Saturday, 06 April 2024 19:53

የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የገባውን ውዝግብ ቀጥሎበታል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት፣ በፑንትላንድ ዋና ከተማ ጋሮዌ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ እንዲዘጋ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ እንደማትቀበል ፑንትላንድ አስታወቀች።
የሶማሊያ  መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባ ነው በሚል በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደር አገሪቱን ለቀው እንዲወጡና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድና ነጻነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ ያሉት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ማዘዙን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡  
ከጎረቤት አገር ኢትዮጵያ፣ ነጻ አገር ነኝ ከምትለው ሶማሊላንድና በከፊል ራስ ገዝ ከሆነችው ፑንትላንድ ጋር ፖለቲካዊ እሰጣ ገባው ውስጥ የገባው የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሦስቱን መንግሥታት የተመለከተ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። የፑንትላንድ አስተዳዳር ትላንት ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ ቆንስላው እንዲዘጋ የተላለፈው ትዕዛዝ፣ የሶማሊያን ሕገ-መንግሥት የሚጥስ ነው በማለት ተግባራዊ እንደማይደረግ አስታውቋል።
የፕሬዚዳንት  ሐሰን ሼክ ሙሐመድ አስተዳደር የኢትዮጵያው አምባሳደር ሙክታር ከድር ዋሬ፣ በ72 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ከማስተላለፉ በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ በሐርጌሳና ጋሮዌ ያላት ቆንስላዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲዘጉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ የሶማሊላንድና ፑንትላንድ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ መሪዎች የፌደራል መንግሥቱ ውሳኔን እንደማይቀበሉ ተናግረው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሩን “ለአጠቃላይ ምክክር” ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
የሶማሊያ መንግሥት በመግለጫው፤ ኢትዮጵያ “በሶማሊያ ሉዓላዊነትና የውስጥ ጉዳይ” ጣልቃ ገብታለች ሲል ከሷል። ኢትዮጵያ ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት መፈረሟ ሞቃዲሾን ያስቆጣ ሲሆን፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኑነትም አጠልሽቶት ቆይቷል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት ያደረገውን የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ በመቃወም ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ለፌደራል መንግሥቱ እውቅና መስጠት አቁሚያለሁ ብላለች።
ይህ የፑንትላንድ ውሳኔ በሶማሊያ ፖለቲካ ውጥረት ፈጥሮ ባለበት ወቅት የፑንትላንድ የገንዘብ ሚኒስትር ባለፈወው  ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጉብኝት አዲስ አበባ ገብተው ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጋር መወያየታቸው ሶማሊያን አስቆጥቷል፡፡
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አሁን የኢትዮጵያን ዲፕሎማት ለማባረርና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቿ እንዲዘጉ ከውሳኔ ላይ የደረሰው የገንዘብ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
የፑንትላንድ አስተዳደር መንግሥት ትላንት ዓርብ  ባወጣው መግለጫ፤ የሶማሊያን ውሳኔ እንደሚቃወም ገልጾ፤ ፑንትላንድ የውጭ ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ከማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥት እውቅና ውጪ በቀጥታ በራሷ አማካይነት ግንኙነቶችን እንደምታደርግም ጨምራ ገልጻለች።

Read 1086 times