Saturday, 06 April 2024 19:57

ነጭ ባህር ዛፍ ላይ ቀይ ባህር ዛፍ አይበቅልም

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 (በጓድዬ ብሽዬ ኤረማ) የቤተ-ጉራጌ ምሳሌያዊ አነጋገር


         አንድ በጣም ባለፀጋ የሆኑ የተከበሩ ባላባት በአንድ መንደር ይኖራሉ፡፡ ጌታዬ ጌታዬ የማይላቸው የለም፡፡ እኝህ የተከበሩ ባላባት አንድ ብርቄ የሚባል ነባር አሽከር ነበራቸው፡፡ ብርቄ አሽከርነት ያምርበታል፡፡ ሲልኩት ወዴት፣ ሲጠሩት አቤት ለማለት ይችልበታል፡፡ ዘወትር ግብር ገብቶ፣ ድግሱ ተበልቶ ጌትዬውን ብርቄ እጅ ሲያስታጥብ፤
“ሰማህ ወይ ብርቄ” ይሉታል፡፡
“አቤት ጌታዬ” ይላል ብርቄ፡፡
“አሁን እኔ ብሞት ምን ታደርግ ይመስልሀል?”
“ጌታዬ፤ እርሶ ከዚህቺ አለም ተለይተው እኔ ከዚህ ቤት አልቀመጥም”
“ታዲያ ምን ትሆናለህ?”
“እመንናለሁ፡፡ አለም በቃኝ እላለሁ፡፡ ጀርባዬን ለአለም ፊቴን ለገዳም እሰጣለሁ”
“ተው፤ አታረገውም ብርቄ?”
“በጭራሽ፡፡ እርሶ ሞተው እኔ እዚህች ቤት አንዲት ቀን እህል ውሃ አልቀምስም!”
“መልካም፡፡ ለዚህ ታማኝነትህ አንድ ኩታ ተሸልመሃል!” ብርቄ እጅ ነስቶ ኩታወን አገኘ፡፡
ሌላም ቀን፤ “ብርቄ እኔ ብሞት ምን ታደርጋለህ?” ይሉታል፡፡
“ምን ያጠያይቃል ጌታዬ? መመነን ነዋ! ከእርሶ ወዲያ አለም ለምኔ” ይላል፡፡
”ብርሌ ጠጅ ስጡት ይባላል!”
ሌላ ቀን፡፡ “ብርቄ እኔ ብሞት ምን ታደርጋለህ”
“እለቱን፤ እኔን ጨርቄን ሳልል፣ ወደ ገዳም ነዋ ጌታዬ!”
“እውነት ታደርገዋለህ፤ ብርቄ?”
“አይጠራጠሩ ጌታዬ! ምን ቀረኝ ብዬ እዚህ ቤት እቀመጣለሁ?”
“እኔ ምልህ ብርቄ?”
“አቤት ጌታዬ?”
“እንደው ለነገሩ፤ ከኔ ቀድመህ መሞት ታስቦህ ያውቃል? አንዳንዴ ለምን እኔ ቀድሜዎት ልሙት እንኳ አትለኝም?”
ብርቄም ትንሽ አሰብ አድርጎ፤
“አይ ጌታዬ ሳላስበው ቀርቼ መስሎት? አስቤዋለሁ፡፡ ግን ከተናገርኩ የጌታዬን የተሻማሁ እንዳይመስልብኝ ብዬ ነው፡፡”
ሌላ ቀን፡፡ ብርቄን ጠርተው ደግመው በጨዋታ መሃል፤
“ከእኔ ቀድመህ የምትሞት አይመስልህም?”
“ኸረ በጭራሽ ጌታዬ?”
“ለምን?”
“እኔ ከሞትኩ ማን እንደኔ ያለቅስሎታል! ኸረ በጭራሽ እግዜር እንደዚህ ያለ ነገር አያድርስብን!! እርሶ ከሞቱ ግን እዚህች ቤት አንዲት ጀንበር አላድርም- ወደ ገዳም ነው!”
“ይህን ያህል ትወደኛለሃ?”
“እንዴት ይጠራጠራሉ?”
ከባድ ጉርሻ ያጎርሱትና “ጠጅ ስጡት!” ብለው ያዙለታል፡፡
ጌትየው እንዳሉት እሳቸው ቀድመውት ሞቱ፡፡  ከሚስታቸው አንድ ትንሽ ወንድ ልጅ ብቻ ነው ያላቸው፡፡ ሚስታቸው 6 ወር ሃዘኑንም መንፈቃቸው ከወጡ በኋላ ሌላ ባል አገቡ፡፡ ብርቄም ያዲሱ ጌታ አሽከር ሆኑ፡፡ “እርሶ ከሞቱ እመንናለሁ!” ማለቱን ቀጠለ፡፡
አንድ ቀን አዲሱ ጌታው ግብር አግብቶ፣ ሰው በድንኳን ግጥም ብሎ እየተበላ፣ እየተጠጣ ብርቄ እንደልማዱ ተፍ ተፍ እያለ እያስተናገደ ሳለ፤ አንድ አዝማሪ ተነስቶ መሰንቆውን እየገዘገዘ ጨዋታ ጀመረ፡፡
ድምፁን አዝልጎ “ትላንትና ማታ ጌታዬን አግኝቼ” አለና ጀመረ፡፡ ህዝቡ በከፊል፤ አዝማሪውም የሞቱትን ጌታ በማንሳቱ “ምን ሊል ይሆን?” በሚል አይነት ፀጥ አለ፡፡ አዝማሪው፤ ደገመና
“ትላንትና ማታ ጌታዬን አግኝቼ” አለ፡፡
አሁን ሰው ሙሉ በሙሉ ጸጥ እርጭ  አለ፡፡ ምን ሊል ነው በሚል መንፈስ፡፡ አዝማሪውም
“ትላንትና ማታ ጌታዬን አግኝቼ
… ሚስቴስ ደና ናት ወይ? (ወደ ሚስትየው እያየ)
… ልጄስ አደገ ወይ? (ወደ ልጅየው እያየ)
… ብርቄስ መ…መ…ነ ወይ!?” (ወደ ብርቄ ቀና ብሎ) ብለው ቢጠይቁኝ፣
ሚስቶት ደና ናቸው፤ ልጆትም አድጓል፡፡
(ቆም አድርጎ ወደ ብርቄ እያየና እያንዳንዱን ቃል እየረገጠ)
…ብ…ር…ቄ….ም አ…ል…መ…ነ…ነ…ም!! ብዬ ብነግራቸው፤
አይጉድ! አይጉድ! አይጉድ! ያሉበት፤ እረገፈ ጣታቸው!!”
ሲል ገጠም፡፡ ሰው ሁሉ ወደ ብርቄ ተመለከተ፡፡ ብርቄን የሰው አይን ከአገር አስወጣው፡፡
*   *   *
ለእምነታቸው የሚኖሩ፣ ማተማቸውን የማይበጥሱ፣ የተናገሩትን የማያፈርሱ፣ በምላሳቸው የማይኖሩ ብቻ ናቸው በህዝብ የሚታመኑት፡፡ ጌታቸውንና አለቃቸውን ለማስደሰት ወይም ለመሸንገል ሲሉ ብቻ “አቤት!” “ወዴት!” የሚሉ የየሥርአቱ አሸርጋጅ ይሆናሉ እንጂ፣ በየተደገሰበት ሁሉ ከበሮ መቺ ይሆናሉ እንጂ ለህሊናቸውና ለእምነታቸው አያድሩም፡፡ “ህዝቡን ልናገለግል” ፣ “አገርን ልናድን” “ምድር ሰማዩ ልናለማ”፣ “የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ልንለውጥ”፣ “ከተማ ልናሰፋ፣ የገጠሩን ህዝብ ልናሰለጥን፣” ወዘተ የሚል አይነት ቃል መግባትና “ይህ ካልሆነ ወንበሬን እለቃለሁ”፣ “ይህ ካልሆነ የጓዶች አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋኝ!”፣ “ይህ ካልሆነ ማናቸውንም ፍዳ ልቀበል!” ማለት የተለመደ ሆኗል፡፡ እንደ ብርቄ “እርሶ ከሞቱ በቃ፤ እመንናለሁ” ማለት፡፡ ከዚያም ምንም ለውጥ ሳይመጣ ሲቀር ለአዲሱ ጌታ ማደር፡፡ አይንን በጨው ታጥቦ “ዛሬም እንደ ትላንት በአላማ ፅናት ራእይን እውን ለማድረግ “እስከ መጨረሻ ድረስ የደም ጠብታ፣ እስከ መጨረሻ አንድ ሰው፤ እታገላለሁ” ሲሉ ቃለመሃላ ማዥጎድጎድ፡፡ ጌታዬ ከሞቱ እዚህች አገር አንዲትም ቀን አልውልም አላድርም ማለት!... ቃል መግባት … እቅድ ማቀድ… ፖሊሲ መንደፍ… በየወንዙ መማል… መማማል መመሪያ ማውጣት… አዋጅ ማወጅ… በየፌርማታው አበጀህ መባባል… መግለጫ ማውጣት… መፅሐፍ መግለጥ… ፕሮጀክት መቅረፅ… መርቆ መክፈት… መጨባበጥ “ከመቸውም በበለጠ በአዲስ መንፈስ ተነስተናል” ማለት… ትላንትን በላጲስ ማጥፋት… ነገን በእርሳስ መሳል… ተግባርና “አፈፃፀም” ግን የለም፡፡ ቃል ይፈርሳል፡፡ ቃል ይበላል፡፡ የሚወገዝ ይወገዛል፡፡ መካድ፡፡ መካካድ ይቀጥላል፡፡ የሚረገም ይረገማል፡፡ በድሮ ጊዜ ብሎ ጥሩምባ ነፊው “ካድሬያችን ኑና አራግሙን ብሏል!” እንደተባለው ነው፡፡ በትብብር፣ በደቦ፣ በብዙሃን ድምፅ መራገም እንጂ ከልብ የሚሆን ምንም ነገር የለም እንደማለት ነው፡፡ “ሲቸግር የእንጀራ እናቱን እምዬ ይልዋል” ነውና የትላንቶቹን ለመርገም የትላንት ወዲያውን መጥቀስና ማወደስ ይቀጥላል፡፡
አዲስ መፈክር ይቀመራል፡፡ በህብረት ያንን መፈክር ማስገር ይቀጥላል፡፡ በልብ መክዳት በአካል አለሁ ማለት ይዘወተራል፡፡ እስከ ሌላ መከዳዳት፣ እስከ ሌላ ቃል ማፍረስ “ልጅ እገሌ” ፣ “ጉድ እገሌ”፣ “ክቡር እምክቡራን” መባባል፡፡ ሆኖም “በጭለማ ማፍጠጥ ደንቆሮን መቆጣት ነው” እንደሚባለው ልብ ውስጥ እውነተኛ ፍቅር፣ እውነተኛ አገር መውደድ፣ እውነተኛ ለህዝብ የመቆም ስሜት፣ ሳይኖር አላማና እቅድን በስራ ላይ ማዋል ከቶም ዘበት ነገር ነው፡፡ መሪና መሪ፣ አለቃና አለቃ፣ ፓርቲና ፓርቲ፣ ባለስልጣንና ባለስልጣን፣ ዜጋና ዜጋ በመካከላቸው ልባዊ መተማነን ከሌለው ስራ አይሰራም፤ እቅድ አይፈፀምም፡፡ ፕሮግራም አይተገበርም፡፡ ቃል ህይወት አይሆንም፡፡ ይስሙላ፣ ለበጣ፣ የአደባባይ ማስመሰል፣ የሸንጎ ዲስኮ፣ የስብሰባ ንግግር ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡
የሀገራችን አንዱ አንኳር ችግር ከእቅድ ነዳፊው እስከ ፈፃሚው ድረስ ልባዊ መተማመን አለመኖር ነው፡፡ “ይህን ያለው ይህን ሊል ፈልጎ ነው” በሚል የግራ ትርጉም የታጠረው አስተሳሰብ ይበዛል፤ ቡድንና ቡድን አይተማመንም፡፡ መስመሩን ሳይሆን በመስመሮች መሃል ማንበብ (Between the lines እንዲሉ) ነው ፈሊጡ፡፡ በውስጡ የተቀበረው ፍላጎት (Hidden motive) ካለ ምንዛሬ ይበዛል፤ ቅጥያና ዘርፍ እያበዙ “ትርጉም የኔ”፣ “ስርዝ ያንተ”፣ “ቅንፍ የነሱ” ማለት ቋንቋ ይሆናል፡፡ አፋዊ የሆነ ያሸበረቀ ቃል ሲበዛ ተግባር ባዶውን ይቀራል፡፡ ዞሮ ዞሮ ወሳኙ ግን ልባችን ውስጥ ምን አለ የሚለው ነው፡፡ ልባችን ትግል እያሰበ አፋችን ድል ቢያወራ ዋጋ የለውም፡፡ ልባችን አትጠጉኝ እያለ አፋችን ስለ አፍሪካ ህብረት እና ጉባኤ ቢያወራ ነገር ሁሉ የይስሙላ ይሆናል፡፡ ልባችን ሹመት እያሰበ አፋችን የኢኮኖሚ ልማት ቢያወራ ነገ የሚጋለጥ ከንቱ ዲስኩር ይሆናል፡፡ ሁሉም የሚያስተጋባውና የሚተገብረው ጥንት የተሰራበትን ንጥረ-ነገር ነው፤ የውስጡን፡፡ የጠዋቱን፡፡
እውነተኛ ፍሬ ከእውነተኛ ተግባር፣ ከእውነተኛ እምነት ነው የሚገኘው፡፡ ያ ሳይኖር ፍሬ መጠበቅ ከንቱ ነው፡፡ ነጭ ባህር ዛፍ ላይ ቀይ ባህር ዛፍ አይበቅልም ማለትም ይኸው ነው፡፡


 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

 

Read 848 times