Monday, 01 April 2024 07:37

የዘመን እውነት!

Written by  ፋሲል የኔአካል ሀብቱ
Rate this item
(5 votes)

 ኪው! ኪው! … ኪው!-- ከወፍጮ ቤቱ የሚመጣ ድምፅ ከእንቅልፌ አናጥቦ ቀሰቀሰኝ። እሙሃይ ነው፤ ወፍጮ ፈጭታው እሙሃይ። ዛሬ ቅዳሜ አይድልንበት ስለሆነ አይፈጭም፤ ከዚያ ይልቅ ቀኑን የወፍጮውን መጅ በመውቀር ሲያስተካክል ይውላል፤ ለዚያ ነው ከሰውም ከአዕዋፋትም ቀድሞ ከእንቅልፉ ነቅቶ እንኳን በወፍጮ ድምፅ ፈንታ ኪው ኪው የሚል ድምፅን የሚያሰማው። “ንቅል እኮ ነው” እየተባባሉ እሱን መቦጨቅ ለመንደሩ የቡና ቁርስ ከሆነ ሰነባብቷል። ከዘመን የቀደመው መቃተቱ ስሙን የቡና ግብጦ ቢያደርገውም፣ እኔ ግን እወደዋለሁ።  ትውውቃችን መጻሕፍትን በመዋዋስ ቢጀምርም  ህመምን  መጋራት የበለጠ ጓደኛማቾች አድርጎናል፤ ህመሜን ይረዳኛል ፤ ብሶቱን ይነግረኛል፤ መፍትሔ ባላበጅለትም እሰማዋለሁ። አንድ ጊዜ የህክምና ካርዱን ይዞ ቢሮዬ ገባ፡፡
“ምንህን አሞህ ነው?” ስል ጠየቅኩት
 “ያመመኝስ ዓይኔን ነው። ግን…” አለ
የወፍጮ ቤት ዱቄት የቦነነባቸው የዓይኖቹ ሽፋሽፍት የሸበቱ መስለዋል። ”ግን ምን?” አልኩት፤ ወሬውን ለማስቀጠል።
“ታውቃለህ ጓደኛዬ፤ እየኖርኩ ሳይሆን ዘመኑን ተኝቼ እያለምኩት ነው የሚመስለኝ። መቼ ነው ከዚያ እንቅልፍ የምነቃው? ምን ባይ? ምን ብነካ? ምን ባሸት ነው ይሄ ዘመን የኔ መሆኑን የምቀበለው? የእውነት እየኖርኩ ነው ብዬ የማምነው? ይሄ ቅዠቴስ መቼ ይቋጫል?” አለኝ።
”ከዘመንህ ተጣልተሃል፤ ከዘመንህ ኮብልለሃል፤ መልሰህ ከዘመንህ ጋር ታረቅ።”
እንደ አስፈሪ ደመና ቀልተው በደፈረሱ ዓይኖቹ ቀና ብሎ ዓይቶኝ ቀጠለ፤ “እኔ ከዘመን አልተጣላሁም፤ የተጣላሁት ከሰዎች ነው!”
”እንዴት?  ማለት…?” አልኩት፤ እኔም በተራዬ የማንበቢያ መነጽሬን አውልቄ የጋዋኔ ኪስ ውስጥ እያስገባሁ።
“የዘመን መልኩ ሰው ነው፤ ዘመን ሰዎችን አይሠራም፤ ሰዎች ዘመኑን ይፈጥሩታል እንጂ” አለኝ። እሙሃይን እወደዋለሁ። ከሾሊት የዘመን መቁጠሪያ የቀደመ መቃተቱና ከሰዎቿ የተለየ ውብ ማንነቱ ንቅል ቢያስብሉትም እንዳላበደ አምናለሁ። ደግሞ ቢያብድስ! እሱ ብቻ ነው እንዴ ሾሊታዊ፤ ቢያብድም እንዳገር ነው።
የእሙሃይ የወቀራ ድምፅ ሾሊትንም የቀሰቀሳት ይመስል ዓይኖቿን ገልጣ ማዛጋት ጀምራለች። በትልልቅ ተራራዎች መካከል ባለ ዝቅተኛ ስፍራ ላይ የተመሰረተችው እድሜ ጠገቧ የሾሊት ከተማ፣ ከዓለም የመነነች ፣ ቅዳሜ ቅዳሜ ከየቀዬው የሚተሙ አስታዋሽ ባላገሮቿ ልዩ ድምቀት ይሰጧታል።እኔም በእንደዚህ አይነት ወከባ ቀን ትርምሱ መሀል መገኘት አልፈልግም፤ ከዛ ይልቅ በጎቹን መስክ ላይ እንዳሰማራ እረኛ የሾሊት ሸለቆ ላይ የተሰማሩ ሰዎቿን ከፍ ያለ ቦታ ላይ ተቀምጬ መመልከትን እመርጣለሁ። ቁርስ መብላት አላሰኘኝም፤ ገና በቅጡ እንኳን ሳይነጋ በማለዳው ሽሽት ላይ ነኝ፤ከትርምሱ ከወከባው ከእሽቅድድሙ  ሽሽት። የከተማዋን ዋና አካፋይ መንገድ ይዤ ብዙ ከተራመድኩ በኋላ፣ ከከተማው ወጣ ብሎ ወዳለ ኮረብታ ወጣሁ። ከኮረብታው በስተቀኝና በስተግራ የከተማዋ ትልቁ መስጊድና እድሜ ጠገቡ የቅድስት ሥላሤ ቤተ-ክርስቲያን  ይገኙበታል። ስለ ከተማቸው ሲፀልዩ፣ሲለምኑ፣ ሲሰግዱ የሚያድሩ አባቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ብለው አያውቁም። ይገርማል ፤ የሰው ልጆች ሐይማኖታቸው ብዙ እምነታቸው ግን አንድ ነው፤ በዚህም ምክንያት ፍፁም ተቃርኖ ባላቸው በተለያዩ ሐይማኖቶች ውስጥ ቢከፋፈሉም እንኳን በአንድ እምነት ግን ተኣምር ከመስራት አይቦዝኑም።
 ፀሐይ በስስ ነጠላ እንደተጋረደች ኩራዝ ነጩ አድማስ ላይ ቦቀታዋን  በስሱ ነስንሳ፣ መጣሁ ወጣሁ እያለች ነው። እንደ ሾሊት ከተማ ነዋሪ የፀሐይ መውጣት ከእንቅልፋቸው የሚቀሰቅሳቸው የጥልያን ሱፍ አበቦች ካቀረቀሩበት ቀና እያሉ፣ ወደ ምስራቅ ሲያንጋጥጡ፣ ለሚመለከታቸው የፀሐይ አምላኪዎች ይመስላሉ። ለነገሩ እኛ ከሱፍ አበባዎች በምን ተሻልን? ቁልቁል ወደ ከተማዋ አማተርኩ፤ ራሷ ላይ የጭጋግ አስኬማ ደፍታለች። ጉሙ ከአንዱ ተራራ ተነስቶ ወደ ሌላኛው ተራራ ሲጠመጠም፣ “ተራራው” በመዳፏ የጨበጠችውን የጥጥ ባዘቶ በጭኗ ላይ እያሾረች ልቃቂት የምትሰራ ኮረዳ ይመስላል። እንደ ድር የመነመነ አካሏ የማይችለውን ራሷን በመሸከም አንገቷ የተቀጨው ሾሊት አሳዘነችኝ። በለም መሬቷ ፋንታ ውሃዎቿ አረንጓዴ ለብሰው የፀደይን መስክ መስለዋል። ከህፃን እስከ አዛውንት ትላንትን በማውራት ተጠምደዋል፤ መምህርና ተማሪ መሆናቸውን ዘንግተው፣ ሰባኪና ምዕመን ሆነዋል። ሾሊት ትናንትን በሚሰብኩ መሀን ሰባኪዎችና ሳያዩ በሚያምኑ ጭፍን አምላኪዎች ተሞልታለች። ትላንታቸውን ከለላቸው እንጂ መሰረታቸው አላደረጉትም።  ታሪክሽ መሰረት ያልሆነሽ አንቺ ከተማ ወዮልሽ፣ አሁንሽን አልተመለከትሽም፣ ዛሬ መሰረት ያልጣልሽለት ነገሽ እንደ በካር ምጥ ያስጨንቀኛል። ከፀሐይ ጋር የምትነቂ፤ ከፀሐይ ጋር የምትጠልቂ አንቺ ከተማ ሆይ፤ ወዮልሽ ጠላቶችሽ ጨለማሽን ተገን አድርገው ይዘምቱብሻልና! ጥንታዊዎቹ ሮማውያን ለገዥዎቻቸው አዛውንት መድበው ሞታቸውን እንደሚያስታውሷቸው፣ እኔም እንዲሁ አማረኝ፤ “ትጠፊያለሽ”! እያለ የሚያነቃት አዛውንት ልመድብላት ተመኘሁ።
ከዛሬ ተነጥሎ የሚተነበይ ነገ የለሽምና፣ ይሄው ስራ እንደፈታ መነኩሴ የራስሽን ቆብ እየቀደድኩ እሰፋለሁ። ሁላችንም የነገ ትላንቶች ነን፤ በለውጥ  የማይለካ ህይወት ግን ትላንቱ ከዛሬ፤ ዛሬውም ከነገው የተለየ አይደለም። ጊዜን ለመቁጠር ከለውጥ የተሻለ ሰዓት ከየት ይመጣል? አሻራችንን ሳናትም የመጣንባቸው አመታት ከምንሄድባቸው የተለዩ አይደሉም። የቀን መልኩ የእጃችን አሻራ ነው። እየደጋገመች የምትቆምበት አንድ አይነት ቀን፣ በመረገጥ ብዛት ጨቅይቶ ቅርጫጭታም አድርጓታል። በአባት እና በልጅ፤ በታላቅ እና በታናሽ፤ በመሪ እና በተመሪ መካከል ልዩነት ጠፍቷል። ፈጣሪ ብቻ እያፈረሰ ሲሰራ የእጁን አሻራ በየሰው ላይ አስተውላለሁ፤ ምናልባት ኗሪዎቿ የሱ የጊዜ መቁጠሪያዎቹ ይሆኑ ይሆን?  እንጃ።
የሲቪል ሰርቪስ ሰፊ ግቢ ያረጁ ቢሮዎችን አቅፎ ከገበያው በስተቀኝ ሰፊ ቦታ ይዟል፡፡ የሾሊት መስሪያ ቤቶች የፈራረሱ ናቸው፤ ውስጥ ያለው አሰራር ደግሞ ከቤቶቹም ይባስ ፍርስርሱ የወጣ ነው። በስራ አጋጣሚዎች የብዙ መስሪያ ቤቶችን ደጅ የረገጥኩ ቢሆንም፣ የዚህን መስሪያ ቤት ያክል ግን የተበላሸ አላየሁም። ስራ በተመደብኩበት ወቅት ቅጥር ለማስጨረስ ተመላልሻለሁ፤ የቤቱ የጭቃ ምርግ ሰዎች ላይ የሚናድ ይመስላል፤ ከቤቱም በላይ ሰዎቹ ጎስቋሎች ናቸው። ምናቸውም ለዚህ መስሪያ ቤት አይመጥንም፤ ወንበራቸው አለቅጥ ሰፍቷቸዋል። የጋራ የስራ መንፈስ የላቸውም፤ ሁሉም የጎሪጥ የሚተያዩ ናቸው። እንኳን ለብሰው ጎርሰው ያድራሉ ለማለትም ይቸግራል፤ ይለይልህ ብሎ ኃላፊው ለመፈረም እስክብሪቶ እንዳውሰው ጠየቀኝ። ዛሬ ቢሆን አልደነቅም፤ በወቅቱ ግን አላስደነገጠኝም ብል ውሸት ነው።
”ደሞዛችሁ ይግባ አይግባ ግድ እንደማይሰጣችሁ ድፍን ሾሊት ያውቃል፤ ታዲያ እንደ ደሞዝተኛ መልበስ ራስን መጠበቁ ቢቀር ለመስሪያ ቤታችሁ እስክብሪቶ እንኳን አትገዙም?” ስል ጠየቅኩት።
“ሁሉም’ኮ ሀብታም ነው ግን አምሮብኝ ብታይ ኦዲት ይደረግ እባላለሁ እያለ ነው’ጂ” አለኝ።
”አታስቡ፤ ከላይ እስከ ታች ልዩነት አልባ ስለሆነ ማንም አያደርጋችሁም፤ ለህዝቡም አትጨነቁ፤ ሁሉንም ያውቃል፤ አውቆ ለተኛ ህዝብ ደግሞ ከዚህም በላይ ይገባዋል።” አልኩት፤ በደም ፍላት፡፡ ነገሩ ግን በማስመሰል ማትረፍ እንጂ መትረፍ እንደማይቻል ሳይገለጥልኝ ቀርቶ አልነበረም።
“አንተ ግን ጤና ነው፣ ፖለቲካ ነው አጠናሁ ያልከኝ?” የፈረመውን ወረቀት ወደፊቴ ገፋ አድርጎ፣ እስክብሪቶዬን ወደ ኪሱ ከተተው፡፡ ብዕሬን ተቀማሁ ማለትም አይደለ? ይሁን ግድ የለም፤ አሁን  ሁሉንም ነገር ለምጀዋለሁ፤ መላመድ መገረሜን አጥፍቶልኛል፤ ከሁሉም በላይ ግን የዘመንን እውነት መጋፈጥ ያስፈራል፡፡ የእውነት መጥፎ ፊቷ ሲገለጥ፣ እንደ ስጋ ደዌ ተስፋን ቆራርጦ የሚጨርስ በሽታ ነው፤ መንገዷም በጨለማ ውስጥ እንደሚደረግ “ከ… እስከ” የሌለው  አስፈሪ የዋሻ ውስጥ ጉዞ ነው።
ሆኖ ይኑር በቃ ህይወት እሩብ ጉዳይ
እውነት ተደበቂ የተስፋዬ ገዳይ
እሙሃይ እውነቱን ነው፤ “ተስፋ ከሚያስቆርጥ እውነት የሚያፅናና ውሸት ይሻላል” የሚለው፡፡
 ቀኑ ቅዳሜ ነው።ንጋት እየጠበቀች ከህይወት ጋር ግብግብ የምትገጥመው ሾሊት፣ እንደተለመደው የአህያ ውድቂያ እየተዋደቀች አቧራ ቅማ ለመነሳት፣ ካረበበባት የእንቅልፍ ዱካክ እየነቃች ነው። የቆመ እንጨት ላይ የተደፋ ጣሳ በየበራፉ ተተከለ፤ መሸታ ቤቶቹ ጠጪን ከሩቅ የሚጠራ ባንዲራቸውን አውለበለቡ፤ የተጫኑ አህዮች፣ በገመድ የሚጎተቱ በጎችና ፍየሎች በየአቅጣጫው ገቡ፤ በትንንሽ ፍርግርግ ሽቦ አጥሮች ውስጥ የሚጠበቁ ዶሮዎች፣ የሾሊትን የቅዳሜ ቀን ውሎ በጩኸት ፊሽካቸው አስጀመሩ፤ ግብይቱ ደርቷል። ፀጉራቸውን ያበጠሩ ወጣቶች ሚዷቸውን በጎፈሬያቸው መሃል ሻጥ አድርገው፣ ባታቸው እንደ ቅቤ ቅል እያበራ በደቦ ይውረገረጋሉ፤ ነፍጥ ያነገቡ ጎልማሶች፣ ረዥም ዘንግ የጨበጡ ጭራ እየነሰነሱ ዝንብ የሚከለክሉ አዛውንቶች በየእውቂያቸው ቆመው ይነጋገራሉ።
አሳቻ ሰዓት የጠበቁ  በሸራ የተሸፈኑ መኪናዎች የሾሊትን አቧራ እንደ ጭፍራ እያስከተሉ ደረሱ። ”መኪና መጣ! መኪና መጣ!” እያሉ የሚቦርቁ አቧራ ጠግበው  አይጥማ የሆኑ፣ እላቂ ጨርቆቻቸውን ጣል ያደረጉ ህፃናት የስኳር እቃ እንዳየ ዘመሚት፣ ከየጉድባው እየዘለሉ ወጡ፡፡ ድንገት ጫጫታውን ጭጭ ያደረገ ጩኸት፤ወከባውን ያዋከበ ወከባ ፤ የገበያውን ቅፅር የሚደረምስ ድምፅ ተሰማ። መለዮ ለባሽ ታጣቂ ኃይሎች ከመኪናው እየዘለሉ ወደየአቅጣጫው አነጣጠሩ። አውሬ እንደገባበት የዶሮ ቤት፣ ህፃን አዋቂው ተሸበረ፤ ሾሊት ከቁና ጠበበች። ከመኪናው ጋቢና ውስጥ የተቀመጠ ሰው እንደ ሴባስቶፖል መድፍ አፉ የሰፋውን የቃል ማጉያ በመኪናው መስኮት አውጥቶ፤ “ሀገር የምታሸብሩ አሸባሪዎች፤ በያላችሁበት ትጥቅ ፍቱ፤ በሰላም እጃችሁን ስጡ” እያለ ተናገረ። አሸባሪዎችም የሚያሸብራቸውን “አሸባሪ” ይሉት ይሆን? ሁሉም የራሱን ወገን ፍለጋ በየቦታው ተፈተለከ። ለወደድነው እና ለወለድነው ክርስቶስ የማልኮስን ጆሮ እንቁረጥ ያሉ የሾሊት ጴጥሮሶች፤ ከልጆቻቸው ጎን ተሰልፈው  ሾተላቸውን በማልኮስ ላይ ይመዙ ጀመር። ዳሩ ግን ‘ ሾተላችሁን ወደ አፎቱ መልሱ!’ የሚል ገላጋይ አልተገኘም። ትርምሱ ተጧጧፈ፤ እንደ ጋለሞታ ሳቅ የሚንፈቀፈቀው የጥይት እሩምታ በሾሊት ተራሮች አስተጋባ፤ ወጀብ እንደ ጣለው የሪፋ አገዳ ሰው በመደዳ ወደቀ። ሞት እና ምት የሚያጠብቃቸው ሀሞተኞች፣ ቀፎው እንደተነካ የንብ መንጋ ከወዲያ ወዲህ በእልህ ሲወራጩ፣ ከፊታቸው ያገኙትን እየነደፉ ሲወድቁ፣ ሰማይና ምድር የገጠመ ያክል ያስጨንቃል። የተረገጡ ህፃናት ድምፅ ከዛም ከዚህም ይሰማል፤ ወጣቶች እንደ እሳት እራት እየበረሩ አረሩ፤ የአባቶች ደም ጎረፈ፤ እናቶች የልጆቻቸውን አስከሬን ታቅፈው አለቀሱ፤ የተበተነ ብር የሚሰበስቡም ይስተዋላሉ፤ የጥሎ ሂያጅ ማጀት የሚበረብሩ ደፋር ሌቦች ቀላል አይደሉም። ነፍጡን እንዳቀፈ ታጥፎ የወደቀን ሰውየ፣ ህፃናት ከበውት ይጮሀሉ፡፡ ልጄን   ልጄን እያለች ደረቷን የምትደቃ እናት፣ ከህፃናቱ ጋር ትላቀሳለች፡፡ ባሌ ትዳሬ የምትል ሴት ፀጉሯን እየነቀለች ታገላብጠዋለች።
   ይሄ ሰው ስንት ነው? አልኩ፡፡
 ቁስለኛና አስከሬን በቃሬዛ እየተሸከሙ ሲሸሹ ሲታይ፣ በአጫጆች ኋላ እየተከተሉ ነዶ የሚሰበስቡ ገበሬዎች ይመስላሉ። ፍርሀትንና ፈስን እኩል የሚያነውር ደፋር ህዝብ፤ ፈሪ ቄሳሮችን ከሾመ መጥፊያው ደርሷል ማለት ነው። ፈሪ ቄሳር በራሷ ላይ ያነገሠችው ሾሊት፣ የሰው ልጅ እየታጨደ የአስከሬን ነዶ የሚሰበሰብባት የመከራ ማሳ ሁና ዋለች። ትላንት ስለ ሀገር ክብር ተዋድቀው ጉልበታቸውን ያስመሰከሩ ጀግኖች፤ ዛሬ እንደ ስጋት ታይተዋል። እነዚህን ስለ ሀገር ፍቅር የሚቆረጡ የሾሊት አበቦችን፣ ስለ ሀገር ኖረው ሳያውቁ ስለ ሀገር መሞትን ማነው ያስተማራቸው?
     በተራበ አንጀት እያሰፈሰፉ
    በየጎዳናው ላይ ጅቦች ሲሰለፉ
   መከራን ማብዛት ነው ሀገር መውደድ ትርፉ።
የሚል ግጥም ለሾሊት ሰማዕታት የሚገባ መሰለኝ። ይቺ የጥንቷ ከተማ ሾሊት ያልተከፈለ የብዙ ሰዎች እዳ አለባት፡፡ ታሪኳን ወደ ኋላም ስንመረምር፣ አሁን እየሆነ ያለውን ስናስተውል፣ ነገ ሊሆን የታሰበውንም ስንተነብይ፣ ከከፈሉላት ይልቅ ላስከፈሏት ከፋይ ሆና ነው የምትገኘው፤ ግን ልጆቿ ተስፋ ቆርጠውባት አያውቁም፤ ስለ ስሟ ህይወታቸውን ለመክፈል አያንገራግሩም።
ትላንት አልጠግብ ባይ ስልቻ ሆድን ለመሙላት የተገነቡ የጥላቻ ሀውልቶች፣ ቫዝሊን እንደጠገበ ገላ አቧራ እየሳቡ ንፅህናዋን አጎደፉት። ከሆዳቸው ነፃ ያልወጡ የነፃነት ታጋዮች፣ በየስርቻው ተወትፈው ስለ ነፃነት ያልማሉ፤ ለባርነት የታጩ ሎሌዎች የምግብ መደራደሪያ አቅርበው፣ ሳምንት በሳምንት እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ቡድን ከቡድን እያማደቡ ያጫርሷቸዋል።
 አንዳንድ ጦርነቶች ነገስታት የወደፊት ስጋቶቻቸውን ለመለየትና አቅማቸውን ለመፈተሽ የሚፈጥራቸው ባህሮች ናቸው፡፡ የነዚህ ባህሮች ጥልቀትም በሞኞች ቁመት ይለካል። በጦርነት ማግኔት ሰላምን የምታስሱ ቄሳሮች ወዮላችሁ። አንተስ የቄሳር አሽከር ማልኮስ ሆይ፤ እስከ መቸ ነውራቸውንና ውሸታቸውን በካባና  በቀሚሳቸው ሸሽገው ካንተ ጀርባ የተጠለሉ ቄሳሮችን በማመን በጭፍን ትጓዛለህ፤ እስከ መቸስ  እውነተኛ ነብያትን ለማነቅ ትጣደፋለህ፤ የተቆረጠ ጆሮህን የቀጠሉ እነሱ አይደሉምን? ማልኮስ ልብ ግዛ፤ ከእውነት ጋር ቁም፤ ፊትህን ከጀርባህ ወደተደበቁ ኃሰተኛ የቄሳር ሰዎች መልስ ማለት አማረኝ ግን...
      “ብቻየን ነኝ ፈራሁ
       እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
       እምፀናበት ልብ አጣሁ”
****
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 541 times