Tuesday, 02 April 2024 20:42

ዛሬን ለማድመቅ---ትናንትን እስከ መፋቅ!

Written by  ባዩልኝ አያሌው-
Rate this item
(1 Vote)

                  
           ከዓለም የመንግሥታት ታሪክ እንደምንታዘበው አዲሱ መንግሥት ከቀዳሚው የበለጠ “ሆኖ” ለመቅረብ የሚያደርገው ትግል አሐዱ ብሎ የሚጀምረው፣ ቀዳሚውን ያስታውሳል ቢሉ ይዘክራል የሚላቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶችን ገለል በማድረግ ነው፡፡ ዋል አደር ሲልም ትርክቶቹንም ቢችል በመቀየር፣ ካልቻለም በመቀየጥ እኔን ያሳንሱኛል፤ ደግሞስ “ከእኔ ወዲያ ላሳር” በሚል መመካት ብዙ ይደክማል፡፡ ይህ ምን ቢደክሙበት የደከሙለትን ያህል ሰምሮ ያልታየው ትጋት (ጥፋትም ቢሉ ይሰዳል)፣ የማህበረሰብን ትውስታና ትዝታዎችን በማደፍረስ፣ በህልውናው አልፎም በቀጣይ እሱነቶቹ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ያህላል የሚሉት አይደለም፡፡ “… Without memory, there is no society, and without memory, there would be no civilization of any kind.” እንዲል Elie Wiesel፡፡
በዚህ ጽሑፍ፣ መንግሥትነትን በጨበጡ ማግስት የቀዳሚውን መንግሥትና መሪዎች አሻራዎች ለማጥፋት በምትኩም የራሳቸውን ለመትከልና አዲስ ያሉትን ታሪክ ለመጻፍ እንቅልፍ አጥተው የተጉ የዓለማችንን አንዳንድ መንግሥታትና መንገዳቸውን እናነሳለን፡፡ ድካማቸውስ ይዞላቸው ይሆን? የሚለውንም እንጠይቃለን፡፡
የታሪክ ጸሐፊያን እንደሚገልጹት፣ እነዚህ ያለፈውን መንግሥት (አንዳንዴም ዘመን) ታሪክ በመፋቅ የራሳቸውን መጻፍን ግብ ያደረጉት መንግሥታት ለዓላማቸው ማስፈጸሚያነት በዋናነት የሚቆጣጠሩት የትምህርት ሥርዓቶችን፣ ሚዲያዎችን ሲሆን፤ የመጨረሻ ግባቸውም የማህበረሰቡን ስነልቡና ቀርጸውታል የሚሏቸውን ታሪኮችና ትርክቶች መተካት ነው፡፡ በዚህም ያለፉትን መሪዎችና መንግሥታቸውን ስኬቶች በማሳነስ ወይም አሉታዊ በማድረግ የራሳቸውን ሌጋሲ ለማጉላት ይሰራሉ፡፡ ወጋችን እንዲጨበጥ አንዳንዶቹን እናንሳ፡፡ በሶቪየት ሕብረት እንጀምር፡፡
በለስ ቀንቶት የሶቪየት ሕብረትን በትረ መንግስት የተቆጣጠረው Joseph Stalin የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ ቀዳሚውን መንግሥትና መሪዎቹን ያስታውሳሉ ባላቸው መዘክሮች ሁሉ ላይ የፈጸመው ውድመት ተወዳዳሪ ያለው አይመስልም፡፡ Stalin ብቸኛና ጠንካራ የሶቪየት መሪ ሆኖ ለመታየትና ትርክቱን ለመቀየር በሀገሪቱ በነበሩ ሐውልቶች፣ ህንጻዎች እና የሥርዓቱ መታሰቢያ ናቸው ባላቸው ሁሉ ላይ አረመኔያዊ በትሩን አውርዶባቸዋል፡፡ የታሪክ መዛግብት ሳይቀሩ አላሳሱትም፤ ከትበው ያቋዩዋቸውን ሁነቶች ፍቀው እንዲቀይሩ ጥሯል፡፡ የStalin በትር ቤተመቅደሶችንና ቤተእምነቶችንም አላፈረም- እምነት የለሽ ለመሆኑ ምስክር ይሆኑት ዘንድ አውድሟቸዋል፡፡ Stalin ሌላም አስቂኝም አስገራሚም ተግባር ፈጽሟል፡፡ የቀድሞ ጓደኛውና የኋላ ዘመን ተቀናቃኙ ከነበረው ከLeon Trotsky ጋር በጋራ ከተነሱት ፎቶግራፍ ላይ የTrotskyን ምስል እንዲፋቅ አድርጓል፡፡  
ወደሩቅ ምስራቃዊቷ ሀገር ቻይና እንሻገር። በMao Zedong መሪነት የተቀሰቀሰውና ለስልጣን የበቃው የባህል አብዮት (Cultural Revolution) ካለፈው አገዛዝና ሥርዓት የጸዳች ቻይናን በመገንባት አዲስ የኮሚኒስት ማህበረሰብ መፍጠር ብሎ በጠራው እንቅስቃሴ “feudalist” እና “capitalist” በመባል የሚታወቁትን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች አውድሟል። በዚህም የቀደመውን የቻይናን ባህልና ታሪክ ለማጥፋት ብዙ ደክሟል፡፡
በዚህ የቀደመውን መንግሥት መታወሻዎች ለማጥፋት በተደረገው ዘመቻም እንቅስቃሴ በርካታ ቤተመቅደሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች እና ባህላዊ የስነጥበብ ሥራዎች ወደቀደመ ማንነታቸው እንዳይመለሱ ሆነው ፈራርሰዋል፡፡ ይህ ቻይናን ታሪክ አልባ፣ ህዝቦቿንም ትውስታ አልባ ያደረገ ድርጊት አሮጌ አስተሳሰቦችን፣ ባህሎችን እና ልማዶችን የማጥፋት አዲስና ጠቃሚ መንገድ ተብሎ በMao መንግስትና በደጋፊዎቹ ይሞካሽ ነበር፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያውያኑ የዘመን ቀመር በ1789 በተካሄደው ህዝባዊ አብዮት በፈረንሳይ ስልጣን የያዘው መንግሥትም፣ ለቀዳሚው መንግሥት መታወሻ አሻራዎችና ታሪካዊ ቅርሶች ርህራሄ አልነበረውም፡፡ አዲሱ መንግሥት አሮጌውን አገዛዝ በአዲስ የነጻነት፣ የእኩልነት እና የወንድማማችነት ዘመን መተካት በሚል በጠራው እንቅስቃሴ፤ ከስልጣን የተወገደው ንጉሳዊ አገዛዝ ቁሳዊ መታወሻዎችን ኢላማ አድርጓል፡፡ በዚህም በርካታ ሐውልቶች ተሰባብረው ከቆሙበት ተነቅለዋል፡፡ ህንጻዎች ተንደዋል፡፡ መቃብሮችም ሳይቀር እንደ እርኩስ ተቆጥረው ፈርሰዋል፡፡ በፈረሱበት ቦታም አዲሱ መንግስት እኔን ይገልጻሉ ያላቸውን ነገሮች አቁሟል፡፡ አደባባዮችን እና መንገዶችን በስሙ ሰይሟል፡፡ መነሻው እኔ ከሁሉም እበልጣለሁ የሚል ከንቱ እምነት ነውና!
እንደ ጎርጎሮሲያውያኑ አቆጣጠር በ1996 በአፍጋኒስታን ስልጣን የጨበጠው ታሊባን፣ በአፍጋኒስታን ታሪካዊ አሻራዎችና ቋሚ የታሪክ ምስክሮች ላይ ያደረሰው ጥፋት የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ የታሊባን ቡድን አራምደዋለሁ ካለው ርዕዮተዓለም ይቃረናሉ ያላቸውን ታሪካዊ ቅርሶችና መታሰቢያዎች ማውደም የጀመረው ገና ከተማዋን እንኳን በቅጡ ተቆጣጥሮ ሳይጨርስ ነው፡፡ ንጹህ እስላማዊ መንግስት መመስረት በሚል ቅድመ እስልምና የነበሩ ቅርሶችን አፈረሰ፡፡ ድርጊቱ ፍጹም ያመነታ አልነበረም፤ በ5ኛው እና በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታነጹ እጅግ ጥንታዊ የባሚያን መታሰቢያ ቅርጾችም በዚህ እንቅስቃሴ ወደሙ፡፡ የራስን ታሪክ ብቻ ለመጻፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ልጓም የለውምና ጥፋቱ ከዚህም ያይላል፡፡
ዓለም ላይ በሯን የዘጋችው፣ ዓለምም የተዋት የምትመስለው ሰሜን ኮሪያም የዚህ ዓይነቱ መዳፍ ጨክኖባታል፡፡ የKimን ስርወ መንግስት (Kim dynasty) በመትከል ፍላጎት የታወረው የKim መንግስት፤ የቀደመው መንግሥት በስህተት እንኳን እንዳይታወስ ለማድረግ ብዙ ድንጋይ ፈንቅሏል፡፡ ቀዳሚዎቹን ሥርዓቶች፣ መተዳደሪያዎችን እና ሥሪቶችን ሁሉ በማጥፋት የKim ቤተሰብን እንከን የለሽነትና የምንጊዜም የሰሜን ኮሪያ መሪ አድርጎ ለመሳል ደክሟል። ለዚህም በዋና መሳሪያነት የተጠቀመው የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት እና ሚዲያዎችን ነው፡፡
በዘመን የራቁትን አነሳን እንጂ በዘመናችንም በርካታ መንግሥታት ያለፉትን መንግሥታትና መሪዎች አሳንሶ በመሳል፣ ራሳቸውን ትልቅ አድርጎ ለማሳየት በሚያደርጉት አላስፈላጊ ከንቱ ድካም በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን፣ የማህበረሰብን ትዝታና ትውስታዎችን ያወድማሉ፡፡ አላስፈላጊና ከንቱ ድካም ማለቴ ራሳቸውን እያወዳደሩ ያሉት፣ አሁን በሥራ ላይ ከሌለና ፍጹም የመስራት እድል ከሌለው ላይመለስ ካለፈ መንግስት ጋር በመሆኑ ነው፡፡
እዚህ ያልጠቀስናቸውን መንግሥታትና መሪዎቻቸውን ማስታወሱን ለአንባቢያን ትተን፣ ለመሆኑ እነዚህ መንግስታት ድካማቸው ያዘላቸው ይሆን የሚለውን ጥያቄ እናንሳ። የጥያቄው አጭር መልስ በፍጹም የሚለው ነው። የተሳካላቸው ቅርሶችን እና መታወሻዎችን ማውደሙ እንጂ፣ የራሳቸውን ታሪክ መጻፉና የማህበረሰቡን ስነልቡና የመቀየር ዓላማቸው ተሳክቶ አልታየም፡፡
ለምሳሌ ቀደምሲል ያነሳነው የፈረንሣይ አብዮታዊ መንግስት፣ የንጉሣዊው ሥርዓት መታወሻዎች ናቸው ያላቸውን መዘክሮች ማፈራረስ ቢችልም፣ ዓላማው የነበረውን የራሱን እሳቤዎችና ታሪካዊ አተያዮች ለመትከል ያደረገው ጥረት አልያዘለትም፡፡ በዚህ ሁሉ ትርምስ ውስጥ ያለፈችው የዛሬዋ ፈረንሳይ፣ ቅድመ አብዮትና ድህረ-አብዮት የሆነውን የምታስታውሰው እኩል የታሪኳ አካል አድርጋ ነው፡፡
የቻይናው የMao Zedong የባህል አብዮትም የድካሙን ፍሬ አልሰበሰበም፡፡ ከጅምሩም ቅርስን ሁሉ እግር በእግር ተከትሎ ማጥፋት የማይቻል በመሆኑ፣ በርካታ ቅርሶች በመደበቅም፣ ባለመታወቅም ተርፈዋል፡፡ ነጥባችን ግን እሱ አይደለም፡፡ የMao መንግስት ድካም ያሰበውን አሳክቷል የሚባል አይደለም። ቆይቶም የጠፉትን ቅርሶች መልሶ ለመተካት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ የዛሬዋ ቻይና የባህላዊ አብዮት ትሩፋቶችን እና ያለፈውን ታሪክና ቅርሶች መንከባከብን እና መጠበቅን አተኩራ ትታገልለታለች፡፡ በሶቪየት ሕብረትም መልኩ እንጂ እውነታው ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ በStalin ውድመት በተአምር የተረፉትን ቅርሶች ለመጠበቅ እና የፈራረሱትን ቤተመቅደሶች እንደገና ለመገንባት ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
ያም ሆኖ ለምን አልተሳካላቸውም ብሎ መጠየቅ ጽሑፋችንን ደርዝ ይሰጠዋልና፣ ይህንኑ አውስተን እንቋጭ፡፡ የራሳቸውን መታወሻዎች ለማቆምና ታሪካቸውን ለመጻፍ ስልታቸው የቀዳሚውን መንግስትና መሪዎች ትውስታዎችን ማጥፋት ያደረጉ መሪዎች ዓላማቸው ላለመሳካቱ ተመራማሪዎች በዋናነት ሁለት ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡
በቀዳሚነት የሚጠቅሱት ምክንያት እነዚህ መሪዎች የሚያካሂዱት ቅርሶችን እና መታወሻዎችን የማጥፋት ተግባር የተሟላ አለመሆኑን ነው፡፡ ቀደም ብለን እንዳልነው፣ ታሪካዊ ቅርሶችን በሉት ባህላዊ መታወሻዎችን እያንዳንዳቸውን ፈለጋቸውን ተከትሎ ማጥፋት የሚቻል አይደለም፡፡ ሐውልቶቹን ከቆሙበት ቦታ ላይ ማንሳት ወይም ማግለል ቢቻልም፣ ስለእነሱ በታሪክ መዝገቦች የተከተቡትን ግን መፋቅ አዳጋች ነው፡፡ እንደውም በተቃራኒው በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች የታሪክ መዛግብት የበለጠ ሊጠናከሩና ሊበለጽጉ ይችላሉ፡፡ ምሁራን እና የታሪክ ተመራማሪዎች እነዚህን በመቅረስና በመሰነድ ረገድ በዚህ ወቅት የበለጠ ሊነቃቁ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የአርኪዎሎጂ መረጃዎች፣ ታሪኮች እና አፈታሪኮችም በታሪካዊ ሁነቶች የበለጸጉ ሌሎች ሊጠፉ የማይችሉ የነገ ምስክሮች ናቸው፡፡
ከእነዚሁ ሁሉ በላይ የመንግሥታቱን ድካም እንዳይሰምር የሚያደርገው ግን፣ መታሰቢያዎችን እና ቅርሶችን በማጥፋት ብቻ፣ ስለእነሱ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን ትውስታ እና ታሪክ ማጥፋት ወይም መቀየር አለመቻሉ ነው፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ መዝገቡ ልቡ ነውና፡፡
ሁለተኛ ምክንያት አድርገው ተመራማሪዎቹ የሚገልጹት ደግሞ የበለጠ አስገራሚ ነው። ይኸውም ትውስታዎችን የማጥፋት ተግባር ውጤቱ ፍጹም ከተፈለገው በተቃራኒው መሆኑ ነው፡፡ ሰዎች እንዲወገድ ስለተደረገው መታሰቢያ ወይም በታሪክ ውስጥ የነበረው ድርሻ እንዲሰረዝ ስለተደረገው መሪና መንግስት የበለጠ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል- “የተከለከለ ፍሬ” እንዲሉ።
የባህል ቅርሶች እና ታሪካዊ ቦታዎች መውደም የዛ ሀገርና የማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሁሉ ኪሳራ ነው። በመሆኑም መሪዎችና መንግሥታቸው በዚህ ዓይነት ውድመት ላይ ሲሰማሩ ሀገራቸውንና ዓለምን ታሪክ አልባ፣ ህዝባቸውንም ትውስታና ትዝታ አልባ ያደርጋሉ፡፡ ታዲያ ነገሩን የበለጠ አሳዛኝም አስገራሚም የሚያደርገው፣ ተግባራቸው የአጭር ጊዜ የፕሮፓጋንዳና የተለየ ምስል በመፍጠር ውጤታማ ቢመስልም፣ የተነሱበትን የራሳቸውን ታሪክ የመጻፍና ትርክት የመቀየር ዓላማ የማያሳካ መሆኑ ነው፡፡ ያም ሆኖ ከዓለም ታሪክ ያልተማሩት የዓለማችን “ከእኔ ወዲያ…” ባይ መሪዎች፤ ከትናንት እስከ ነገ እዚሁ ላይ ተጠመደው ይስተውላሉ፡፡ እንዳለመታደል!
ቸር እንሰንብት!
***
ከአዘጋጁ፡- ባዩልኝ አያሌው በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነጽሑፍ መምህር ሲሆኑ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የኪነጥበብ መድረኮች ላይ በሚያቀርቧቸው ግጥሞችና አዲስ አድማስን ጨምሮ በሌሎች የሕትመት ውጤቶች ባስነበቧቸው ሥነጽሑፋዊ ሂሶቻቸው ይታወቃሉ፡፡

Read 335 times