Saturday, 06 April 2024 20:51

ነገረ ዳግም ምጽአት!

Written by  ባዩልኝ አያሌው-
Rate this item
(1 Vote)

“ደብረ ዘይት” በጥሬ ትርጉሙ፣ የወይራ ዛፍ የበዛበት፣ በርክቶ የበቀለበት ተራራ ማለት ነው (ደብር- ተራራ፤ ዘይትም ወይራ ማለት ነውና- ደብረ ዘይት!)፡፡ ነገራችን እነሆ ነገ (በዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት) በዓለም በሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመናን ሁሉ ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት የሚከበረው፣ የሚዘከረውም የደብረ ዘይት በዓል ነው፡፡ መነሻችን የደብረ ዘይት ምንነት፣ መድረሻችንም በዓሉ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና በአማንያኑ ዘንድ ያለውን ቦታ ቢሉ መንፈሳዊ በዓልነት ማውሳት ነው፡፡ ለዚህም ከቅዱሳት መጻሕፍትም፣ ከሊቃውንትም (ከመጣፍም ከሊቅ አፍም እንዲሉ) እንጠቅሳለን፡፡ ነገረ ዳግም ምጽአት!
የደብረ ዘይት ተራራ፣ በጥንታዊቷ ቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ሲሆን፣ በመካከሉ ቄድሮን ሸለቆ፣ ከግርጌውም ጌቴ ሴማኒ በመባል የሚታወቀው ለምለም የአትክልት ሥፍራ ይገኛል፡፡ ተራራው በዚህ ስም ለመጠራቱም ሰበቡ ቀደምሲል እንዳልነው፣ የወይራ ዛፍ በብዛት የሚበቅልበት መሆኑ ነው፡፡ ቦታው ላይ የሚበቅለውን ወይም የሚገኘውን መነሻ አድርጎ ቦታን መሰየም ልማድ ነውና፣ ተራራው ደብረ ዘይት ተብሎ መጠራቱ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ይልቅስ ጥያቄ የሚሆነው ደብረ ዘይት ተራራ ከሌሎች መሰሎቹ ስለምን ገነነ? እንዴትስ በቅዱሳን መጻሕፍት ተደጋግሞ ተጠቀሰ? አልፎም የቅዱስ በዓል  ስያሜ እስከመሆን ደረሰ የሚለው ነው?   
ቅዱሱ መጽሐፍ በወንጌላውያኑ ብዕር እንደሚነግረን፣ ደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሱስ ጋር በተገናኘ በርካታ ታሪኮች የተፈጸሙበት፣ ዕጹብ ድንቅ ሁነቶችን የመዘገበ ሥፍራ ነው፡፡ ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ አዳሩን በዚህ ተራራ ላይ ያደርግ ነበር- በኤሌዎን ዋሻ፡፡ በርካታ አንደበትን የሚያስከፍቱ፣ ልብንና ማስተዋልን የሚገዙ ትምህርቶችን በዚህ ተራራ ላይ አስተምሯል፡፡ የኢየሱስ እናት የድንግል ማርያም መቃብርም የሚገኘው በዚህ ተራራ ግርጌ ነው፡፡ ለታላቅ መከራና መዘባበት በይሁዳ እጅ ተላልፎ ይሰጥ ዘንድ ኢየሱስ የተያዘውም በዚህ ሥፍራ ነው፡፡ ሰማያዊውን መንገድ ይፈጸምበት ዘንድ የታደለ ተራራ- ደብረ ዘይት! ወንጌላውያን ሐዋርያቱ እንዳቆዩሉን መረጃም፣ በመጨረሻ ኢየሱስ ያረገው ከዚሁ ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው፡፡ (በዳግም ምጽአትም ለፍርድ የሚመጣው እዚሁ ተራራ ላይ እንደሆነ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍቷን እማኝ አድርጋ ታምናለች (ሉቃ. ፳፬፥፶፤ ዘካ. ፲፬፥፫-፭)፤ ይህንንም ትሰብካለች፡፡
ከእነዚህ ሁሉ በላይ ግን ደብረ ዘይት ተራራን ገናና እና ተወሺ ያደረገው ሌላ ነው- ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ስለዓለሙ ፍጻሜና ዳግም ምጽአት የተናገረበት ሥፍራ መሆኑ (ማቴ. ፳፬፥፫)፡፡
“እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው- ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት” ተብሎ እንደተጻፈው በተራራው ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ስለዳግም ምጽአቱ፣ ስለዓለም ፍጻሜ፣ ስለትንሣኤ ሙታን በሰፊው ማስተማሩን ወንጌላውያኑ ማቴዎስና ሉቃስ መዝግበዋል፡፡ በምጽአቱ ዋዜማ ስላለው እጅግ አስጨናቂው ዕለተ ደይን (የፍርድ ቀን) በሰፊው የመዘገበውም ማቴዎስ ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት፣ የዐቢይ ጾም እያንዳንዱ ሳምንታት ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ታሪክ ጋር የተያያዘ ስያሜ አላቸው፡፡የዚህ ስያሜ ባለቤትም በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረው ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ ድርሳናት ይገልጻሉ፡፡
ማሕሌታዊው ያሬድ የዐቢይ ጾምን ሳምንታት በሙሉ ከብሉይ መጻሕፍት፣ ከመዝሙራት፣ ከሐዲስ ኪዳን ትምህርትና ከክርስትና ታሪክ ጋር አስማምቶና አስምሮ በመከፋፈል ቀምሯል፡፡ በቅዱስ ያሬድ ስያሜ መሠረትም የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት እሑድ ሙሉውን ሳምንት ጨምሮ “ደብረ ዘይት” ተብሎ ይጠራል፡፡ ስያሜው ኢየሱስ ስለዳግም ምጽአት ያስተማረበትን ተራራ የወሰደ ሲሆን፣ ዕለቱም የሚያዘክረው የትምህርቱ ማዕከል የሆነውን የዓለምን ፍጻሜ፣ ዳግም ምጽአትን ነው፡፡
ዕለቱ ሌሎች መጠሪያዎችም አሉት፤ ዳግም ምጽአት፣ የፍርድ ቀን፣ የጌታ ቀን፣ ሕልቀተ/ሕልፈተ ዓለም፣ ዕለተ ፍዳ፣ ዕለተ ደይን ዳግመኛ ልደት እና ትንሣኤ ዘጉባዔ በመባል በመጽሐፍ ቅዱስና በቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ይጠራል።
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለምን የደብረ ዘይት በዓልን ታከብራለች ለሚልም፣ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ለደቀመዛሙርቱ ስለዓለም ፍጻሜ እና ዳግም ምጽአቱ አስተምሯልና ነገረ ዳግም ምጽአቱን ለማስታወስ በዚህም በንስሐ መዘጋጀትን ለማሰብ ነው፡፡ ነውናም፣ በዚህ ዕለት የሚሰበከው ምስባክ፣ የሚሰጠው የወንጌል ትምህርትና የሚነበቡት የሐዋርያት ሥራና የመልእክታት ንባባት በሙሉ የጌታችንን የክርስቶስን ዳግም መምጣትን የሚናገሩ ናቸው፡፡፡
ስንጀምር እንዳልነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ደብረ ዘይትን ከነገረ ዳግም ምጽአት ጋር አጣቅሶ እጅግ በወፍ በረር ማውሳት ነውና፣ ትንቢቱን እና ምስጢራቱን ትተን (ብንገባበትም አንዘልቀውምና) ክርስቲያኖች የደብረ ዘይት በዓልን እንደምን ያከበሩታል (ያዘክሩታል)? የሚለውን ጠይቀን እናብቃ፡፡
የደብረ ዘይት በዓል የተራራው መገኘ በሆነችው በኢየሩሳሌም ይህ ነው የሚባል አከባበር ያለው አይደለም (ወይም ይህንን የሚያሳዩ መረጃዎች አላጋጠሙኝም)፡፡
በእርግጥ በቦታው ላይ (በደብረ ዘይት ተራራ) ከየዓለማቱ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት (ለመሳለምም) የሚሄዱ ምእመናን የሚሳተፉባቸው በተራራው ዙሪያ ያተኮሩ ሌሎች ሥርዓቶች አሉ፡፡  
ወደሀገራችን ስንመጣ ግን መልኩ ቢሉ መንገዱ የተለየ ነው፡፡ በሀገራችን ኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ በዓሉ የሚዘከረው በደማቁ ነው፡፡ የአከባበሩ መሠረትም ቤተክርስቲያኒቱ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትንቢቶች መሠረት አድርጋ፣ እለተ ደብረ ዘይት የኢየሱስ ዕለተ ዳግም ምጽአት መሆኑን የምታምን እና ይህንኑ የምታስተምር መሆኗ ነው፡፡ ይህንን መሠረት አድርገው በዓሉን የሚያከብሩት የኦርቶዶክስ ምዕመናን አልፎ አልፎ ከቦታ ቦታ፣ ከዘመንም ዘመን እንዲሁ ጥቂት ጥቂት ልዩነቶች ቢታዩባቸውም፣ እለቱን ከለሊት ጀምሮ በቤተክርስቲያን ደጆች በመገኘት በጥሞና፣ በጸሎትና በንስሐ፣ ቅዱስ ቁርባኑን በመቀበል ያሳልፋሉ፡፡ የአንዳንድ ቦታዎችን አከባበር እናንሳ፡፡
በአብዛኛው የገጠሩ የሀገራችን ክፍል ደብረ ዘይት ተከብሮ የሚውለው በበጎ ሥራ፣ በክርስቲያናዊ ሥነምግባር እና ትሩፋት ነው። ምዕመኑ ካጣ ደሀ፣ ያደርገው እስካጠ ባለጸጋ ድረስ እህል ውሃ ይዞ ወደቤተክርስቲያን በመሄድ ድሆችን ይመግባል፡፡
 ከድሆች የተረፈውንም እርስበርስ በፍቅር ይገባበዛል፡፡ የተጣላ ይታረቃል፤ የበደለ ይክሳል፡፡… በዚህ መሰሉ ተግባር ተጠምዶም በደጀ ሰላሙ ቅጽር ከተዘናፈለው ጽድና ዝግባ ሥር አርፎ ይውላል፡፡
እንዲሁም የደብረ ዘይት በዓል በትግራይ ክልል በማይነብሪ በናዝሬት በተለየና በደማቁ እንደሚከበር የአካባቢው አባቶች ይገልጻሉ፡፡
በዓሉ በአካባቢው በምትገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ታላቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥርዓትና ድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ በዕለቱም ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች ይከወናሉ፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑም ከቤቱ ነቅሎ በበዓሉ መንፈሳዊ ተግባራት ላይ ይሳተፋል፡፡
ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላም ምዕመናን የሚመገቡት ከጥራጥሬ የተዘጋጀ በቆልት ነው፡፡ በቆልት የመመገብ ተምሳሌትነቱም የሞተ፣ የደረቀ ከሚመስለው ጥሬ ዳግም ሕይወት ዘርቶ መብቀሉ የትንሣኤ ምልክት ሲሆን፣ ምዕመናን ይህን በቆልት መብላታቸው በዳግም ትንሣኤ እንደሚነሡ ለማጠየቅ ነው፡፡ በቆልቱን
ሲመገቡ፣ ያልበቀለ ጥሬ ካገኙ ከአፋቸው አውጥተው ይተፉታል፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት፣ በዳግም ትንሣኤ ለኩነኔና ለዘላለም ጥፋት ከሚነሡት ፈጣሪያቸው እንዳይደምራቸው በመመኘት ነው፡፡
አንዳንድ መልኮችን ቢያሳየን ብለን እኒህ አነሳን እንጂ፣ የደብረ ዘይት በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በደማቅ ሥርዓት፣ በልዩ ልዩ መንፈስን በሚቀድሱ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚከበር በዓል ነው፡፡
ዕለቱም የጌታ የዳግም ምጽአት ቀን እንደሆነ ይታመናልና፣ ምዕመናኑ ከአብያተ ክርስቲያናቱ ደጅ የሚደርሱት የለሊቱ ግርማ ሳይገፍ እጅግ ቀድመው ነው፡፡ በዚህም በፍጹም መረጋጋት፣ በጸሎትና በእንባ ፈጣሪያቸውን ይማለላሉ- ከፍርድ ቀን ያድናቸው ዘንድ፡፡ ቸር እንሰንብት!
**
ከአዘጋጁ፡-
ባዩልኝ አያሌው በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነጽሑፍ መምህር ሲሆኑ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የኪነጥበብ መድረኮች ላይ በሚያቀርቧቸው ግጥሞችና አዲስ አድማስን ጨምሮ በሌሎች የሕትመት ውጤቶች ባስነበቧቸው ሥነጽሑፋዊ ሂሶቻቸው ይታወቃሉ፡፡


Read 462 times