Monday, 01 April 2024 07:27

መነሣት ይከብዳል እንጂ መብረርና መምጠቅ አያስቸግርም።

Written by  ዩሃስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

ትምህርት እንደ ሮኬት በረራ ቢሆን እንዴት ጥሩ ነበር? እንደ ሮኬት መሆኑ ነው ፈተናው!
መቼም ግዙፎቹን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከፍ ዝቅ እያደረጉ መተቸት፣ የዘመናችን ወግ ነው። በኩባንያዎቹ ላይ የሚጎርፈው ዕለታዊ የፖለቲከኞች ወቀሳና የጋዜጠኞች ትችት እስከወዲያኛው የሚያባራ አይመስልም። አድማጭና ተመልካችም አይጠፋም። ሞልቷል። ለነገሩ ለመጽሐፍ ሽያጭም ጥሩ ሳይሆን አይቀርም።
ትልልቆቹን ኩባንያዎችና ቢሊዮነር ባለሐብቶችን የሚያብጠለጥል መጽሐፍ፣ በሽያጭ ሰንጠረዥ ላይ እስከ 10ኛ ደረጃ ድረስ የመግባት ዕድል ካገኘ፣ ገበያው ደርቶለታል ማለት ነው። በፖለቲካ ውዝግብ ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትም እንደተለመደው ደህና ገበያ ያገኛሉ።
ዛሬ ዛሬማ፣ የፖለቲካ ነቆራ የበዛበት ዘመንም አይደል?
የዶናልድ ትራምፕ የክስ ክምሮችን እያበጠረ የሚተነትን አንድ መጽሐፍ ከግራ በኩል እየተመዝገዘገ ይመጣል። ከተቃራኒ ጎራ፣ ከቀኝ በኩል ደግሞ የፕሬዚዳንት ባይደን ደካማ አስተዳደርን የሚተች ሌላ መጽሐፍ ተወርውሮ ገበያውን ይቀላቀላል። ሁለቱም መጻሕፍት በሽያጭ ሰንጠረዡ አናት ላይ ቦታ አግኝተዋል። መናቆር ነው።
በእርግጥ፣ ገበያ የሚደራላቸው መጻሕፍት፣ “ተሳዳቢ ነገረኛ መጻሕፍት” ብቻ አይደሉም።
የግዙፎቹን ኩባንያዎች እንከንና ኀጢአት አውርቶ የማይጠግብ መጽሐፍ በብዛት ስለተሸጠ፣ ሚዛኑን የጠበቀ መጽሐፍ ብዙ አንባቢና ገዢ የለውም ማለት አይደለም። ኩባንያዎቹን ወይም ባለሀብቶቹን በበጎ የሚመለከት መጽሐፍም፣ በቅጡ ከተዘጋጀ በሰፊው ይነበባል።
የኢሎን መስክ የቢዝነስ ገድሎችን የሚተርክ መጽሐፍ ለበርካታ ወራት የሽያጭ ሰንጠረዥ ውስጥ ቤተኛ ሆኖ ከርሟል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየገነኑ እየበረከቱ የመጡ “የባህል ነውጠኛ” መጻሕፍትም አሉ።
ያው… የተሳከረ አስተሳሰብ እንደ አሸን የፈላበት፣ “የጾታ ቀውስ” እንደ ፋሽን የተዛመተበት ዘመን ላይ እንደመሆናችን፣ በዚሁ ዙሪያ ከግራና ከቀኝ የሚላተሙ መጻሕፍት ሰንጠረዡን መጎብኘታቸው አልቀረም። “የጾታ ዐይነቶች ሁለት ናቸው፣ እነሱም ወንድ እና ሴት ናቸው” ብሎ የሚጽፍ አንባቢ ባያጣም፣ ከየአቅጣጫው የውግዘትና “የቦይኮት” ዘመቻ እንደሚመጣበት ግን አያጠራጥርም። አሳታሚና አከፋፋይ እስኪያጣ ድረስ መውጫ መግቢያ ሊያሳጡትም ይችላሉ። የተሳከረ ዘመን ላይ ነን ሰዎች።
በዚህ ውጥንቅጥ መኻል፣ የአንጎል ተፈጥሯዊ አሠራርን በዘመናዊ የኒሮሳይንስ ጥናቶች ጋር እያዛመደ የሚተርክና የሚያስረዳ የዕውቀት መጽሐፍ፣ ተነባቢነትን ማግኘቱና ከሽያጭ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባቱ ያስገርማል። መልካም ነው።
“Why We Remember” ይላል ርዕሱ። መጽሐፉ ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ቢሆንም፣ በተለይ በትምህርት ዙሪያ ለተሰማሩ ምሁራን እጅግ ጠቃሚ ነው።
የትምህርት ነገር ምንኛ ተስፋ አስቆራጭ እየመሰለ እንደመጣ ታውቃላችሁ። ምሥጢር አይደለም። አብዛኛው ሰው ያውቃል።
መነሻ ምክንያቱ ባይገለጥላቸው እንኳ፣ ብዙ ሰዎች የአገራችን ትምህርት እንደተበላሸ መረዳት አያቅታቸውም። ለነገሩ ትንሽ ለማስተዋል ከሞከራችሁ፣ የብልሽት ሰበቦችና ምልክቶችን በጨረፍታ ማየትና መስማታችሁ አይቀርም።
“ልጆች በትምህርት ክፍለ ጊዜ ከሚደርስባቸው ጫና ነጻ መሆን አለባቸው” የሚል ግራ የገባው ሐሳብ በምሁራዊ ድምጽ በሚዲያ ሲስተጋባ ትሰማላችሁ። “ክፍል ውስጥ የዕውቀት ትምህርትን ከመከታተል ይልቅ ጨዋታ ላይ እንዲያተኩሩ መደረግ አለበት” የሚል ፈሊጥስ አልሰማችሁም?
“አስተማሪ የሚሰጣቸው የቤት ሥራ እና የመልመጃ ጥያቄ ላይ ሳይሆን፣ በራሳቸው ምርጫ ደስ የሚያሰኛቸው ጉዳይ ላይ ቢያተኩሩ ይሻላል” የሚል ሐሳብም ወደ ጆሯችሁ ይደርሳል - ልብ ብላችሁ ሳትሰሙት ሊያልፍ ይችላል። ወይም ደግሞ፣ መስማቱን ብትሰሙትም፣ ለማመን ሲቸግራችሁ፣ “ተሳስቼ ይሆናል፤ በደንብ ስላልሰማሁ ይሆናል!” ብላችሁ ራሳችሁን የወቀሳችሁበት ጊዜም ይኖራል። ግን፣ ጨዋታው እንደዚያ ሆኗል።
“ልጆች ደስ በሚያሰኛቸው ላይ፣ ቀልባቸውን በማረካቸው ጉዳይ ላይ እንዲያተኩሩ ሁኔታውን ማመቻቸት፣ የትምህርት ዋና ዓላማ ነው” ይላችኋል - ያለ ምንም ይሉኝታ። እንዲያውም “ኩራት” በሚመስል ፈጣጣ ድፍረት።
እውቀት ምናምን ብሎ መናገር የልጆችን ዝንባሌ መቅጨት ነው ይላችኋል - ሌላኛው።
“ተማሪዎች እውቀት እንዲጨብጡ፣ በመልመጃዎች አማካኝነትም መሠረታዊ ዕውቀት እንዲገነቡ”… እያልን ልጆችን ማስጨናነቅ የለብንም በሚል ፈሊጥ የተቃኘ ነው የዘመናችን የትምህርት ፍልስፍና። የስካር ፍልስፍና ቢሆንም፣ እንዲሁ በወሬ ብቻ በከንቱ ባክኖ አልቀረም። በተግባር “ውጤታማ” መሆን ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።
እንደምታዩት፣ ግንዛቤም ዕውቀትም ከተማሪዎች ዘንድ እጅግ እየራቀ መጥቷል።
እንግዲህ ምን ይደረግ? ምንስ ይሻላል? ሌላ ምን ይደረጋል? መፍትሔ ዎችን መሻት ነዋ የሚሻለው። ለዚህ ስለሚረዳም ነው፣ በዚህ ወር በአሜሪካ ሰፊ ተነባቢነት ያገኘውን መጽሐፍ የምጠቅስላችሁ።  
ጸሐፊው፣ የሥነ አእምሮ ባለሙያና የአንጎል ተመራማሪ ናቸው። Charan Ranganath ይባላሉ። የመጽሐፉ ርዕስ፣ Why We Remember ይላል።
ለልጆች ትምህርት የዘወትር ጥረትና ጥናት ዋነኛ የስኬት መንገዶች መሆናቸውን ጸሐፊው ያስረዳሉ። የመልመጃና የሙከራ ጥያቄዎች ለተማሪዎች ስኬት እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑም ይገልጻሉ። ትምህርት ማራኪ ሊሆን ቢችልም፣ “ትግል” ነው፤ ትግል መሆኑም ጥቅም አለው ሲሉም ያብራራሉ።
ትምህርት ጨዋታ አይደለም!
ትምህርት በትክክል ከተቀረጸና ከተከናወነ፣ የተማሪዎችን ቀልብና ዝንባሌ የመማረክ አቅም አለው። ልጆች ሊወዱት ይችላሉ። እንዲያውም፣ የሚመሰጡበትና የሚዝናኑበት ሊሆንላቸው ይችላል።
ነገር ግን፣ ባለሙያዎች ከመነሻው “ትምህርት ትልቅ ሥራ እንጂ መዝናኛ ጨዋታ እንዳልሆነ” ተገንዝበው ከቀረጹትና በጥብቅ ካከናወኑት ብቻ ነው ተማሪዎችን የመማረክ አቅም የሚኖረው።
“ትምህርት፣ እንደማንኛውም ሥራ ትኩረትን ይፈልጋል።
ዓላማና ፍላጎትን ይሻል።
ጥረትን ይጠይቃል።
Focus, Purpose, Effort እንዲሉ ነው።
የመጽሐፉ አዘጋጅ እነዚህን ሐሳቦች በአጽንዖት የሚገልጹ ቃላትን ይጠቀማሉ።
አንደኛ ነገር፣ በሌላ ጨዋታ ላይ የተጠመደ አእምሮ ለትምህርት ትኩረት መስጠት ይቸግረዋል። ለመማር Attention ያስፈልጋል።
ይሄም ግን በቂ አይደለም።
ሁሌም ትኩረታችንን የሚሻሙ እልፍ ጉዳዮች በዙሪያችን ያንዣብባሉ። ከግራና ከቀኝ፣ በጉንተላም ይሁን በጥቅሻ ትኩረታችንን ይሰርቃሉ። የተማሪዎች አእምሮ እዚህና እዚያ እንዳይባክን፣ ትኩረታቸው እንዳይበታተን ማድረግ የሚቻለው፣ ሥራዬ ዓላማዬ ብለው ከያዙት ብቻ ነው።
Intention ያስፈልጋል።
እንዲህ በአንድ ቃል ሲገልጹት ቀላል ይመስላል። ግን ቀላል አይደለም። ትምህርት ይፈታተናል።
ትምህርት፣ ገና ገለጥ አድርገው ሲያዩት ወዲያውኑ ትኩረትን እየማረከ እንደ ዘበት በተመስጦ ኀይል አንከብክቦ ወደ ሽርሽር የሚወስድ ቢሆን ጥሩ ነበር። ግን እንደዚያ የማይሆንበት ጊዜ በተደጋጋሚ ያጋጥማል።
በተለይ “መሠረቱን” እስክንጨብጠው ድረስ፣ እያንዳንዱ አዲስ የትምህርት ምዕራፍ ይፈታተነናል፤ ያንገዳግደናል። ለተወሰነ ጊዜ በጽናት ከያዝነው፣ እኛም እያወቅንበት ትምህርቱም እየማረከን ይመጣል። መንገዳችን እንደ ሽርሽር እስኪያምርልን ድረስ ግን፣ ለጊዜው ጥረትን ይጠይቃል።
ይህን ቁም ነገር ለማስረዳት፣ የመጽሐፉ አዘጋጅ “Some Pain More Gain” በሚል ርዕስ የኒሮሳይንስ ጥናቶችን በማጣቀስ ያብራራሉ።
ወደ ላቀ ዕውቀት መራመድ፣ አዲስ ችሎታ ማግኘት፣ በሙያ መራቀቅ… ገና መነሻ መንደርደሪያ ላይ ጥረትን ይጠይቃሉ።
አንዴ ከተለማመድነውና ከተረማመድንበት በኋላ ግን፣ አብሮን የተወለደ ያህል ያዋሐደናል። ከጊዜ በኋላ ስናስበውማ፣ በጣም ቀላል ሆኖ ሊታየን ይችላል።
የመራመድና የመናገር ችሎታ…
አንድ ሁለት ብሎ መቁጠር…
ሀሁ ብሎ ማበብ…
መደመርና መቀነስ…
እነዚህን ሁሉ ስንማርና ስንለምድ ቅንጣት ታህል ጥረት የጠየቁን አይመስለንም።
ነገር ግን እነዚህ ሁሉ እግጅ ከባድ ሥራዎች ናቸው።
ሕጻናት “ዳዴ” ለማለት ሲሞክሩ፣ ምን ያህል እንደሚውተረተሩና ምን ያህል እንደሚታገሉ አይታችሁ መታዘብ ትችላላችሁ። እየወደቁ መነሣት ነው። ትግል ነው።
ቃላት ለማወቅና ለመልመድ ስንቴ ሲደጋግሙት እንደሚውሉም አስታውሱ። እንደ ዐዋቂ፣ የልባቸውን በፍጥነት ለመናገር በሕጻን አንደበት ይታገላሉ። ደግሞ አይሰለቻቸውም። ቀልድ አይደለም። ጨዋታ አይደለም። ከባድ ሥራ ነው የያዙት። ዐቀበት ነው።
ደግነቱ፣ ውጤቱ ብዙ ነው። ከለመዱትና ካወቁት በኋላ፣ መራመድም ሆነ መናገር እንደ “ዘበት” ይሆንላቸዋል። እንደ ልብ ይሮጣሉ። ፈንጠዝያ ነው። ጨዋታ ነው። ሲፈታተናቸውና ሲያስቸግራቸው እንዳልነበረ፣ እንዳሻቸው ይራቀቁበታል።
“Some Pain More Gain” እንዲሉ ነው።
የመጽሐፉ አዘጋጅ፣ የሥነ አእምሮ ምሁርና የአንጎል ተመራማሪ ናቸውና፣ እነዚህን ቁም ነገሮች ለማስረዳት እውነተኛ ክስተቶችን ይተርካሉ። በዘመናዊ ቴክኖሎቹ የተከናወኑ የኒሮሳይንስ ምርምሮችን በሙያዊ ቃላት ብቻ ሳይሆን በመደበኛ አገላለጽ በማቅረብ ያብራራሉ።
የትምህርት ይዘትና አቀራረብ ውጤታማ የሚሆነውም፣ በዚሁ የዕውቀት መንገድ እንጂ በሌላ የዘፈቀደ ጨዋታ አይደለም።
ትኩረትን ይፈልጋል።
ሥራዬ ብለው ሊይዙት ይገባል።
የዕውቀት መሠረቶችን መጨበጥና መገንባት፣ ለብዙ ተጨማሪ ዕውቀት አስተማማኝ መደላድልና መነሻ ዐቅም ይሆናል።
ለጊዜው ቢፈታተንም፣ ለጊዜው ቢያደክምም፣ መነሣትና መንደርደር ቢከብድም፣ በጽናት ከጀመሩት በኋላ ወደ ከፍታ መብረርና መምጠቅ አያስቸግርም።
እንደ ሮኬት ነው። ትልቁ ፈተና፣ ከምድር መነሣት ላይ ነው። የመጀመሪያዎቹ 3 ደቂቃዎች ላይ ነው ከባዱ ውጥረት። ሮኬቱ ይግለበለባል። አካባቢው ይንቀጠቀጣል። ባለ በሌለ ኀይሉ ይታገላል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን፣ መንገዱ አልጋ በአልጋ ይሆንለታል። አየር በአየር ማለቴ ነው። ወይም ሕዋ ለሕዋ!
የታሪከኛውን ሮኬት የሙከራ በረራ ተመልከቱ። የኤለን ሞስክ ሮኬት ነው (የስፔስኤክስ ፈጠራ)።
የሮኬቱ ጉልበት ከእስከዛሬዎቹ በዕጥፍ ይበልጣል።
ስታርሺፕ ይሉታል -  አሳጥረው ሲጠሩት። እንዲሁ “ሮኬት” እንደለዋለን እንጂ፣ “ሮኬት ከነመንኮራኩሩ” ብለን ብንጠራው ይሻላል። የሮኬቱ አገልግሎት፣ መንኮራኩሩን ወደ 65 ኪሎሜትር ከፍታ አድርሶ መሸኘት ነው።
የ3 ደቂቃ ጉዞ ነው። እንዲያውም ሦስት ደቂቃ አይሞላም። 2 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ ብቻ!
ጊዜዋ አጭር ናት። ፈተናውም ግን እዚህችው የመነሻ በረራ ላይ ነው የተከመረው።
የሮኬቱ 33 ሞተሮች ተለኩሰዋል። መቼስ “ሞተር” እንላቸዋለን እንጂ፣ እሳተ ጎመራ ናቸው።
ከዘመነኞቹ የቦይንግ አውሮፕላኖች መካከል፣ እጅግ ግዙፉ “B777-300ER” ይባላል። ሁለት ሞተሮች አሉት። የሞተሮቹ ጉልበት፣ ከአንድ ሺ የቤት መኪኖች ጠቅላላ ጉልበት ይበልጣል።
የስታርሽፕ ሮኬት ጉልበት፣ ከ”B777-300ER” ጋር ሲነጻጸር ከ70 ዕጥፍ በላይ ነው።
800 ሺ ኪሎግራም ነዳጅ ይጠቀማል። (1 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እንደማለት ነው)።
ይሄ ሁሉ ጉልበትና ነዳጅ፣ 3 ደቂቃ ለማይሞላ የመነሻ በረራ ነው። ያኔ የሮኬቱ ሥራ ያበቃል።
ሮኬቱ ወደ ምድር ይመለሳል።
የበረራው ከፍታ ወደ 65 ኪሎሜትር ደርሷል። የበረራ ፍጥነቱም ወደ 5500 ኪሎሜትር በሰዓት ሆኗል።
በእርግጥ የሮኬቱ ሥራ ቢያበቃም፣ መንኮራኩሩ ግን ገና ብዙ ጉዞ ይቀረዋል። ቢያንስ ቢያንስ ወደ 200 ኪሎሜትር ከፍታ መጓዝ አለበት። ፍጥነቱም፣ በአራት ዕጥፍ መጨመር አለበት። ወደ 27ሺ ኪሎሜትር በሰዓት መድረስ ይኖርበታል።
ያኔ ያለ ሞተር “በቀላሉ” ምድርን መዞር፣ ጉልበት ሳያስፈልገው እንዲሁ “እንደ ዘበት” መሽከርከር ይችላል።
እስከዚያው ግን፣ የሞተር ጉልበትና ጥረት ያስፈልገዋል።       
በእርግጥ ትልቁ ትግል ስለተቃለለ፣ ብዙም አያስቸግረውም። በ33 የሮኬት ሞተሮች ጉልበት ወደ 65 ኪሎሜትር ከፍታ ደርሷል። ከዚህ በኋላ መንኮራኩሩ ሮኬቱን ተሰናብቶ የራሱን 6 ሞተሮች አስነሥቶ ወደ ጠፈር በረራውን ይቀጥላል።
መንገዱ ቀና ነው። መንኮራኩሩ 3 ደቂቃ በማይሞላ ተጨማሪ የበረራ ጊዜ፣  ፍጥነቱንና ከፍታውን በዕጥፍ ይጨምራል። ወደ 130 ኪሎሜትር ከፍታ ይደርሳል። ፍጥነቱም 10ሺ ኪሎሜትር በሰዓት ይሆናል።
አምስት ደቂቃ ቆይቶም፣ ፍጥነቱ እንደገና ከዕጥፍ በላይ ይጨምራል። 26ሺ ኪሎሜትር በሰዓት! ከዚያም ያልፋል እንጂ። ከዚያ በኋላ፣ ያለ ሞተር መንሸራሸር ይችላል።
ትግልና ፈተና የተከመረው መነሻው ላይ ነው።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ ከአጭር የውጥረትና የጽናት ጊዜ በኋላ፣ ፈተናው ይቃለላል።
ከዚያም ያለ ምንም ትግል እንደልብ መዞርና መሽከርከር! ሁሌም ጥረት ያስፈልጋል። ግን ትግል ፈተና አይሆንብንም። እንደ መናገር እንደ መራመድ።
ትምህርትና ዕውቀት፣ ሙያና ጥበብም እንዲሁ ናቸው።

Read 722 times