሞ በትከሻዎቼ ገመናውን ሰውሯል። ውስጤ የደበቅኩት ብዙ እንፋሎት፥ የቀበርኩት ደማምነት አለ። ምሳር ይዞ ከዱር በገባ አንድ ዛፍ ቆራጭ ዛፎች እንደሚጨነቁት ሁሉ፣ እኔም ከተማዬ ሊፈርስ ሲሽቀረቀር ፍርሃት ፍርሃት ይለኛል።
የመጀመሪያዋን የወተት ጥርሴን ፣ የእቃ እቃ የአስኳላ ዳሴን ቢንዷት ልጅነቴን ፈልጌ እስካገኝ የወጣትነት ጎርፍ አሳፍሮ ለእርጅና ይሰጠኛል። የአባቶችን ተግሳፅ ፣ የእናቴን በጊዜ ግባ ተማፅኖ፣ የጓደኞቼን የአቻ ልፊያና ሳቅ ፣ የልጃገረዱን መሽኮርመም ከታች እስከላይ ባስስ ከፍርስራሹ ውስጥ የማወጣው የተሰባበረ ብኩን የትዝታ ገላ ብቻ ነው።
ትላንት በዛሬ ውስጥ ህያው የሚሆንበት ትልቁ ነገር፣ ያን ዘመን የሚወክለው ግዑዝ ነገር ነው። ዋርካው ፣ ሲኒማ ቤቱ፣ መቀጣጠሪያ ካፌው ፣ ሙዚቃ ቤቱ አቧራው ሳይቀር የትውስታ በቅሎ ነው። ያን ከአይኔ ሲሰውሩ ውስጤ ቅያሜን ያረግዛል ፣ አይኔ ከእምባ ይወዳጃል።
እኔ ለከተማዬ ሀውልት ነኝ። ሲፈርስ የምፈርስ የሸክላ ምሳሌ ነኝ። ፍፃሜዬ በውስጡ፣ ጅማሮዬም በውስጡ ነው። አይኔ ማየት የጀመረው - ጆሮዬ ከመስማት የተወዳጀው ፣ መኖሬ ከተረክ አልፎ እውነት የሆነው በሰፊው ሰውነቱ ውስጥ በተራመድኩባቸው እርምጃ ነው። ዞር ስል የማየውን ባጣ እፈራለሁ። ቀና ስል ፍርስራሽ ካየሁ ራሴን ከካብኩበት ደርብ ለንደት አኮበኩባለሁ። የማያልቅ ታሪኬና የእኔነቴ መሰላል በማህበረሰብ ጠባይ ውስጥ ስግስግ ያለ ነው። እውር እንደዘራው ባቄላ የበተኑብኝ ቀን ቀለሞቼን በመልቀም እባክናለሁ። የጩኸት መንደሮቼ ውስጥ ዝምታ አለ። እኔን ለማግኘት የሚንደረደር ሁሉ በመንደሬ በኩል ያልፋል። ይመጣል። ይሄዳል። የዘበት ከተማ ውስጥ ለነብስ የሚተርፍ የአብሮ መኖር ባህል አይኖርም። ልቦና ከለመደበት ራሱን ከገነባበት ወሰን ሲያርቁት መሰልቸት ያመጣል።
በአንዲት መንደር ውድመት ውስጥ  የኔ የመቀጠል ተስፋ ተረት ተረት ነው። መዳፌ ላይ ህይወት ሳጣ ፤ በእጦት ፍቅር ስቀናጣ ፥ አዝኜ ስመለስ...ሄጄ ስቅለሰለስ ከነባራዊው አለም ጋር እጋጫለሁ። አበክሮ ያሰረኝን ጠይም የህይወት እትብት ሲነጥቁኝ በላምባዲና የምኮበልል ባካኝ እሆናለሁ።
የፊት መልኬን ከመቀላወጥ አልዳንኩም። አለሁ። ብርሃኖቼን ሸነሸንኩ። ሰፋሁ። ጠፋሁ። ብንን ስል ትራስጌዬ አቧራ አቧራ ይሸታል። ለአይኔ ሙሉ የነበረው እንደተመነጠረ ዳዋ ከባዶ ከባቢ ጋር ተቃቅፎ ይታየኛል። ከተማዬ የስልጣኔ ድር አመጣሽ ጅቡን ተከናንባለች። ከስልጣኔ ጋለሞታ ጋር በአስረሽ ምቺው ስትቃበጥ ካመጣችው ዲቃላ ጋር መላመድ ቸገረኝ። ዘመን ሄደ እኔ ጠፋሁ። ቀን መሸና እኔ በራሁ።
ሰው አለ ትዝታው ማነው ? ሰው አለ አክራሚው ምንድነው? ምንስ ነው?
የከረረ የአብሮነታችንን ማህተብ የበጠሰው የፈረሰ ደጅ ፣ የተነጠለ ቤትና የተበተነ ሀገር እንጂ ሌላ አይደለም። የአንድ ግለሰብን የስነልቦና ጣጣ ከሚያመጡና ከሚያጎድሉ ነገሮች አንዱ የተለመደን የማህበራዊ እሴት በረከት መንጠቅ እንደሆነ ደጋግመን ባየናቸው የህይወት ገጠመኞቻችን ውስጥ ተመልክተናል።
ከባቢያዊ በሆነ የእለት ተዕለት ልምዱ ስር ዘላለም ከተጋመዳቸው አያሌ ጠባዮች ሲነጠል ጤነኝነቱ ይከስማል። ከብቻነቱ ጋር እየዳኸ የግለኝነት ጎጆውን ይወጋግራል። ጓደኝነቱን ለግሉ የመገልገያ መሳሪያነት ብቻ ያውላል። ነበርን እንኳን በወጉ እንዳያከብር በፈራረሱ አድባራቱ መሀል እየተንከላወሰ በድብርት የሚጠቃ ፍጡር ነው።
እንደኛ ሀገርና ህይወት ከመፍረስ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ማህበረሰብ እምብዛም ነው። በታሪካችን ውስጥ የሚታየን ማውደም ፣ መደምሰስ ከዚያም ግንባታ ነው። ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ ዘመኗ ከግንባታ የመፍረስ እጣ አርፋ አታውቅም። ቃሉን መላመዳችንን ከሚያመለክቱ ነገሮች መሀል  ለተነሳው የሰፈር ጠብ ሁሉ ብሄራዊ መፈክራችን “ኢትዮጵያ አትፈርስም “ ነው። አሜን አትፈርስም!5 ጥቂት የመፅሐፎቻችን ርዕሶችስ ፅንሰ ሀሳቦቻቸው ወደ እዛው የሚያሶመሱም አይደለም?!
ነገር ግን አፍራሾቿ መገንባት እንደማፍረስ ይመስላቸዋል። ደሳሳ ቤት አፍርሶ ህንፃ ማቆም ስኬት መሆኑን እንጂ በዛ ውስጥ የሚወድም ማህበራዊ እሴት አይታያቸውም። ለዘመናት አብረው የኖሩ ጎረቤታሞችን ጎጃምና ከፋ አራርቆ አስፍሮ የደፈረሰውን የስነልቦና ሁከት በውይይት መመለስ የሚጥረው ብዙ ነው።
የአብሮነት ድሩን አለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በጣጥሶ የጣለ ህዝብ፣ ትዝታም ሆነ ባህሉ ከወደመ እንጀራና ወጡን እንኳን ማስተረፍ የመቻል አቅምን የሚያገኝ አይመስለኝም። ለዚህም ነው መደብዘዝ የጀመረ ፀሀያችን ከስንቱ አላፊ አግዳሚ ጋር የሚያጎናትለን። የሚያሸናግለን።
ናፖሊዮን መጣሁ ሲል የሞስኮ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ላይ እሳት በመልቀቅ ሸሹ። ናፖሊዮን ወደ ከተማዋ ሲገባ እሳት ተቀበለው። ትልቁ ሽንፈቱን ያሰመረለት ግዙፍ ክስተት ሆነ። በአንፃሩ ለራሺያ ዜጎች የከተማቸውን በእሳት መነጠቅ መልካቸውን ቀይሮት አለፈ። አክሱም በዮዲት ስትወድም ገናናው የአክሱም ዘመንና ስልጣኔ የተረት ቀሚስ ለብሶ ለምሳሌ ብቻ የሚጠራ ባልቴት  ሆነ።
የግሪክ ታላላቅ ከተሞች በጦርነት እሳት ጭዳ ከሆኑ ወዲህ መንፈሳቸው ለማንሰራራት ለግሞ ዘመናትን ተሻገረ። በአንፃሩ ግን ለጥንታዊ ከተሞቻቸው ምህረት በማድረግ በገላጣ መሬት ላይ ቅንጡ ከተማ ለሚገነቡት ቻይና እና የአረብ መንግስታት ከማህበራዊ እሴት ትርፍ በተጨማሪ በቱሪዝም ዘርፍም ሀገራቸውን መታደግ ቻሉ። ወደ እኛ ሀገር ስንመለስ ገፅታው ሌላ ነው።
በጦርነት ካጣናቸው ሰዎች በላይ የየኑረቱን መልክ በችሎታቸው የሰደሩ የከተማ ገፅታዎች መፍረስ በነዋሪው ላይ የስነልቦና መታወክን እንደፈጠረ ይሰማኛል። በውስጡ ካለው እውነት ፣ ስሜትና ትውስታ የራቀ ልብ፣ የቱም ፍስሃ ቢቀርብለት ሀሳቡ ከውድመት እንጂ ከብልፅግና ጋር አይወዳጅም። ይህም ከሶስቱ በአንዱ destruction የሚባለውን የድባቴ አይነት በአንድ ሰው ላይ ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።
እንደነዛ ቀለማም ወፎች በብኩን ሩጫ ውስጥ የጎበጠ የትውልዴ እጣ ያሳስበኛል። የትዝታውን ጠረን ፈልጎ ሲያጣ ፣ የአብሮ መኖር መንፈሱን ተነጥቆ በተሰበረ ቅስሙ ሲብከነከን ማየት ያስፈራኛል።
የዘበት ከተማ ሁሌም ከመፍረስና ባህሉን ከማጥፋት ጋር የታሰረ ነው። በእዛ ውስጥ የማህበረሰብ ቀጣይ የህይወት ዳናው ምንድነው ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ይመስለኛል። የጋራ ድልድዮቻችንን እያፈረስን ስለመሻገር ማውራት ይቀፋል። በዘመኔም ይህ የዘበት ከተማነት ቀለሙ እየተስፋፋ መጥቶ የግለኝነት ጠባይን እያበዛው ሰውን ከእሴቱ በመንጠቅ ተጠምዷል። እውን ሰው ያለ ትዝታው ማነው? ሰው ያለ አክራሚው ምንድነው? ምንስ ነው?
¹ ሲራክ ወንድሙ - የሲኦል ገበሬ 2013 (ያልታተመ)

የአዲስ አድማስ  የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ
        =====
      አዲስ አድማስ https://bit.ly/2V1zyZQ
      ፌስቡክ↠ https://bit.ly/2V0I6jx
      ትዊተር↠ https://bit.ly/33fDhaP
      ቴሌግራም↠ https://bit.ly/2JgeCvG
      ዩቲዩብ ↠ https://bit.ly/3q2hXiv
                                 

 

 

Read 333 times Last modified on Sunday, 31 March 2024 20:43