Monday, 01 April 2024 20:08

ሰውን ሰው ሲቸግረው…

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ-
Rate this item
(3 votes)

 አንዳንዴ…
…. ሰውን እንቸገራለን፤ ለህይወት አስፈላጊ እንደሆነ ቁስ ሁሉ በሰው መደህየታችን ህይወታችንን አደጋ ላይ ጥሎት እናገኛለን፡፡ እንደ ገንዘብ ዕጦት ሁሉ ሰውን “መመንዘር” ግዳችን ሆኖ ሳንችል እንቀራለን፡፡ ሰው እንራቆታለን፤ እንደ አልባሳት መጎናጸፍ እያስፈለገን በብቸኝነት መለመላነት ላይ እንወድቃለን፡፡ ማርክስ ይሄን ያለው ይሄን ተመልክቶ ሳይሆን ይቀራል?
“Mans most precious treasure, his greatest wealth, is man himself”
“የሰው ጌጡ እራሱ ሰው ፤ ኃብቱም” ብለን ብንተረጉመው ይበቃዋል፡፡ አንድ የጉራጌ አዛውንት ሲያጫውቱኝ ይሄን እንዳሉኝ አስታውሳለሁ፡፡
“ሰውየው ተጠየቀ አሉ፡፡
‘ግንድ ቢወድቅብህ ይሻላል፣ ወይስ ህዝብ?’
መለሰ ሰውየው፡-
‘ግንድ ይውደቅብኝ’
‘ለምን?’
‘ግንድ ቢወድቅብኝ ህዝብ ያነሳልኛል፡፡ ህዝብ ቢወድቅብኝ ማን ያነሳልኛል?”
ልክ ነው፤ ‘ግንድ’ ወድቆባቸው በህዝብ የተነሳላቸው ብዙ ሰዎች እናውቃለን፡፡ ህዝብ ወድቆባቸው የሚያነሳላቸው አጥተው….
…. ይቺን፤ ሰው በሰው የመሸነፉን ድክመት የተረዱ ነገስታቱ፤ ሁሉም የሚፈራው ቅጣት ከውስጡ አዋልደዋል - ግዞት፡፡ የግዞት ቅጣት ውስጥ አካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ባዕድነት ተቀጪው ላይ ይሆናል፡፡ ህዝቡ እንዲወድቅበት “አንተ ያከበርከው ንጉስህ ላይ አምጷልና በቸልታና በማግለል ቅጣው” የሚል ትዕዛዝ ውስጥ ለውስጥ ይስለከላካል፡፡ ግዞተኛው በስሙና በማዕረጉ አይጠራም፡፡ “ውለታቢሱ” ይባላል፡፡
“ከውለታቢሱ ቤት ወዴት?”
ከአንድ ወዳጄ የሰማሁት የግዞት ትርክት ባስታወስኩት ቁጥር ሀዘን የሚለቅብኝ ነው። ደጃዝማች ዓለማየሁ ይባላሉ፡፡ “ህዝብ እንዲወድቅባቸው” ተፈርዶባቸው ባይተዋርነቱ ይቆጠቁጣቸዋል፡፡ እሳቸውን ማናገር የንጉስ ትዕዛዝ እንደመናቅ ይቆጠራልና ሰው ሁሉ እርቋል፡፡ “ደጃዝማች” ቀርቆ በሌጣው “ዓለማየሁ” እንኳ የሚላቸው የለም፡፡ “ውለታቢሱ” ነው ከተጠሩም። እና ደጃዝማቹ የአካባቢውን ህፃናት ሰብስበው የልጅ ወሬ ሲያስተናግዱ ይውላሉ፡፡ ቀስ በቀስ ዋነኛ ተሳታፊ እየሆኑ፣ በልጅ ወሬ ከልጅ ጋር ሲነታረኩ ይውሉ ጀመር፡፡ እንዲሁም ብይ እየተጫወቱ፣ ብስክሊት በተራ እያሽከረከሩ፡፡
የግዞት ቁልቁለት እስከዚህ ድረስ ወርዶ ያወርዳል፡፡ የሰው ማጣት ንጣት እንዲህ ያገረጣል፡፡
…ሀዘን!!
ሰውን ከሰው መነጠል እድሜ ጠገብ ቅጣት መሆኑን የሚነግረን ብዙ ነባር ታሪክ አለ፡፡
የቆሮንቶሱ ንጉስ ፔሪያንደር በልጁ (ሊከፍሮን) ላይ ይህንን አሰቃቂ ከሰው የመነጠል ፍርድ አፅንቶበት እንደነበር ታላቁ የታሪክ ሰው ሔሮዶቱስ ይነግረናል፡፡ ንጉስ ፔሪያንደር የልጆቹን እናት ይገድላል፡፡ ሁለት ልጆቹ አያቶቻቸው ጋ ለጥየቃ ሲሄዱ ይህንን የአባታቸውን ግፍ ይሰማሉ፡፡ ታላቅየው ጉዳዩን ከቁብ ሳይቆጥረው ቢቀርም  ታናሹ ግን ክፉኛ አመረረ፡፡ አባቱን ማናገር ሆነ በአንድ ክፍል ውስጥ አብሮ መገኘት ሳይፈልግ ቀረ፡፡ በዚህም ንጉሱ መጀመሪያ ከቤተመንግስቱ ልጁን አባረረ፤ ቀጥሎ ማንም ሰው እንዳያስጠጋው ከለከለ፡፡ የንጉስ ልጅ በየታዛው ስር እና በየሜዳው ይተኛ ጀመር፡፡ የልጁን አለመበገር ያየው ንጉስ ቅጣቱን አጠበቀ፤ “ከልጁ ጋር ሲያወራ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ለአፖሎ የሚከፍል ይሆናል” አለ፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ ልጁ ጠወለገ፡፡ ሊሞት ደረሰ፡፡ በአራተኛው ቀን ግድም አባት ልጁን አገኘው፡፡ በአየው ነገር እጅግ አድርጎ አዘነ፡፡
“ልጄ ሆይ የትኛው ይሻላል? አሁን ያለህበት የጉስቁልና ሁናቴ ወይስ ለእኔ ለአባትህ በመታዘዝ ብቻ እኔ የምደሰትበትን ሀብትና ሥልጣን የመውረስ ተስፋ ይሻልሃል?” ሲል ጠየቀው።
ልጁ አንዲት መልስ ብቻ ሰጠው፡፡
“ከእኔ ጋር በመነጋገርህ ለአፖሎ የሚከፈል መቀጫ እንዳለብህ እንዳትዘነጋ”
“ንጉስ ፔሪያንደር፣ የልጁ ስቃይ የሚያስፈራና መድሃኒት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ፣ ከፊቱ እንዲለይለት ብቻ በመርከብ ጭኖ የግዛቱ ክፍል ወደ ሆነው ወደ ኮርሲራ ሰደደው” ይለናል ሔሮዶቱስ፡፡
ያልታደለ ልጅ፤ በአባቱ ግዛቶች ሁሉ ተፈፃሚ የሚሆነው የአባቱ አዋጅ ሰለባው ላያደርገው ይተወዋል? በአራት ቀን እንዲያ የተጎሳቆለ አርባ ቀን ሲሞላው ምን ያደርገው ይሆን? እዚህ ላይ የካርል ማርክስን አባባል ደግመን እንጥቀስና እንለፍ…
`Man’s most precious treasure, his-greatest Wealth, is man himself”
(“የሰው ጌጡ እራሱ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሀብቱ!”)
አፄ ቴዎድሮስ ማንም ያልመለሰው አንድ ጥያቄ ለሊቃውንቱ አቀረቡ አሉ፡፡ “ከሁሉ በላይ የሚያስደስት ጥቀሱ” ተዘረዘረ፡፡ ከልባቸው አልደረሰም፡፡ በኋላ እራሳቸው መለሱ፡፡ “የማያውቁት ሀገር ሄደው የሚያውቁት ሰው ማግኘት” ግሩም ነው፤ ይሄን ስንቅ አድርገን እንቀጥል፡፡  ታላቁ ፈላስፋ ባሩች ስፒኖዛ (1632-1677) የሞተው የሰው ዕጦት አንገላቶት ነው፡፡
በዘመኑ ከመገለልና ከመወገዝ የከፋ ስቃይ አልነበረምና፣ ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬዴሪክ ኒች የስፒኖዛን ህይወት በመስቀል መሰለው። “በመስቀል ላይ የሞተው የመጨረሻው ክርስቲያን” ሲል ጠራው፡፡ በእርግጥ ቃላቸውን አንድ አድርገው በአደሙ ሰዎች መካከል መኖር የመስቀል ላይ ሞት ነው፡፡
ስፒኖዛ በገዛ ዘመዶቹ በአይሁድ ሲወገዝና ሲታደምበት ገና የ24 ዓመት ለግላጋ ነበር። በ1656 ዓ.ም የስፒኖዛ ጓደኞች ወደ አይሁድ ቤተመቅደስ አስተዳዳሪ አንድ ወሬ ይዘው ቀረቡ፡፡ ወሬው አስደንጋጭ ነበር፡፡ ስፒኖዛ በአይሁድ አምላክ ላይ ከአስተምህሮ ውጭ ተናግሯል የሚል ነው፡፡ አስጠሩት። አስተዳዳሪው የገመቱት የወጣቶቹ የሀሳብ ንትርክ እንደሆነ አድርገው ነበር፡፡ ስፒኖዛን ያውቁታል፡፡ ለአይሁድ ማኅበረሰብ መጠናከር ተስፋ የተጣለበት ነው፡፡ እናም ጠየቁት፡-
“ቁስ የእግዚአብሄር አካል ሳይሆን አይቀርም ትላለህ አሉ፡፡ መላዕክታትን የቁም ቅዥት የወለዳቸው ናቸው፤ ነፍስ ከዘፈቀደ ህይወት የማታልፍ ነገር ነች ብለሃል አሉ፤ ብሉይ ኪዳንም ስለዘላለማዊለነት ያወሳበት ስፍራ የለም ትላለህ አሉ…”
ስፒኖዛ አልካደም…
… ጉዳዩ ስር እየሰደደ ተካረረ፡፡ የቤተመቅደሱ የበላይ ኃላፊዎች ተሰብስበው ስፒኖዛ ወደ ቀደም የይሁድ አስተሳሰብ ለመመለስ ተጣጣሩ። አልሆነም፤ ደለሉ፣ አልሆነም። ስለዚህ በዚያው አመት ላይ ስፒኖዛን አውግዘው፣ የአይሁድ ማኅበረሰብ ከዚህ ሰው ጋር ትብብር እንዳይኖረው አወጁ፡፡ ባለ ስድስት ነጥብ የማግለል ብይን ተላለፈ፡፡ ማንም አይሁድ ከስፒኖዛ ጋር እንዳይነጋገር፣ የጻፈውን እንዳያነብ፣ የሚናገረውን እንዳያዳምጥ፣ ከተወሰነ እርቀት በላይ እንዳይቀርብ፣ አንድ ጣሪያ ሥር እንዳይገኝ፣ ማንኛውም አገልግሎት እንዳይሰጥ…
የስፒኖዛ ህይወት ከበደች፤ የገዛ አባቱ እንዳያናግራቸው በጣታቸው የአጥሩን ውጭ አሳዩት፡፡ እህቱ፣ አብሮ አደግ ጓደኞቹ ሁሉም አደመ፡፡ አድማው ህይቱ አመሰቃቀለው፡፡ ይሁን እንጂ ከቅጣቱ አልራቀም፤ አላፈገፈገም። ከሀይድልበርግ ዩኒቨርስቲ የቀረበለትን የፍልስፍና መምህርነት ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ፡፡ የተለያዩ ግለሰቦች አመታዊ ድርጎ ሊቆርጡለት ቢጥሩም አልፈልግም ሲል ውድቅ አድርጓል። እስከ ህይወቱ ፍፃሜ በብቸኝነትና ልጅ ሆኖ ከአይሁድ ማህበረሰብ በተማረው በመነጽር ስራ ተዳድሯል፡፡
ስፒኖዛ ሕዝብ ከሚወድቅበት ግንድ ቢጫንበት አልተሻለም ነበር ትላላችሁ? በስንት ጣዕሙ?!
ስፒኖዛ የአይሁድን ማህበረሰብ ተፃርሯል በሚል የተወገዘበትን አስተሳሰብ አዳብሮ አንድ የፍልስፍና ዘርፍ አድርጎታል፡፡ ፍልስፍናው “ሁል አምላክነት” ወይም “pantheism” ይሰኛል። እግዚአብሔር ሰዋዊ በሆነ ስልት የመቅረቡን ጉዳይ በፅኑ በመቃወም፣ “እግዚአብሄር ከተፈጥሮ ጋር አንድ ነው” የሚል ፍልስፍና ነው-ሁል አምላክነት፡፡ ስፒኖዛ “ተፈጥሮና ህግጋቷ በእግዚአብሄር ኪነጥበብ ተፈጠረ” የሚለውን አመለካከት ፈፅሞ በመካድ “የእግዚአብሄር ከተፈጥሮ ደንብ ውጭ መሆን ስልጣኑን የሚያሳንስና ሁለንተናዊነቱን የሚገስ እምነት ነው፡፡” በማለት ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል፡፡
ስለ ስፒኖዛ ሌላ ጊዜ በሰፊው፤ አሁን በጠባብ ወዳነሳነው ሰውን ስለመቸገር …. ሰውን ስለመደህየት….ሰውን ስለመራቆት…. እናምሰልስል፡፡ አይሻልም?



የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 730 times Last modified on Monday, 01 April 2024 20:15