Thursday, 04 April 2024 07:07

"ክቡር ልጆች" መጽሐፍ የፊታችን እሁድ ይመረቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)
“አንዲት እናት ልጆቿን ብቻዋን ታሳድጋለች፡፡ የአስተዳደግ ዘይቤዋ ከሌሎች ወላጆች ለየት ይላል፡፡ ልጆቿ ከሰፈር ልጆች ጋር ተቀላቅለው ሲጫወቱ አይቼ አላውቅምና ሁሌም ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበር፡፡ ልጆችሽ ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ሲጫወቱ አይቼ አላውቅም አልኳት፡፡
“በልጅነቴ ብቸኛ ወንድሜን ያጣሁት ሰፈር ውስጥ በተወረወረ ድንጋይ ነው” ወዲያውም ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡
“በጣም አዝናለሁ፤ መጠየቅ አልነበረብኝም” አልኳት፡፡
“እነዚህን ብርቅዬ ልጆች እንደ ወንድሜ ማጣት አልፈልግም፡፡ ውጭ እንደ ሌሎች ልጆች ቢጫወቱ ይሞቱብኛል ብዬ እፈራለሁ፡፡” አለችኝ::
ህክምና ያላገኘ የልጅነት ጠባሳ ጊዜ ጠብቆ በትዳር ህይወትም ይገለጣ:ል፡፡”
**
በደራሲ ብርሃኑ በላቸው አሰፋ የተዘጋጀው “ክቡር ልጆች፣ የልጆች ስነ ልቦና ለመገንባት እና የስሜት ስብራት ለመጠገን የሚረዱ ቁልፍ መንገዶች ” የተሰኘው መጽሐፍ፤ የፊታችን እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ሳር ቤት በሚገኘው በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን እንደሚመረቅ ደራሲው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ (ለመግቢያ የተጠቀምንበት ጽሁፍም ከመጽሐፉ የተቀነጨበ ነው፡፡)
መጽሐፉ፤ በልጆች ስነ ልቦና ላይ ጥናትን መሰረት ያደረገና ሀገራዊ ለዛ ያለው እውነተኛ ታሪኮችን የሚያስቃኝ ሲሆን፤ በተለያየ ተግዳሮት ውስጥ ለሚገኙ ልጆች የመፍትሄ ሃሳብ ይዞ መቅረቡም ተጠቁሟል፡፡ በዋናነትም ልጆች የሚስተዋልባቸውን የስነ ልቦና ጫና እና የስሜት ስብራት የሚተነትን ሲሆን፤ በጥናት ላይ የተደገፈ የመፍትሄ ሃሳብን በተጨባጭ እንደሚያመላክትም ተነግሯል፡፡
“ክቡር ልጆች“ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ተዘጋጅቶ የተቀረበ ሲሆን፤ በዋናነትም ለትዳር ለሚዘጋጁ፣ ለወላጆች፣ ለመምህራን፣ እንዲሁም በልጆች ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎችና ለሌሎችም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ደራሲው በሆሊስቲክ ቻይልድ ዴቨሎፕመንት ሁለተኛ ዲግሪ ፣ በሶሽዮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪና በስነፅሑፍና ቋንቋ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሲሆን፤ ከልጆችና ወጣቶች እድገት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በተጋባዥ እንግድነት እየቀረበ ሙያዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡
 
Read 299 times