Sunday, 14 April 2024 20:23

በጭለማ እየሄዱ ጅብ ነገረኛ ነው ይላሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን ድመት አንድ ጫካ ውስጥ ቀበሮ ታያለች፡፡ ከዚያም ለራሷ እንዲህ ትላለች፡-
“ቀበሮ በጣም ቀልጣፋ ነው፡፡ ብዙ ልምድ ያለው ነው፡፡ በሰፊውም የተከበረ ነው፡፡ ስለዚህ መልካም ሰላምታ ላቀርብለትና ልቀርበው ይገባል”፡፡ ቀጥላም፤ “እንደምን አደርክ አያ ቀበሮ! እንዴትስ ከርመሀል? ለመሆኑ ሁሉ ነገር በጣም በተወደደበት በዚህ በአሁኑ ጊዜ ኑሮን እንዴት ተቋቋምከው?”
ይሄኔ ቀበሮ በጣም እየተኩራራ ተጎማለለ፡፡ ድመቷንም ሽቅብ ቁልቁል እያየ ገረመማት፡፡ ከኩራትና ከእብሪቱ የተነሳም ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ መስጠት ብዙ ጊዜ ፈጀበት፡፡ በመጨረሻም እዲህ አላት፡-
“አንቺ ምስኪን ጢም-ላሽ ፍጥረት! አንቺ የቤት አሽከር! ደካማ፣ የአይጥ-አባራሪ! ማነሽና ነው እኔን የተከበርኩትን ቀበሮ ኑሮ ከበደህ ወይ የምትይኝ? ማነሽናስ ነው የኑሮ ውድነቱን ተቋቋምከው ወይ? ብለሹ የምትጠይቂኝ? ለመሆኑ እስከዛሬ ድረስ አንቺ ምን ተምረሻል? በምንስ ጥበብ ሰልጥነሻል? ምን ችሎታ አለሽ?”
ድመቲትም፤ ትህትና በተላበሰ ቃና፤
“አንድ ጥበብ ብቻ ነው ያለኝ” አለችው፡፡
አያ ቀበሮም፤
“ምን ጥበብ ትችያሽ? ተናገሪ እስቲ?” አለና ጠየቃት፡፡
ድመቲትም፤
“ውሾች ድንገት መጥተው ሲያባርሩኝ ፈጥኜ ዛፍ ላይ እወጣለሁ፡፡ ይሄ ነው ጥበቤ”
ቀበሮም በጣም በኩራት ተነፋፍቶ፤
“ይሄ ብቻ ነው እንዴ ችሎታሽ? ጥበብሽ ይሄ ብቻ ሆኖ እንዲህ በአደባባይ ስትፎክሪ መስማትሽ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፡፡ ጉረኛ ነሽ! እኔን ስላላየሽ ነው፡፡ እኔ ከመቶ በላይ ጥበብና ችሎት አለኝ፡፡ ከዛ በተጨማሪም አንድ ከረጢት ሙሉ ዘዴና ትሪክ አለኝ፡፡ እኔ አንቺን ከልቤ እወድሻለሁ፡፡ ነይ፡፡ ነይ አብረን እንሂድና ከውሾች የምታመልጪበትን ዘዴ አስተምርሻለሁ” አላት፡፡
በድንገት ከየት መጣ ሳይባል አንድ አዳን ይመጣል፡፡
አራት ትላልቅ አዳኝ - ውሾች ይዟል፡፡
ይሄኔ እመት ድመት በከፍተኛ ፍጥነት ተቀላጥፋ ዛፍ ላይ ትወጣለች፡፡ በቅርንፎቹም ተንጠላጥላ ሙሉ በሙሉ በቅጠሎቹ ተሸፋፍና ተደብቃ ትቀመጣለች፡፡ እቅጠላ -ቅጠሎቹ መካከል ሆና፤
“አያ ቀበሮ፤ ቦርሳህን ከፈተው፡፡ ቶሎ ብለህ ቦርሳህን ክፈትና ከዘዴዎህ አንዱን አውጥተህ ተጠቀም” እያለች ትጮህ ጀመር፡፡
ግን ምን ያደርጋ፤ አያ ቀበሮ!” አለች በጮክታ፡፡ “አሁን የገባህበትን አጣብቂኝ ተመልከት፡፡
አጠራቅሜያለሁ ካልካቸው ከመቶ በላይ ዘዴዎች አንዱን እንኳ ስራ ላይ ሳታውል ፈፅሞ ከማትወጣበት ችግር ውስጥ ገባህ፡፡ እኔ ከልቤ አምኜ የያዝኳትና በረዥም ጊዜ ልምድ የተካንኳትን ሀቀኛና ፈጣን ዘዴ ተጠቀምኩ፡፡ ዛፍ የመውጣት ዘዴ ብታውቅ እንደዚህ ሆነህ አትቀርም ነበር” ብላው የበለጠ ጥቅጥቅ ወዳለ ቅጠል - ቅጠል ውስጥ ገብታ ስታበቃ በመጨረሻ አዳኙና ውሾቹ ሲሄዱ ወረደች፡፡
***
በአንድና በሁለት ነገር ብልጥ ሆኖ ሌሎችን መብለጥ ይቻላል፡፡ በሁሉም ነገር ብልጥ መሆን ግን ዘበት ነው፡፡ ሁሉ መፎከር፣ ሁሉ እኔ እበልጣለሁ እያለ መደንፋት፤ ሁሌ የትም አይደርስም እያለ መናቅ፤ ሁሌ በጊዜያዊ ድል መኩራራት የሚሰምርና ፍሬ ያለው ውጤት ሆኖ አለመገኘቱ ብቻ ሳይሆን ለችግር የሚያጋልጥ አባዜ ነው፡፡ ሥጋት፣ ጥርጣሬና አለመረጋጋትን ያነግሳል፡፡ ጥንት እንሰማ ከነበረው “አብዮታችን ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል” ከሚባልበት አይነት ሁኔታ ወጥተን በውይይት ወደምናምንበት ደረጃ መሸጋገር መቻል አለብን፡፡ አለበለዚያ ሁሌ የግጭት ሁሌ የእልቂት ሀገር መሆን አንድንችም፡፡ አንድ የሀገራችን ምሁር “ታሪክ ራሱን ይደግማል” የሚባለውን አነጋገር በእኛ አገር አንፃር ሳየው ያስገርመኛል፡፡ በእኛ አገር አንዳንዴ ታሪክ፤ ታሪክ ሆኖ ሳያልቅ ይደገማል፡፡ ሲብስበትም ከናካቴው ታሪክ ሳይሆን በፊት ራሱን ይደግማል” ብለው ነበር፡፡ የበለጠ እሚያስገርመው ደግሞ የሚገርመው ክፉ ክፉው፣ ተንኮል ተንኮሉ፣ ምሬት ምሬቱ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሀገር ስታለቅስ ትኖራች፡፡ የሐዘን እንባ አይለያትም፡፡
መሰረታዊው የኢኮኖሚ ውስብስብ ችግርና ጥያቄ ሳያበቃ በፖለቲካው መስክ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች እየበዙ፣ እየተሸረቡ፣ እየደነደኑ፣ ሲመጡና ትላንት ያከማቸነው ጥበብና ዘዴ ሁሉ አልሰራ ሲል፣ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ “መድሃኒቱን ሰውነትህ ለምዶታልና አይሰራልህም፡፡ ሌላ ለውጥ”፤ እንዲል መጽፅሀፈ-ሀኪም፡፡ የዲሞክራሲ ጥያቄ፣ የፍትህ ጥያቄ፣ የፕሬስ ነፃነት ጥያቄ፣ የብዙሃን ፓርቲ  ጥያቄ፣ የሰብአዊ መብት ጥያቄ… መልስ ካላገኙ ሰልፉ ሁሉ ቀኝኋላ ዙር ነው!
የሃያሎች አማላጅነትም ቢሆን የሀገርን ችግር በዘላቂነት ፈትቶ አያውቅም፡፡
የሃያላኖች እርዳታም ሆነ ምልጃ፤ የህመም ማስታገሻ እንጂ መፈወሻ አይደለም፡፡ እነሱም የራሳቸውን ጥቅም መሰረት ያደረገ አቅጣጫ እዳላቸው አለመዘንጋት ነው፡፡
ሥራና ሰራተኛን ለማገናኘት ዋንኛ መመዘኛው ሙያዊ ብቃት ነው፡፡ ፖለቲካዊና ወገናዊ ድልደላ ካለ ከሙስና የተለየ ትርጓሜ የለውም፡፡ ለምሁር፣ ለባለሙያ፣ ለሰለጠነ የሰው ኃይል ያለን እምነት ከፖለቲካ ታሳቢነት ነፃ ካልሆነ፣ ኖሮ ኖሮ የአገርን ጥቅም የሚሸረሽር፣ ነገ ፍሬ የማያፈራ የብልጣ ብልጥ ተግባር ከመሆን አያልፍም፡፡ ስለሆነም የኋሊት እንጂ ወደፊት አያራምድም፡፡
 በዲፕሎማሲው ረገድም ሊደርስ የሚለውን ቀውስ አለመዘንጋት ተገቢ ነው፡፡ ብቃት ያላቸው አምባሳደሮችን አለመመደብ የሚያስከትለውን ቀውስ ማስዋብ ያሻል፡፡ በዚህ በሰለጠነው ዓለም አምባሳደርነት አገርን የመወከል ታላቅ ኃላፊነት እንጂ መጦሪያም ግዞትም፤ ፖለቲካም ማስታመሚያም፣ ቁሳቁስ በሻንጣ መሸከፊም አሊያም ደግሞ ቤተሰብ ማጓጓዣም አይደለም፡፡ የሀገርን ክብር በባህል፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ማጎልበቻ ነው፡፡ ውሎ አድሮ ከሚከሰት ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈትም መዳኛ ነው፡፡
“አውቀን በድፍረት ሳናውቅ በስህተት በሰራነው ሁሉ ይቅር ይበለን” የሚለው የማሳረጊያ ንሥሐ የሚያስፈልግበት ዘመን ነው፡፡ ደፍሮ ተናግሮ መፅደቅ የሚሸዳ ጠፋ እጂ!!
በሀገራችን ውስጥ በየፈርጁ የሚታየው በቂም መፈላለግ ሆነ ብሎ አለመግባባት፣ ሰበብ እየፈጠሩ ነገር መፈላለግ፣ የ”ሳታመሀኝ ብላኝ” እሮሮ፣ “የብቆጣም እመታሻለሁ፣ ብትቆጪም እመታሻለሁ” ድንፋታና ማን አለብኝ፤ “በጨለማ እየሄዱ ጅብ ነገረኛ ነው ይላሉ” አለ አያ ጅቦ፤ የሚለውን ተረት የሚያስጠቅስ ክስተት ሆኗል፡፡ በዚህ ክስተት አገር አታድግም፡፡

Read 848 times