Sunday, 31 March 2024 20:30

‹‹አካሌ››ን የመሰልሽ ሙዚቃ ከወዴት አለሽ!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

ኤፍሬም ታምሩ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ከ1973 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ድረስ ጾታዊ ፍቅርን፣ የአገር ፍቅርን፣ ናፍቆትን፣ ይቅርታን፣ ትዝብትን፣ ሰውኛ ባሕሪን ወዘተረፈ አስመልክቶ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል።
ሙዚቃን የጀመረው ከአያሌው መስፍን ጋር እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡ ኤፍሬም ‹‹ገና ልጅ ነኝ ጋሜ›› የሚል ዘፈን አለው፤ ገና ልጅ ነኝ ጋሜ፣ ለአቅመ አዳም አልደረስኩ አላውቅም ታምሜ የሚል፤ መጀመሪያዎቹ አካባቢ ላይ የተዘፈነ ነው እንግዲህ
…ኤፍሬም በ‹‹ገና ልጅ ነኝ ጋሜ›› (1973 ዓ.ም.)፣ ‹‹ጀማዬ ነይ›› (1974 ዓ.ም.)፣ ‹‹ሸግዬ›› (1975 ዓ.ም.) እና ‹‹ነዪልኝ›› (1976 ዓ.ም.) አልበሞች ተወዳጅነትን አገኘ፤ እንዲህ እንዲህ እያለ አስራ አንድ (11) - ከሪምክስ ጋር - አልበሞችን ለአድማጭ አድርሷል፡፡ በድርሰት ረገድ ከአንጋፋዎቹ ከአያሌው መስፍን፣ ይልማ ገ/አብ፣ ተስፋዬ ለማ፣ አበበ መለሠ፣ አክሊሉ ሥዩም፣ አበበ ብርሃኔ፣ ሞገስ ተካ፣ ጸጋዬ ደቦጭ፤ ብሎም ከወጣቶቹ ከመሠለ ጌታሁን፣ ቴዲ አፍሮ፣ አማኑኤል ይልማ፣ እንዳለ አድምቄ እና ሌሎችም ጋር ሠርቷል፡፡ ሮሃ ባንድ፣ ናይል ባንድ፣ ኢትዮ ስታር ባንድ እና ሌሎችም አብሮ የተጫወታቸው ባንዶች ናቸው።              
ኤፍሬም ታምሩ ሲነሳ ይልማ ገ/አብ እና አበበ መለሠ አብረው መነሳታቸው ግድ ነው። ወቅቱ 1985 ዓ.ም ነው፤ ‹‹ሞንሟኔ ነሽ›› አልበም ተሰማ፤ በዚሁ አልበም ይልማ ገ/አብ፣ አበበ መለሠ፣ አክሊሉ ሥዩም እና ዘላለም መኩሪያ በድርሰት ረገድ ተሳትፈዋል። አጃቢው ናይል ባንድ ሲሆን ምህረት ታምራት (ቤዝ ጊታር)፣ ምትኩ ተፈራ (ኪ-ቦርድ)፣ ሞገስ ሀብቴ (አልቶ እና ቴነር ሳክስ) ተጫውተዋል።
ይልማ ገ/አብ የስድስቱን (6፡- ሞንሟኔ ነሽ፣ ይቸግር የለም ወይ፣ ወይ ልቤ፣ ቀን ሲጥል፣ የጥበቡን ነገር፣ ገዳይ ነሽ ገዳይ እና እረፈው ልቤ) ዘፈን ግጥም ሲደርስ፤ አበበ መለሠ ደግሞ የአራቱን ዜማ (ሞንሟኔ ነሽ፣ ገዳይ ነሽ ገዳይ፣ ወይ ልቤ እና ጎጆሽ ይሻላል) እና የአንዱን ግጥም (ጎጆሽ ይሻላል) ደረሰ፤ አክሊሉ ሥዩም በበኩሉ ሁለት ዜማ (ይቸግር የለም ወይ እና ቀን ሲጥል) የደረሰ ሲሆን፤ ዘላለም መኩሪያ የሁለቱን ዜማ (የጥበቡን ነገር እና እረፈው ልቤ) ደርሷል።
የይልማ ገ/አብ የግጥም ድርሰቶች እንደዜና ተደምጠው የሚቀሩ ብቻ አይደሉም። ውስጠ-ወይራነት አለባቸው፤ በዚሁ አልበም ይልማ አንድን የተረታ አፍቃሪ ለመወከል በሚመስል ጥበብ፣ የደርግን ‹ተሸናፊ› ወታደር ታሪክ ‹‹ገዳይ ነሽ ገዳይ›› ሲል ያስቃኘናል። በወንድማማችነት ጸብ ተረቶ በየስፍራው ሲንከራተት የተመለከተውንና መግቢያ ያጣውን የደርግ ወታደር ሁናቴ ነው በሚያባባ የናፍቆት ስልት ያተተው።
ወርሃ መስከረም፣ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ስድስት ዓመተ ምሕረት (1976)፣ የኤፍሬም ታምሩ ‹‹ነዪልኝ›› አልበም ለሰሚ ጆሮ በቃ። በዚህ አልበም ውስጥ ከተካተቱ ዘፈኖች መካከል ለ‹‹አካሌ›› ልዩ ፍቅር አለኝ፤ ‹‹አካሌ›› የአበበ መለሠ ዜማ እና የይልማ ገ/አብ ግጥም ሙዚቃ ነው፤ ሮሃ ባንድ (ሰላም ሥየም፡- ሊድ ጊታር፣ ዳዊት ይፍሩ፡- ኪ-ቦርድ፣ ጂኦቫኒ ሪኮ፡- ቤዝ ጊታር፣ ፈቃደ አምደመስቀል፡- ሳክስፎን) አቀናብረውታል። በዕድሜ ከፍ ስል፣ እዚያ ላይ ለተሳለች ኢትዮጵያዊት ቆንጆ እና ጠንካራ ሴት የሕግ ሁሉ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር አድሮብኛል።
በሙዚቃ ውስጥ ለምትሳል ሴትም ትሁን አገር በልባችን ውስጥ የረቀቀ ሥፍራ ይኖረናል፤ አገሬን የተዋወቅኋት ተዟዙሬ ጎብኝቻት አይደለም። ከማውቃቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ካፋ (ትውልድና ዕድገት)፣ ጅማ፣ አዲሳባ፣ ሚዛን፣ ጉራጌ፣ ዲላ፣ ሰላሌ፣ አምቦ፣ ደብረብርሃን፣ አርባምንጭ፣ ደብረማርቆስ ብቻ ተጠቃሾች ናቸው። ነገር ግን ከዚህ የተረፉትን የማውቃቸው በሙዚቃና በመጻሕፍ ነው፤ የአገር ፍቅር ያደረብኝም ልዩ ጥቅም አግኝቼ ሳይሆን መጻሕፍት በማንበብና ሙዚቃ በማድመጥ ነው…
…ወደ አሁኔ ልስከንተር…  
…አሁኔ ‹‹አካሌ›› ነው…
…ውብ እና ተናፋቂ እንስት እዚያ ውስጥ ትታየኛለች። ለአመል ቢጤ እንኳን የምትግደረደር…
‹‹አካሌ፣ ሸግዬ - ነዪ፣
በምትወጃት እናት፣ ሰው ጠራኝ ሳትዪ፤
አካሌ፣ ሸግዬ - ነዪ፣
ከውበትሽ ጋራ፣ ገለጠ ሰማዪ፤›› የተባለላት።
በዘፈኑ ውስጥ ያለ ተብከንካኝ አፍቃሪ ማፍቀሩን ከመግለጹ በፊት ሠላምታ ይሰድላታል፤ ኳስ በመሬት ዓይነት ስልታዊ ማዳከም፤ ደግሞ እኮ ውበቷ ንጋትን እንዲያበስር ሆኖአል፤ የንጋት ፀሐይ ነች፤ ውበቷን ይሞቃል፤ ለልብ ትሆናለች፤ ለመንደርደር እንዲሆነው ሠላምታ እንኪ ይላል…
‹‹እንደምን አድረሻል፣ አንቺ አመለ ኩሩ፣
አማላጅ ጠፋልሽ፣ ባገር በመንደሩ፣›› ሲል።
ዘለስ ይልና ደግሞ፣ በልቡ ምን ያህል ሥፍራ እንዳላት በሚያባቡ ስንኞች ይተርካል፤ በውስጡ መግዘፏን፣ አለያም ስለ-እሷ ሲብከነከን እንደሚውል እንደዚህ…    
‹‹….የማብሰልሰል ሚስጢር፣ የሃሳብ ሹክሹክታ፣
መወያየት ሆኖአል፣ ገጥሞ ከትዝታ፣›› ሲሰኝ እናደምጠዋለን።
መልሶ ደግሞ መከታው ያደረጋት እንስት ትሆናለች፤ እናም…
‹‹የትከሻዬ ጌጥ፣ የጫንቃዬ መስፋት፣
ያዕምሮዬ ድባት፣ ሸክሜ ትዝታ፤›› ይላታል።
አፍቃሪው ንፉግ አይደለም፤ ፍቅር መስጠት መሆኑን ልብ ብሏል፤ ሌላው እጅ መስጠቱ ጸጋ እንጂ ቀጋ እንዳይደለ ገብቶታል። ይህቺ ልዕለ ሰብ በሸጋ አመልና በድንቅ ውበቷ ልቡን ገዝታዋለች፤ አይገዳደራትም። ለዚያ ነው…
‹‹ተራመጅ በልቤ፣ በለመድሺው መንገድ፣
ያንቺማ ትዝታ፣ በሰው አይታገድ፤›› የሚላት።
ኑዛዜ ነው ይኼ፤ መረታቱን ተንትኖ ያስረዳል፤ ያለንበትንና የተሰማንን እንድናውቅ፣ አውቀንም እንድንገልጽ ልብ ይስጠን! መልሶ ይብከነከናል፤ ናፍቆት እያደር ይጣምነዋል፤ እናም ገሃድ አውጥቶ በሸንጎ መዳኘትን ይሻል። ጥቃቱን እንደዚህ በማለት ይለፍፋል…
‹‹ቢፈርደኝ ምን አለ፣ ዳኛው ተሰይሞ፣
ቂመኛው ልቧማ፣ አጠቃኝ አድሞ፤››
በገሃድ እንደከሰሳት ከላይ ያሉ ስንኞች እማኝ ይሆናሉ፤ መላ ቢያጥረው መዳኘትን ሽቷል፤ ሆኖም መዋቀስን ቸል ብሎ ይቅርታን ይቋምጣል…  
…ፍቅር ይቅርታ መሆኑ የገባው አፍቃሪ ነው፤ እናም ጣመነኝ ብሎ አያቄምባትም። ይልቅዬ በፍቅረኞች መካከል ዳኝነት የልብ እንደማያደርስና ከእርሷ ውጭ ሕማሙን የሚፈውስ ሰው እንደሌለ ስለተረዳ ፋይሉ ተዘግቶ እርሱ ዘንድ እንድትመጣ ይጋብዛታል፤ እንደዚህ ነው ደግሞ…
‹‹ድረሽ ልቀበልሽ፣ እጆቼን ዘርግቼ፣
አልካስ በዳኛ፣ አንቺን ረትቼ፤›› በማለት።
ፍቅር አብዛኛውን ጊዜ የመተሳሰብ፣ የመዋደድ እና የመላመድ ውጤት ነውና፤ እንኳን እርሱ ቀርቶ የለመዳት ቤት መናፈቁን እንሰማለን…
‹‹የለሽ ካጠገቤ፣ ኃይሎ ትዝታ፣
ይማጸንሽ ጀመር፣ ምሰሶና ዋልታ፤››
እሱ የሚተነፍሰው ይቅርና ልባሹና የቤቱ ቁሳቁስ እንደለመዳትና እንደናፈቃት አያይዞ ያትታል…
…አፍቃሪው ጮሌ ነው፤ ይወራረድላችኋል። እናም በአካል ተገኝታ ከተዘፈቀበት የትዝታ ማጥ እንድታወጣው በውስጡ ስለቀመረ በመምጣቷ ውርርዱን እንዲያሸንፍ ይማጸናል፤ በውርርድ ሰበብ ሊያገኛት እንደማለት ዓይነት ብልጠት…
‹‹ውበትሽ ተወርቶ፣ ሙግት ተነስቶበት፣
ተወራርጃለሁ - እንዳልረታበት፤›› በሚሉ ስንኞች ውስጥ አለ፡፡
በውርርዱ ወቅት አፍቃሪው ባቀረበላቸው ማብራሪያ መተማመን ላይ ያልደረሱ ተቃራኒ ቁማርተኞችን ለማሳመን ምስክር ጠርቶ ከሚንከራተት ራሷ በአካል ብትገኝ ምን ያህል ውብ እንደሆነች ይገባቸዋል ብሎ ያምናል፤ የሚረታው ደግሞ ትዝታውንና ተጻራሪዎቹን ነው፡፡ ለዚያ ነው…
‹‹ይቅር ለምስክር፣ እርቄ መሄዴ፣
ባካል ድረሺና፣ ልርታልሽ መወደዴ፤›› የተሰኘው፡፡
ስጠቀልል፣ ‹‹አካሌ›› አመለ ሸጋ እና ተናፋቂ እንስትን የተዋወቅንበት ዘፈን ነው፡፡ ያ-ነኹላላ አፍቃሪ፣ ውበቷ ልቡን ሞልቶት ለውርርድ ሲበቃ እናስተውላለን፡፡ ይህቺን የመሰልሽ ሴት ከወዴት አለሽ!?
* * *
ከአዘጋጁ፡-
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።


 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

 

 

Read 229 times Last modified on Monday, 01 April 2024 07:52